የድንጋይ ላይ ጽሁፎች፣ ጥንታዊ የመገበያያ ሳንቲሞች፣ የሸክላ ውጤቶችም በተሄደበት ቦታ ሁሉ የሚታዩ የሀገሩ መለያ ናቸው። በአርሶ አደሮቹ የቤት ግርግዳ ላይ እነዚህና መሰል ቅርሶችን ተሰቅሎ ማየት የተለመደ ነው። ነገር ግን አርሶአደሮቹ ከእነርሱ አልፎ ሌላ ሰው ሊነካው በፍጹም አይፈልጉም። ይህንን ያደረጉበት ግን ምክንያት አላቸው። ማንም እየመጣ ላጥና በሚል ሰበብ የቅርስ ከተማነታቸውን እያወደመባቸው በመገኘቱ ነው። ስለዚህ ቅርሶቹ እንዳይበላሹና እንዳይጠፉ ራሳቸው በራሳቸው ጥበቃና እንክብካቤ ያደርጋሉ።
እኛም በቦታው ስንደርስ የገጠመን ይኸው ነበር። «ምን ታመጣላችሁ፤ ከማውራት ውጪ ንብረታችን እየወደመ ነው። ለዚህ ደግሞ በቀበሌ ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥበቃ እያደረግን ነው። እዚህ ብዙ ሰው ይመጣል የሚፈይደው ግን የለም። የመስኪድ ፍርስራሽ አለ ከማለት ውጪ። እናም ፍርስራሹ እንኳን እንዳይገኝ ማህበረሰቡ ጭምር ድንጋዩን እየወሰደ ቤት መስሪያ እያደረገው ነው። እናም ቅርስን ጠብቆ ለትውልድ የሚያስተላልፍ አካል ከሌለ ማስነካት አንልፈልግም›› አሉ በንዴት ፊታቸውን እየሸበሸቡ። እኛም ምን እያሉን እንደሆን በሚገባ አልገባንም ነበርና ንዴታቸውን ብቻ ከፊታቸው ገጽ ላይ እያነበብን ችግሩን ለማወቅ ሞከርን ። ሆኖም ከመካከላችን የሚናገሩትን ቋንቋ የሚችሉ ስለነበሩ አግባቧቸው። ሀሳባቸውንም ነገሩንና ገባን። ከዚያም ታሪኩን ተረዳን። የሰውዬውም ሙግት ከምን እንደመነጨ አወቅን፡ ፡ ከዚያ ታሪኩን ምንም ሳይሸሽጉ ማውራታቸውን ቀጠሉ።
በስፍራው የሚገኙት የቅርሱ ጥበቃ እንዳሉን፤ ሀርላ ጥንታዊ የንግድ ከተማ ነች። ከላሊበላ ጋር በአንድ ሥረወመንግሥት ጊዜ እንደተመሰረቱ ይነገርላታል። ምስራቅ ላይ የሚያብረቀርቁ ቦታዎችን ከመረጡ የመጀመሪያ የምትሆነው እርሷ ነች። ምክንያቱም ጥንታዊ ቅርሶቿ በተራራ ላይ ሆነው እንኳን ያበራሉ። እናም በ13ኛው ክፍለዘመን የሀርላ ሥርወመንግሥት መቀመጫ እንደሆነች ሰምተናል። ለዚህም ማሳያው የበርካታ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ ነው።
ሥረወመንግሥቱ ከሩቅ ምስራቅ አገራት ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያካሂድ እንደነበር ይነገራል። ለዚህም ማሳያው በየጊዜው የሚገኘው ቅርስ እንደሆነ የነገሩን ጠባቂው፣ ሀርላዎች በጣም ግዙፍ ሰውነት ያላቸው፤ ረጃጅም መሆናቸውን ከአባቶቻቸው የሰሙትን መነሻ አድርገው አጫውተውናል። በሀርላ በአርኬዎሎጂስቶች ጥናት ያልተደረገባቸው ወይም ጥናቱ ተደርጎ ያልተጠናቀቀባቸው 10 ቀበሌዎች መኖራቸውንም ገልጸውልናል። ግን አሁንም ቢሆን ብዙ ጥበቃ ካልተደረገለት ታሪክ ይጠፋል ይላሉ። ምክንያቱም እኛ ባየነው እንኳን ከ10 ክፍለዘመን በላይ አስቆጥሯል የተባለለት መስኪድ ሳይቀር ፈራርሶ ድንጋዮቹም ተወስደው እያለቁ ነው።
የሀርላዎች የንግድ ከተማን ከድሬዳዋ ወደ ሐረር በሚወስደው መንገድ ላይ 15 ኪሎሜትር ወደ ውስጥ ገባ ሲባል ተራራን እየቧጠጡ በእግር ወጥተው የሚያገኙት ነው። እናም ይህ ቦታ ብዙ የሀርላዎችን ማንነት መንጥሮ የሚያሳይ እንደሆነ ይነገርለታል። ነገር ግን በደንብ ተጠንቶ ስላልታየ ምን እንደሚጠቀሙ፣ እንዴት ቁሶችን እንደሚገለገሉባቸው አይታወቅም። ለአብነት የቀን መቁጠሪያቸው ነው፤ የጆሮና የአንጌት ጌጥ ነው የሚሉ የተለያዩ ቁሶች ተገኝተዋል። ምንነታቸው ግን በትክክል አልተረጋገጠም።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቱሪስት ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር የሆኑት አቶ እንድሪስ ታደሰ እንደሚናገሩት፤ የቢዮ ሀርላ ገበሬዎች ለእርሻ ወይም ለቤት ሥራ መሬት ሲቆፍሩ የከበሩ ድንጋዮች፣ የተለያዩ አገራት ሳንቲሞችና የሸክላ ውጤቶችን ያገኛሉ። ይህ ደግሞ ስለሀርላዎች ምንነት በጥቂቱም ቢሆን ለማወቅ ጠቅሟል። ለአብነት ሀርላዎች አቅጣጫዎችን ለማወቅ የቀኝ እግር ዳናን ይጠቀሙ እንደነበር የታወቀው በተገኘው መረጃ ነው። በዘመኑ መብራት ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ሌጦ እያቀለጡ ጎድጓዳ ድንጋይ ላይ በማድረግ ይለኩሱና ይጠቀሙት እንደነበርም በቅርሶቹ አማካኝነት ታውቋል።
ሀርላዎች ከ700 ዓመታት በፊት ከ13ኛው እስከ 16ኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ሀርላን ጥንታዊ የንግድ ከተማ አድርገዋት ነበር። በዚህም ነጋዴዎቿ በዘይላ ወደብ አድርገው አረብያን ፔንሱላን አልፈው ቻይና ድረስ በመዝለቅ ይነግዱ እንደነበር የሚያሳዩ በርካታ ቅርሶች መገኘታቸውን የሚናገሩት አቶ እንዲሪስ፤ የሀርላ ህዝብ በተለያየ መልኩ እንደጠፉ ይነገራሉ። የመጀመሪያው በውስጣቸው በተፈጠረ ቁርሾ ሲሆን፤ ሁለተኛውና ሌላው ግምት ደግሞ በበሽታ፣ በጦርነት፣ አለያም በፈንታሌ አዋሽ አካባቢ በተፈጠረ እሳተገሞራ አማካኝነት ሊሆን እንደሚችል መላምቶች መቀመጣቸውን ያነሳሉ። ከአዋሽ ተሻግረን እስከ ሱማሌና ኬንያ ድረስ የሚገባ ከሀርላ ጋር የተገናኙ ህዝቦች መኖራቸውንም መረጃዎችን ሲያገላብጡ እንደተመለከቱ ይጠቅሳሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያስ በበኩላቸው ለኢቲቪ በአንድ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ ሀርላዎች በኢትዮጵያ የሰፈሩት ከ10ኛው ክፍለዘመን በፊት ነበር። ለዚህም ማስረጃው እነርሱ የሚጠቀሙበት የድንጋይ ላይ ጽሁፍ ናቸው። በስድስተኛው ክፍለዘመን ይጠቀሙበት የነበረ የቻይና ገንዘብ መገኘቱ ምን ያህል ነባር ማህበረሰብ እንደነበሩ ያመላክታል። ምን ያህል ርቀት ተጉዘውም ግብይት እንደሚያደርጉም ያሳየናል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ አሁንም ጠለቅ ብሎ ከተሰራበትና ምርምሩ ከተደረገበት ሀርላ ብዙ ነገር ታሳየናለች ይላሉ። የሀርላ መንግሥት በኢትዮጵያ ታሪክ ተጠቅሶ የተገኘው በንጉስ አምደጺዮን መጀመሪያው ማለትም ከ1314 ዓ.ም መሆኑንም ያስረዳሉ። ቀጥሎ የሚያሳየው ደግሞ የአረቦቹ መረጃ ሲሆን፤ ይኸውም ፈታልአል ሀበሻ የሚባለው ሰውዬ በሐረር ከፍተኛ አካባቢዎች በእርሻና በከብት ዕርባታ ይተዳደሩ የነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደነበሩ ያወሳል ብለዋል።
በሌላ በኩል ስልጣኔያቸውም መሰረት ያለው መሆኑን የሚናገሩም አሉ። ይሁንና የዓለም ስልጣኔ ምንጮች ከቀይባህር ማዶ የኤፍራጠስና ታይግረስ የምንላቸው አካባቢ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። በአፍሪካ ስንመጣ ደግሞ የአባይ ተፋሰስ አካባቢ ነዋሪዎች የስልጣኔው ምንጭ ይሆናሉ። ስለዚህ በዚህ መካከል ስላለች ሀርላም የስልጣኔ ምንጭ ልትሆን የምትችልበት ሁኔታ ይሰፋል ይላሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ሁለቱን በድልድይ የምታገናኘው ሀርላ ስለሆነች ነው።
በሀርላዎች መኖሪያ አካባቢ ቤት ለመስራት መሬት ሲቆፈር ማህተሞች፣ የተለያዩ የሚያስገርም ዲዛይን ያላቸው ቅርጻቅርጾች፣ ገንዘቦች፣ ወርቅና ብርም ይገኛል። እናም ሀርላዎች የሚጠቀሙበት መሳሪያ ብዙ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች ናቸውና አሁን ብዙዎች እየተመራመሩባቸው እንደሚገኙ ሰምተናል። ገንደ ብዮ፣ ገንደ ኦዳ፣ ገንደ ኢጅሩ፣ ገንደ ኮርፋ፣ ገንደ ሱጋ፣ ገንደ አሪጋያ፣ ገንደ ቀበሌ፣ ገንደ ሂና፣ ገንደ ሙዲ አዲ፣ ገንደ ጣቢያ፣ ገንደ አንበሪቱ፣ ገንደ ወንጪቱ፣ ገንደ ዋሬ እየተባሉ የሚጠሩ መካነ መቃብሮች በስፋት ያለባት የሀርላዎች መኖሪያ ከተማን ፤ የጥንታዊ መስኪድ ፍርስራሾች መነኃሪያ መሆኗንም ተገንዝበናል። ስለዚህ ይህንን ስፍራ መታደግ የአካ ባቢው ሰዎች ሥራ ብቻ አይደለምና ትኩረት ይቸረው ብለን አበቃን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው