‹‹አንድ ሆነ ፆማቸው!›› መፈክር አይደለም!

የአንደኛ ደረጃ ተማሪ (ከ7ኛ ክፍል ወደ 8ኛ ክፍል) እያለሁ በክረምት ነው። የገበሬ ልጅ ግዴታው ነውና በክረምት ወላጆችን በሥራ እናግዛለን።

አንድ ዕለት የጤፍ አረም የምንሄድበት የእርሻ ማሳ ራቅ ያለ ነውና በጠዋት ተነሳን። ወደ ሥራ ለመሄድ ቁርስ እየበላን ‹‹በደንብ ብሉ!›› ተባለ። ምክንያቱ ለካ እንደሌላ ቀኑ ምሳ በአገልግል አይቋጠርም። በአረም ወቅት ደግሞ በጠዋት ስለሆነ የምንነሳው ሰውነት ስለማይፍታታ በጠዋት ብዙም አይበላም።

እየተነጫነጭኩ ለምን አገልግል እንደማይቋጠር ስጠይቅ፤ የተሰጠኝ መልስ የዕለቱ አረም ላይ አንድ ሙስሊም አብሮን እንደሚውል ነው። ወንፈል ይሁን ሌላ ነገር አሁን ላይ ባላስታውሰውም የዚያን ዕለት አንድ ሙስሊም አባት አረም አብረውን ይውላሉ።

ወቅቱ የሙስሊሞች የሮመዳን የፆም ወቅት ነበር። ሙስሊሙ አብሮን ሥራ ላይ እያለ እኛ ተነስተን ምሳ እንዳንበላ መሆኑ ነው። ምግብ የማይበላ ሰው ሌሎች ሲበሉ ሲያይ ይርበዋል ተብሎ ይታሰባል። በዚህም ምክንያት አብሮን የሚውለው ሙስሊም የፆም ወቅት ላይ ስለሆነ እኛ ስንበላ ምግብን እያሰበ እንዳይርበው መሆኑ ነው። ይህ የቆየ ልማድ ነው፤ ብዙ ጊዜ እንደዚያ ይደረጋል፤ የሚፆም ሰው ፊት ምግብ አይበላም፡፡

ምሳ እንደማይቋጠር ሲነገረኝ ‹‹ታዲያ እኔ ምን አገባኝ!›› ብዬ ተነጫነጭኩ። እኔ ስነጫነጭ ታላቅ ወንድሜ (እሱ ገበሬ ነበር) እና እናቴ ነገሩን ከምክር ወደ ቁጣ ወሰዱት። ‹‹ያንተ ባልንጀሮች ያለምግብና ውሃ በረሃ ይውላሉ አንተ ግን አንድ ቀን እንኳን ምሳ መዝለል አቃተህ! ሆዳም!›› በሚል ወረዱብኝ፡፡

በአካባቢያችን ልማድ ደግሞ ስለምግብ ማሰብ የሰነፍ ሰው ምልክት ነው፤ ታታሪ ሰው ዋና ጉዳዩ ሥራ እንጂ ስለምግብ አይደለም። በወቅቱ በነበረኝ ዕድሜና ሁኔታ አጉል ሠለጠንኩ፣ ተማርኩ… ያዝኩት ያዝኩት ላይ ስለነበርኩ እነርሱ ለፆም የሚሰጡትን ክብር መረዳት አልቻልኩም ነበር ማለት ነው።

ፆሙ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር የነበረውን ማኅበራዊ እሴት ያኔ በነበረኝ ግንዛቤ መረዳት አልችልም ነበር። ጉዳዩ ግን ወዲህ ነው ለካ! በማኅበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ የተዋሓደ ሞራላዊ ግዴታ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሙስሊምና ክርስቲያን ግንኙነት እንዲህ አይነት ነው። በበኩሌ ‹‹ሃይማኖታዊ መከባበር አልለውም!›› መከባበር ሳይሆን ባህል ሆኗል። ከሞራል እና ከሕሊና ጋር የተያያዘ እንጂ ‹‹እኔን እንዳከበረኝ እሱንም ላክብረው›› በሚል አይደለም፡፡

ከማንነታቸው ጋር የተዋሓደ ነው። ከላይ የገለጽኩት የአካባቢው ባህል እንጂ የእኔ ቤተሰቦች የተለየ የዋህነትና ቸርነት አይደለም። በራሴ ያጋጠመኝን ልናገር ብዬ እንጂ ይህ የሁሉም የአካባቢው ሰዎች ልማድ ነው፡፡

አንድ የሚገርመኝ ነገር፤ ይህን ሲያደርጉ እኛ እንደምንለው ‹‹መቻቻል፣ መከባበር›› በሚባለው አይደለም። በቃ ባህል ነው! ከሞራልና ማንነት ጋር የተዋሓደ ነባር ሕይወት ነው።

‹‹አንድ ሆነ ፆማቸው!›› የሚባል መፈክር የሚመስል ነገር አለ። በአንድ ታዋቂ ዘፋኝ ዘፍን ውስጥም ‹‹አንድ ሆነ ፆማቸው›› ተብሎበታል። ብዙዎችም በየመድረኩና በየጽሑፉ ይጠቀሙታል። ለመሆኑ ‹‹አንድ ሆነ ፆማቸው!›› ሲባል ምን ለማለት ይሆን?

ወደ ብዙዎቹ አዕምሮ የሚመጣው ልክ እንደ አሁኑ (በዚህ ዓመት እንደሆነው ማለት ነው) የክርስቲያን እና የሙስሊም ፆም በአንድ ወቅትና በአንድ ወር ውስጥ አብሮ የሚፆም (አንድ ላይ ሲሆን) የሚለውን ነው፤ ‹‹አንድ ሆነ ፆማቸው›› የሚለው መሪ ሀሳብም ከዚሁ የመጣ ይመስለኛል።

በበኩሌ ግን ‹‹አንድ ሆነ ፆማቸው›› ሲባል የፆም ሥርዓታቸው በአንድ ወር ውስጥ አብሮ መሆኑ ብቻ አይደለም። በየትኛውም ጊዜ ቢሆን የክርስቲያኖች ፆም የሙስሊሞችም ጭምር ነው፤ የሙስሊም ፆም የክርስቲያኖችም ጭምር ነው። የአንደኛው ፆም የሌላኛውን ሕይወት ይነካል፤ የሌላኛው የሥራ እንቅስቃሴ ላይ የራሱ ሚና አለው።

ክርስቲያኖች በብዙ እንቅስቃሴዎቻቸው ውስጥ ‹‹የሙስሊሞች ፆም ሳይገባ…›› የሚሉት ነገር አለ። ይሄ ማለት የሙስሊሞች ፆም ሲገባ የሚቀየር የሥራ ባህል ወይም የአዋዋል ሁኔታ ስለሚኖር ነገሮችን ከዚያ ጋር ለማመቻቸት ነው፡፡

ሙስሊሞችም በተመሳሳይ ከክርስቲያኖች በዓላት ጋር የሚያመቻቹት የአሠራር እና የአዋዋል ሁኔታ አለ። ስለዚህ ፆማቸው አንድ ሆነ ማለት አይደለም? ምክንያቱም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአንዱ የሌላኛውን ሕይወት ይነካል፤ አብሮነት ማለት ደግሞ ይሄ ነው!

በሠርግ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሙስሊሞች ለክርስቲያኖች፤ ክርስቲያኖችም ለሙስሊሞች ለብቻ እንደሚያርዱ የታወቀ እና ብዙ የተባለበት ነው። ይህን የሚያደርጉት ማንንም ፈርተው ወይም ማንንም ለማስደሰት ብለው ሳይሆን ነባር ልማድና አብሮነት ስለሆነ ነው።

ይሄ ማለት ግን ፍቅርና አንድነቱ ፍፁማዊ ነው ማለት አይደለም! አልፎ አልፎ ግጭት የለም ማለት አይደለም፤ ግጭቶች አሉ። ልብ ያልተባለ ነገር አለ ብዬ የማምነው እዚህ ላይ ነው እንግዲህ!

ጥቂት የተማሩ ናቸው የሚባሉ አካላት ነገሩን ያከሩታል፡፡

ለምሳሌ፤ አንድ ሙስሊምና አንድ ክርስቲያን ቢጋጩ፤ ግጭቱን የሰው እና የሰው ከማድረግ ይልቅ የሙስሊምና የክርስቲያን ያደርጉታል፤ ሰዋዊ በሆነ ባሕሪ መጣላታቸውን ወደ ጎን ትተው የተጣሉት በሃይማኖታዊ ጉዳይ አድርገው ያራግቡታል።

ክርስቲያን እና ክርስቲያን ወይም ሙስሊም እና ሙስሊም ሲጠዛጠዝና ሲጨፋጨፍ ምንም ያልተባለውን፤ አንድ ሙስሊምና አንድ ክርስቲያን ሲጋጩ ግን ሰዋዊ ነው ከማለት ይልቅ ይሄኛው ሃይማኖት ይሄኛውን አጠቃው በማለት ነገሩን ወደሚፈልጉት አጀንዳ ይወስዱታል፡፡

በግጭት ውስጥ አንዳንድ ጊዜ በግልፍተኝነት ንዴት ሃይማኖታዊ ስድብ የሚሳደቡ ሊኖሩ ይችላሉ። ልክ ማንኛውም ሰው ሌላ ሰው ላይ የሚያየውን ነገር እንደመሳደቢያ እንደሚያደርገው ማለት ነው። ለምሳሌ፤ ክርስቲያን እና ክርስቲያን ሲጣሉ፤ በአካላዊ ሁኔታው፣ በአለባበስ ሁኔታው፣ በኑሮ ሁኔታው፣ በግለሰባዊ ባሕሪው ሊሰዳደቡ ይችላሉ። ይህ ሲሆን የሰው ባሕሪ ተደርጎ ይወሰዳል። የተለያየ ሃይማኖት ሲሆኑ ግን ሃይማኖቱን ታሳቢ አድርገው የተጋጩ ያስመስሉታል።

እንደ አጠቃላይ ግጭት ባይኖር ጥሩ ነው፤ ያም ሆኖ ግን ሰዋዊና ተፈጥሯዊ ስለሆነ ማስቀረት አይቻልምና በክርስቲያን እና በክርስቲያን መካከል ወይም በሙስሊም እና በሙስሊም መካከል እንደሚኖረው ሁሉ፤ በክርስቲያን እና በሙስሊም መካከልም ግጭት ቢኖር ምን ችግር አለው? ምን ችግር አለው ማለቴ የግድ ግጭት ይኑር ለማለት ሳይሆን ለምን እንደ ሰዋዊና ተፈጥሯዊ ባሕሪ አይታይም?

ይህ የማይሆንበት ምክንያት አንዳንድ ወገኖች የራሳቸው የጥላቻ እና የጥፋት ዓላማ ያላቸው ስላሉ ነው። ከጠባብ አመለካከትና ከልክ ባለፈ ጥላቻ ምክንያት፤ እነርሱ ያሰቡት ነገር ይሆንላቸው ዘንድ አንዳንድ አጋጣሚዎችን እንደ ማቀጣጠያ ይጠቀሟታል።

‹‹በዚህ አጋጣሚ›› በሚል በውስጣቸው የተጠራቀመውን ጥላቻ አውጥተው ይናገራሉ። ሲናገሩ በቀጥታ የራሳቸው እሳቤ መሆኑን ከመናገር ይልቅ ‹‹ተመልከቱ የእነ እገሌን ጥላቻ!›› በሚል ሌሎችን ማነሳሻ ያደርጉታል! ምክንያቱም ራሳቸው እንዳይጀምሩት ይፈራሉ፤ ወይም ትንሽዬ ይሉኝታ ነገር ትኖርባቸዋለች!

እነሆ የሙስሊምና ክርስቲያን ፆም ‹‹አንድ ሆነ ፆማቸው›› ሲባል ቆይቶ በሃይማኖታዊ ቀመሩ መሠረት የሙስሊሞች ሊፈታ ነው። የሙስሊሞች ፆም ሲፈታ ክርስቲያኖችን የሚጠሩት የክርስቲያኖችን ፆም ታሳቢ ባደረገ መንገድ ነው።

ለምሳሌ፤ የኦርቶዶክስ አማኞች ዓርብ ረቡዕ እና በሌሎች የፆም ወቅቶች የሥጋ ተዋፅዖ አይበሉም። የሙስሊሞች ፆም ሲፈታ እርድ ይታረዳል። በአጋጣሚ ኢድ አልፈጥር ዓርብ ወይም ረቡዕ ቀን ቢሆን፤ ወይም እንዲህ እንደ አሁኑ የሁዳዴ ፆም ሲሆን፤ በዕለቱ ለሚመጡ የኦርቶዶክስ አማኞች የሚዘጋጀው ምግብ የፆም ምግብ ነው።

‹‹እኛ ያዘጋጀነው የፍስክ ምግብ ነውና ብትበላ ብላ ባትበላ የራስህ ጉዳይ!›› የሚል ሙስሊም አይኖርም! ምክንያቱም አብሮነቱ ደስ የሚለው የዚያኛውን ባሕሪ ማክበሩ ጭምር ነው፡፡

የፋሲካ በዓል ከኢድ አልፈጥር በፊት ሆኖ ቢሆን ኖሮ እንበል! አንድ ክርስቲያን ከአፍጥር ሰዓት በፊት ሄዶ አንድን ሙስሊም ‹‹ና ብላ!›› ሊለው አይችልም። ለሙስሊም ጎረቤቶቹ የሚሆነውን ምግብ የሚያዘጋጀው ለማታ ነው። ምግቡም የሚዘጋጀው በሙስሊሞች ሃይማኖታዊ የአመጋገብ ሥርዓት መሠረት ነው። ‹‹አንድ ሆነ ፆማቸው!›› የሚባለው ለመፈክር አይደለምና ይህን አብሮነት ሁሉም ሊረዳውን ሊያከብረው ይገባል!

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You