አዲስ አበባ፡- በአንድ ሀገር ውስጥ ሊኖር የሚችለው አንድ የመከላከያ ሰራዊት ብቻ ነው ሲሉ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ ተናገሩ፡፡
በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ የሚታየውን የሰላም መደፍረስ አስመልክቶ አቶ ሌንጮ ለታ ለአዲስ ዘመን በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፤ ኦነግና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የደረሱበትን ስምምነት እስከ ዛሬም ይፋ አላደረጉም፤ ይዘቱም ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ስለዚህ የትኛው አካል ተሳሳተ የሚለውን ለመለየት አዳጋች ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሀገር ውስጥ የገቡት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እንደመጡ ይታወቃል፡፡
በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ተስማምተው ወደ ሀገር ከገቡት ሌሎች ፓርቲዎች የተለየ አያያዝ ለኦነግም የሚኖርበት ምክንያት አይኖርም የሚሉት አቶ ሌንጮ፤ የኦነግ ሰራዊት ትጥቅ ፈትቶ ወደ ሰራዊቱ መቀላቀል ያለበት ወደ ሰራዊት መግባት አለበት፤ የቀረው ደግሞ ሌላ ሥራ ሊፈለግለት ይገባል ብለዋል፡፡ የኦሮሚያ መስተዳድርና የኦነግ መሪዎች ችግሩን የመፍታት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በመሆኑም ሁለቱ አካላት ውይይት ማድረግ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ በአንድ ቡድን ብቻ የመጣ ነው ብለው እንደማያምኑ የተናገሩት አቶ ሌንጮ፤ የለውጡ ባለቤትና አሸናፊ ህዝቡ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ውድድር ውስጥ መግባትም ምንም ፋይዳ የለውም ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ሌንጮ ማብራሪያ፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ለሚታየው የሰላም መደፍረስ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚህም የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች በመካከላቸው ያለው የፖለቲካ ውድድር አላስፈላጊ መልክ እየያዘ መምጣቱና ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች በኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ያለውን ልዩነት ማራገባቸው ነው፡፡
የተጀመረው ለውጥ ሙሉ በሙሉ ዴሞክራሲያዊ ወደሆነ ስርዓት እንዲሸጋገር ሁሉም መረባረብ አለበት ያሉት አቶ ሌንጮ፤ ለውጡን የማስቀጠል ሸክም ለውጡን እየመራ ላለው አካል ብቻ የሚተው አይደለም ብለዋል፡፡ ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አገር ትሆናለች፡፡ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለኦሮሞም ትበጃለች በማለት ተናግረዋል፡፡
በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) መካከል ተደርገው የነበሩ ስምምነቶችን ኦነግ ተግባራዊ አለማድረጉ አሁን በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት መሆኑን ኦዴፓ ማስታወቁ እንዲሁም በአንድ ሃገር ሁለት መንግሥት የማይኖርበት እና የኦነግ ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ በተመለከተ ተደርሶ የነበረው ስምምነት አለመከበሩን ኦዴፓ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ኦነግ በበኩሉ በሰጠው መግለጫ በሁለቱም ወገኖች እንዲከበሩ የሚጠበቁ ስምምነቶች አለመከበራቸውን ገልጾ ነበር፡፡
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል አለማየሁ እጅጉ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ባለፉት አራት ወራት ብቻ በኦነግ አማካኝነት በተፈጠሩ ችግሮች የ29 ንጹሃን ዜጎች ህይወት መጥፋቱን፣ የ12 የፖሊስ አባላት ህይወት ማለፉንም እንዲሁም 77 የፖሊስ አባላት እና 40 ሚሊሻዎች መቁስላቸውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2011
በወንድወሰን መኮንን