ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም መከበር መቆም ማለት ሕግና ሥርዓትን ማክበር ማለት ነው፡፡ ሀገር የምትጸናው ሰላምና ደህንነቷ ተጠብቆ መኖር መቀጠል ስትችል ብቻ ነው፡፡ የተጀመረው የተሀድሶ ለውጥ መሰረታዊ ስኬት በማስገኘት መቀጠል የሚችለው አሁንም ሕግና ሥርዓት ሲከበር ልዕልናም ሲያገኝ ነው፡፡
ለውጡ ያስመዘገባቸውን ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ያልታዩና ያልነበሩ ምናልባትም ሊሆኑና ሊደረጉ ይችላሉ ተብለው የማይታሰቡ በሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍን ያስገኙ እርምጃዎችን የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል የሚቻለው በከፍተኛ ሕዝባዊ ዲስፕሊን በመጓዝ ብቻ ነው፡፡ ስሜታዊነት፣ ጀብደኝነት፣ ጎጠኝነት፣ ከፋፋይነትን አጥብቆ መታገል የሁሉም ዜጋ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል፡፡
ለውጡ ለውጥ የሚሆነው ሁሉም ዜጋ በተሰለፈበት የሥራ መስክ ለሀገሩ ሰላም መከበር ለኢኮኖሚው እድገትና ለልማት የየበኩሉን ሀገራዊ ድርሻ መወጣት ሲችል ነው፡፡ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረጉት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴዎች ሀገራዊ ወድቀትን ከማስከተል ውጪ ለሕዝብና ለሀገር ሰላም የሚበጅ ትሩፋት የላቸውም፡፡ እጅግ የገዘፈና የተንሰራፋ ሙስና፤ የፍትህና የመልካም አስተዳደር እጦት ገኖና ስር ሰዶ በኖረባት ሀገር ከስር ጀምሮ ለውጥ ለማምጣትና የሕዝቡንም መሰረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ሰፊ ሥራና ጊዜን ይጠይቃል፡፡ በአንድ ጀምበር የሚሠራ ሥራ አይደለም፡፡
በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በተለያዩ ክልላዊም ሆነ መንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ በነበራቸው ኃላፊነት ከከፍተኛው እስከ ዝቅተኛው አመራር ድረስ የነበሩ ተዋናዮች በነገ እንጠየቃለን ስጋት ለውጡን እያደቡ ለማሰናከል የአቅማቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ አርፈውም እንደማይ ቀመጡ በገሀድ እየታየ ነው፡፡ ይህም እኩይ ድርጊት በወጣ ገባ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች መከሰቱ ለዚህ ማሳያ ማስረጃ ነው፡፡
በተለያዩ ወቅቶች ከኃላፊነታቸው የተነሱ ሰፊ ገንዘብ ያካበቱ፤ በንግዱ መስክ ከተሰማራውም ኃይል ጋር ቁርኝት ያላቸው ክፍሎች በተለይ ሰፊ ግዛት ባለው ኦሮሚያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ ገንዘባቸውን እያፈሰሱ ሁከቱ እንዲበራከት ጥረት እያደረጉ ቆይተዋል፡፡ የመንግሥትን ሰፊ ትዕግስት ከፍርሃትና ከአቅም ማነስ ቆጥረውት በወንጀል ድርጊታቸው ገፍተውበት ቆይተዋል፡፡
ያደረሱት መጠነ ሰፊ ጥፋት በሕዝብና በሀገር ላይ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በመንግሥት በኩል የታየው ሰፊ ትዕግስት ይበልጥ የጸረ ለውጥ ኃይሎቹ ሴራ በሕዝብ እንዲታወቅ ማንነታቸው ጎልቶ እንዲወጣና እንዲጋለጥ እርቃናቸውን እንዲቀሩ አድርጓል፡፡ በምናባዊ አስተሳሰብ አለን ብለው የሚገምቱትን የሕዝብ ድጋፍ አሳጥቷቸዋል፡፡
የሕዝብ የዘወትር ፍላጎት ሀገሩ ሰላሟ ተጠብቆ እንዲቀጥል እንጂ፤ እንዲደፈርስ አይደለም፡፡ ትጥቅ ፈተው በሰላማዊ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በሰላምና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ፖለቲካዊ እምነታቸውንና ዓላማቸውን እንዲያራምዱ የተደረገው የበለጠ ሀገራዊ ሰላም ለመፍጠር፤ በሀሳብ የበላይነትና በሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር በምርጫ ተሳትፈው ሕዝብ ይሆነኛል ያለውን እንዲመርጥ ነው፡፡
በሀሳብ የበላይነት ገዢና አሸናፊ የሆነው ፓርቲ ፖሊሲውን ዓላማና ግቡን በነጠረ መልኩ አቅርቦ በሕዝብ ተቀባይነት የሚያገኘው የፖለቲካ ድርጅት የመሪነቱን ቦታ ይዞ ሀገራችን በሰላማዊ ሁኔታ የእድገት ጉዞዋን እንድትቀጥል፤ ይህም የሠለጠነና ያደገ ባሕል ሆኖ በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥል ለማድረግ ነው፡፡ ሆኖም ግን ዛሬም ከዘመናት ትግል ውጣ ውረድ መውደቅና መነሳት፤ ትውልድን የመረረ ዋጋ ካስከፈለ የመተናነቅ የመጎሻሸም በጠላትነት የመፈራረጅ፤ የእኔ እበልጥ ብቻ ብልጣ ብልጥና ኋላቀር የፖለቲካ አስተሳሰብ ያልተላቀቁ፤ አድሮ ቃሪያ አድሮ ጥጃ እንደሚሉት አባቶች በጥንት እሳቤያቸው ተቸክለው ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን በገሀድ እያስተዋልን ነው፡፡
ትውልድና ዘመን ሲለወጥ አለመለወጥ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ የትናንቱና ዛሬ ያለው ኢትዮጵያዊ ትውልድ በፖለቲካ አስተሳሰቡ የሰማይና የመሬት ያህል ርቀት ነው ያላቸው፡፡ በድሮ ዘመን የነበረ የኖረ የፖለቲካ ትግል አካሄድ ዛሬ ላይ የሚሠራበት አመክንዮ የለውም፡፡ በ1960 ዎቹ የነበረ እምነትና አስተሳሰብ የዛሬውን ዘመንና ትውልድ ሀገራዊ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ለውጦችን ትኩሳቶችን የህብረተሰብ እድገትና ለውጥን አጣጥሞ አንብቦ ተንትኖ መራመድ ካልቻለ ያለው ዕድል የማያዳግም ውድቀት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ በሕዝብ መተፋትን ያስከትላል፡፡
ዘረኝነትና ጎጠኝነት ሀገርና ትውልድ ገዳይ ካንሰር የሆኑ በሽታዎች ናቸው፡፡ አዲሱ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ይሄንን ሊቀበለውም ሆነ ሊከተለው ከቶውንም አይችልም፡፡ ዓለም በሥልጣኔ በእውቀት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምጥቀት ተራቃለች፡፡ ኋላ ቀር በሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ መዳከር እንደገና ሀገርና ሕዝብን ለከፋ ውድቀት ይዳርጋል፡፡
በሀገራችን የታየውን ለውጥ እንዲመጣ ያደረገው በኦሮሚያ፣ በአማራውና በሌሎችም ክልል የሕዝቡ በተለይም የወጣቱ መጠነ ሰፊ ትግል ነው፡፡ ይህንንም መሰረታዊ እውነት የተቀበለው በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው የለውጡ አራማጅ ኃይል የሕዝቡን ጥያቄዎች ተቀብሎ በራሱም ውስጥ ለውጥ አድርጎ ዛሬ ላይ የታየውን ቀድሞ ያልነበረ ለውጥ ማምጣት ችሏል፡፡
በአጭሩ የትግሉም የድሉም ባለቤት በሀገር ውስጥ ያለው ሕዝብና መሰረታዊ ለውጥ እንዲደረግ ወስኖ የተንቀሳቀሰው አዲስ አመራር ወደ ሥልጣን ያመጣውና ለውጡን ያስቀጠለው ኢሕአዴግ ነው፡፡ ይህን ግዙፍ ለውጥ የትኛውም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አልመራውም፡፡ ሰባና ሰማንያ ተቃዋሚ ድርጅቶች የተለያየ ፕሮግራም ድርጅታዊ ቅርጽ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ይዘው፤ እርስ በርስ መግባባትና መናበብ በማይችሉበት ተቀራርበውም ለመሥራት በማይችሉበት፤ አንዱ ሌላውን በጠላትነት እየፈረጀ በጎሪጥ በሚተያዩበት ሁኔታ ውስጥ ይህን የመሰለ ሀገራዊ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎም አይታሰብም፡፡
ይልቁንም በሀገር ውስጥ የተደረገው ለውጥ በውጭ ያሉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በይቅርታና በምሕረት ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ በሰላምና በሰላም ብቻ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን እንዲያራምዱ፤ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩትም ትጥቃቸውን ፈተው ለሰላማዊ ትግል እንዲሰለፉ ለሀገራቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በርና መንገድ የከፈተ ነው፡፡
በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ከእስር ቤት የለቀቀ፤ ከስደት የወጡትም ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ያበቃ፤ በውጭ ያሉ ሚዲያዎች በሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ ማድረግ ያስቻለ ፤ በተቃዋሚነትም ሆነ ከተቃዋሚነት ውጪ ያሉ ዜጎችንም በእውቀትና ችሎታቸው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ወደ አመራር ያመጣ፤ ፍቅርን መቻቻልን ተግባብቶ መሥራት እንደሚቻል ያሳየ በዓይነቱም የተለየ ሀገራዊ ለውጥ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በተሰመረለት መስመር ላይ እየተጓዘ ያለ ለውጥ ነው፡፡
የዚህ ለውጥ መሪ ሕዝብና ራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው የለውጥ ኃይል ነው፡፡ የትኛውም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አልመራውም፡፡ ስለዚህም ለውጡን ያመጣሁት የመራሁት እኔ ነኝ ብሎ ሊፎክር ሊያቅራራ የሚችል አንድም የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት የለም፡፡ ግማሾቹ ከስማቸው መብዛት የተነሳ የማይታወቁ የተረሱ፤ ምንም ተጨባጭ ለውጥ ያላሳዩ በተረት ተረት ያፈጁ የነበሩትን ሁሉ ይሄ ለውጥ ነፍስ እንዲዘሩና የሌለ ሕልም እንዲያልሙ አብቅቷቸዋል፡፡ እንቅፋት ከመፍጠር ይልቅ ሊያመሰግኑ በጽናት ከጎኑ ሊቆሙና በሰላም ለውጡን ለማስቀጠል መሥራት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
በሀገር ውስጥ ሕዝብና ልጆቹ ኢሕአዴግ ውስጥም የነበሩና ያሉ የለውጡ አራማጅ ኃይሎች በከፈሉት መስዋዕትነትና ትግል የተገኘውን ድል ጠቅልለው ወደራሳቸው በመውሰድ አርበኞቹ ታጋዮቹ ታግለን ይሄን ለውጥ ያመጣነው እኛ ነን በማለት ያለአንዳች ኃፍረት ለመመጻደቅ የሚከጅሉም ታይተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ከታሪክ ከስህተትም ያለመማር አደጋ ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት መከበር ሲያሰሙት የነበረውን ድምጽ መካድ አይቻልም፡፡ በሀገር ውስጥ ዛሬ የታየውን ለውጥ በወሳኝነት የመራው ግን ዛሬ ወደ ሥልጣን የመጣው የለውጥ ኃይል ነው፡፡
የታሪክ ሽሚያና ስርቆት ለማንም አይበጅም፡፡ ባልዋሉበት ባልነበሩበት እራስን ማግዘፍ ዘራፍ ማለቱ ሕዝብ ሁሉንም ስለሚያውቅ ትርፉ ታላቅ ትዝብት ነው፡፡ ስለዚህም ከምንም በላይ ለውጡን በአግባቡ መያዝ፤ የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ነቅቶ መጠበቅ፤ ለውጡን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ መሥራት፤ ከዘረኝነትና ከፋፋይ ልክፍት መላቀቅ፤ ከመናቆርና ከመባላት መውጣት፤ የሠለጠነ ፖለቲካን መከተል፤ ከሴራ ፖለቲካ መውጣት፤ የመደማመጥ የመነጋገር ልዩነትን አቻችሎ በውይይት መፍታት፤ ለጋራ ሀገር በጋራ ጸንቶ መቆም ከመቼውም በላይ ጊዜውና ሀገራዊው ተጨባጭ ሁኔታ የሚጠይቀው ግዴታ ነው፡፡ ሀገርንም ሕዝብንም ከአደጋ የምንታደግበት መንገድ ይኸው ብቻ ነው፡፡ ያለፉት አስከፊ የክፍፍል የመጠፋፋት የመወነጃጀል በጠመንጃና በግድያ የሚያመልክ ኋላ ቀር ፖለቲካ ሊበቃን ይገባል፤ ይብቃን!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2011
መሐመድ አማን