ስለወሎ ብዙዎቻችን ብዙ እንሰማለን። ማህበረሰቡ የፍቅር ማህበረሰብ ነው። በተለይም የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ የሆነው ማህበረሰብ ከየትኛውም አካባቢ በተለየ የሃይማኖት መቻቻል እና መዋደድ እንዳለው ይነገርለታል። የተነገረለት ደግሞ በተግባር ስለታየ ነው። ለዚህ ደግሞ ኪነ ጥበብ ምስክር ነው።
ኪነ ጥበብ ከሌሎች ፖለቲካዊ አገላለጾች ይለያል። ፖለቲካ ለማስመሰል ተብሎም ይነገራል፤ ይጻፋል። እገሌ የተባለው ጎሳ፤ብሄር ወይም ሃይማኖት ይውጣልኝ፤ እንዳላየው የሚል ማህበረሰብ ባለበት ውስጥ ‹‹መቻቻል ያለበት እገሌ ማህበረሰብ›› እየተባለ በየመድረኩ ማውራት ይቻላል። ይሄ የሚሆነው በፖለቲካዊ ዓውድ ውስጥ ነው። በኪነ ጥበብ ግን ይለያል።
ኪነ ጥበብ የአንድ ማህበረሰብ ትውፊታዊ ክዋኔዎች ውጤት ነው። ከእነዚህ ትውፊታዊ ክዋኔዎች አንዱ ደግሞ የቃል ግጥም ነው። የቃል ግጥም በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሲወርድ ሲወራረድ የሚመጣ ክውን ጥበብ ነው። ምናልባት እንደየቃል ግጥሙ ባህሪ ሁሉም የሚከወን ላይሆን ይችላል። አንዳንዱ አካላዊ እንቅስቃሴ ባይኖረውም እንደ ተረትና ምሳሌ የሚነገር ብቻ ሊሆን ይችላል። አብዛኛው የቃል ግጥም ግን ዜማ እና ክዋኔ ያለው ነው።
የወሎ ማህበረሰብ የሃይማኖት መቻቻል ነባራዊ መሆኑን የምናውቀው በእነዚህ የኪነ ጥበብ መገለጫዎቹ ነው። በወሎ ማህበረሰብ ውስጥ የሙስሊም የሚመስሉ የመንዙማ ግጥሞችን ክርስቲያኑ ያንጎራጉራቸዋል፤ የክርስቲያን መዝሙሮችን ሙስሊም ያንጎራጉራቸዋል። ዜማዎችና መንዙማዎችም የየራሳቸው መልዕክት አላቸው። እስኪ ለዛሬው በወሎ ማህበረሰብ ትውፊቶች ላይ የተደረገ ጥናትን ዋቢ አድርገን ጥቂቶችን የወሎ አኩሪ ባህሎች እናስተዋውቃችሁ።
ዶክተር ሩቅያ ሀሰን በወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው። ‹‹በወሎ ክርስቲያንና ሙስሊም ህዝብ መካከል የሀይማኖት መቻቻልና የአብሮነት መንፈስ ዲስኩር ትንተና›› በሚል ርዕስ አንድ ጥናት ሰርተዋል።
አጥኝዋ ከአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች ነው የሚጀምሩት። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች በሚባል የሚታወቁት አራቱ ቅኝቶች መነሻቸው ወሎ ነው። በተለይም አምባሰል እና ባቲ ደግሞ በቦታዎቹ ስም የተሰየመ ነው። ትዝታ እና አንቺ ሆየም መነሻቸው ወሎ ነው። በራሳቸው በአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶችም እንዲህ ተብሏል።
ክራር ቢደረደር ማሲንቆ ቢመታ በገና አንች ሆየ
ኧረ ባቲ ባቲ አምባሰል ትዝታ የቅኝቱ ጥለት የኪነቱ ጌታ ወሎ ባህሉ ነው
እንግዳ መቀበል ቁምነገር ጨዋታ።
አጥኝዋ እንደነገሩን ይህ ግጥም በ2006 ዓ.ም ደሴ ሸዋበር መስጊድ በተከበረው የመውሊድ በዓል ላይ ተነቧል።
መንዙማም እንዲሁ የኪነ ጥበብ ሥራ ነው። የወሎ ኡላማዎች ለተለያየ መልዕክት ያዜሙታል። ለጸሎት ይዜማል፣ ለሃይማኖታዊ አስተምህሮት ይዜማል።
አንዴ በዘፈኑ አንዴ በመንዙማ
ሲያወድስ ይውላል የፍቅርን ዜማ።
የተባለውም ለዚህ ነው። በወሎ አካባቢ መንዙማን በማዜምና በማስተዋወቅ የታወቁ ሰዎች አሉ። በጥናቱ ላይ ከተጠቀሱት፤ ሼህ ሁሴን ጅብሪል፣ መርሳ አባ ጌትየ፣ ጉና ንጉሥ፣ ሼህ መሐመድ አወል… ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሰዎች ኪነ ጥበቡን ብቻ ሳይሆን ፍቅርንም አስተዋውቀዋል። የስነ ቃል ግጥሞች ፍቅርን የሚሰብኩት ወሎን ምሳሌ አድርገው ነው።
ባቲና ኮምቦልቻ ከሚሴና ሀርቡ
የነሸግየ አገር የነአይጠገቡ::
የተባለውም ለዚህ ነው። ቀጥሎም በእነዚህ ስንኞች ተዘፍነውለታል።
አርሂቡ ግቡ ነው ወሎ በር አይዘጋም
‹‹እየመጡ ቀሩ እያሉ ልክክ›› ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ምቹነትም ሆነ በህዝቦቿ እንግዳ ተቀባይነት የውጭ አገር ዜጎች የሚወዷት ናት። እዚሁ ለምደው ልክክ ብለው የሚቀሩም አሉና!
ሌላው ‹‹እኛም ዱኣ አርገናል ሥላሴ ይባርክ›› የሚለው ነው። ይሄ የወሎን ማህበረሰብ በትክክል ይገልጻል። ከአንድ የቤተሰብ አባላት ውስጥ ክርስቲያንም ሙስሊምም ስለሚኖር። ይህን አንድነታውን ለመግለጽ ነው እንዲህ የተባለው። ‹‹ዱኣ›› ለእስልምና እምነት ነው፤ ‹‹ሥላሴ›› የክርስትና እምነት ነው። ስለዚህ ዱኣ አድርጎ ሥላሴ ይባርኩት ማለት ይቻላል ማለት ነው። በነገራችን ላይ የኪነ ጥበብ ሰዎች እንደሚሉት ግጥም ከፍተኛ ነፃነት ያለበት ጥበብ ነው። በግጥም ውስጥ ፈጣሪን አገኘሁት ብሎ መፈላሰፍም ይቻላል።
በወሎ ሀገራችን ክርስቲያን እስላም
ተጋብተው ወልደዋል በፍቅር በሰላም።
መስጅድና ገዳም ባንድ ስፍራ ሲኖሩ ፋሲካና አረፋን ባንድ ቀን ሲያከብሩ
የእምነት አክራሪዎች ከወሎ ይማሩ።
በወለጋ አርሲ በአፋር በሱማሌ
በሐረር በባሌ
ወሎ ክፍለ ሀገር ይቅረብ ለምሳሌ።
ይህ የአብሮነት ባህል በወሎ አካባቢ የተለመደ መሆኑ እነርሱንም እንዲኮሩ አድርጓል። እንደማንነት አይተውታል።
እስልምናው የኔ ክርስትናው የኔ
በጣም ተደሰትኩኝ ወሎየ መሆኔ።
የተባለውም ለዚህ ነው። አንዳንዶቹ ግጥሞች ደግሞ ከባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ውበታዊ መልዕክትም ባለፈ የአዳኝነት (ህክምና) ይዘትም ያላቸው ናቸው።
የዚህ አገር አድባር ቁጥቡ እንደምነው
የጤና ጠባቂው ጨንገር በረኛው
እበር ላይ ቁሞ አቤት የሚለው
ያገሩ ጠባቂ ጨንገር እንዴት ነው
እስቲ አጫጭሱና አህሪብ እንበለው።
አርብ ሮብን ጿሚ ሰንበትን አክባሪ
አይደለም ወይ ጨንገር ጉድ የልቡን ሰሪ።
ላሊበላ ውሎ ግሸን አዳሪው
ባለ ወርቅ መስቀል ባለቃጭል ነው
ቤተክርስቲያን ገብቶ ቅኔ የሚያወራው
የአርባ አራቶች ወዳጅ ጨንገር በረኛው።
አቤት አንበሶ አቤት አንበሶ
እሱ ኪታብ ቀሪ ባለጦሃራው
ባለቀይ ቆቲ ባለቄጠማው
የሸሆቹ ወዳጅ ተነጋጋሪው
ግራ ቀኝ ትክሻ የሚራገጠው
ባለቀይ ኮርማ ባለጅብማው
እንክትክት ስብርብር አርጎ እሚገዛው
እሱ ደም አስቀማጭ ጀርባ ቆማጭ ነው
ማርልኝ ነው እንጂ ሌላ ምን አልነው
ግብር እንደሞላ እያስረከብነው።
እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ልብ እንበል። አንዳንድ ቦታ ላይ ሃይማኖታዊና ባህላዊ መልዕክቶች ይደበላለቃሉ። ብዙ ጊዜ የሃይማኖት አባቶች ሲሉ እንደሚሰማው በእምነት ቦታዎች ላይ የሚባለው ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ብቻ ነው። ዳሩ ግን በስነ ቃል ውስጥ ደግሞ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ውጭ የሆነ መልዕክትም ሊኖር ይችላል፤ ምናልባትም የባዕድ አምልኮ በሚደረግበት ጊዜ ከሚሉት የቃል ግትም ጋርም የሚገናኝ ነገር ሊኖረው ይችላል። በእርግጥ በስነ ጽሑፍ ውስጥ የሚታየው የፈጠራ ጥበባቸው እንጂ መልዕክቱ ብቻ አይደለም። ምክንያቱም ገጣሚዎች ሼህ ወይም ቄስ ላይሆኑ ይችላሉ።
ከስነ ቃል ባለፈም በዘፋኞች የሚታወቁ ስንኞች አሉ። በእርግጥ ዘፋኞችም ስነ ቃልን መነሻ አድርገው የዘፈኗቸው ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ የታዋቂዋ የክራር ንግስት ሜሪ አርምዴ ዘፈን ይጠቀሳል።
እስላምም አረደ ክርስቲያ አረደ ጨጓራና ጉበት
ያም ሥጋ ያም ሥጋ በላሁ ምናለበት።
እንዴት ይጣፍጣል የእስላም ቤት እንጀራ
በእሁድ በቅዳሜ በበዓል የተሰራ።
ምግብህና ምግቤ አይመሳሰሉ
አንተም ለብቻህ እኔም ለብቻዬ እየተባባሉ
አለያዩትና ሰውን ሰው በሙሉ
ውሸት ሲናገሩ አንድ ነን ይላሉ
ማንም ማንን እንዳያምን እየተማማሉ
ሰውን አስጨረሱት እየተጋደሉ።
ይህ የሜሪ አርምዴ ግጥም ትልቅ መልዕክት አለው፤ በፍቅር ውስጥ ደግሞ የምንም ነገር ገደብ የለም። እዚሁ ላይ የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ሼመንደፈር››ን እንጠቃቅስ።
ተዋዶ ያለበት እስላም ክርስቲያኑ
ተዘነጋሽ እንዴ ኢትዮጵያ መሆኑ
አንቺም በሃይማኖትሽ እኔም በሃይማኖቴ
መኖር እንችላለን አይጠበንም ቤቴ።
እኔ ሀገሬ ሐረር ትውልዴ ቁልቢ
ንግስ ብለሽ መጥተሽ ከልቤ ብትገቢ
ካልወጣሁ ከአስርቱ ከሴፈቱ ሲታ
አንቺን በመውደዴ አይቆጣም ጌታ
ሸገር አዲስ አበባ አንቺ ያለሽበት
ራጉኤል አይደል ወይ የአንዋር ጎረቤት
ቅዳሴና አዛኑን አጥር ቢለያቸው
ፈጣሪ ከሰማይ በአንድነት ሰማቸው።
እኔም ልማል በአላህ አንቺም በቁልቢ
ክርሽን ሳትፈችው ነይ ከቤቴ ግቢ።
ፍትሕ መጽሔት ላይ ባነበብኩት አንድ ገጠመኝ ሀሳቤን ልደምድም። አብሮ አደግ ጓደኛሞች የነበሩ ሙስሊም እና ክርስቲያን ናቸው። ሙስሊሙ በንግድ ሥራ ሲሰማራ ክርስቲያኑ ትምህርቱን ጨርሶ የመንግስት ሥራ ተቀጠረ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ተገናኝተው የልጅነታቸውንና የትምህርት ቤት ትዝታቸውን ሁሉ ሲጫወቱ ቆዩ። በኋላም ስለሥራ ማውራት ተጀመረ። በዚህም መሃል የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ሁሉ ሲያወሩ በሃይማኖት ላይ የተሰሩ ጥናቶች ተነሱ።
በሙስሊምና በክርስቲያን ግጭት ላይ የተሰሩ ናቸው። በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው በግርምት፤ ‹‹እኔ እምለው! እናንተ ጥናትና ምርምር የምትሰሩ ሰዎች ግን ይሄን ግጭት ከየት ነው የምታመጡት? አሁን እኔና አንተ ስናድግ ይሄ ነበር? እኔም ይሄን ያህል ስቆይ ያው ልጅ እያለን የምታውቀው ማህበራዊ ግንኙነት ነው ያለው፤ ታዲያ ከየት ነው የምታመጡት?›› ብሎት ነበር።
እንዲህ ነው እንግዲህ! ጥናቶቻችን እንኳን የሚያተኩሩት በግጭት ላይ እንጂ በመልካም እሴቶችና ባህሎቻችን ላይ አይደለም። እንዲህ አይነት ነገሮች ደግሞ የዋሁን ማህበረሰብ ጭምር ማሳሳት ይሆናል። ምሁራኖቻችን እንዲህ አይነት ትውፊታዊና ጥበባዊ የማህበረሰቡን አብሮነት ሊያስተዋውቁ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2012
ዋለልኝ አየለ