የተወለዱት ማይጨው ከተማ በ1928 ዓ.ም ሲሆን የተወለዱበት ወቅት ጣሊያን ኢትዮጵያን የወረረበት ጊዜ ስለነበርም ከዚያ ጋር የተያያዘ ታሪክ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ በደሴና አዲስ አበባ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ዲፕሎማቸውንም ከሐረር መምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያገኙ ሲሆን የመጀመሪያ፥ የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አሜሪካ በሚገኙ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ወስደዋል፡፡
ኮረም1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፥ ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት፥ ባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ካገለገሉባቸው ተቋማት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስማቸው ጎልተው ከሚጠሩ ግለሰቦች አንዱ ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ የኢህአዴግ መንግሥትን በመቃወም በኢዴፓ፥ ቅንጅትና አንድነት ፓርቲ ውስጥ በግንባር ቀደምነት ተሳትፈዋል፡፡የአንድ ወንድና የአንድ ሴት ልጅ አባት የሆኑት የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር ሃይሉ አርዓያ ሲሆኑ ከእርሳቸው ጋር በተለያዩ ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከጣሊያን ጋር የተያያዘ ታሪክ እንዳሎት ይነገራል፤ እስቲ በዚህ ጉዳይ ውይይታችን ብንጀምር?
ዶክተር ሃይሉ፡- እንዳልሽው የተወለድ ኩት ጣሊያን አገራችን በወረረችበት ወቅት በመሆኑ ከጣሊያን ጋር የተያያዘ ታሪክ አለኝ። በተለይም ደግሞ የመጨረሻው ጦርነት የተካሄደው ማይጨው ከተማ ውስጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወራሪው ሃይል የእኛን ቤት ወደ ዳር ገፍቶ ካምፕ ሰርቶበት ስለነበር በልጅነት አዕምሮዬ የነበረውን ብርቱ ተጋድሎ እንዲቀረፅ አድርጎት ነበር። በዚህም ምክንያት ገና በለጋ እድሜዬ ወደ ውትድርና የገባሁበትም አጋጣሚ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ይሄ ማለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቶን ሳይማሩ በፊት ማለት ነው?
ዶክተር ሃይሉ፡- በአካባቢያችን ዘመ ናዊ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ መጀመሪያ የተማርኩት የቤተ ክህነት ትምህርት ነው። ዳዊቴን እያጠናሁም ከብቶች አግድ ነበር። እድሜዬ ወደ ዘጠኝ አካባቢ ሲደርስ ወደ ደሴ ሄድኩና የቄስ ትምህርቴን ቀጠልኩ። ዳዊትን ከጨረስኩ በኋላ ሳላይሽ የሚባል የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገባሁና 1ኛ ክፍል ተማርኩ። ብዙም ሳልቆይ አዲስ አበባ መጣሁ ቀበና አካባቢ ከሚገኙ ቤተሰቦቼ ጋር መኖር ጀመርኩ። እዛም እያለሁ በወቅቱ ቦይስ ካውት የሚባል ታዳጊዎችን ለውትድርና የሚያሰለጥን ተቋም ነበር።
እኔም በተወለድኩበት አካባቢ ከወታደሮች ጋር የመቀራረቡ እድል ስለነበረኝ እንደነሱ ለመሆን ስል ገና የ12 ዓመት ታዳጊ ሳለሁ ያንን ተቋም ተቀላቀልኩ። ይሁንና አስተዳደጌ በመንፈሳዊ ትምህርት የታነፀ ስለነበር ውትድርና ውስጥ ሳለሁ የመንፈሳዊ ሰው የመሆን ስሜቴ እየጎለበተ ሄደ። በአጋጣሚ ደግሞ በዛው ቦይስ ካውት ውስጥ ስለቅርስና ስለሃይማኖት የሚያስተምሩ ወጣቶች ነበሩና ከእነሱ ጋር መቀራረብ ጀመርኩ። ውሎ ሲያድርም የመንፈሳዊ ሰው የመሆን ስሜቴ እያደገ መጥቶ ከአራት ቦይስ ካውቶች ጋር በመሆን ለመመነን አስበን ካምፑን ጥለን ጠፋን።
አዲስ ዘመን፡- እናም በዚያ እድሜዎ ከውትድርና ወደ ምንኩስና ገቡ?
ዶክተር ሃይሉ፡- አይ እንደ እሱ አልነበረም የሆነው። ከእነዛ ቦይስ ካውቶች ጋር ከካምፑ እንዳመለጥን በቀጥታ የሄድነው ወደ ዝቋላ አቦ ገዳም ነበር። የገዳሙ ሰዎች እናንተ ወታደሮች ስለሆናችሁ በመጀመሪያ እዛ ላለው አስተዳደር እዚህ መቆየት አትችሉም አሉንና ታስረን ወደ ደብረዘይት በፖሊስ ታጅበን ተወሰድን። ከዚያም ወደ ናዝሬት ወሰዱንና አንድ ወር ያህል ከቆየን በኋላ ተመልሰን አዲስ አበባ ወደሚገኘው ካምፕ መጣን። የሚገርመው ግን አሁንም በካምፑ ውስጥ አንድ ወር ያህል ከታሰርን በኋላ እንደገና ጠፋን።
አዲስ አበባ፡- ተመልሳችሁ ወደ ገዳሙ ሄዳችሁ?
ዶክተር ሃይሉ፡- አይ ተመልሰን ወደ ገዳሙ አልሄድንም፤ ሁላችንም አዲስ አበባ ወደሚገኙ ቤተሰቦቻችን ነበር የሄድነው። የእኔ ቤተሰቦች መንፈሳዊውንም ሆነ ውትድርናውን ሙሉ ለሙሉ እንድተውና ወደ ዘመናዊ ትምህርት እንድገባ አደረጉኝ። የውትድርናው ትምህርት ተቆጥሮልኝ በቀጥታ ከስድስተኛ ክፍል ኮከበ ፅብሃ ትምህርት ቤት ነው የጀመርኩት። ይሁንና እኔ የነበረኝ እውቀት ደካማ የሚባል ስለነበር ስድስተኛ ክፍል ደገምኩኝ። በኋላ ግን የቤተሰብ ችግር ተፈጠረና ተመልሼ ወደ ማይጨው ሄድኩኝ። በዚያን ጊዜ ደግሞ ትምህርት ቤት ተከፍቶ ስለነበር 7ኛና 8ኛ ክፍልን ተማርኩ።
ከዚያ ከስምንተኛ ክፍል በኋላ በወቅቱ ትምህርት ቤት ስላልነበር ፈተና ያለፉ ልጆች ወደ አዲስ አበባ መጥተው አዳሪ ትምህርት ቤት ይገቡ ነበር። በዚያ መሰረት እኔም ዳግመኛ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩና ኮተቤ በሚገኘው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባሁ። እዛም አንድ ዓመት ከተማርኩ በኋላ ወደ ሐረር መምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሄድኩኝ። እዛም ለአራት ዓመት በዲፕሎማ በመምህርነት ሰለጠንኩ። ወዲያውኑም በመምህርነት በዚያን ጊዜ የወሎ ክፍለ ሃገር ውስጥ በነበረው ኮረም በሚገኝ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ደሴ ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት አስተማርኩኝ።
አዲስ ዘመን፡- ወደ አሜሪካ የመሄድ እድሉን ያገኙበትን አጋጣሚ ያስታውሱን?
ዶክተር ሃይሉ፡- በቀድሞ ስሙ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ አሁን ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል ለሁለት ዓመታት ከተማርኩኝ በኋላ የቀረውን ሁለት ዓመት በአሜሪካ የመማር እድል ተሰጠኝ። በወቅቱ ግን እኔ የመጀመሪያ ዲግሪዬን እዚሁ ጨርሼ ለሁለተኛ ዲግሪ ወደ አሜሪካ መሄድ ነበር የፈለኩት። እነሱ ግን ያገኘኸውን እድል ተጠቅምና ተመልስና ባህርዳር ሊከፈት ለታሰበው ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የእንግሊዘኛ መምህር እንድትሆን እንፈልጋለን አሉኝ።
በዚያ መሰረት አሜሪካ በሚገኘው ኒዮርክ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያዝኩ። ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ግን ወዲያውኑ አልተመለስኩም። አንድ ዓመት ትምህርት ሚኒስቴርን ጠይቄ ስለተፈቀደልኝ ጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪዬን አገኘሁ። ከዚያም ወደ አገሬ ተመልሼ እንደተባለው ባህርዳር ፖሊቴክኒክ ማስተማሬን ጀመርኩ። እዛም ለሦስት ዓመት ካስተማርኩ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር ተስማማሁና ገባሁ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ለአንድ ዓመት አስተማርኩኝ። ከዚያም ለዶክትሬት ዲግሪ የመማር እድል አገኘሁና ዳግመኛ ወደ አሜሪካ በመሄድ ስነ -ልሳን አጠናሁ። ለሁለት ዓመታት እዛው አሜሪካ በሚገኝ የትምህርት ተቋም ውስጥ አስተማርኩ። በ1966 ዓ.ም ለመመለስ ፈልጌ የነበረ ቢሆንም አብዮቱ የፈነዳበት ወቅት ስለነበርና አብዮቱን እንፈልገውም ስለነበር ለውጡ በሚፈለገው መልኩ እንዲሄድ ለማገዝ አሜሪካ የነበረኝን የማስተማር ሥራ ትቼ ለመመለስ ወሰንኩ። ይሁንና በነበረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት አየር መንገዱ ተዘግቶ ስለነበር በፈለጉት ወቅት መምጣት አልቻልኩም። ከአንድ ዓመት በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ በወረዱ በሁለተኛው ቀን ወደ አገሬ ተመለስኩ።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ በቀጥታ ወደማስተማሮት ተመለሱ?
ዶክተር ሃይሉ፡- አዎ! በመጀመሪያ ላይ እዛው በፊት ወደነበርኩት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው የተመለስኩት። በኋላም እድገት በህብረት መጣና በዘመቻው ምክንያት ዩኒቨርሲቲው ተዘግቶ ስለነበር ለሁለት ዓመት በዘመቻው ተሳተፍኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ግን ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመለስኩኝና ማስተማሬን ቀጠልኩ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ 1983ዓ.ም ድረስ ማስተማሬን አላቋረጥኩም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የኢ.ሰ.ፓም አባል ነበሩ፤ በወቅቱ የነበረውን ስርዓት አምነውበት ነበር ፖለቲካውን የተቀላቀሉት?
ዶክተር ሃይሉ፡- አዎ! እንዳልሽው በኢ.ሰ.ፓ ውስጥ ለዘጠኝ ዓመት ቆይቻለሁ። በዚያን ጊዜ እንግዲህ ዩኒቨርሲቲው መሠረታዊ የመዋቅር ለውጥ አደረገና አራት አዲስ የትምህርት ክፍሎች ተከፍተው ነበርና አራቱም የትምህርት ክፍሎች የመጀመሪያው ዲን ሆኜ ተመደብኩ። እዛ እያለሁ ገና ኢ.ሰ.ፓ አልተመሰረተም ነበር። ነገር ግን ኢ.ሰ.ፓን ለመመስረት ኢሰፓኮ የሚባል ድርጅት ነበር። በዚያ ወቅት ሊቀመንበር መንግስቱ ሃይለማርያም ቢሮ ትፈለጋለህ ብዬ ተጠራሁ። ሪፐፕሊክ መንግሥት ለማቀቋም ፍላጎት ስላለን ከተለየዩ ሙያተኞችን እየሰበሰብን ስለሆነ ፍቃደኛ ከሆንክ አንተም ተሳተፍ የሚል ጥሪ ቀረበልኝ።
እኔም ሪፐፕሊክን የመሰለ ነገር ይፈጠራል ሲባል እኔም መሳተፍ ይገባኛል ብዬ አመንኩና ጥሪውን ተቀበልኩ። በዚያ ጊዜ እንግዲህ ኢ.ሰ.ፓ በፓርቲ ደረጃ አልተቋቋመም ነበር። ስለዚህ ወደ ድርጅቱ ስገባ በመጀመሪያ የፓርቲን አላማ ይዤ አልነበረም የገባሁት። ነገር ግን ወዲያው እዚህ ኢሰፓኮ በተባለው ተቋም ውስጥ የብሄረሰቦች መምሪያ ተቋቋመና ምክትል መምሪያ ኃላፊ ሆኜ ተመደብኩኝ። በመሃል ደግሞ ኢ.ሰ.ፓ በይፋ ተቋቁሞ ስለነበር ይህንን አላማ የምትደግፍ ከሆነ አባል እንድሆን ስጠየቅ እኔም በዚያ ጊዜ አባል ሆንኩ።
አዲስ ዘመን፡- የኢ.ሰ.ፓ አባል በነበሩበት ወቅት ሊቀመንበር መንግስቱን በቃ ይበቃሃል ውረድ ብለውት እንደነበር ይነገራል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
ዶክተር ሃይሉ፡- አይ ውረድ አይደለም ያልኩት። በዚያን ጊዜ ብዙ ችግር ነበር። የብሄር ብሄረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ህገመንግሥት ረቂቅ አጥንቶ ለፓርቲው ከቀረበ በኋላ ነው ፓርቲው አዲስ መንግሥት ያቋቋመው። በወቅቱ ለሸንጎው ከተመረጡ ሰዎች አንዱ ነበርኩ። በዚያን ጊዜ ውይይት በሚደረግበት ጊዜ አንዱ ችግር የተለያዩ ሃሳቦች ቢመጡም ለእርሳቸው የማይጥም ከሆነ ወይ ያጣጥሉታል፤ አለበለዚያ ደግሞ ያቋርጡታል። ወይም ወደ ሌላ አቅጣጫ ይመሩታል። በዚህ ምክንያት ብዙ ቅሬታዎች ነበሩ። በተለይም በሰሜን ያለው ጦርነት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ ይሄ ችግር በጦርነት ሊፈታ ስለማይችል ሰለማዊ መንገድ መፈለግ አለበት የሚል ሃሳብ ለሸንጎው አቀረብኩ።
በዚያን ጊዜ ፕሬዚዳንቱ የሰዎችን ሃሳብ ከመቀበል ይልቅ ወደ ሃይል ነበር የሚያዘነብሉት። የጦርነት ሃሳብ ሲሆን ይቀበሉታል፤ ይደግፉታል፤ ያጠናክሩታል፤ ነገር ግን የሰላም ጉዳይ ሲመጣ ተገቢውን ትኩረት አይሰጡትም። እናም ዋናው ችግራችን እሱ ነበር። በዚያ መሰረት በወቅቱ የነበረኝን ቅሬታ ገልጫለሁ። ሁለተኛው ችግር ደግሞ ለመጨረሻ ጊዜ በተሰበሰብንበት ጊዜ በነፃነት ተናገሩ ቢባልም የተለየዩ ሰዎች የተለየየ መፍትሄ ሀሳብ ሲያመጡ የመግፋትና አቅጣጫ የመለወጥ ነገር ስለነበር ይሄ አቅጣጫ ትክክል አይደለም። በነፃነት ልንነጋገር ይገባል የሚል ሃሳብ ነው የሰነዘርኩት።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ከዚህ ንግግር በኋላ ምን ጠበቆት?
ዶክተር ሃይሉ፡- እንደመታደል ሆኖ ምንም አላገጠመኝም። የተለየዩ ሰዎች ግን ብዙ ነገር ነግረውኛል፤ ፕሬዚዳንቱ በንግግሬ በጣም ተናደው ስለነበር ያንን ቁጣቸውን ለማብረድ ጥረት ማድረጋቸውን ሰምቻለሁ። በተለያዩ መፃሃፍት ላይም አንብቤያለሁ። ለምሳሌ ኮሎኔል ፍስሃ በፃፈው መፃሃፍ ውስጥ እኔንና ፕሮፌሰር መስፍን ላይ በጣም ተቆጥተው እንደነበር ማለት ነው።
ፕሮፌሰር መስፍን የሽማግሌዎች ቡድን ይፈጠርና አዲስ የሽግግር መንግሥት ይፈጠር የሚል አቋም ነበረው። ያ ሃሳብ ፕሬዚዳንቱን አስቀይሟቸው ነበር። እንዳውም ሸንጎ ውስጥ በነበርንበት ወቅት ስለ መስፍን ሲናገሩ ፕሬዚዳንቱ «መስፍን ብቻ አይደለም ለዚህች አገር መፍትሄ አለኝ የሚለው፤ ሌላም እዚህ ቤት ውስጥ ይህንን ሃሳብ የሚያራምድ ሰው አለ» በማለት ስሜን ሳይጠቅሱ ሸንቆጥ አድርጎኝ ነበር።
ግን እዛ መፃሃፍ ላይ እኔና መስፍንን እንድንታሰር በደህንነቱ ሰው ተስፋዬ ወልደስላሴ ትዕዛዝ ተሰጥቶ እንደነበር ነው ያነበብኩት። በወቅቱ ምን አይነት እርምጃ እንደሚወሰድ ግን አናውቅም ነበር። በወቅቱ የፕሬዚዳንቱ ረዳት የነበረው መንግስቱ ገመቹ ለምኗቸው ሃሳባቸውን እንዳስለወጠ ነው የተረዳሁት። ፕሬዚዳንቱ ወደ ሐራሬ ከሄዱ በኋላ በፃፉት መፅሃፍ ላይ ንዴታቸውን የገለፁበት መንገድ አለ። እኔ ግን እስካሁን ድረስ መንግስቱ ገመቹ እንዴት ሃሳባቸውን ሊያስቀይር እንደቻለ ይገርመኛል። ለማንኛውም ግን ተርፈናል።
አዲስ ዘመን፡- ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላስ በምን ሁኔታ ላይ ቆዩ?
ዶክተር ሃይሉ፡- ለዘጠኝ ዓመት በፓርቲ ውስጥ እያለሁም ማስተማሬን አልተውኩም ነበር። ስለዚህ ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላም ሙሉ ለሙሉ ወደ ማስተማሩ ገባሁ። ትንሽ ከሰራሁ በኋላ ግን መለስ ዜናዊ አባረረን። በ1985 ዓ.ም ጡረታዬ ተከብሮልኝ እንድወጣ ተደርጌያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከደርግ ውድቀት በኋላ አብዛኛቹ የደርግ ባለስልጣናት ታስረዋል፤ እርሶስ ይህ ሁኔታ አላጋጠሞትም?
ዶክተር ሃይሉ፡- በመጀመሪያ ላይ የተደረገው ከስራ መባረር ነው። በአጋጣሚ ኢህአዴግ በገባበት ወቅት እኔ ለስብሰባ ወደ አሜሪካ ሄጄ ነበር። በወቅቱ ብዙዎች ወደ አገሬ እንዳልመለስ ቢመክሩኝም አዲሱ መንግሥት ሰላምና ዴሞክራሲ ለማምጣት እንደሚሰራ ይናገር ስለነበር ምክራቸውን ችላ ብዬ ወደ አገሬ ተመለስኩ። ከዚያ እንደመጣሁ ግን የኢሰፓ ባለስልጣኖች ሪፖርት ያደርጉ ስለነበር እኔም እንግዲህ ምክትል መምሪያ ሃላፊ ስለነበርኩኝ እንደስልጣን ተቆጥሮ ሪፖርት ማድረግ ነበረብኝና ሪፖርት ለማድረግ ሄድኩ። እዛ ስደርስ ግን እስርቤት አስገቡኝ። በወቅቱ የታሰርኩት ከሌሎች የኢ.ሰ.ፓ አባሎች ጋር ሳርቤት አካባቢ በሚገኝ ሱዳን ጥላ በሚባል እስር ቤት ውስጥ ነበር። ግን ብዙ ካጣሩ በኋላ ምንም ሊያገኙብኝ ስላልቻሉ ከ50 ቀን በኋላ ለቀቁኝ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ሦስት የተለያዩ መንግሥታትን ያዩ እንደመሆንዎ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያምንና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ባህሪ ያነፃፅሩልኝ?
ዶክተር ሃይሉ፡- ለእኔ ሁለቱም አምባገነኖች ነበሩ። አምባገነን የሚለው ቃል ይጠቀልላቸዋል። መንግስቱ የሌሎችን ሃሳብ እንደሚቀበሉ አድርገው ቢያስመስሉም መጨረሻ የሚፀናው ግን የእርሳቸው ሃሳብ ብቻ ነበር። መለስ ዜናዊን በቅርበት ባላውቃቸውም በአጠቃላይ ከውጭ በማስተውለው ዴሞክራሲያዊ ካባ የለበሱ ነገር ግን አምባገነን ነበሩ ብዬ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡- እስቲ አሁን ደግሞ ደርግን ከመሰለ ሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ተከታይነት ወጥተው የሊበራሊዝም ተከታይ ወደ ሆነው ቅንጅት የገቡበትን አጋጣሚ ምን እንደነበር ያስታውሱን?
ዶክተር ሃይሉ፡- እኔ ዳግመኛ ወደ ፖለቲካው የተመለስኩበት ምክንያት በወቅቱ በአገሪቱ ዴሞክራሲና ነፃነት አለ ቢባልም በተግባር ግን አልነበረም። ደግሞ የነበረው የኢህአዴግ የጎሳ ፖለቲካ ለመቀበል የሚያስቸግር ሁኔታ ነው።
እናም ወደ ፖለቲካው ለመመለሴ አንዱና ትልቁ ጉዳይ እሱ ነው። ነፃነት እናመጣለን ብለው ነበር የመጡት ፤ነገር ግን ነፃነት አልነበረም። ድርጅቶችም ሆኑ ፓርቲዎች ነፃነት ስላልነበራቸው መስራት የሚፈልጉትን ነገር የማይሰሩበት ሁኔታ ነበር። በአጠቃላይ እናመጣለን ያሉት ዴሞክራሲ ስራ ላይ አልዋለም። ህገ መንግስቱ ስለነፃነት ስለዴሞ ክራሲ ብዙ አውርቷል። ነገር ግን በተግባር መሬት ላይ የለም። ይሄ መለወጥ አለበት በሚል ነው ወደ ፖለቲካው የገባሁት። በመጀመሪያ ኢዴፓ ውስጥ ገባሁ። ከዚያም ኢዴፓ ቅንጅትን ከፈጠሩ ፓርቲዎች ጋር ሲዋሃድ በዚያ መልኩ ነው ወደ ቅንጅት የመጣሁት።
አዲስ ዘመን፡- በ1997ዓም በነበ ረው ምርጫ በፓርቲው ውስጥ የእርሶ ሚና ምን ነበር?
ዶክተር ሃይሉ፡- በአጠቃላይ የፓርቲውን እንቅስቃሴ ከማገዝና ነቅቶ ከመሳተፍ በተጨማሪ ምርጫ ስለነበር እኔም አዲስ አበባ ጉለሌ አካባቢ ተወዳድሬ አሸንፌ ነበር። በመሰረቱ ቅድም እንዳልኩሽ ለነጻነት ቆመናል ሲሉ የነበሩት አካላት ነፃነትና እኩልነትን አላመጡም። ከዚያ ይልቅም መርዘኛ የሆነውን የጎሳ ፖለቲካ ነው ያመጡት። እናም በዚያ ምክንያት እኔም ራሴ ይህንን ሁኔታ ለመቃወም ነው ወደ ተቃዋሚ ፓርቲ የገባሁት። በዚያም በተቻለኝ አቅም ስርዓቱ እንዲቀየርና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመጣ ታግያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለቅንጅት መፍረስ ዋነኛ ምክንያት ምን ነበር ይላሉ?
ዶክተር ሃይሉ፡- በአጠቃላይ በቂና የበሰለ ፖለቲካ አልነበረም። በሁለተኛ ደረጃ በፖለቲካ ስራ የመተባበር ነገር አልነበረም። የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያስቀድሙት የራሳቸውን አጀንዳ ብቻ ነበር። አጀንዳቸው የህዝብ አይደለም። ህብረት አልነበራቸውም። ቢተባበሩና የህዝቡን አጀንዳ ቢያራምዱ ኖሮ ለዚህ አይበቁም ነበር ባይ ነኝ። ነገር ግን ህብረት ስላልነበራቸው እውነተኛውን የህዝብ አጀንዳ ማራመድ የማይችሉበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። በመሰረቱ አጀንዳው የየግላቸው ከሆነ እና አስተሳሰባቸው የተለየያ ከሆነ የህዝብን አላማ የማራመድ ሁኔታ ስላልነበር ይመስለኛል ፓርቲው የመፍረሱ ዋነኛ ምክንያት።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ቅንጅት ውስጥ የነበረው ስብስብ እንዳውም ከየትኛውም ፓርቲ በተሻለ ምሁራንና ልምድ ያላቸውን ሰዎች ያቀፈ እንደ መሆኑ ለፓርቲው መፍረስ በፖለቲካ አለመብሰል ነበር ለማለት ይቻላል?
ዶክተር ሃይሉ፡- ለእኔ በፖለቲካ አለመብሰል ነው። አለመብሰል ማለት እኮ የተነሳንበት ህዝባዊ አላማን ይዞ ማራመድ አለመቻል ነው። ያንን ለማራመድ አንደኛ የበሰለ እውቀት ይጠይቃል። ሁለተኛ ደግሞ የስልጣን ጉዳይ አለ። ሁሉም ስልጣን የሚፈልግ ከሆነ ደግሞ አንድ ላይ ሆኖ መስራት የሚችሉበትን እድል አይፈጠርም። የተለያየ ዓላማ ስላላቸው በጋራ ቆመው የህዝብን ርዕይ እውን ማድረግ አልቻሉም።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚያውቁት ልክ እንደቅንጅት የተለየዩ ፓርቲዎች ውህደት ፈጥረው እየሰሩ ነው። እንደቅንጅት አይነት ችግር እንዳያጋጥማቸው ምንአይነት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ይላሉ?
ዶክተር ሃይሉ፡- እንግዲህ ሁልጊዜ ግንባር ቀደም መመሪያ ሊሆን የሚገባው የህዝቡን ፍላጎት ነው። የህዝቡን ችግር ለመፍታት ቁርጠኝነቱ ያስፈልጋል። እውቀትና ብስለት ያስፈልጋል። ይሄ ነገር እንደገና በእነሱም ላይ እንዳይደገም ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። በመጀመሪያ ህዝቡ ምን እንደሚፈልግ ማወቅና ያንን ለማሳካት እውቀቱ፥ ብስለቱ፥ ዝግጁነቱ ያስፈልገናል ማለት ነው። እንደእኔ እምነት ቅድሚያ የስልጣን ባለቤት መሆን ያለበት ህዝቡ ነው። ግን የህዝቡ ተወካይና መሲህ የመሆን ሁኔታ አለ። እኛ እናውቅልሃለን የሚል እና ሞግዚት የመሆን ዝንባሌ ይታያል።
ግን እኮ ስልጣኑ ለህዝቡ ቢሰጥ ህዝቡ ራሱ ያውቅበታል። ለዚያ ደግሞ ህዝቡን የማሳወቅ ስራ መስራት ከፓርቲዎች ይጠበቃል። በእኔ እምነት ትልቁ ስራ ያ የስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማብቃት ነው። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የራሳቸውና የህዝቡ ፍላጎት የሚጋጨው። ስለዚህ አሁን ያሉት ፓርቲዎች የግላቸውን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው የተነሱበትን የህዝብ አለማ ለማሳካት ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ እርሶ ቅንጅት ከፈረሰ በኋላ ተመልሰው ወደ ፖለቲካ አልመጡም። ምን ነበር ምክንያትዎ?
ዶክተር ሃይሉ፡- ቅንጅቱ በራሳችን ድክመት ነው የፈረሰው፤ ቅድም እንዳልኩሽ የስልጣኑ ባለቤት ህዝቡ ነው። የእኛ ስራ ህዝቡ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ከማብቃት ይልቅ ራሳችንን በማብቃት ላይ ነበር የምናተኩረው። በዚያ ምክንያት ፓርቲው ፈረሰ፤ ደግሞም ከዚያ በኋላ ቅንጅት የህግ ችግር ስለነበረበት እንደቅንጅት መቀጠል የማይችልበት ሁኔታ ነበር። እናም ቅንጅት የሚለውን ስም እንተውና አላማውን ይዘን ቅንጅት አንድነትን መሰረትን። እዛም የተወሰነ ጊዜ ከቀጠልን በኋላ በድርጅት ውስጥ መግባባት ጠፋ። ስራውንም በሚገባ መስራት አልተቻለም። በፓርቲው ውስጥ ሁለት ቡድን ተፈጠረናም እኔ ነኝ፤እኔ ነኝ በሚል ተጋጭተው ምርጫ ቦርድ ለአንዱ ወገን ሰጠው። ስለዚህ እኔ ይህንን ሁኔታ አልፈልግም ብዬ ወጣሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚያ ወዲህ ፖለቲካውን እርግፍ አድርገው ተውት ማለት ነው?
ዶክተር ሃይሉ፡- አይ እንደሱ ለማለት እንኳ ይከብደኛል፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ የፖለቲካ እንስሳ እንደሚባለው ሁሉ እኔም ሙሉ ለሙሉ ከፖለቲካ ልርቅ አልችልም። ፖለቲካ የአገር ጉዳይ በመሆኑ የሚተው ነገር አይደለም። እናም በፓርቲ ውስጥ ንቁ አባል ሆኜ ባልሳተፍም በሃሳብ ግን እደግፋለሁ። አላማቸውን በምደግፋቸው ፓርቲዎች ውስጥ ለአባልነት ተመዝግቦ ማገዝ የሚያስፈልግ ከሆነ ለማገዝ ፍቃደኛ ነኝ። ለእኔ ግን ጥሩ የሚመስለኝ በዚህ እድሜዬ ምክር መስጠት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ተከትሎ በርካታ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል፤ አጠቃላይ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን ከዳር ሆነው ምን ምን ታዘቡ?
ዶክተር ሃይሉ፡- አንደኛ ለውጡ ጥሩ ነው፤ በዚህ አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ተስፋ የሚሰጥና የሚያበረታታ ሁኔታዎችን ለመመልከት ችያለሁ። ለእኔ እንዳውም ፈፅሞ ያልጠበቅሁት ነገር ነው የተከሰተው። በዚያው ልክ ደግሞ ችግሮች አሉ። እንደተባለው ፓርቲዎች ተቋቁመዋል፤ ነገር ግን ይህን ያህል ፓርቲ መኖር በራሱ ምን ትርጉም ይኖረዋል። እርግጥ ነው፤ ሌሎች አገሮችም የዚህ አይነት ቁጥር ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ ህንድ ውስጥ በርካታ ፓርቲዎች ቢኖሩም ትላልቆቹ ፓርቲዎች ሁለት ብቻ ናቸው። ስለዚህ ዴሞክራሲው ክፍት መሆኑ ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን የፓርቲዎች መብዛት ለአገሪቱ የሚጠቅም ነገር ለመስራቱ ያስችላል ብዬ አላስብም።
ለመሆኑ በዚህች አገር ውስጥ ከ 130 በላይ ፓርቲዎች መኖር ለምን አስፈለገ? እኔ እንደሚገባኝ 130 አስተሳሰቦች አሉ ማለት እኮ ነው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የተለየየ ሀሳብ ያላቸው በርካታ ፓርቲዎች መፈጠራቸው ህዝቡን ውዥንብር ውስጥ ይከታል፤ አገርንም ይጎዳል። ግርግር መፍጠር ወይም ግራ ማጋባት ነው እንጂ ህዝብን የሚያግዝ አይደለም።
ለአንድ ህዝብ በእንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ውስጥ ገብቶ ለአገር የሚጠቅም ነገር ማግኘት የሚያስቸግር ይመስለኛል። በአንድ አገር ውስጥ የእኔ ፍላጎት ሁለት ፓርቲ ቢኖር ግፋ ቢል ሦስት አራት ቢሆኑ ነው። በእውነት ግን ይህ ህዝብ ይህን ያህል የሃሳብ ልዩነት አለው ማለት ነው? እኔ አይመስለኝም። በዚህ ሁኔታ ህዝቡ ግራ መጋባት ውስጥ ነው የሚገባው። ስለዚህ ተቀራርቦ መስራትና ወደ አንድ ሃሳብ መምጣት ነው የሚገባቸው።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫ ቦርድም በቅርቡ አንድ ፓርቲ እውቅና ማግኘት የሚችለው እስከ 10ሺ አባል ሊኖሩት እንደሚገባ የሚደነግግ ህግ አውጥቷል። ይህንን ተከትሎ በርካታ ፓርቲዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው። እርሶ በዚህ ላይ ምን ሃሳብ አሎት?
ዶክተር ሃይሉ፡- እኔ በእውነት አጀንዳቸው የህዝብ ከሆነ ይህ ጉዳይ እንቅፋት ሊሆን አይገባም፤ ቁርጠኝነቱ ካላቸው ለምን ከዚያም በላይ አይሆንም? አጀንዳቸው የህዝብን ፍላጎት ማሳካት ከሆነ ያንን ለማሳካት የሚፈለገውን ነገር ለማሟላት ለምን አይፈልጉም? እኔ አይታየኝም። ስለዚህ እኔ በግሌ ሃሳቡን እደግፋለሁ። ህዝቡ ውዥንብር ውስጥ መግባት የለበትም። ለምንድን ነው የአይን አዋጅ ነገር የሚያደርጉት? የግዴታ የፓርቲዎች አላማ የህዝብ ፍላጎት ከሆነ ያንን አላማ ለማሳካት የሚፈለገውን ማሟላት አለባቸው እንጂ መቃወም አይገባቸውም።
አንድ ህብረተሰብ አይን አዋጅ ውስጥ እንዲገባ አይፈለግም። በግላችን ብዙ ነገሮች እንዲኖረን ብንፈልግም ሁሉንም ለማሳካት አንችልም። ነገር ግን ወደ ስኬት ለመሄድ ማቻቻል አለብን ማለት ነው። ሁሉንም ነገር የምንፈልግ ከሆነ ወሳኙን ነገር ማሳካት አንችልም። ማንኛውም ህብረተሰብ በአገር ብቻ ሳይሆን በግለሰብም ደረጃ የምንፈልጋቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። እነዛን ነገሮች እንደፈለግን ማሳካት አንችልም። ማቻቻል ካልቻልን ግን እንደሚታየው 130 ቦታ እንከፋፈላለን። ፓርቲዎች ልዩነታቸውን አቻችለው በጋራ መስራት ካልቻሉ ህዝቡን ችግር ውስጥ ይጥሉታል። ስለዚህ የማቻቻል ችሎታ ሊኖረን ይገባል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያዊነት ለእርሶ ምንድን ነው?
ዶክተር ሃይሉ፡- ኢትዮጵያዊ ነኝ ከማለቴ እኔ ሰው ነኝ። ነገር ግን ደግሞ ድንበር አለማቀፍ ህግ ሆኖ በህግ የተከለለና በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባላት አገር ውስጥ እንደምኖር ነው የማስበው። እኔ ከሰውነቴ ባሻገር አነስ ባለ ክልል ውስጥ ነው የምኖረው። ታሪክ ቋንቋና የመሳሰሉት እሴቶች መገለጫ ባለት አካበቢ ማለት ነው። ያ ክልል የትም አካበቢ ይሁን የዚያ አካል ነኝ ማለት ነው።
እኔ እዚህ ነው የተወለድኩት፤ እዚህ ጋር ነው ግንኙነቴ የምልበት ነገር አይደለም ያለው። በእርግጥ በአካል ከተወሰነ አካባቢ ተወልጄ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከዚያ ውጭ የሌላው ህዝብ አካል አይደለሁም ማለት አልችልም፤ ነኝ። ኢትዮጵያዊነት ለእኔ እንግዲህ ቋንቋችን እና ባህላችን ያየዘ ማንነት ነው። እኔም የእነዚህ ጉዳዮች መገለጫ ሰው ነኝ። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ይሄ ነው። ለነገሩ ይሄ ጥያቄ ብዙ ጊዜ ቀርቦልኛል፤ ግን ያደኩበትና ራሴንና አካባቢዬን ከዚያም አልፎ ዓለምን ለመገንዘብ የቻልኩበት ሃሳብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁን አሁን እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ከማለት ይልቅ የገሌ ብሄር ነኝ ማለት የሚቀናቸው ሰዎች ተበራክተዋል። ይህ ሁኔታ ወደምን ያመራል ብለው ያስባሉ? በተለይ እርሶ በተወለዱበት አካባቢ ድንበር እንደመሆኑ ከዚህ ቀደም በትግራይና በአማራ ህዝብ መካከል የነበረው ተቻችሎ የመኖር እሴት እንደተዳከመ ይገለፃል። በዚህ ጉዳይ ላይ ያሎትን ሃሳብ ጨምረው ይግለፁልን?
ዶክተር ሃይሉ፡- ይሄ አስተሰብ በራሱ ገና ሳስበው ያመኛል። እንዲህ ያለውን ነገር አልችለውም። እኔ እንደአጋጣሚ አንድ ቦታ ላይ ተወልጄያለሁ። ነገር ግን እኔነቴ አንድ ቦታ ላይ አረፈ እንጂ የመላው ኢትዮጵያ አካል ነኝ። እኔ እዚህ ነው የተወለድኩት ብዬ ማሰብ ራሱ ያመኛል። አጥብቤ እዚህ ነኝ ብዬ ለማመልከትም ያስቸግረኛል። በእርግጥ የተወልዱበትን ቦታ አውቀዋለሁ፤የተገነባሁት ያደግሁት የዚያ አካባቢ አስተዋፅኦ ነኝ ብዬም አምናለሁ፤ የአስተዋፅኦ ግን በዚያ የሚገደብ አይደለም። የአጠቃላይ የአገሪቱ አስተዋፅኦ ነኝ። እናም አሁን የተፈጠረው ነገር አይገባኝም።
ራያ ስለሚባል ነገር ይነግሩኛል፤ የተወለድኩት እዛ መሆኑ እሙን ነው፤ በቃ ይሄውነው፤ በዚያ አካባቢ መወለዴ ከሌላው የሚለየኝ አይደለም። መስመር የሚሰራ ሰው ያመኛል፤ መስመር የሚባል ነገር የለውም፤ ምክንያቱም እኔ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር አካል ነኝ። ልክ የምንተነፍሰው አየር እዚህና እዚያ ብለን ልንከፍለው እንደማንችል ሁሉ አገርንም በትውልድ ቦታ ልንከፍለው አንችልም። እናም የማይከለለውን ነገር ከልዬ የዚህ አካባቢ ተወላጅ ነኝ ብል የተፈጥሮ ህግን የምቃወም ነው የሚ ሆነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ይህን ቢሉም በሁለቱ ክልሎች ያለው ውዝግብ አሁንም እንዳለ ነው፤ የመሬቱ ይገባኛል ጥያቄ ባልተመለሰበት ሁኔታ ሰላም ማስፈን አስቻጋሪ ነው ብለው አያምኑም?
ዶክተር ሃይሉ፡- ድንበር በሌለበት ሁኔታ ምንድን ነው ይገባኛል ብሎ ጥያቄ? በአይምሯችን የፈጠርነው ነገር ነው። የድንበር ጉዳይ ከሆነ የግዴታ መሆን ካለበት የሰውየው ፍላጎት ነው። የግድ ማካለል ካስፈለገም የህዝቡን ፍላጎት ማዳመጥ ማወቅ ወሳኝ ነው። በመቀሌ በኩል ያለው ሰው ይሄኛውን የራያ ሰው ወደዚህ ነው መሄድ ያለብህ ብሎ ሳይፈልግ የሚጎትትበት መንገድ የለም።
በአማራ በኩል ያለውም ካለፍላጎቱ ህዝቡን ቢጎትተው ወንጀል ነው የሚሆነው። ሰብአዊ ህግን መቃወም ጭምር ነው ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ የህዝቡን ፍላጎት ያንን ፍላጎት ማክበር ይገባል። ለዚህ ደግሞ ነገሮችን ግልፅ ማድረግ የፖለቲካ እውቀት እንዲኖረውና ማንቃት ማድረግ ያስፈልጋል። ምንም እውቀት ሳይኖረው በጨለማ ውስጥ ወደዚህና ወደዚያ ሂድ ልንለው አይገባም። ስለዚህ በመጀመሪያ የህዝቡን አይን መግለጥ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ሃይሉ፡- እኔም እዚህ ድረስ መጥታችሁ ከእኔ ጋር ቆይታ በማድረጋችሁ በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2012
ማህሌት አብዱል