አዲስ አበባ፡- ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል እአአ ከ2014 እስከ አሁን ድረስ 11 ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፎ ለህግ ከመስጠት አኳያ ከኢትዮጵያ ጋር በመስራት ላይ ነው፡፡
የኢንተርፖልና ዓለም አቀፍ የፖሊስ ትብብር ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ጸጋዬ ኃይሌ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤በቅርቡ ሁለት ሰዎች ተላልፈው ለኢትዮጵያ የተሰጡ ሲሆን፣ አንደኛው ከባንክ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ የሚፈለግ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ነው፡፡ እኤአ በ2014 እና 2015 ባለው ግዜም ዘጠኝ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ከተለያዩ አገሮች ለኢትዮጵያ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡
በቅርቡ ኢትዮጵያ ድንበር ዘለል ወንጀልን በተመለከተ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር የተደረገውን ስምምነት አስመልክተው፣ በኢንተርፖል የሚደረጉ ስምምነቶች ሊኖሩ እንደሚችሉና ከኢንተርፖል ውጭ ደግሞ የሁለትዮሽና የሦስትዮሽ ስምምነቶች በአገሮች መካከል ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ተናግረው፤ እነዚህ ስምምነቶች አንዳንዴ የኢንተርፖል መስመርን በመከተል የሚደረጉ አንዳንዴ ደግሞ መስመሩን መከተል ሳያስፈልግ ስምምነት ሊደረግ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ለትብብሩ ኢንተርፖል ደጋፊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እንደ ምክትል ኮማንደሩ ገለፃ፤ ኢንተርፖል በትኩረት ከሚሰራባቸው ወንጀሎች መካከል ሙስናና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በለውጥ ላይ ያለች አገር እንደመሆኗ የተጠቀሱትን አይነት ወንጀሎች ሰርተው ተጠርጣሪዎች ከአገር ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረትና ከአገር ውጪም የወጡት ላይ በትኩረት ከመስራት አኳያ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ መንግሥት ገንዘብን ከማስመለስ አኳያ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ነው፡፡ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል እንጂ ማንኛውም ሰው ከተጠያቂነት እንደማያመልጥም ይታመናል፡፡
እኤአ በ2018 ኢትዮጵያ ለፊንላንድ መንግሥት የቻይናን ዜጋ አሳልፋ መስጠቷን የተናገሩት ምክትል ኮማንደር ጸጋዬ፣ ተጠርጣሪ ወንጀለኛው ፊላንድ በነበረበት ወቅት የገንዘብ ማጭበርበር አድርጎ ከፍተኛ የሆነውን ገንዘቡን ወደ አገሩ መላኩን አስታውሰዋል፡፡ ግለሰቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሥራ ይሰራ እንደነበርም ተናግረው፤ የፊንላንድ መንግሥት ሙሉ መረጃውን በመላኩ ኢንተርፖል ቀይ ማስታወቂያ እንዳወጣበት ገልፀዋል፡፡ ይህን ያደረጉትም ከቻይና መንግሥት ጋር ከመከሩበት በኋላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት ኢንተርፖል ከዚህ በፊት በተባበሩት መንግስታት ኒዮወርክ ላይ እንዲሁም በአውሮፓ ደግሞ ብራሰልስ ላይ ተጠሪ ጽህፈት ቤት ያለው ሲሆን፣ አሁን ላይ ደግሞ ሦስተኛ የሆነውን ተጠሪ ጽህፈት ቤቱን ከሁለት ዓመት በፊት በአፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ መክፈቱ የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የዚህ ተቋም አባል የሆነችው እኤአ በ1951 ነው፡፡ በቅርቡም የኢንተርፖል ዋና ኃላፊ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቸውና ከሰላም ሚኒስቴር ጋር መምከራቸው ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2011
በአስቴር ኤልያስ