ጎበዝ አንድ ልብ ያልተባለ ነገር አለ። ሥራ ፈላጊዎች ማስታወቂያ የሚያነቡባቸውን ቦታዎች በማየት ‹‹አቤት የሥራ አጥ ብዛት›› ይባላል። በተለይም አራት ኪሎ ያለው የማስታወቂያ ሰሌዳ እና ጋዜጣ ማንበቢያ ብዙ ሥራ ፈላጊዎች ይበዙበታል። ያ! ሁሉ ግን ሥራ ያልያዘ ብቻ አይደለም፤ ሥራ ቀያሪዎችም ናቸው። ለዚህማ ጥናት ማድረግም አያስፈልግም፤ ማስተዋል ብቻ በቂ ነው።
ሥራ ፈላጊ በነበርኩበት ጊዜ በሚገባ ያስተዋልኩት ነው። እኛ ሥራ የሌለን (በወቅቱ ማለቴ ነው) ማስታወቂያ ያወጣውን ተቋም የት እንደሚገኝ ስንጠያየቅ ከጎናችን ያሉ ሰዎች ግን ስለተቋሙ ባህሪ ሁሉ ያወራሉ። ይሄ ብቻም አይደለም። ለፈተና ተጠርተን ከሄድንም እዚያ ቦታ ላይ የሚያወሩት ከዚህ በፊት ስለሰሩባቸው ተቋማት ነው። አንዳንዴ ደግሞ ‹‹ኧረ ሥራ ትተን እኮ ነው የመጣን ለምን ቶሎ አይፈትኑንም!›› ብለው ሲበሳጩ እንሰማለን። ያኔ እኛ ደግሞ በእነርሱ እንበሳጫለን፤ ለምን የእኛን ዕድል ያጠባሉ ነው ነገሩ።
እንድንበሳጭ የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ደግሞ ፈተና ላይ ይበልጡናል በሚል ሥጋት ነው። የሚገርመው ፈተናው ደግሞ ሥራ ላይ ላሉ ሰዎች የሚወጣ ነው የሚመስል። የሥራ መደቡ የሚጠይቀውን ሳይንሳዊ ትምህርት ሳይሆን የተቋማትን ባህሪና ደንቦች የሚጠይቅ ነው። ይሄን ነገር በኋላ እመለስበታለሁ።
ሰሞኑን በማህበራዊ ገጾች መነጋገሪያ የነበረውን ፎቶ አይታችሁ ይሆናል። የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ከ800 በላይ ሰራተኞችን ፈልጎ ማስታወቂያ አወጣ። ለምን እንደተመረጠ ባላውቅም (ምናልባት ሰፊ ሆኖ ይሆናል) ምዝገባው ሜክሲኮ ገነት ሆቴል ነበር። የተመዝጋቢዎች ብዛት የተጋነነ እንደሚሆን ስለተገመተ ይመስላል ምዝገባው በስማቸው የፊደል ተራ (አልፋቤት) ነበር።
በምዝገባው ሰሞን ታዋቂ ብሎገሮች ሁሉ ፎቶውን ተቀባበሉት። ልብ በሉ! ያ! አስገራሚ ፎቶ የተነሳው በተወሰኑ ስሞች ብቻ ነው። ለምሳሌ የመጀመሪያውን ቀን ብናይ አራት ፊደል ብቻ ነው። በA B C እና D ስማቸው የሚጀምር ብቻ ተብሎ ያ! ሁሉ ሰው ተገኘ። እንግዲህ አስቡት፤ ከA እስከ Z ያለው አንድ ቀን ሄዶ ቢታይ ምን ይሆን ነበር? የሆነው ሆኖ ግን ፈተናው እንዴት ሊሆን ነው? በእርግጥ ይሄ ሁሉ ለፈተና አይቀርብም፤ በውጤት ሊለይ ይችላል።
የመጨረሻው ቀን የነበረውን አጋጣሚ በቦታው ደረስኩና ለመታዘብ ቻልኩ። ይህ የመጨረሻው ቀን ከU እስከ Z ነበር። እነዚህ ፊደሎች 6 ይሁኑ እንጂ ሦስት ማለት ነው፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ በU V እና X የሚጀምሩ ስሞች ብዙም የሉም። በእነዚህ ሦስት ፊደላት ብቻ እንኳን የነበረው እስከ አፍሪካ ህብረት ሊደርስ ምንም አልቀረውም ነበር።
ያ! ሁሉ ሥራ ፈላጊ ምንም ያልተቀጠረ ብቻ አልነበረም። ጠያይቄ እንኳን ባገኘሁት መረጃ ብዙ ከሥራ ላይ የመጡ ነበሩ። አንዳንዶቹ የደመወዝ ለውጥ ስላለው፤ አንዳንዶቹ ያሉበት ደመወዝ ቢሻልም መስሪያ ቤቱን ለመቀየር… ብቻ በተለያየ አጋጣሚ ሥራ ላይ የነበሩም ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንዳንድ ተቋማት ከዚህ ዓመተ ምህረት ወዲህ የተመረቀ ማለት ጀምረዋል። ምክንያታቸው ግልጽ ነው። ለአዳዲስ ተመራቂዎች የሥራ ዕድል ለመስጠት ነው። እኔ ግን አመስግኛቸዋለሁ። እንዲያውም የሚሰጡት የአንድ ዓመት ዕድል ብቻ ሳይሆን የሁለት እና የሦስት ነው። ለምሳሌ አሁን ላይ የሚወጣ ማስታወቂያ የ2011 ተመራቂ ብቻ ቢል ጥሩ አይሆንም ነበር፤ ምክንያቱም ከ2010 ጀምሮ ሥራ ያላገኘ ሊኖር ስለሚችል። ችግሩ ግን እንዲህ አይነት ዕድል ሲሰጡ ደግሞ ሥራ ላይ ያለውም ለመመዝገብ ዕድል ይሰጠዋል።
ሥራ ላይ ያሉ ሰዎች አዲስ ከተመረቁት ጋር አብረው ቢወዳደሩ ምን ችግር አለው? ይባል ይሆናል። ምንም ችግር አልነበረውም፤ ግን ቀጣሪ ተቋማት (በተለይም የመንግስት) የሚያወጡት ፈተና ተማሪዎች የተማሩትን ትምህርት ይዘት ያለው አይደለም። እንዲያ ቢሆንማ እንዲያውም አዲስ ተመራቂዎች ነበሩ ፈተናውን የሚያልፉት። ችግሩ ግን ፈተናው ወይ ጠቅላላ እውቀት አይሉት፤ ወይ የአካዳሚ ፈተና አይሉት፤ የቢሯቸውን አሰራር ነው የሚጠይቁ። ይሄ ደግሞ ተቀጣሪው ከገባ በኋላ የሚያውቀው እንጂ ትምህርት ቤት እያለ ሊያውቀው አይችልም።
መፈተን ያለበት ከሚቀጠርበት የሥራ መደብ ጋር የሚገናኘውን ሳይንሳዊ ፈተና ነው። ብዙ ጊዜ ተፈታኞች ሲያማርሩ የሚሰማው ይሄ ቢ.ፒ.አር፣ ቢ. ኤስ. ሲ… ምናምን የሚባል ነገር ነው፤ ይሄን እኮ የሚያውቀው ሥራ ላይ የቆየ ሰው እንጂ በዜሮ ዓመት ለወጣ ማስታወቂያ እንዴት ይሄን ይጠየቃል? ወይ ደግሞ ከሥርዓተ ትምህርቱ ጋር ቀድሞ መተዋወቅ አለበት።
አንድ የሥራ መደብ ሲወጣ ለዜሮ ዓመት ወይስ ልምድ ላለው የሚለው ቀድሞ ነው በቀጣሪው ተቋም መወሰን ያለበት። የሥራ መደቡ በዜሮ ዓመት የሚሰራ ከሆነ ምንም ሥራ የሌላቸውን መመዝገብ፤ የሥራ መደቡ በልምድ የሚሰራ ከሆነ ግን ለይቶ ማሳወቅ ነው።
እዚህ ላይ ግን የተቋማቱንም ችግር ልብ እንበል። ሰራተኛ በሚሰራበት መስሪያ ቤት ውስጥ ተረጋግቶ አይቀመጥም። ማስታወቂያ ባየ ቁጥር መስሪያ ቤት የሚቀያይር ሰራተኛ ነው ያለው። ያ! የተለቀቀው የሥራ መደብ በየጊዜው 0 ዓመት እያስገባ መደቡ መለማመጃ ሊሆን ነው ማለት ነው። ስለዚህ ልምድ ያለው ያስገቡበትና ይገላገላሉ። በእርግጥ የሥራ ዝውውር ልምድ ባለው ይብሳል። ዞሮ ዞሮ ግን የሥራ መደቦች የሚዘበራረቁት እንዲህ በሰራተኛው መቀያየር ነው።
እዚህ ጋ ደግሞ ሌላ ወከባ
ክፍት የሥራ ማስታወቂያ የሚያነቡ ሥራ ፈላጊዎች ላይ ደግሞ አንድ ችግር አለው፤ ይሄውም በጣም ቀላል ችግር የነበረ ነው። ማስታወቂያውን በትክክል አንብቦ መረዳት አለመቻል! አንዳንዶቹ የሚፈልጉት የሥራ መደብ ስላለ ብቻ የሚመለከታቸው ይመስላቸዋል፤ አንዳንዶቹም የተመረቁበት የትምህርት ክፍል ስም ስላለ ብቻ የሚመለከታቸው ይመስላቸዋል፤ አንዳንዶ ቹም ስለተመረቁ ብቻ በየትኛውም ነጥብ መመዝገብ የሚቻል ይመስላቸዋል። እነዚህን ሁሉ ባለማስተዋል ቀጣሪው ተቋም ጋ ሄደው የሚጨቃጨቁ ቀላል አይደሉም።
ብዙዎች ልብ የማይሉት ነገር ደግሞ 0 የሚል በማየት ብቻ ነው። ማስታወቂያው ‹‹አግባብነት ያለው የሥራ ልምድ›› በሚለው ሠንጠረዥ ሥር ቢኤ/ኤም ኤ ይልና 2/0 የሚል ያስቀምጣል። ‹‹ቢኤ›› እና ‹‹ኤም ኤ›› የሚሉ ነገሮችን ልብ ባለማለት ሁለት ዓመት ወይም 0 ዓመት ያለ ይመስላቸዋል። ለዚህ ስህተት የሚዳረጉት ደግሞ አንዳንድ ተቋማት በአንድ አይነት ዲግሪ ልምድ ያለውም ዜሮ ዓመትም ቢሆን ብለው ስለሚያወጡ ነው። ተቋማቱም ሆኑ ሥራ ፈላጊዎች ማስተካከል ያለባቸው ነገር ግልጽ አድርጎ መጥቀስና ማንበብ ነው። ሥራ ፈላጊዎች የዲግሪውን አይነት ልብ ማለት አለባቸው።
ጉዳዩን ካነሳነው አይቀር ስለተቋማት የቅጥር ማስታወቂያ አንድ ሌላም ነገር እንታዘብ። ደመወዙ ገና የጀማሪ ተቀጣሪ ሆኖ ፒ ኤች ዲ እና ማስተርስ የትምህርት ደረጃ የሚጠይቁ አሉ። ፒ ኤች ዲ ዲግሪ ያለው ሰው በዚያች ደመወዝ የሚገባ የት የቆየ መስሏቸው ይሆን? እሺ እሱም ይሁን ሌላ ጥቅማጥቅም ሊኖረው ይችላል ብለን እንለፈው፤ ግን እነዚህ ተቋማት ሰው ሲያጡ ‹‹በድጋሚ የወጣ›› ብለው ያወጣሉ፤ እንዲህ ጊዜ ማባከን ለምን አስፈለገ?
ሌላው ጣጣ ደግሞ ለፈተና የሚጠሩበት ሁኔታ ነው። አንዳንዱ መስሪያ ቤት ለዚያ ሁሉ ሰው አንደውልም ይሉና በውስጥ ማስታወቂያ ይለጥፋሉ፤ ያንን የውስጥ ማስታወቂያ ስንት ሰው ያየዋል? ሥራ ፈላጊ በየዕለቱ እየሄደ ማየት አለበት?
የሥራ ፈላጊ እና የሥራ ቀያሪዎች ነገር ግን ሊታሰብበት ይገባል። ሥራ ቀያሪ እና ሥራ ፈላጊን እኩል ማወዳደር አይመችም። ሥራ ለመቀየር የሚወዳደሩ ሰዎች ከቀያሪዎች ጋር ይወዳደሩ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2012
ዋለልኝ አየለ