
ልጅነት…
ለእሷ የልጅነት ሕይወቷ በመልካም ትዝታ ይዋዛል። ለእናቷ ብርቅዬ ልጅ ናትና ያለችግር አድጋለች። ወላጅ አባቷ በሞት ሲለዩ ገና ሕጻን ነበረች። የእሳቸውን ማለፍ ተከትሎ እናት አንድዬ ልጃቸውን በስስት እያዩ ማሳደግ ጀመሩ። የዛኔ ትንሽዋ ልጅ የፈለገችውን ለማግኘት ቸግሯት አያውቅም። ያሻት ሁሉ እንደልቧ ይሟላላታል፡፡
ደስተኛዋ ፋጡማ ሁሴን ልጅነቷን በምቾትና በደስታ ማጣጣም ያዘች። የእሷ ዓለም ከእኩዮቿ የተለየ ነበር። በየቀኑ ከቤት የምታገኘው ፍቅር በስስት ይገለጻል። ወጥታ በገባች ቁጥር የሚናፍቁት እናት ስለእሷ የማይሆኑት የለም። ከዓይን የሚገባው የእናትና ልጅ ፍቅር ስብራት ሳያገኘው ዓመታትን ቆጠረ፡፡
አሁን ፋጡማ ዕድሜ ጨምራለች። ልጅነቷ አልፎ ወጣትነቷ ሲጀመር ደግሞ ልቧ አርቆ ማሰብ ያዘ። ብዙዎች እንደሚያደርጉት ዓረብ ሀገር ሄዳ ሠርታ መመለስ ፈለገች። እናቷ መቼም ከዓይናቸው እንድትርቅ አይሹም። ልጃቸው ካጠገባቸው እንድትሆን ፍላጎታቸው ነው። እንዲያም ሆኖ ሀሳቧን አልገደቡም። ከፈለገችው ደርሳ የልቧን እንድትሞላ ፈቀዱ።
በዓረብ አገር …
ፋጡማ ሕይወትን በዓረብ ሀገር አደረገች። ተወልዳ ካደገችበት የወሎዋ ‹‹ወግዲ›› ባሕር አቋርጣ የሄደችበት የሰው ሀገር ኑሮ ቀላል አይደለም። ስለነገ ዛሬን ዋጋ መክፈል የግድ ይላል። ጊዜ ቆጥሮ የሚመጣው ገንዘብ በዋዛ አይገኝም። ብዙ ላብና ድካም ይጠይቃል። እሷም ብትሆን ይህ አልጠፋትም። እናቷን እየናፈቀች፣ ሀገሯን እያሰበች በምትደክምለት ሥራ ነገን አሻግራ ታያለች፡፡
ፋጡማ ወደ ሀገር ቤት ልትመለስ ተዘጋጀች። የናፈቀቻት እናቷን የራቀቻት ሀገሯን ልታይ ጓግታለች። ጊዜው ሲደርስ ሁሉም እንዳሰበችው ሆነ። በሰላም ተመልሳ ከእናቷ የስስት ዓይኖች ጋር ተያየች። ሁለቱ ነፍሶች የልባቸው ሞላ፤ የሀሳባቸው ደረሰ። ሀገር ቤት በመጣች ጊዜ ወቅቱ ለመላው ዓለም ፈታኝ የሚባልበት ነበር። የሚሰማው ዜና ጆሮን ያስይዛል፣ የሚታየው ሐቅ ስለነገው ያሳቅቃል። የዛኔ በየትኛውም ቦታ የኮሮና ቫይረስ በስፋት መከሰቱ ነበር። ይህ ወቅት ለሁሉም በእጅጉ ፈታኝ፣ አሳሳቢ የሚባል ነው፡፡
ፋጡማ አሁን ከውድ እናቷ ጋር ነች። ኀዘንም ይሁን ደስታ በእናት ቤት ሲሆን ያምራል። ሀገሬው የወቅቱን እውነታ እንደመላው ዓለም እየተጋፈጠው ነው። ፋጤና እናቷም በዚህ መንገድ ማለፍ ይዘዋል፡፡
ዋል አደር ሲል የፋጡማ እናት ጤናቸው ይቃወስ ያዘ። ሁሉም ሁሉንም በሚሸሽበት ፈታኝ ጊዜ ይህ አጋጣሚ ከባድ ነበር። ሕመሙ የኮሮና ምልክት ባይኖረውም አብዝቶ የሚጠራጠር አይጠፋም። ይህ አጋጣሚ ለፋጡማ ከባድ የሚባል ነው። አሁን ‹‹አለችኝ›› የምትላት እናቷ በጽኑ እየታመመች ነው። ስሜቱን ስቃዩን መተው አትችልም። ይህ ስሜት በውስጧ ሲያልፍ እየተሰማት ነው፡፡
የእናት ሕመም የቀን መጨመር አላዳነውም። ችግሩ እያደር መባባስ ያዘ። ሁኔታው መክፋት ሲጀምር ደሴ ከሚገኝ ሆስፒታል መሄድ ግድ ሆነ። በሆስፒታሉ በቂ ምርመራ ያደረጉት እናት አስፈላጊውን ሁሉ ጨርሰው ውጤቱን መጠበቅ ጀመሩ። ከቀናት በኋላ የተገኘው የሕክምና ውጤት አስደንጋጭ ነበር። የወይዘሮዋ የምግብ መተላለፊያ ቱቦ ካንሰር ባጠቃው ዕጢ ተዘግቷል። በፍጥነት ለአስቸኳይ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ ተላኩ፡፡
ሕክምናው በሆስፒታሉ ቀጠለ። ከቆይታ በኋላ ታማሚዋ ኬሞ ቴራፒ ታዞላቸው መውሰድ ጀመሩ። አስቀድሞ የሕመሙ መሰራጨት ሁኔታውን የከፋ አድርጎታል። ስቃይ ያለበት የኬሞ ሂደት በፈተና የተሞላ ሆነ፡፡
ለስምንት ወራት ከባዱን የካንሰር ሕክምና መውሰድ የጀመሩት እናት እያደር ሕመማቸው ከፋ። ‹‹ተሰራጭቷል›› የተባለው በሽታ ውስጣቸውን መጉዳትና ማድከም ያዘ። ይህ ጭንቀት ልባቸው የገባው ወይዘሮ ሁሌም ስለአንድ ጉዳይ ማሰባቸው ቀጥሏል። ይህን ሃሳብ መወጠን ከጀመሩ ቆይተዋል። ዓላማቸው ዕውን ይሆን ዘንድ ልጃቸውን ማስገደድ ግድ ሊላቸው ነው፡፡
ከቀናት በአንዱ እናት ከሕመማቸው እየታገሉ የፋጤን እጅ ያዙ። ያሰቡትን ትፈጽምላቸው ዘንድም ተማጸኗት። እሳቸው በሕይወት ሳሉ ልጃቸው ባል አግብታ፣ ዓለሟን እንድታሳያቸው ይሻሉ። ይህ ምኞት ከሕመማቸው እየታገለ ቀን መቁጠር ጀምሯል፡፡
እሳቸው በሕይወት እያሉ የልጃቸውን ወግ ማዕረግ ማየት ናፍቀዋል። እሷን ድረው ኩለው፣ ማግስቱን ሞት ቢወስዳቸው ይቆጫቸው አይመስልም። ፋጤ እሳቸውን አስታማ ማዳን እንጂ ባል አግብታ ጎጆ መውጣትን አስባ አታውቅም። አሁን ግን ከውድ እናቷ አይቀሬው ጥያቄ ቀርቦላታል። ምርጫ አልነበራትም፡፡
ፋጡማ ከፈጣሪ የታዘዘላትን የትዳር አጋሯን በክብር አግብታ የእናቷን ፈቃድ ፈጸመች። ወይዘሮዋ የልባቸው ውጥን ሞላ፣ የሀሳባቸው ውል ተፈታ። አሁን ተወዳጇ ልጃቸው ሙሽራቸው ሆና አይተዋታል። እናት በሕመሙ ጠቁረው ቢከሱም ውስጣቸው ትርጉም ባለው ብርሃን ደመቀ። በአንዴ ደስታቸው ድካማቸውን አሸንፎ ታየ። ለዚህ እውነት ፈገግ ብለው ስሜታቸውን ገለጹ።
ከፋጡማ ጋብቻ በኋላ የወይዘሮዋ ሕመም ተባባሰ። በሽታው በፍጥነት ያዳክም ያዝላቸው ጀመር። ፋጡማ የሠርጓ ዕለት እንደወጉ ወደቤቷ አልሄደችም። እንደሙሽራ በሆታ፣ ዕልልታ ተሸኝታ ከአዲስ ጎጆዋ አልገባችም። ቤት ጓዳዬን ሳትል ከእናቷ ቤት፣ ቀረች፡፡
አሁን እናት በሕክምናው ሕመማቸውን ካወቁ ድፍን አንድ ዓመት ሆኗል። ቀድሞ የሕመሙ መባባስ መድኃኒቱን እያሸነፈ ይታገላቸው ይዟል። ከቀናት በአንዱ ግን ፍጹም ተሸንፈው እጅ ሰጡ። ሲያንገላታቸው የቆየው ሕመም ዳግም ላያቆማቸው ኅልፈታቸው ተሰማ። እንዲህ ሲሆን የፋጡማ ጋብቻ ገና አንድ ወር ማስቆጠሩ ነበር።
ከባዱ ጊዜ …
ይህ ጊዜ ለፋጡማ በእጅጉ ከባድ ይሉት ነበር። ተወዳጅ እናቷን ተሰናብታ ከሸኘች በኋላ በእጅጉ ባዶነት ተሰማት። ኀዘን ውስጧን ዘልቆ አሰቃያት። በትዝታ፣ የእናቷ ደግነት ተመላልሶ ፈተናት። ከዚህ በኋላ ፋጤ ወደ ራሷ ከመመለስ ውጭ ምርጫ አልነበራትም። ውሰጧን አበርትታ የእናቷን ቃል ለመሙላት ወደ ትዳር ጎጆዋ ተመለሰች። አዲሱ ጎጆ በጥንዶቹ ዓለም ደመቀ። ባለቤቷ እንደእሷው የዓረብ ሀገር ሕይወትን ያውቃል። አስቀድመው ሁለቱ በአንድ ባይቆዩም ስሜቱን በእኩል ተጋርተዋል፡፡
ቀን አልፎ ቀን ተተካ። ከጊዜያት በኋላ የጥንዶቹ ጎጆ በሴት ልጅ ስጦታ ተባረከ። ሁለቱን አንድ ያደረገችው ጨቅላ አብሮነትን አጽንታ አጣመረቻቸው። ጥቂት ጊዜያት እንዳለፉ ግን የቤቱ ሰላም ተናጋ። በባልና ሚስቱ መሐል አለመግባባት ሰፍኖ ለቅያሜ አደረሳቸው፡፡
አሁን ፋጤ ከአንድ ውሳኔ ደርሳለች። ውሳኔዋን ባለቤቷም አልተጋፋም። ልጇን ከእሱ ዘንድ አኑራ ወደ ዱባይ መጓዟን በእኩል አምኖ ይሁንታውን ሰጥቷል። ከዚህ ሃሳብ በኋላ ፋጤ ትንሽዋን ፈርያን ተሰናብታ ወደ ዓረቦቹ ምድር አቀናች። አሁን ስለነገ የምታስብ፣ የምትጨነቅላት ጨቅላ አለቻት። ለእሷ በወጉ መኖር ዋጋ መክፈል እንዳለባት አምናለች፡፡
የአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ዕድሜ ያላት ፈርያ በአባቷ እጅ ጥቂት ቆይታ ወደ አያቷ ቤት ሄዳለች። እንዲህ የሆነው አባቷ ወደ ዓረብ አገር ለመሄድ መወሰኑ ነበር። አንዳንዴ ፋጤ ፈርያ የሁለቱን ፍቅር ርቃ ማደጓ ያሳስባታል። ሁኔታዎች ግን ከሌላ መፍትሔ ለመድረስ የፈጠኑ አይደሉም፡፡
አሁን ትንሽዋ ልጅ በአባቷ እናት እጅ ማደግ ጀምራለች። ይህን የምታውቀው እናት በየጊዜው የልጇን ኮልታፋና ጣፋጭ አንደበት በስልክ ትሰማለች። ይህ ድምፀት ለእናት ፋጤ ትርጉሙ ይለያል። አንድ ቀን ደግሞ ጸሎት ልመናዋ ተሰምቶ ከልጇ ጎን እንደምትሆን ተስፋ አላት።
ይህን ስታልም ውስጧ በልዩ ደስታ ይሞላል። እሷ ትናንት የሆነውን ሁሉ አትረሳም። ተወዳጅ እናቷን በትዝታ ታስታውሳለች። የእሳቸው ውለታና ፍቅር ውል ይላታል። ዛሬ ደግሞ በእሷ ማንነት ውስጥ ልጇ ‹‹ፈርያ›› እያቆጠቆጠች ነው። ለእሷ በወጉ ማደግ ኃላፊነቷ መሆኑን ስታውቅ ልቧ በጽናት ይበረታል፡፡
የስልክ ጥሪው…
ከቀናት በአንዱ ከሀገር ቤት የተቀበለችው የስልክ ጥሪ ውስጧን ሲረብሻት ዋለ። ስልኩ የተደወለው ከእሷ የቅርብ ቤተሰብ ነበር። የደወለችላት ልጅ ነገሩን አቅልላ ልትነግራት ሞክራለች። ቆይቶ ግን ልጇ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዳለች አወቀች። ፋጤ ሆስፒታል ይሉትን ቃል ስትሰማ የምትይዘው ጠፋት። ከጥቂት ዓመታት በፊት እናቷን በዚህ ስፍራ ማስታመሟን ታውቃለች። አሁን ደግሞ ይህ አጋጣሚ በልጇ መደገሙን እየሰማች ነው፡፡
ፋጡማ ሁኔታውን በቀላሉ ልትቀበለው ተሳናት። ከስፍራው የምትሰማው ቃል ሕመሟ ቀላል መሆኑን ነው። እንዲያም ሆኖ መጥታ ብታያት እንደሚሻል ደግሞ ተነግሯታል። በጭንቀት የተዋጠችው እናት በአፍታ ድብልቅልቅ ስሜት ፈተናት። እንደምንም ተረጋግታ የልጇን ድምፅ እንዲያሰሟት ጠየቀች፡፡
ትንሽዋ ፈርያ ሁኔታዋ ከሌላው ጊዜ ይለያል። ኮልታፋ አንደበቷ የእሷ አይመስልም። እየደጋገመች ‹‹እናቴ ቶሎ ነይ፣ አድኝኝ» እያለቻት ነው። እናት ይህን ስትሰማ ራሷን መግዛት ከበዳት። ባለችበት ለመቆየት አልቻለችም። ሥራዋ በሰው ቤት ቢሆንም የእነሱን ድጋፍ አላሻትም። በአስቸኳይ ትኬት ቆርጣ። ወደ ሀገር ቤት ተመለሰች፡፡
አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስትደርስ የልጇ ሁኔታ ካሰበችው በላይ ነበር። ሕፃኗ ነጭ የለበሱትን ሐኪሞች ስታይ እናቷ እንድታድናት ትማጸናት ያዘች። ፋጡማ በናፍቆት የተሳቀቀችውን ልጇን እንደ ሃሳቧ ሆና ከጭንቅ አለማስጣሏ ለጸጸት ዳረጋት። በዚህ እውነት ፈርያ ተስፋ እንደቆረጠችባት ሲገባት ከልቧ አዝና በምሬት አነባች።
ፈርያ- ከጊዜያት በፊት
ፈርያ በእጅጉ የምታምር ሕጻን ናት። ጤናማነቷ በደስታ ሲያስቦርቃት ይውላል። ቤተሰቦቿ ለክትባት ካልሆነ ለሌላ ሕመም ሆስፒታል ወስደዋት አያውቁም። እንደ ልጅ ትኩሳት የማያውቃት ሕጻን ሁሌም በሳቅ ፈገግታ ትገለጻለች። ትንሽዋ ልጅ እናት አባቷ ከሀገር ከወጡ ወዲህ በአያቷ ቤት መኖር ከያዘች ወራት ተቆጥረዋል። ሕጻን ብትሆንም ወላጆቿን መናፈቋ ያሳብቃል፡፡
ሕፃኗ ሁሌም በኮልታፋ አንደበቷ የእናት አባቷን ስም እየጠራች ታስታውሳለች። ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በትንሸዋ ልጅ የሚታየው የጤና ለውጥ ቤተሰቡን እያሳሰበ ነው። መላ ሰውነቷን እያሳከከ መቅላት የጀመረው ምልክት እያደር መባባስ ጀምሯል። ሁኔታው ያሳሰባቸው ቤተሰቦች ዝም አላሉም። ጤና ጣቢያ ወስደው መፍትሔ ፈለጉ። የደም መቆሸሸና አለርጂ መሆኑ ተነገራቸው። የታዘዘላትን ሽሮፕና መድኃኒቶች እየወሰደች ጥቂት ቀናት ቆየች። እንዲያም ሆኖ ለውጥ አልመጣም። የሰውነቷ ምልክት መጥቆርና መለወጥ ያዘ፡፡
ዳግመኛ በግል ሆስፒታል መታየት ለጀመረችው ፈርያ መላ ሊገኝ አልቻለም። የሚያስፈልጋት መድኃኒት ባለመኖሩ ለተሻለ ሕክምና ወደ ደሴ ሆስፒታል መሄድ እንዳለባት ተወሰነ። ደሴ የሄደችው ሕጻን ከተገቢው ምርመራ በኋላ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መሄድ እንዳለባት ታውቋል። በጉዳዩ ግራ የተጋቡት ቤተሰቦች ስለሕመሟ አበክረው ጠየቁ። የትንሽዋ ፈርያ የምርመራ ውጤት የ‹‹ደም ካንሰር›› እንደሚያሳይ ተነገራቸው፡፡
በጊዜው ከልጇ ጎን ያልነበረችው እናት ፋጡማ ከዱባይ አዲስ አበባ በደረሰች ጊዜ እውነታውን ሁሉ ተረዳች። ለእሷ የሰማቸውን ሐቅ አምኖ መቀበል ከባድ ነበር። በሆስፒታሉ አልጋ የተኛችውን ልጅ ባየች ጊዜ እናቷን አስታወሰች። ከዓመታት በፊት እሳቸውም በዚሁ ሆስፒታል የካንሰር ሕክምና ይወስዱ ነበር። እንዴት ለምን የሚሉት ጥያቄዎች ከአቅሟ በላይ ሆኑ። እናቷን በትውስታ ልጇን በአካል እያየች በማያቋርጥ ዕንባ ታጠበች፡፡
ፋጡማ በእናቷ የሕመም አጋጣሚ ስለካንሰር ምንነት አውቃለች። በሕጻናት ላይ ስለመከሰቱ ግን ፈጽሞ መረጃው የላትም። በወቅቱ እናት ፋጡማን የሚያጽናና ቃል አልነበረም። በከባድ ኃዘንና ጭንቀት ተዋጠች። ልጇን በአፍታ የምታጣት ሲመስላት ዓለም የጨለመባት ያህል ተሰማት፡፡
ከፋጡማ መምጣት በኋላ ትንሽዋ ፈርያ የመጀመሪያው ኬሞ ቴራፒ ተሰጣት። ይህ ሂደት ሕክምናውን ለሚወስዱ ሁሉ ከባድ የሚባል ነው። አጋጣሚ ብዙዎች በሚፈተኑበት ኢንፌክሽን አልተጠቃችም። እስካሁን በሁለት ዙር ከአስራ ሁለት ጊዜ በላይ ኬሞ የወሰደችው ሕጻን አልፎ አልፎ በሚያጋጥማት ሕመም ትፈተናለች። እንዲያም ሆኖ ከዕድሜዋ በላይ ብርታት መገለጫዋ ነው፡፡
ፈርያን ለአንድ አፍታ…
ከቀናት በአንዱ በማቴዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ ግቢ ተገኘሁ። በዚህ አፀድ በእንግድነት ያሉ በርካታ የሕጻናት ካንሰር ሕሙማንና ቤተሰቦቻቸው ተገቢው ድጋፍ ይደረግላቸዋል። አሁን ከትንሽዋ ፈርያና ከእናቷ ፋጡማ ጋር ነኝ። ፈርያ ድንቡሼዋ፣ ቀልጣፋዋ፣ ሳቂታዋ ሕጻን፡፡
ፈርያን ገና እንዳየኋት የልጅነት ገፅታዋ ማረከኝ። የተላጨው ፀጉሯ ልጅነቷን አስውቦታል። በየምክንያቱ እናቷን የምትጠራበት አንደበት ጣፋጭ ነው። ጠጋ ብዬ ስሟን ጠየቅኋት። ‹‹የእናቷ ንግሥት የሴቶች አለቃ›› ስትል መለሰችልኝ። ሁኔታዋ ቢያስገርመኝ ለትርጉሙ ወደ እናቷ አተኮርኩ። እሷ ‹‹የኔ ንግሥት›› ስለምትላት ይህን ቃል እንደምትደጋግመው ነገረችኝ፡፡
አሁንም እንደተገረምኩ በወጉ አራት ዓመት ያልሞላትን ሕጻን አስተዋልኳት በእርግጥም ይህ ስሜት በእኔ ውስጥ አልፎ ሲሄድ እየተሰማኝ ነበር። እናት ፋጤ ማንነቷ የሚለካው በልጇ ጤንነት ነው። እንዲህ በደስታ መተማመኗን ስታሳያት ፈገግታዋ እንደብርሃን ይደምቃል። ጥቂት አሟት ስብር ስትል ደግሞ ውስጧ በከፋ ኀዘን ይመታል። እንዲህ ሲሆን ዓለም ጥላት የሸሸች ይመስላትና በዕንባዋ ትጣጠባለች፡፡
እንደ መጽናኛ…
በፋጡማ ዙሪያ ያሉ አንዳንዶች ሁሌም ካንሰር ገዳይ በሽታ መሆኑን የሚያምኑ ናቸው። እሷ ግን በፈጣሪዋ የበረታ ዕምነት አላት። እናቷን በሞት ስታጣ ልጇን በምትክ አግኝታለች። እውነታው ይህን ያደረገ አምላክ እንደማይጥላት አሳምኗታልና ጽናቷ ጥብቅ ነው። አሁን ላይ የፈርያ ነገ ለእሷ መልካም ሆኖ ይታያታል። አድጋ ተምራ ካሰበችው ደርሳ መካሻዋ ትሆናለችና፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም