በለውጥ ሒደት ላይ እንዳለን፤ ከወራት በኋላ ብሔራዊ ምርጫ እንደምናካሂድ፤፤ የማንነት ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች አሁንም በየቦታው እንደሚነሱ፣ የሕግ የበላይነት ክፍተት እንደሚስተዋል ብዙዎቻችን የምንስማማበት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሀገርና ሕዝብ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት Political Correctness ( PC ) የልብ ትርታው መሆኑ ለቅፅበት እንኳ ልንዘነጋው አይገባም። ለውጡ ካለፉት 19 ወራት ወዲህ እንኳ ብዙ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። በገለልተኛ ወገን በጥናት ባይረጋገጥም በለውጡ ተቀባይነት legitimacy ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በአብነት ማንሳት ይቻላል።
የሴራ ፖለቲካና የበሬ ወለደ “ወሬ” ከፖለቲካ ትክክለኝነት ልምሻ ጋር ተጃምሎ ፣ አብሮ እንደ ሰደድ እሳት ሲዛመት ታዝበናል ። በሁለቱ እኩይ ኃይላት መካከል ማለትም በሴራና በፖለቲካዊ ኢትክክለኝነት ያለውን እሳትና ጭድነት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተከስተው ከነበሩ ግጭቶች አኳያ ያስተውላል። የፖለቲካዊ ትክክለኝነትን አንድምታዊና ታሪካዊ ዳራ በስሱ ከሸመን በኋላ ወደ ሀገራችን ፖለቲካዊ መልክዓ አውርደን እንከናነበዋለን። ክንንቡን ግን ለሀገራችን ለሕዝባችን ክብር ስንል መልሰን እናወርደዋለን ።
ፖለቲካዊ ትክክለኝነት በ1930ዎቹ ጀምሮ ጥቅም ላይ እንደዋለ የተለያዩ በዘርፉ ላይ የተከተቡ ድርሳናት ያትታሉ። ወደ ኋላ ተመልሰን ይሄን ዘመን ስንቃኝ የዘር፣ የሀይማኖት፣ የፆታ፣ ሰብዓዊ መብት፣ የእኩልነት ጥያቄዎቸ ወዘተ . ጮህ ብለው መሰማት የጀመረበት ነበር። ፅንሰ ሀሳቡ በዚህ ተመሳሳይ ዘመን ጥቅም ላይ መዋል የጀመረበት መግፍኤም ይሄው ነው። በሌላ በኩል ፅንሰ ሀሳቡ ከግራ ዘመም አይዶሎጂ ማለትም ከሶሻሊስትና ኮሚኒስት ርዕዮት ጋር ተያይዞ እንደመጣ ይነገራል።
ሆኖም ብያኔው ግን በርዕዮት አለሙ ልክ የተሰፋ ነው። የፓርቲውን ሕገ ደንብ የሚያከብር መሪ ወይም አባል እንደ ፖለቲካዊ ትክክለኛ ይቆጠራል። በ1980ዎቹ አጋማሽ ደግሞ ሀሳቡ ከተለያዩ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ፕሮግራሞች እና ከአካዳሚያዊ ነፃነት ጋር ተያይዞ ይወሳ ነበር። ይሁንና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1991 ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ በሚቺጋን ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ስለ “ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት “ አሳሳቢነት ከተናገሩ ወዲህ ፅንሰ ሀሳቡ ከስርዓተ ትምህርት ክለሳ ፣ ከምረቃ ስነ ስርዓት ንግግር ደንብ ፣ ከጾታና ዘር ጥቃት ፣ ወዘተ ጋር መያያዝ ጀመረ ።
የፅንሰ ሀሳቡ ተገዳዳሪዎች ደግሞ ከአስተሳሰብ ፖሊስነት thought police እና መልካም ስምን ፣ ዝናን ከማጥፋት ፣ ከማጉደፍ (McCarthyism ) ጋር ያያይዙታል። ሆኖም ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ፖለቲካን ከሁሉም ማለትም ከሰብዓዊነት፣ ከፍትሐዊነት፣ ከእኩልነት፣ ከግልፅነት ፣ ከተጠያቂነት ፣ ከመብት ፣ ከአብሮነት ፣ ከእርቅ ፣ ከሰላም ፣ ከመነጋገር፣ ከመቀባበል፣ ወዘተ . አስበልጦ የመመልከት መጥፎ አባዜን መሞገት ነው።
ፅንሰ ሀሳቡ ስራ ላይ ከዋለ ከ80 ዓመታት በኋላም ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ዛሬም አወዛጋቢ፣ አነጋጋሪ ነው። በተለይ የአሜሪካው የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቲዊተርም ሆነ በመደበኛ ሚዲያዎች መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት ማንን እንደሚያስቀይም ? የማንን መብት እንደሚጋፋ ? የንግግራቸው ፣ የቲውታቸው ትርጉሙ ፣ አንድምታው ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀድመው ስለማያመዛዝኑ ከፖለቲካዊ ትክክለኝነት አንጻር በተደጋጋሚ ነጥብ ሲጥሉ ይስተዋላል ።
ቲዊት ባደረጉ ለጋዜጠኞች መልስ በሰጡ ቁጥር ፊደላቸው ፣ አፋቸው ወለም እያለው ምህረት የማያውቀው ሚዲያም እግር በእግር እየተከተለ ሲያብጠለጥላቸው እሳቸውም አፋቸውን ጣታቸውን መሰብሰብ ቢቸግራቸው እውነቱን መዘርገፍ እንጂ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ጉዳዬ አይደለም ማለት ጀመሩ። በእርግጥ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ማለትም ሚዲያ፣ ሕግ አውጭና ተርጓሚ ፣ ሲቪል ማህበራት ፣ ወዘተ . ባለበት ሀገር የፕሬዝዳንቱም ሆነ የፖለቲከኞች፣ የጋዜጠኞች፣ የተሟጋቾች፣ የሀይማኖት መሪዎች ፣ ወዘተ . የአፍ ወለምታ ሆነ ፖለቲካዊ ኢትክክለኝነት ሳይውል ሳያድር በቅቤ ስለሚታሽ ስለሚታረም ያስተዛዝብ ይሆናል እንጂ ያን ያህል ዘላቂ ጉዳት አያደርስም። ሰሞኑን ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደራቸው ከሳኡዲ አረቢያ ጎን የሚቆመው
“ ለምናደርግላት ወታደራዊ እገዛ እጅ በእጅ በጥሬው ስለምትከፍለን ነው።“ በማለት የሳቱት ፖለቲካዊ ትክክለኝነት የአሜሪካ ወታደሮች ለግዳጅ የሚሰማሩት የሀገራቸውን ደህንነት፣ ጥቅምና እሴት ለማስከበር እንጂ በቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይነት mercenaries አይደለም በሚል ከግራም ከቀኝም አቧራ እያስነሳ ነው። ፕሬዚዳንቱ በዚያ ሰሞን ትውልደ ሶማሊያዊ ሴት የምክር ቤት አባልንና ሌሎችን ሶስት ባልጀሮቿን “ የምንሰራው ነገር ካልተዋጠላቸው ወደ ሀገራቸው መመለስ ይችላሉ ። …” ከዚያ በፊት ደግሞ ሴቶችን ፣ ቀደምት አሜሪካውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን ፣ አፍሪካውያንና ሜክሲኮአውያን በተመለከተ አይደለም ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትላንት ከተወለደ ብላቴና የማይጠበቅ ነውረኛ ነገር በመናገራቸው ማወዛገቡ ይታወሳል ።
በሽግግር ወይም በመሰራት ላይ ላለች እንዲሁም አንድነቷ በቋፍ ላይ ለሚገኝ ሀገር ግን ፖለቲካዊ ትክክለኝነት የልብ ትረታዋ ነው ። እንደ ‘ ጥላ ወጊ ‘ stroke በድንገት ሊጥላት፣ ሽባ አድርጎ አሳስሮ የአልጋ ቁራኛ ሊያደርጋት ይችላል ። ለውጡን ሊቀለብሰው ከፍ ሲልም ወደለየለት ብጥብጥ ሊዘፍቀን ይችላል። ለመሆኑ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ምንድን ነው ?
መሪዎች ፣ ፖለቲከኞች ፣ ተሟጋቾች ፣ ጋዜጠኞች፣ ልሒቃን ፣ መምህራን ፣ የሀይማኖት መሪዎች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ አባ እማ ወራዎች ፣ በአጠቃላይ ሰዎች አንድን ቡድንም ሆነ የሕብረተሰብ ክፍል የሚያስከፋ፣ የሚያስቆጣ ንግግርም ሆነ ሌላ ያልተገባ ድርገት መፈፀም እንደሌለባቸው የሚያሳስብ ፅንሰ ሀሳብ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ይባላል። ሀገራችንም በፖለቲካዊ ኢትክክለኝነት የምትንጠራወዝ ፣ የምትላጋ ፣ የምታተኩር (Obssesed ) ናት ማለት ይቻላል። በተለይ ካለፉት 19 ወራት ወዲህ በአዳራሽ ፣ በአደባባይ ፣ በመደበኛ ሚዲያ ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ፣ ወዘተ . በለውጥ ኃይሉ፣ በተፎካካሪው ፣ በተሟጋቹ ፣ በልሒቁ ፣ በሀገር ሽማግሌው፣ በሀይማኖት መሪው ፣ በታዋቂ ሰው ፣ ወዘተ… በተደረጉ ንግግሮች ፣ በተሰጡ አስተያየቶች ፣ መልሶች ፣ በተላለፉ ንግግሮች ፣ በመግለጫዎች ፣ ወዘተ . የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ልምሻዎች ተከስተው ያስከፉት ብሔር፣ ሀይማኖት ፣ ማንነት ፣ አይዶሎጂ ፣ “ መስመር “ ፣ ወዘተ ነበር ።
ይሁንና የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ሆን ተብሎም በአፍ ወለምታም ሊጣስ ይችላል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ኃላፊነት እንደመጡ ወደ ተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ሕዝብ ባነጋገሩ ወቅት የተለያዩ ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን የሚያስነሱ ግርታዎችን ቀስቅሰው ነበር። የዛሬው የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር የዛን ጊዜው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር የአዲስ አበባ ከተማን ሕዝብ ምጣኔ በተመለከተ ተናገሩት ተብሎ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ እንደ ሰደድ እሳት ተዛምቶ ፖለቲካዊ ሰብዕናቸው ላይ ጥላ አጥልቶ ነበር። ከብዙ ዝምታ በኋላ የተናገሩበትን አውድና ንግግራቸውም ተዛብቶ መጠቀሱን በአንድ መድረክ ከገለጹ በኋላ በተወሰነ ደረጃ ጉዳቱን መቀነሰ ቢችሉም።
ወደ ቀደመው ቦታው ግን መመለስ የቻለ አይመስልም። እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ደግሞ ኦዴፓ አዲስ አበባ ላይ ያነሳው የባለቤትነት ጥያቄ ከፖለቲካዊ ትክክለኝነት አንጻር ዛሬ ድረስ የሚንከባለል ውዝግብ ቀስቅሷል። የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “ አክሱም‘ ለእንቶኔ ‘ ምኑ ነው ? “ እንዲሁም የተወለዱበትን ሕዝብ ስም ጠርተው “… ከዚህ ወርቅ ሕዝብ መፈጠሬ ያኮራኛል ። …” በማለታቸው ከፖለቲካዊ ትክክለኝነት አንጻር ትልቅ ነጥብ አስጥሏቸው ነበር። ፓርቲን ከሕዝብ ጋር ማመሳሰል፣ ገዥ መደብን ከአንድ ብሔር ጋር ማያያዝ፣ አንድን ዕምነት ከአንድ ብሔር ጋር ማቆራኘት ፣ ሰንደቅ አላማን ከአንድ ቤተ ክርስቲያንና ጎሳ ጋር ማመሳሰል አንድ ማድረግ እንደ ዜጋም እንደ ሀገርም ሁል ጊዜ የምንስታቸው የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ኢላማዎች ናቸው ።
በተለይ በአዲስ አበባ የኢሬቻ በዓል በታላቅ ድምቀትና በሰላም ለመጀመሪያ ጊዜ መከበሩ የፈጠረውን ደስታ በወጉ አጣጥመን ሳንጨረስ ለሀገር ግንባታ የሚኖረውን አውንታዊ አስተዋጽኦ አስልተን ሳናበቃ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ኦቦ ሽመልስ አብዲሳ ሳቱት የተባለው የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ኢላማ ቀደም ሲል ከተፈጠሩ ፖለቲካዊ ኢትክክለኝነቶች ጋር ተዳውሮ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ መሆናቸው የፈጠረብንን ሀሴት በቅጡ ሳናጣጥም አዲስ አበባ ላይ የተቃውሞ ሰለፍ መጠራቱ የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል። ከእያንዳንዱ ፖለቲካዊ ኢትክክለኝነት ጀርባ የሚከፋ፣ የሚያኮርፍ ፣ የተገለለ፣ ኢላማ የተደረገ የሚመስለው የሕብረተሰብ ክፍል መኖሩን ለምን በተደጋጋሚ እንደምዘነጋ ሁል ጊዜ እንቆቅልሽ ይሆንብኛል።
ይሁንና የሀገራችንም ሆነ የውጭ አንዳንድ ልሒቃን ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን የንግግርና የሀሳብ ነፃነትን እንደሚገድብ ያወሳሉ። የሜሪ ላንድ ዩኒቨርስቲው ዳን ሞለር ፖለቲካዊ ትክክለኝነት የንግግር ነፃነት የመገደብ ጉዳይ ሳይሆን ነፃነቱ የሌላውን መብት ፣ ባህል ፣ ታሪክ ፣ ማንነት ፣ ወዘተ . በማይነካ ፣ በማያንቋሽሽና በማይሸረሽር መንገድ የመጠቀም አግባብ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። አላማውም፦
1ኛ. ተጋላጭ ፣ ተገላይ እና በታሪክ አጋጣሚ ተጠቂ የሆኑ የሕብረተረብ ክፍሎችን መከላከል ።
2ኛ. ሕዝቡ የሚወያይባቸው ፣ የሚነጋገርባቸው ርዕሰ ጉዳዮችን በማረቅ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቂ እንዳይሆኑ መስራት።
3ኛ. በዜጎች መካከል ቁጣን ፣ ግጭትን ፣ ጥላቻን የሚቀሰቅሱ ንግግሮችን መከላከል መሆኑን ያሳያሉ ።
ይሁን እንጂ ቀለል ባለ ምሳሌ ሲያስረዱ አንድን የሕብረተሰብ ክፍል ዝቅ የሚያደርግ የታሪክ
የመማሪያ መፅሐፍት እንዲታረም መጠየቅ
የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም።
እንደ ታዋቂው የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ግሌን ሎሪ ያሉም ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ሀሳብን የመግለፅና የንግግር ነፃነትን እንደሚገድብ አድርገው የሚወስዱ አሉ። ሎሪ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት የሚቃወሙበት ሌላው መከራከሪያ ራስን መመርመር ማቀብ ( self cencorship) ያስከትላል በሚል ነው። የጀርመኑ ፖለቲከኛ ፊሊፕ ጄኒንገር ስለናዚ ዘመን ጀርመናውያን በማውራቱ ብቻ የናዚ ደጋፊ ወይም ፀረ ፂወናዊ እንዳልሆነ እየታወቀ በመናገሩ ብቻ ከፖለቲካ ህይወቱ እንዲገለል ተደርጓል። የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ በሚል መሆኑ ነው ። የዋሽንግተን ከንቲባ ሹመኛም በአንድ ወቅት ጓደኞችን “ niggardly“ ( ቆንቋኖች ) ብሎ መሳደቡ ቁጣ በመቀስቀሱ ከኃላፊነቱ በገዛ ፈቃዱ ለመልቀቅ ተገዷል። ከዚህ ከዚህ አንፃር ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ስንመዝነው ለምዕራባውያን ለቅንጦት የቀረበ ሊመስል ይችላል እንደኛ በለውጥ በሽግግር ላይ ላለ ሀገር ግን የህልውና እንዲሁም የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል ።
እንደ መውጫ
በሀገራችን ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን በማበረታታት ረገድ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የአንበሳውን ድርሻ እና ቀድሞ ተነሳሽነቱን በመውሰድ አርዓያ ሊሆን ይገባል። የዛሬው ግንባርም ሆነ ነገ ውህድ ሆኖ የሚወጣው ፓርቲ ከመሰል ፓርቲዎች ልምድ በመቀመር በሕገ ደንቡ ላይ በማያሻማና ግልፅ በሆነ ቋንቋ ስለፖለቲካዊ ትክክለኝነት አስፈላጊነት ሊደነግግ በቀጣይም ለአባላቱና ለደጋፊዎችም የግንዛቤ ማስጨበጫ ተከታታይ መድረኮችን ሊያዘጋጅ ይገባል።
በከፍተኛ ትምህርትም ሆነ በሌሎች ተቋማት የሚገኙ ልሒቃን በፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ምንነትና አስፈላጊነት ላይ ሀሳብ በመለዋወጥና ችግሩን ከእነ መፍትሔው በማመላከት የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት ይጠ በቅባቸዋል። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የድርሻቸ ውን ከመወጣት ባሻገር የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ጥያቄን የሚያስነሱ ጉዳዮችን በመለየት መሪዎቻቸው በመግለጫዎቻቸው በንግግሮቻቸው በቅስቀሳቸው ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ታሳቢ እንዲያደርጉ አባሎቻቸ ውና ደጋፊዎቻቸውም ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል ።
ሚዲያው በአርትኦት ፖሊሲው ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን በማካተት ኃላፊነቱን ለመወጣት አበክሮ መስራት ይጠበቅበታል ።
እንደ ዜጋ ደግሞ ሁላችንም የምንፅፈው፣ የምንና ገረው፣ የምንስለው ፣ የምናዜመው ፣ የምንቀርፀው፣ ወዘተ . የሌላውን ወገን ታሪክ ፣ ባህል፣ እሴት ፣ ሀይማኖት፣ ማንነት ፣ ወዘተ . የማያናንቅ ፣ የማያንኳስስ እንዲሁም በሌላው ቁስል ላይ እንጨት የማይሰድ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባናል ።
የሰለጠነ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ እስክንጨብጥ፤ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት በአግባቡ እስኪጎለብቱ፤ በመንግስት አካላት ማለትም በሕግ አውጭው፣ ተርጓሚውና አስፈፃሚው መካከል ያለው ግንኙነት ሚዛናው እስኪሆን ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን የሙጥኝ ብሎ መያዝ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ስንከተለው የነበረ አገዛዝ ያመጣብን መለያየት መጠራጠር ሳያንስ በፖለቲካዊ ኢትክክለኝነት ሀገር ልትታመስ ሕዝብም ሊደናገር አይገባም ።
ፖለቲካዊ ትክክለኝነት አሁኑኑ ! ! !
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2012