አዲስ አበባ፡- ኢትዮ ቴሌኮም የታሪፍ ቅናሽ ይፋ ካደረገ በኋላ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ያገኘው ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ330 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱን ገለጸ፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም የስትራቴጂና ፕሮግራም ማኔጅመንት ሃላፊ አቶ መሀዲ ጀማል በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የታሪፍ ቅናሽ ከተደረገ በኋላ በመጀመሪያው ሩብ አመት 9 ነጥብ 16 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም በ2010 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 8 ነጥብ 83 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር የ330 ሚሊዮን ብር ጭማሪ እንዳለው ያመለክታል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም እስከ ሃምሳ በመቶ ቅናሽ በማድረጉ ግማሽ ያህሉን ገቢውን ማጣት ነበረበት ያሉት አቶ መሀዲ፤ ይህ ያልተከሰተው የታሪፍ ቅነሳው በጥናት ላይ ተመስርቶ የተተገበረ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ከታሪፍ ቅነሳው በኋላ የድምጽና የዳታ ፍሰቱ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
አቶ መሀዲ እንዳሉት፤ ኢትዮ ቴሌኮም በ2010 ዓ.ም ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 37 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ በ2011 ዓ.ም 47 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዷል፡፡ ካለፈው ዓመት በ 10 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ ገቢ ለማግኘት ዕቅድ የተያዘው ከፍተኛ የታሪፍ ቅናሽ በተደረገበት ወቅት ቢሆንም፤ በርካታ የማካካሻ ስራዎች ታቅደው እየተሰሩ ነው፡፡
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ የኔት ወርክ ጥራትን ለማሻሻል መጨናነቅ ባለባቸው አካባቢዎች የማስፋፊያ ሥራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ ደንበኞች የአየር ሰዓት በብድር የሚያገኙበት አገልግሎት ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በውጭ ሀገር የሚኖሩ ሰዎች ባሉበት ሆነው ካርድ እንዲሞሉላቸው የሚያስችል አገልግሎትም ቀርቧል፡፡ በኃይል አቅርቦት ረገድ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ኢትዮ ቴሌኮም የራሱን ኃይል የሚያገኝበትን መንገድ ለመቀየስ ከመብራት ኃይል ጋር የተለየ ስምምነት ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ማሻሻያ የተደረገባቸውና አዳዲስ አገልግሎቶች ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የታሪፍ ቅናሽ ይፋ ያደረገው ከነሐሴ 16 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን፤ የስልክ ድምፅ ጥሪ 40 በመቶ፣ የስልክ ኢንተርኔት አገልግሎት 43 በመቶ ፣የብሮድባንድ ኢንተርኔት የ54 በመቶ እንዲሁም የሞባይል አጭር የፅሁፍ መልዕክት (SMS) ደግሞ የ43 በመቶ የአገልግሎት ቅናሽ ተደርጎባቸዋል፡፡ ከሳምንት በፊት ደግሞ ወደ ውጭ ሀገር ለሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች እስከ 40 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ቅናሽ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2011
በየትናየት ፈሩ