
ሰዎች ለመዝናናት የተለያ ስፍራን ምርጫቸው ያደርጋሉ። አንዳንዶች በቤታቸው ረጅም ሰዓትን ሲያሳልፉ ሌሎች ደግሞ የምሽት ሰዓትን በተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎች ላይ ያሳልፋሉ። ሌሎች ደግሞ አዕምሯቸውን ከውጥረት ነጻ ለማድረግ የሚያሳልፉት ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቢሆን ይመርጣሉ። የመዝናኛ ስፍራዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ በርከት ብለው በየደረጃው ይገኛሉ። አንዳንዶች ከረጅም ሥራ ቀን በኋላ በፍጥነት ወደቤታቸው መግባት ምርጫቸው ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ ከአድካሚ የሥራ ቀን በኋላ ወደቤታቸው ከመግባታቸው በፊት ከጓደኞቻቸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ራሳቸውን በመጠጥ ራሳቸውን ለማዝናናት ይሞክራሉ።
ሰለሞን እና ገዛኸኝ በአንድ ተቋም ውስጥ የሚሰሩ ሲሆን የሥራ ባልደረቦች ናቸው። በሥራ ቀናቸው አብረው ከመዋል አልፈው ከሥራ በኋላ የሚኖራቸውንም ጊዜ በአብዛኛው አብረው ያሳልፋሉ።
ሰለሞን ታደሰ እና ገዛኸኝ አበበ በሚሰሩበት ተቋም አኩል የተቀጠሩ በመሆናቸው የሥራ ቦታቸውን ለመልመድ በሚያደርጉት ሂደት ሊቀራረቡ ችለዋል። ታዲያ ከሥራ በኋላ የሚያሳልፉበት የከበደ ግሮሰሪ ደንበኛ ሆነዋል፣ በዚያ ሲጫወቱ አምሽተው ወደየቤታቸው ይሄዳሉ።
ሙያ በልብ
ሰለሞን እና ገዛኸኝ በሥራ ቦታቸው አንዲት አይናቸው ውስጥ የገባች የሥራ ባልደረባቸውን ተመልክተዋል። ተመልክተው በልባቸው ከጅለዋታል። ነገር ግን እርስ በእርሳቸው አንዳችም እንኳ የሚሰማቸውን ትንፍሽ አላሉም። ነገር ግን እርስ በእርሳቸው በሚያደርጉት ድርጊት ሳይጠረጥሩ አልቀሩም።
ሁለቱም ወጣቶች ልጅቷን ለየብቻ ለማነጋገር ጥረት አድርገዋል። ነገር ያገኙት መልስ ሰው አለኝ የሚል በመሆኑ አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠራጥረዋል።
ከሥራ በኋላ
ልክ እንደሁልጊዜው በሥራ ያለፈ ቀን ነበር። ሥራቸውን በእለቱ ደንበኞቻቸውን በመቀበል፣ የተቀበሏቸውን ትዕዛዞች በመስራት፣ ሰርተው የጨረሱትን ሥራዎች እንዲሁ ለአለቆቻቸው በማስረከብ የሥራ መውጫ ሰዓት መድረሱን አልተመለከቱም።
በዛሬው ቀን የነበሯቸውን ሥራዎች አምሽተው እንዳጠናቀቁ ሁልጊዜ ወደሚያመሹበት 6 ኪሎ አካባቢ የሚገኝ ከበደ ግሮሰሪ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ነው። በተደጋጋሚ በመምጣታቸውም በዐይን የሚያውቋቸው ሰዎች በዚሁ መዝናኛ ቦታ አሉ። ከአስተናጋጆቹም ጋር የወዳጅ ያህል ቅርበት አላቸው።
ሰለሞን በባህሪው በመሆኑም ተጫዋች እና ከሰዎች ጋር በቶሎ ተግባቢ ሲሆን በአንፃሩ ገዛኸኝ ደግሞ ዝምተኛ የሚባል እና ከቅርቡ ሰዎች ጋር ብቻ በይበልጥ ተጫዋች የሚሆን ነው።
ታዲያ በመዝናኛ ስፍራ ጨዋታም አልኮልም አንድ ሁለት እየተባለ ጨዋታ የሚነሱ ጨዋታዎችም በሌላ ርዕስ እየተተኩ ሰዓቱም በዚያው ይነጉዳል።
ታዲያ በዚህ ወቅት ጓደኛማቾቹ ስለፍቅር ሕይወታቸው ጫፍ ጫፉን ማውጋት ጀመሩ። ነገር ግን በሥራ ባልደረባቸው ዐይን ፍቅር መውደቃቸውን አስቀድሞ ሰለሞን የጨዋታውን መስመር ከፈተው። በሁኔታው የደነገጠው ገዛኸኝ አስቀድሞ ዐይኑ ውስጥ እንደገባች ለመናገር ጥረት ቢያደርግም ባለመግባባት ተጠናቀቀ። በጉዳዩ የተበሳጨው ሰለሞን ጓደኛው ላይ አትቀማኝም አይነት ፉከራ ፎክሮ እዚያው ጥሎት ከግሮሰሪው ወጣ።
እላፊ ሰዓት
ሰኔ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ሰለሞንና ገዛኸኝ እንደቀድሞው አብረው በመሀልም አልዋሉም በሥራ ቦታቸው ሰላምታም አልተለዋወጡም። እንዲሁ ሳይነጋገሩ የሥራ ሰዓት አለፈ። ሰለሞን አስቀድሞ ወደ ሚያመሽበት ግሮሰሪ ብቻውን አመራ። በግሮሰሪው ካሉ ሰዎች ጋር አንዳንድ ጨዋታዎችን እየተቀባበለ ያደርጋሉ።
ታዲያ ሰዓቱ እየመሸ ሲሄድ ገዛኸኝም ወደተለመደው ቤት አቀና ፣ ነገር ግን እንደከዚህ በፊቱ ከጓደኛው ጋር አልተቀመጠም። ፈንጠር ብሎ በቅርብ ርቀት ተቀምጦ ከራሱ ጋር በልቡ ማሰላሰሉን ቀጠለ። ተለያይተው መቀመጣቸውን የተመለከቱ ደንበኞች በጉዳዩ ግራ ቢጋቡም ቀልድ ቢጤ ጣል ከማድረግ ባለፈ ይህ ነው የሚባል የከረረ መሆኑን አላስተዋሉም።
አስቀድሞ በግሮሰሪው ተቀምጦ ሲዝናና የነበረው ሰለሞን በአጠገቡ ባንኮኒ ሰራተኛ ጋር ንግግር ያደርጋል። ታዲያ በዚህ ወቅት ድምጹን ከፍ አድርጎ በመሆኑ ገዛኸኝ እርሱን የተመለከተ መሆኑን ልብ ብሏል። ቀና ብሎ በመመልከትና በመገላመጥ ተጨማሪ ንግግሮችን አስቀርቷል። በመሀል ግን ሰለሞን ንግግሩን ወደ ስድብ በመቀየር ፈሪ ነህ ስለዚህ ምንም አታመጣም ሲል ወደገዛኸኝ የማጥቃት የሚመስል ንግግር ይሰነዝራል። ይህ ሊታገሰው የማይችለው የሆነው ገዛኸኝም ለምን አትተወኝም በሚል ጉዳዩ የሥራ ባልደረባቸው ምርጫ እንጂ የእነርሱ ውሳኔ አለመሆኑን በመሆኑም ተጨማሪ ንግግር እንደማያስፈልግ ይነግረዋል።
በዚህ ግዜ ባላሰበው መልኩ ሰለሞን የሥራ ባልደረባውን አንገት አንቆ በመያዝ ግብግብ ፈጠሩ ። ገዛኸኝም ራሱን ለማዳን በሚያደርገው ግብረመልስ በድንገት ሰለሞን ባንኮኒው አጠገብ የነበረውን የቢራ ጠርሙስ አንስቶ ጭንቅላቱን በተደጋጋሚ መታው። በግሮሰሪው ውስጥም ሁካታ ሆነ።
በአካባቢው በተፈጠረው ጩኸት የአካባቢው ፖሊስ በቦታው የተገኘ ሲሆን ግጭቱን ካስቆመ በኋላ ሰለሞንን ወደ ጣቢያ ገዛኸኝን ደግሞ ወደ ሕክምና ተቋም እንዲያመራ አደረገ። በጉዳዩ ላይ ጥርት ያለ መረጃን ለመያዝ እና የተጎጂውን የሕክምና ውጤትና የጉዳት መጠን ለማጣራት በሚያደርገው ሂደትም ገዛኸኝ ጭንቅላቱ ውስጥ በፈሰሰ ከፍተኛ ደም ምክንያት ከቀናት በኋላ ሕይወቱ አለፈ።
የወንጀሉ ዝርዝር
ወንጀሉ በተፈጸመበት እለት ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ ጉዳዩ በተፈጸመበት በ ሰኔ ወር ቀን 17/2015 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ አራት ሰዓት ከበደ ግሮሰሪ አንደኛ ምስክር በረከት ግሮሰሪ ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሟች ገዛኸኝ ሕይወት መጥፋት ጥፋተኛ ናቸው ያላቸውን ተጠርጣሪዎችን እና በቦታው የነበሩ ምስክሮችን በመያዝ ወንጀሉን ማጣራት ጀመረ። በዚህም ተከሳሽ ሰለሞን የሥራ ባልደረባው የሆነውን ገዛኸኝ እኔ የምወዳትን ሴት ቀምተኸኛል በሚል በግሮሰሪ ውስጥ በተፈጠረ ፀብ አንገቱን አንቆ በመምታት እና በቢራ ጠርሙስ ጭንቅላቱን በመምታት ሟች በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል። በዚህም ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539 (1) ( ሀ ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በተራ የሰው መግደል ክስ መስርቷል።
ማስረጃዎች
ዐቃቢ ሕግ በመሰረተው የክስ ወንጀል ያስረዱልኛል ያላቸውን ሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች አጠናክሮ አቅርቧል።
በሰው ማስረጃዎች ወንጀሉን የፈጸሙት ተከሳሾችን ይለዩልኛል ያላቸውን በቦታው የነበሩ ሰዎች በመሰብሰብ ወንጀለኞችን የመለየት እና የማረጋገጥ 11 የሰው ማስረጃዎችን ተጠቅሟል ሥራ ተሰርቷል። ዐቃቢ ሕግ ባሰናዳው የሰነድ ማስረጃ ሟች የመጀመርያ ሕክምና ካደረገበት የየካቲት 12 ሆስፒታል የሕክምና ማስረጃ ከነትርጉሙ የሞት የምስክር ወረቀት ማረጋገጫ፣ የሟች ማንነት ጉዳት የደረሰበትን የሟች የሰውነት ክፍል ፣ ወንጀሉ የተፈጸመበትን ቦታ ለማሳየት የተነሱ 31 የፎቶግራፍ ማስረጃዎችን አቅርቧል። እንዲሁም 11 ምስክሮች ተከሳሾችን ሲመርጡ ለማሳየት የተነሳ የተነሳ 54 ፎቶ ቀርቧል።
እንዲሁም የሟች አስክሬን ምርመራ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ የተላከ የአስክሬን ምርመራ በውጫዊ እና ውስጣዊ ክፍል ላይ ደረሰውን የጉዳት መጠን አስቀምጧል። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በላከው እና ዐቃቢ ሕግ ካስቀመጠው ትርጉም ጋር ውጫዊ አካል ሟች ጉዳት በደረሰበት የሰውነት ክፍሉ ላይ የደረሰበት መጠን የሞቱ መንስኤ ከደረት ጀርባ በስለት ጉዳት መድረሱን እና በጭንቅላቱ ውስጥ ደም መፍሰሱን ገልጾ የጉዳት መጠን አብራርቶ ለፍርድቤቱ ልኳል።
ውሳኔ
በዚህ የክስ መዝገብ አራት ተከሰሾችን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በቀን 4 ሕዳር ወር 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ክስና ማስረጃዎችን ከሕግ ጋር አገናዝቦ በሰጠው ውሳኔ ተከሳሽ ሰለሞን ታደሰ በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ ሰጥቷል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም