በጥቅምት ወር 1925 ዓ.ም የአቶ ተክሌ ማሞ ባለቤት ወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ በታሪካዊቷ አንኮበር ከተማ ወንድ ልጅ ተገላገሉ። ስሙንም አፈወርቅ ብለው ሰየሙት። ይሁን እንጂ የህፃኑ አፈወርቅ የልጅነት ጊዜ የመከራ ወቅት ነበር። ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በግፍ ስለወረረች፣ የአፈወርቅ የልጅነት ትዝታም ይሄው የግፍ ወረራ እና ጦርነት ያስከተለው የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ በነበረው ውጊያ ምክንያት ሕፃኑ አፈወርቅ ቆስሎ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
ከፋሺስት ኢጣሊያ መባረር በኋላ አፈወርቅ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በአርበኞች እንዲሁም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤቶች ትምህርቱን ተከታተለ። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ቆይታውም ከመኳንንት ልጆችና ከነፃነት በኋላ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ መስኮች ጉልህ አስተዋፅዖ ካበረከቱ ተማሪዎች ጋር የመገናኘት እድል አገኘ።
የኢትዮጵያ ጠበቃና ባለውለታ የነበሩት እንግሊዛዊቷ የፀረ-ፋሺስት ንቅናቄ መሪና የሴቶች መብት ተሟጋች ሲልቪያ ፓንክረስት የነአፈወርቅን ትምህርት ቤት በጎበኙበት ወቅት የትምህርት ቤቱ መምህራን አፈወርቅ ደብተሩ ላይ የሚስላቸውን ስዕሎች ለሲልቪያ አሳይተዋቸው ስለነበር ሲልቪያ ለታዳጊው አፈወርቅ አደናቆታቸውን ገለጹለት።
ገና በአሥራ አምስት ዓመቱ፣ በ1940 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው ወደውጭ ከሚላኩ ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን ትምህርቱን ለመከታተል ወደ እንግሊዝ አገር ሄደ። ወደ እንግሊዝ በመሄጃቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቤተ መንግስት ተጠርተው የቀረቡት እነአፈወርቅ፤ ንጉሰ ነገሥቱ ‹‹ጠንክራችሁ መስራት አለባችሁ፤ ስትመለሱ በአውሮፓ ስላያችኋቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ወይም ሰፋፊ መንገዶች እንድትነግሩን አንፈልግም፤ ይልቁንም ኢትዮጵያን ዳግም ለመገንባት በሚያስፈልገው ክህሎትና አስተሳሰብ ራሳችሁን አስታጥቃችሁ መመለሳችሁን እርግጠኛ ሁኑ›› የሚል ምክር እንደለገሷቸው ከብዙ ዓመታት በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።
እንግሊዝ እንደደረሱም ከሲልቪያ ፓንክረስትና ከልጃቸው ከስመጥሩ የታሪክ ምሑር ከሪቻርድ ፓንክረስት ጋር ተገናኘ። ከዚያም ሌይተን ፓርክ የሚባል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (Leighton Park Secondary School) ገባ። በትምህርት ቤት ቆይታውም፣ የባዕድ አገር ባህሎች፣ የአየር ለውጥ እና የተለመደው የተማሪ ቤት ሀሜትና ሽሙጥ (ዝንጠላ) ቢያስቸግረውም ትምሕርቱን በትጋት ሲከታል ቆይቶ በተለይም በሒሣብ፣ በኬሚስትሪ እና በታሪክ ትምሕርቶች ጥሩ ውጤት በማምጣት ሰለጠነ። አፈወርቅ በነዚህ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት እንኳን ዘወትር በእርሳስም ሆነ በብዕር ንድፎችንና ሥዕሎችን በመተለምና በመሳል ሥራ ተጠምዶ ይታይ እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል።
የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት አፈወርቅ እንዲያጠና የፈለገው የማዕድን ቁፋሮ ትምህርት ነበር። የአፈወርቅ ፍላጎት ደግሞ ሰዓሊ መሆን ነበር። ወላጆቹና ዘመዶቹም ቢሆኑ የስዕል ችሎታውን ቀደም ብለው ተገንዝበውት ነበር። ይሁን እንጂ ሲልቪያ ፓንክረስት የአፈወርቅን የስዕል ችሎታ ያውቁ ስለነበር ታዳጊው አፈወርቅ ፍላጎቱን እንዲያሳካ እንዲፈቀድለት ወደ አዲስ አበባ ደብዳቤ ፃፉ። ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ አፈወርቅ ለንደን ውስጥ ወደሚገኝ የስነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት (Central School of Art and Design) ገባ። በኋላም ለንደን ከተማ ውስጥ በሚገኘው በዝነኛው የስሌድ የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት (Slade School of Fine Art) ተቀባይነት ያገኘ የመጀመሪያው አፍሪካዊ በመሆን ወደዚሁ ትምህርት ቤት ገባ። በትምህርት ቤት ቆይታውም በተለያዩ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ አሸንፎ ሽልማቶችን ያገኝ ነበር። እግሩ በረገጠባቸው ቦታዎች ሁሉ ስለኢትዮጵያ ታሪክና ባሕል ያለመታከት ይናገር ነበር። ስዕል፣ ቅርፃ ቅርጽ እና አርክቴክቸር አጥንቶ ተመረቀ።
ወደ ኢትዮጵያ ከመመለሱ በፊትም ከወዳጁ ሀብተ-አብ ባይሩ እና በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደረባ ከነበሩት ብርሃኑ ተሰማ ጋር በመሆን አውሮፓን ጎብኝቷል። ይህ ጉብኝትም የአውሮፓን ስነ ጥበብ የማየት እድል አስገኘለት። በፓሪስ፣ በማድሪድ፣ በሮም፣ በለንደንና በሌሎች አውሮፓ ከተሞች ያሉ የስነ ጥበብ ውጤቶችን ተመለከተ።
ትምሕርቱን አጠናቆ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ በየጠቅላይ ግዛቶቹ እየተዘዋወረ የኢትዮጵያን ታሪክ እንዲሁም የሕዝቡን ባህልና ወግ ለማጥናት ሞክሯል። ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ ለመሆን ህልም የነበረው አፈወርቅ፤ ይህን ህልሙን እውን ለማድረግ የመረጠው መንገድ የምዕራባውያን ጠበብትን የአሳሳል ዘይቤ መቅዳት ሳይሆን የራሱን ዘይቤ መፍጠር ነበር። ‹‹የዓለም አቀፍ ሰዓሊ ዋናው ጉዳይ የሥነ ጥበብ ሥራው የተወለደበትን ስፍራ ቃና እንዲይዝ ማድረግ ነው›› የሚል እሳቤ ነበረው። ከውጭ ሲመለስ የተመደበበትን ሚኒስቴራዊ ሥራ በመተው በኪነ-ጥበብ ሥራው ላይ በማተኮር ስዕሎቹን በአገር ውስጥና በውጭ አገራት እያሳየ ለማገልገል ወሰነ። በብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት (ወመዘክር) ውስጥ የስዕል ስቱዲዮ በመክፈት ስነ-ጥበባዊ ስራውን ቀጠለ።
በ1946 ዓ.ም ሥራዎቹን የሚያሳይ የመጀመሪያውን የኪነ-ጥበብ አውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቀረበ። ይህ አውደ-ርዕይ የተከፈተው በንጉሰ ነገሥቱ ነበር። አውደ ርዕዩ ከፋሺስት መባረር በኋላ የመጀመሪያው የሥዕል ትርዒት ሆኖ ተመዝግቧል። ከአውደ ርዕዩ ባገኘው ገቢ ወደ አውሮፓ ተመልሶ በመሄድ የጠለቀ የኪነ-ጥበብ ጥናት አጠና። በኢጣልያ፣ በፈረንሳይ፣ በስፔን፣ በፖርቱጋል እና በግሪክ በመዘዋወር ጥናታዊ ጉብኝቶችን አደረገ። በአውሮፓ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ የብራና መጻሕፍት በጥልቀት ተመለከተ። በፓሪስ ብሔራዊ ቤተ መፃህፍትና በሮም የቫቲካን ቤተመዘክር ውስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ የብራና ሥዕላዊ ፅሁፎች ላይ ጥናት በማካሄድና ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ሲወራረድ የመጣውን ኢትዮጵያዊ የሥዕል ቅርፅ በመገምገም የራሱ ስለሆነው የሥነ-ጥበብ ምንጭ ጥልቅ እውቀትንም ገበየ። ከጥንታዊው የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ጋር ያስተሳሰረን ልምድ ያገኘውም በዚህ ጊዜ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የመስታወት ስዕል (Stained Glass Art) እና የሞዛይክ አሠራር ጥበብን ተምሮ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።
ከዚያም ንጉሠ ነገሥቱ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒን ለመግደል የተደረገውን ሙከራ ለመበቀል የፋሺስት ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ ጉዳት ደርሶበት የነበረውን የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያንን በሃይማኖታዊ የግድግዳና የጣሪያ ስዕሎች፣ የሞዛይክ ሥራዎች እንዲሁም መስኮቶቹንም በመስታወት ስዕሎች እንዲያሳምር ትዕዛዝ ሰጡት። ትዕዛዙንም በሚገባ ፈጸመ።
በሐረር ጦር አካዳሚ የሠሯቸው የኢትዮጵያ አራት የጦር ጀግኖች ኢዛና፣ ካሌብ፣ ምኒልክና ራስ መኰንን የሚታዩባቸው የመስተዋትና የመስኮት ሥዕሎች ናቸው። ይህንን በሚሠሩበት ጊዜ ያጋጠማቸውን ነገር ከዓመታት በፊት እንዲህ ገልጸውት ነበር …
‹‹ … በሐረር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚና የተጫወቱ የቅርብና የጥንት ነገሥታት እንዲሠሩ ተፈልጎ አንድ ጣሊያናዊ ሠዓሊ ከቅርቦቹ አፄ ምኒልክና ራስ መኰንን፤ ከጥንቶቹ ጀግኖች ለአካዳሚ ተማሪዎች ምሳሌ እንዲሆን ናፖሊዮንና ታላቁ እስክንድርን ለመሣል ሃሳብ ያቀርባል። ጃንሆይም ‹አንተ ተምረህ የለ እንዴ ለምን አትሠራውም?› ብለው ይጠይቁኛል። የሥራ ሚኒስትሩን አዝዘው ሔጄ ጥናቱን ተመለከትኩ። ‹የምኒልክና የራስ መኰንን ይገኛል። ታላቁ እስክንድርንና ናፖሊዮንን ግን ምን አመጣቸው? እኛ ከክርስትና በፊትና በኋላ የተነሱ ብዙ ጀግኖች አሉን። እነርሱን መሥራት አለብን። ይኸ ‹‹ሰልፍድ ዊል ኮሎኒያሊዝም›› ስለሚሆን ኢዛናና ካሌብ መሰራት አለባቸው› ብዬ ለጃንሆይ ሐሳብ አቀረብሁ። ሁለቱም መሠረቶች ናቸው። ካሌብ የመርከብ ኃይላችን በነበረ ጊዜ እስከ ፋርስ ድረስ ይንቀሳቀስ ነበር። ባቀረብኩት ሃሳብ መሰረትም እንድሠራ ተደረገ›› ብለዋል።
አሁን በሐረር ከተማ የሚገኘውን የልዑል ራስ መኮንን ሐውልት የሠሩትም እርሳቸው ናቸው። ይህ ስራቸውም በቅርፃ ቅርፅ ስራቸው ስማቸው ገዝፎ እንዲታወቅ አስቻላቸው። አፈወርቅ ስለኢትዮጵያ ህዝብ የሚገልፁ አያሌ ሥራዎችን በቅርፃ ቅርፅ ለመስራት ቢተልሙም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከራስ መኮንን ሐውልት በስተቀር ሌሎቹ እንዳልተሰሩ መረጃዎች ያሳያሉ። የስዕል እና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸው በቴምብሮች፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የኪነ ጥበባት ትርዒቶች ላይ እጅግ በጣም እየታወቁና እየገነኑ መጡ።
በ1950 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የአፍሪካ አዳራሽን የማስዋብ ስራ ተሰጣቸው። በአዳራሹ መግቢያ ላይ ‹‹አፍሪካ ያኔ፣ አፍሪካ አሁን እና አፍሪካ ወደፊት›› የሚለውና የአፍሪካን የትናንት የቅኝ አገዛዝ ዘመን፣ የአሁን የነፃነት ትግል እና የነገ ነፃ አፍሪካ መፃኢ እድል ያሳያል የተባለው የመስታወት ላይ ሥራቸው ዓለም አቀፋዊ አድናቆት ብቻ ሳይሆን ከፍ ያለውን ‹‹ወርልድ ሜዳል ኦፍ ፍሪደም›› የተሰኘውን ሽልማት እንዲጎናጸፉ አስቻላቸው። ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላም በሥነ ጥበብ ሥራቸው ውስጥ ስለ ሰው ልጅ የመንፈስ ነፃነት፣ የሰው ልጅ የሌላ ዓይነት መጥፎ ሐሳብ ባርያ መሆን እንደማይገባውና፣ ወደ ሰላምና ወደ አንድነት ሃሳብና ድርጊት የሚመራ በአንድ ሥራ ብቻ ሳይሆን በብዙ ሥራ ውስጥ እንደሚታይ ተናግረዋል።
በ1954 ዓ.ም በአዲስ አበባ የቀረበው የሰዓሊው ትዝታ ጠቀስ ትርኢት፤ በአገሪቱ የሥነጥበብ ዘርፍ ከፍተኛ ምዕራፍ የያዘ ሲሆን፤ በወቅቱ ከቀረቡ 73ቱ የቀለም ቅብ ሥዕሎች አንዷ የነበረችው ‹‹የመስቀል አበባ›› ሥዕል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። በዚህ ትዕይንት ስኬታማነት ባገኙት እውቅና የተነሳም በሶቭየት ኅብረት፣ በአሜሪካና በሴኔጋል ዓለም አቀፍ የስነ ጥበብ ትዕይንቶች ላይ ሥራዎቻቸውን ለማሳየት መንገድ ተከፍቶላቸዋል። በመቀጠልም የአፍሪካ አህጉርን ተዟዙረው የተመለከቱት አፈወርቅ፤ ከቅኝ ግዛት ሙሉ በሙሉ ያልወጡት አፍሪካውያን ለነፃነት ያደርጉት በነበረው ትግል ተነሳስተው ‹‹የአፍሪካ ስልጣኔ የጀርባ አጥንት››፣ ‹‹አፍሪካዊ አንድነት›› እና ሌሎች አፍሪካዊ ይዘት ያላቸውን ሥዕሎች ስለዋል። ‹‹ጨለምተኛ አይደለሁም፤ ሰዎች ሥዕሌን አይተው ተስፋ እንዲያገኙ እፈልጋለሁ፤ ሰዎች ስለኢትዮጵያ፣ ስለአፍሪካ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው እሻለሁ… ከሁሉም በላይ ደግሞ ‹ይቻላል› ብለው እንዲያስቡ እፈልጋለሁ›› ብለው ነበር።
አፈወርቅ ተክሌ ከፍ ያለ ችሎታና ስነ ምግባር ያላቸው አርቲስት ከመሆናቸውም ባሻገር፣ በብዙ የሥዕል ሥራዎቻቸው ክፍለ ዓለማቸውን አጉልተው ስለገለፁና በኢትዮጵያ ስነ ጥበብን በዘመናዊ ቴክኒክ መሥራት ከጀመሩት ከቀዳሚዎቹ መካከል አንዱ ስለሆኑ በ1957 የመጀመሪያውን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ብሔራዊ የሥነ ጥበብ ሽልማት አሸነፉ። በስነ ጥበብ ዘርፍ ሽልማት እንዲዘጋጅ ሃሳቡን ያቀረቡትም እርሳቸው ነበሩ። በአንድ ወቅት ስለ ጉዳዩ ሲያስረዱ ‹‹ … በአገራችን አምስት ማዕረግ ያላቸው ሰባት ኒሻኖች አሉ። ሁሉም የጦር ሜዳና የሃይማኖት ናቸው። በሥነ ጥበብ የለንም። በአገራችን ሥነ ጥበብ ረዥም ታሪክ ያለው ስለሆነ በግርማዊነትዎ ዘመነ መንግሥት እንደ ፀሐይ የሚያበራ ሽልማት መስጠት አለበት። እንደ ኖቤል ያለ ሽልማት ለአርቲስቶች መስጠት አለብዎት። እኔ ዲዛይኑን ለመሥራት ዝግጁ ነኝ። ከኢትዮጵያ የኒሻን ዓይነቶች አንዱ መሆን አለበት› ስላሏቸው ለመቋቋም ችሏል›› ብለው ነበር።
ስራዎቻቸው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመሰራጨታቸው ዝናቸው ከአገር ውስጥ ባሻገር በውጭ አገራትም እየናኘ መጣ። የሥነ-ጥበብ ትዕይንት እንዲያቀርቡ ተጋብዘው ወደ ሶቭየት ኅብረት በሄዱበት አጋጣሚ በተለያዩ ግዛቶች እየተዟዟሩ ንግግር አድርገዋል። ይህን ተከትሎም የአሜሪካ መንግስት በዋሺንግተንና በኒውዮርክ የራሳቸውን የሥነ ጥበብ ትዕይንት እንዲያቀርቡ ጋብዟቸዋል። በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎችም ንግግሮችን የማድረግ እድል አግኝተዋል። በሴኔጋል፣ በቱርክ፣ በዛየር፣ በግብፅ፣ በቡልጋሪያ፣ በጀርመን፣ በኬንያና በአልጀሪያ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ትዕይንቶችን ማቅረብ እንደቻሉም መረጃዎች ያመለክታሉ።
በ1974 ዓ.ም ሁለተኛውንና ትልቅ ግምት የተሰጠውን የሥዕል ትዕይንት በሞስኮ ከተማ ያቀረቡ ሲሆን፤ በዓለም ዝነኛው የኡፉዚ ሙዚየም ከአፍሪካ የሥነጥበብ ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በር ከፋች አድርጐ ‹‹ራሱን በራሱ›› (Self Portrait) የተባለውን ሥዕላቸውን በመቀበል ተገቢ የክብር ስፍራ ሰጥቶታል።
ከስራዎቻቸው መካከል ‹‹ኪዳነ ምሕረት››፣ ‹‹እናት ኢትዮጵያ››፣ ‹‹የመስቀል አበባ››፣ ‹‹የዳግም ምፅዓት ፍርድ››፣ ‹‹ደመራ››፣ የራስ መኮንን ሐውልት፣ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስዕሎችና ሞዛይኮች፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካ አዳራሽ ስዕሎችና ሞዛይኮች፣ በሐረር የጦር አካዳሚ የሚገኙ የመስታወት ስዕሎች፣ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን የዘውድ ስርዓት እንዲሁም ንጉሥ ሰለሞን በኢየሩሳሌም ለንግሥተ ሳባ ያደረገላትን አቀባበል የሚያሳዩት ሥራዎች … ጥቂቶቹ ናቸው።
ከመቶ የማያንሱ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን እንዳገኙ የሚነገርላቸው አፈወርቅ ተክሌ የአራት ዓለም አቀፍ የሥነጥበብ አካዳሚዎች አባል ነበሩ። በ1964 ዓ.ም የሰው ልጆችን ወንድማማችነትና የሰላም ልዕልናን የሚመሰክረውን ሥራቸውን በተለያዩ አገሮች አቀረቡ። በዚህ ሥራቸው በ1971 ዓ.ም በአልጀርስ የጥበብ ፌስቲቫል ላይ የወርቅ ሽልማት ክብርን አግኝተዋል። በፈረንሳይ ባቀረቡት የሥዕል ሥራ የጃፓን፣ የፈረንሳይና የሜክሲኮ ተወዳዳሪዎችን በልጠው አንደኛ ወጥተው ከመሸለማቸውም በላይ፣ የቤናል የሎሬት ማዕረግን ክብር አገኙ። በ2001 ዓ.ም ኢትዮጵያንና አፍሪካን የሚወክሉ አዳዲስ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን ዋሽንግተን ዲሲ (በወርልድ ፎረም ፌዴሬሽን) ላይ አቅርበው የ21ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ ታላቅ አርቲስት በመባል ከተመረጡት መካከል የምርጦች ምርጥ ‹‹ዘ ግሬተስት ማን›› ክብርን አግኝተዋል። እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ በተጠራው 27ኛው የአሜሪካ ባዮግራፊካል ኢንስቲትዩት ጉባኤ የዓለም ሎሬት ክብርን ተቀዳጁ። እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም ደግሞ በአየርላንድ ደብሊን ላይ በተካሄደው የሳይንስ፣ ባህልና ጥበብ ጉባኤ ለሰው ልጆች ትምህርትና ለጥበብ ዕድገት ለዓለም ባበረከቱት መልካም ተግባር ‹‹የዳቪንቺ አልማዝ ሽልማት››ን ሲቀበሉ፣ በዚሁ ጉባኤ ላይ ዩናይትድ ካልቸራል ኮንቬንሽን (United Cultural Convention) የተባለው ተቋም ለዓለም ጥበብ ዕድገት ላበረከቱት መልካም ሥራ የጀግና ክብር ኒሻን ሸልሟቸዋል። ያ ከፋሺስት ኢጣሊያ የቦምብ ናዳ የተረፈው ሕፃኑ አፈወርቅ ተክሌ ‹‹እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ›› ለመባል (ለመሆን) በቃ! ለመጀመሪያ ጊዜ የአገራቸው ስምና አጭር የሕይወት ታሪካቸው ተጽፎ ወደ ጨረቃ ከተላከላቸው 200 ታላላቅ የአገር መሪዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ደራስያን፣ ሠዓሊያን … መካከል አንዱ የእኛው አፈወርቅ ተክሌ ናቸው።
ሰዓሊው መኖሪያ ቤታቸውን፣ እንዲሁም ስቱዲዮና ጋለሪ ያካተተውንና ‹‹ቪላ አልፋ›› የተሰኘውን ሕንፃ ራሳቸው ዲዛይን ያደረጉት ሲሆን ስራውም 15 ዓመታት እንደፈጀ ይነገራል። 22 ክፍሎች ያሉት ‹‹ቪላ አልፋ›› ጥንታዊቷን አክሱምን፣ የጎንደር ቤተ መንግስትንና የሐረር ግንብን በሚያንፀባርቅ መልኩ የታነፀ ነው። የሥዕል ንድፎችና የቀለም ቅቦች፣ የግድግዳ ላይ ሥዕሎች፣ ሞዛይኮች፣ የመስታወት ቅብ ሥዕሎችና ቅርፃ ቅርፆች፣ እንዲሁም ቴምብሮች፣ የመጫወቻ ካርታዎች፣ የአደባባይ ፖስተሮች፣ የሰንደቅ ዓላማና የብሔራዊ ክብረ በዓላት ልብሶች ሳይቀሩ አፈወርቅ የኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሥነ ጠቢብ እንደሆኑ መስክረዋል፤ ዓለም አቀፍ ዝናቸው እንዲናኝም አድርገዋል።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ባደረባቸው ጽኑ ሕመም በሕክምና እየተረዱ ሳለ፣ ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም በተወለዱ በ79 ዓመታቸው በአዲስ አበባ ካዲስኮ ሆስፒታል አርፈዋል። የቀብር ስርዓታቸውም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 5/2012
አንተነህ ቸሬ