
ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር ነች። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከ25 ዓመት በታች ነው። ይህ ማለት የወደፊቷ ኢትዮጵያ በወጣቶች እጅ መሆኗን ያሳያል፤ ወጣቶች የሀገር ተረካቢዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስጠባቂዎች ናቸው። ወጣቶች ዓለምን የመለወጥ ጉልበት፣ ሃሳብ እና ችሎታ አላቸው ብዬ አምናለሁ። ለዚህ ነው በተከታታይ ሳምንታት በመጋቢ አዕምሮ አምድ ላይ ወጣቶች አንዴት እራሳቸውን ለተሻለ ዓላማ ማነሳሳት አንዳለባቸው ስፅፍ የነበረው።
እንደሚታወቀው በሀገራችን አብዛኛዎቹ ወጣቶች ሥራ አጥነት ውስጥ ይገኛሉ፤ በዚህ ሁኔታ መሰላቸትና ተስፋ መቁረጥ እየተፈታተናቸው ነው። ከሥራ አጥነት፣ ከተመቻቹ ዕድሎች እጦት እና ከኢኮኖሚ ችግሮች ጋር እየታገሉና እራሳቸውን እየወቀሱ ይገኛሉ። እንዲያውም አንዳንዶች ስኬትን በዚሁ በሀገራቸው ማሳካት አይቻልም የሚል እምነት ላይ ደርሰዋል። በዚህም ባሕር ማዶ ተሻግረው ለመሄድ ሲሞክሩ ለበርካታ ፈተናዎችና ስቃዮች ተዳርገዋል። ስኬት ከኢትዮጵያ ውጭ ብቻ ነው የሚገኘው የሚለው አስተሳሰብ ለበዙዎች ተጨማሪ ውስብስብ ችግር ይዞ እየመጣ ነው።
በዚህ ምክንያት በዛሬው ፅሁፌ ላይ ስኬታማ ለመሆን፣ በሕይወት ዘመኑ ለአገር ኩራት የሆኑ ታላላቅ ነገሮችን ለመስራት ለሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አገራቸውን ሳይለቁ ሕልማቸውን ማሳካት አንደሚችሉ አመላክታለሁ። የተሻለ ሕይወትን ለሚመኙና ውጤታማነትን ለሚናፍቁ ነገር ግን ከየት መጀመር እንዳለባቸው ለማያውቁ የሚከተሉት መፍትሄዎች ለመነሻነት እንደሚጠቅማቸው አልጠራጠርም። ለዚህ ነው ወደፊት ለመራመድ ተነሳሽነት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ትክክለኛ ምርጫ መሆኑን የምገልፀው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ለወጣቶች ሕይወት ቀላል ነው የሚል እምነት የለኝም። ብዙዎች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ ማግኘት ፈተና ነው። አንዳንዶች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ሲገደዱ በሌላ የሙያ ስልጠና ላይ ለመሳተፍና ሙያዊ ትምህርታቸውን ለመቀጠል አዳጋች ይሆንባቸዋል። አንዳንድ ወጣቶች በራሳቸው ጥረት ንግድ ቢጀምሩም በድጋፍ እጦት ሲከስሩና አልባሌ ቦታ ላይ ሲውሉ ማየት የተለመደ ነው። ብዙዎች ትልቅ ሀሳቦች እያሏቸው ነገር ግን እንዴት ወደ መሬት ማውረድና ወደስኬት መቀየር እንደሚችሉ አያውቁም። እነዚህ ፈተናዎች ብበዙ ወጣቶች ላይ ብስጭትን፣ ተስፋ መቁረጥን እና ወዳልተፈለጉ ባሕሪና ልምዶች ይወስዷቸዋል። ለዚህ ነው አንዳንድ ወጣቶችን ስንመለከት ለችግሮቻቸው መፍትሄ በማፈላለግ ፋንታ በማማረር ጊዜያቸውን የሚያባክኑት። ምን አልባት አንተም የዚህ ችግር ሰለባ ልትሆን ተችላለህ። ታዲያ አንድ ነገር ልትገነዘብ ይገባል። ዛሬ ለዚህ ችግር መፍትሄ የሚሆኑ ሀሳቦችን ይዤያለሁ መጥቻለሁ። አንድ ነገር ልታውቅ ይገባል። እሱም ተግዳሮቶች የሕይወት መጨረሻ አለመሆናቸውን ነው። እንዲያውም ችግሮች ለማደግ እድሎች ናቸው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ብለህ ልትሞግት ትችላለህ። እውነታው ግን ይህ ነው። ታላላቅ የስኬት ታሪኮች የሚመነጩት ተስፋ ለመቁረጥ ፈቃደኛ ካልሆኑ ሰዎች ነው። ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮችን አሸንፈው ስኬት ያስመዘገቡ ወጣቶች አሏት። ታዲያ አንተ ከእነዚህ ጥቂት ወጣቶች መካከል አንዱ ለመሆን ተዘጋጅተሀል? ምን ማድረግ አለብኝ የሚል ጥያቄስ በአዕምሮህ ይመላለሳል። ምላሹን ከሚከተሉት ነጥቦች ታገኘዋለህ።
አንድ ነገር ማወቅ ይኖርብሀል ሰርቆ አሊያም ከስነምግባር ባፈነገጠ ድርጊት ውስጥ ተሰማርቶ ካልሆነ በስተቀር በአንድ ጀምበር የተሳካለት ማንም የለም። ዛሬ የምታያቸው ታላላቅ ሰዎች (ውጤታማ ሥራ ፈጣሪዎች) ሁሉ ከትንንሽ ጉዞ በትጋት የጀመሩ ናቸው። ኢትዮጵያዊ ታዋቂ አትሌቶቻችን ዛሬ የወርቅ ሜዳሊያ ከማግኘታቸው በፊት ለዓመታት ብቻቸውን በየጫካው፣ ተራራና ጉድባዎች ብርድ፣ ፀሀይ እና አስፈሪ ጨለማን ተቋቁመው ሰልጥነዋል። ስኬታማ የንግድ ሥራ ባለቤቶች ዛሬ የጥረታቸውን ፍሬ ከማየታቸው በፊት ብዙ ጊዜ ወድቀው ተነስተዋል። ታዋቂ ሙዚቀኞች፣ አርቲስቶችና ደራሲዎች ዛሬ ታዋቂና ተወዳጅ ከመሆናቸው በፊት ለብዙ ሰዓታት ቤታቸውን ዘግተው ልምምድ አድርገዋል፤ ለስኬታማነታቸው ላባቸውን አንጠፍጥፈዋል።
ለዚህ ነው ወጣቶች (ኢትዮጵያውያን) ጠንካራ የሥራ ስነምግባር ማዳበር አለባቸው የምለው። እንቅልፍህን ምርጫ ከማድረግ ቀደም ብለህ መነሳት፣ እቅዶችን ማውጣት እና እራስህን ሁሌም ዝግጁ ማድረግ የጠንካራ ሰራተኛና የስኬታማ ሰው መገለጫ ነው። አሁን አሁን ብዙ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ወይም ቴሌቪዥን በመመልከት ጊዜ ሲያባክኑ እመለከታለሁ። ምናልባት አንተም በማይመለከቱህ ጉዳዮች ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ እያጠፋህ ይሆናል። እውነቱን ስነግርህ ግን ስኬታማ ሰዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ ይጠቀማሉ፤ ያነባሉ፣ አዳዲስ ክህሎቶችን ይማራሉ፤ እንዲሁም ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ሌት ተቀን ይሰራሉ።
አንተም የእነዚህን ሰዎች ፈለግ ተከትለህ ስኬታማ ለመሆን ከፈለግክ እራስህን አበክረህ ጠይቅ። ‹‹ጊዜዬን እንዴት እየተጠቀምኩ ነው? በየጊዜው ምን ዓይነት ችሎታዎችን እየተማርኩ ነው? በየቀኑ እየተሻሻልኩ ነው?›› የሚሉ ጠንካራ ጥያቄዎችን በማንሳት እራስህን ሞግት። ይህንን ማድረግ የጀመርክ ግዜ የእውነትም መንቃት ትጀምራለህ።
ሕልምህን እውን ለማድረግ ትምህርት ለስኬት ቁልፍ ነው። የግዴታ ግን ስኬታማ ለመሆን ድግሪ፣ ማስተርስ፣ ፒ ኤች ዲ ሊኖርህ አይገባም፤ መደበኛ ትምህርት የእውቀት ምንጭ ቢሆንም እርሱ ብቻ ግን ስኬታማ አያደርግም፤ ለዚህ ነው ከመማር መቆም የለብህም የምልህ። አንድ ሁል ግዜ የሚያጋጥመኝ ነገር አለ፤ አንዳንድ ወጣቶች ትምህርት ከዩኒቨርሲቲ በኋላ ያበቃል ብለው ያስባሉ። ነገር ግን እውነተኛ ትምህርት እንዲያውም ከትምህርት በኋላ እንደሚጀምር አምናለሁ።
አሁን አሁን የዘመኑ ቴክኖሎጂ መማርን ቀላል አድርጎታል። ዛሬ በኦላይን ላይ ማንኛውንም ነገር በነጻ የመማር እድል ማግኘት ትችላለህ። እንግሊዘኛህን ለማሻሻል፣ ንግድ እንዴት እንደሚጀመር መሰረታዊ እውቀት ለማግኘት ወይም የቴክኒክ ችሎታዎችን ማግኘት ትችላለህ። በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ወጣቶች ሕይወታቸውን ለመለወጥ ኢንተርኔት ይጠቀማሉ። የኢትዮጵያ ወጣቶችም ይህንን መንገድ መከተል እንዳለባቸው አምናለሁ። በዚህ ምክንያት ነው አንተም የሕልምህ ዳርቻ ለመድረስ ክህሎትህን ማሳደግ እንዳለብህ የማምነው።
ዲግሪ ከማግኘት ይልቅ ችሎታን ማዳበር በጣም አስፈላጊ መሆኑን አምናለሁ። አሁን አሁን አሰሪዎች የምስክር ወረቀቶችን ብቻ አይመለከቱም፤ ችሎታን ጭምር እንጂ። ችግሮችን መፍታት የሚችሉ፣ በፈጠራ ችሎታቸው የላቁ እና ጠንክረው የሚሰሩ ሰዎችን በገበያው ላይ ይፈለጋሉ። ተምረህና ክህሎት ኖሮህ ሥራ ማግኘት ካልቻልክ የራስህን እድል መፍጠር ይኖርብሀል። ለዚህ ደግሞ ቀልጣፋና ለነገሮች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የሰለጠነ አዕምሮ ሊኖርህ ይገባል። እነዚህን ባወቅህ መጠን የበለጠ ዋጋ ያለህና ስኬታማ ትሆናለህ።
ኢትዮጵያ ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ብዙ እድሎች እንዳላት አምናለሁ። አንተስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ታስባለህ? ሀገሪቱ ችግሮችን ለመፍታት እና አዳዲስ ሀሳቦችን ለማምጣት የፈጠራ ክህሎታቸው የላቀና ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ወጣቶች ያስፈልጋታል ብለህ አታስብም? ለምሳሌ የኮምፒውተር ድግሪ አለህ ብለን እናስብ፤ ሆኖም ምንም ሥራ ከሌለህ በራስህ መፍጠር ይኖርብሀል፤ ስኬታማ ሰዎች የሚያደርጉት ይህንኑ ነው። ለምሳሌ የትራንስፖርት አገልግሎትን ቀልጣፋ እንዲሆን ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ መተግበሪያዎችን በኢትዮጵያ የጀመሩ ሰዎችን ተመልከት። እነዚህ ሥራ ፈጣሪዎች ላንተ ሕልም እውን መሆን መንገድ እንደሚያመላክቱህ አምናለሁ።
በእርግጥ ንግድ መጀመር ቀላል አይደለም። ነገር ግን በዓለም ላይ ያሉ እያንዳንዱ ትልልቅ ኩባንያዎች በጥቂቱ ጀምረው ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈው ነው ዛሬ ላይ የደረሱት። ይህንን ለማሳካት ኢትዮጵያውያንም ጠንክሮ የመስራት ባሕል አለን። ከቡና አምራች ገበሬዎች እስከ ጫማ ሰሪዎች ብዙዎች ከምንም ነገር ተነስተው ስኬታማ ነጋዴ ሆነዋል። ለዚህ አንተም ሆንክ ወጣቶች ይህንን ምሳሌ መከተል የሚኖርባችሁ። መንግሥት ወይም ሌላ ሰው እንዲረዳህ አትጠብቅ፤ ባለህ ነገር ጀምር። አነስተኛ ንግድ ለመጀመር ከፈለግህ እና ተሰጥኦ ካለህ ግዜህን አታባከን፤ አሁኑኑ ወደ ተግባር ግባ። የውሳኔ ሰዎች ናቸው ስኬታማ የሚሆኑት።
የዛሬው አስተሳሰብህ የወደፊትህ ማንነትህን ይወስናል። ኢትዮጵያ ምንም እድል የላትም ብለህ ካመንክ ውጤቱ ያው ያመንከው ነገር ነው የሚሆነው። ነገር ግን ሊሳካልህ እንደሚችል ካመንክ በሁሉም ቦታ እድሎችን ማየት ትችላለህ። አንድ ነገር በእጅጉ ያስቆጨኛል። ብዙዎች ኢትዮጵያውያን የውጭ ዜጎችን ያደንቃሉ። ምን ይሄ ብቻ ስኬት የሚገኘው ከኢትዮጵያ ውጭ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። ነገር ግን ይህ እውነት አይደለም። ይህንን ታውቃለህ? ብዙ ነጋዴና ኢንቨስተሮች ለንግድ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። አንተ ያላስተዋልከውን እና አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ችላ የሚሏቸውን እድሎች በሚገባ ይጠቀሙባቸዋል። ለዚህ ነው ችግሩ አገር አይደለም የምልህ። ችግሩ የአስተሳሰብ ነው። ለዚህ ነው ተስፋ ከመቁረጥህ በፊት አስተሳሰብህን ማረቅ የሚኖርብህ። አወንታዊ አስተሳሰብ ስኬትን ይስባል፤ ከማማረር ይልቅ መፍትሄዎች ላይ አተኩር። የሌለህን ከማሰብ ይልቅ ያለህን ተጠቀምበት። ስኬት ከአእምሮ ይጀምራል። ዛሬውኑ ግዜህን ሳታባክን እምነትህን አስተካክል!
ስኬታማ ሰዎችን ማድነቅ ብቻ ትርጉም የለውም፤ ከነሱ ተማር። ስለ መጡበት አስቸጋሪ መንገድ ጠይቅ፤ ለስኬት ስላደረጉት ትግል ለመረዳት ሞክር፤ ችግሮቻቸውን እንዴት እንዳሸነፉ መርምር። ስኬት ገንዘብ ማግኘት ብቻ አይደለም፤ ሌሎችን መርዳት ጭምር ነው። ኢትዮጵያ ለማኅበረሰባቸው የሚያስቡ ወጣት መሪዎች ያስፈልጓታል። ለዚህ ነው ሙሉ ስብዕና እንድትገነባና ልህቀት ላይ እንድትደርስ ከተሳካልህ ሌሎች እንዲሳካላቸው መርዳት የሚጠበቅብህ። ለስኬትህ የረዳህን እውቀት ለሌሎች አካፍል፤ አንተ የመጣህበት መንገድን የሚከተሉ ሀሳቦችን፣ አነስተኛ ንግዶችን ደግፍ፤ ለሌሎች አርአያ ሁን።
ሌላው እንደ ሀገር ከሀያላኑ ተርታ ለመሰለፍ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በጋራ መሥራት አለባቸው ብዬ አምናለሁ። ዓለማችን የግለሰቦች ጥረት ውጤት ነች። አንድ ሰው ከተሳካለት መላው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ይሆናል። ግለሰቦች ባደጉ ቁጥር ሀገር እየጠነከረ ይሄዳል። ለዚህ ነው አንተም ለሌሎች ግለሰቦች እድገት ቀና አመለካከት ሊኖርህ የሚገባው።
በመጨረሻም ይህንን ብዬ ልሰነባበት። የኢትዮጵያ ወጣቶች ትልቅ አቅም አላችሁ ብዬ አምናለሁ። የሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ በአንተ (በአንቺ፣ በእነሱና በእናንተ) ላይ የተመሰረተ ነው። እርግጥ ነው ፈተናዎች ሁል ጊዜ ይኖራሉ፤ ነገር ግን ከጥረትህ የሚያደናቅፍ ሰበብ ሊሆኑ አይገባም። ለዚህ ነው ጠንክሮ መሥራት፣ መማር፣ ማኅበራዊ ግንኙነትን ማጠናከር እና ትዕግስት የስኬት ቁልፎች መሆናቸውን የምነግርህ። በመሆኑም በራስህ እምነት ይኑርህ። ሕልምህን ከዳር ለማድረስ ተግተህ ሥራ። ኢትዮጵያ ሀገራችንን ብሎም ዓለምን ለመለወጥ ዝግጁ የሆኑ ወጣቶች ያስፈልጉናል። አንተም ያን ሰው ሁን። እርግጥ ነው ጉዞው ቀላል አይሆንም፤ ነገር ግን ሽልማቱ ከፍ ያለ ስለሆነ ጉዞህን እንዳታቋርጥ!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም