ለብሮድካስት ጣቢያዎች የስርጭት ፈቃድ መስጠትና ለሕትመት ሚዲያው የምዝገባ አገልግሎት ማከናወን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በአዋጅ ከተሰጡት ተግባርና ሀላፊነቶች መካከል ይጠቀሳሉ። በዚህ መሰረት ባለሥልጣኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለበርካታ የህዝብ ብሮድካስት አገልግሎቶች፣ የንግድ ሬዲዮ ጣቢያዎችና ለማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ሰጥቷል። በሕትመት ሚዲያው በኩልም ለተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶች የምዝገባ አገልግሎት አከናውኗል። እኛም በባለስልጣኑ አሰራሮችና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ከአቶ ወንድወሰን አንዱዓለም ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ ብሮድካስት ባለስልጣን በአዋጅ የተሰጡትን ስልጣንና ሀላፊነቶች በምን ያህል ደረጃ ተግባራዊ እያደረገ ነው?
አቶ ወንድወሰን፦ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአገር ውስጥ የሚደመጡ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፍቃድ መስጠትና በአገሪቱና በዓለም አቀፍ ህጎች እንዲሁም በብሮድካስቱ አዋጅ መሰረት እየሰሩ መሆናቸውን መከታተል፤ በአግባቡ እየሰሩ ያሉትን ማበረታት፤ በትክክል የማይሰሩት ላይ ደግሞ ህጋዊ እርምጃን መውሰድና በመከታተል እንዲስተካከሉ ያደርጋል። በሌላ በኩልም የሚዲያውን ኢንደስትሪ አቅም የመገንባትና የሙያ ነጻነታቸው እንዲጠበቅ የማገዝ ስራንም ያከናውናል።
እነዚህን ስልጣንና ሀላፊነቶች በተግባር ለመተርጎም ደግሞ የተለያዩ ስራዎችን የሚሰራ ሲሆን ይህንንም ለመግለጽ ምናልባትም ከለውጡ በፊትና በኋላ ብለን ማስቀመጥ ሊኖርብን ይችላል።
ከለውጡ በፊት ያለውን ሁኔታ ብናይ የተሰጡት ስልጣንና ሀላፊነቶች በትክክለኛው መንገድ ተተርጉመው መሬት ላይ እንዳይወርዱ የተደረገበት ሁኔታ ነበር፤ በዚህም በመገናኛ ብዙሀኑና በባለስልጣኑ መካከል የድብብቆሽ ዓይነት ሁኔታ ነው ያሳለፍነው። ይህ ማለት ግን ብሮድካስት ባለስልጣን በህግ የተሰጡትን ስልጣንና ሀላፊነቶች መሉ በሙሉ አልተወጣም ማለት አይደለም። ሆኖም በብዛት የመገናኛ ብዙሀን ባለቤቶች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ደግሞ ዋና ተዋናይ የሆኑት ጋዜጠኞች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱን የሚረዱበት መንገድ አስቸጋሪ ነበር። በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ግን ፍቃዶችን ከመስጠት፣ ከማደስ፣ ከመሰረዝ፣ ከመቆጣጠር ጋር በተያያዘ ብዙ ተግባራትን ሲያከናውን ነበር የቆየው።
ከለውጡ ወደዚህ ያለውን ነገር ደግሞ ጠፍቶ የነበረው ነጻነትና ተገድቦ የነበረው ሀሳብን የመግለጽ መብት በሰፊው ተሰጥቷል። በዚህ እድል በመጠቀምም በውጭ አገር ያሉ መገናኛ ብዙሀን ሳይቀሩ ወደ አገር ውስጥ ገብተው ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ።
እዚህ ላይ ግን ዝግት ብሎ የነበረው ነገር በአንድ ጊዜ ሲከፈት የመጡ ችግሮች አሉ፤ እነዚህም ነጻነቱን በውል ተረድቶ ያለመንከባከብ፣ በተሰጠው ነጻነት ልክ ለህዝብ የሚገባውን ነገር ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ የሆኑ ችግሮች ይስተዋላሉ። በነጻነትና በልቅነት መካከል ያለውን ድንበር በውል ያለመገንዘብም ታይቷል። ሆኖም የትኛውም ለውጥ ያለምንም መንገራገጭ ወይንም ደግሞ ያለምንም እንከን ከአንዱ ገጽ ወደሌላው ገጽ ሊሸጋገር አይችልም። ከለውጡ ጋር ተያይዞ በሌላውም ዘርፍ የመጡ ክፍተቶችና ጉድለቶች በመገናኛ ብዙሀኑ ላይም እየተስተዋሉ ናቸው። ይህንን ማመንና መቀበል ያስፈልጋል። ነገር ግን ትልቁ ነገር ከመገናኛ ብዙሀን ነጻነት ጋር ተያይዞ ሲጮህ የነበረው አሁን መልኩን ቀይሮ በተለይም ከህብረተሰቡ የሚደመጠው ነጻነቱ በዝቷል የሚል ሆኗል። ከዚህ ቀደም የነጻነት እጥረት ያስጨነቀንን ያህል አሁን ደግሞ የነጻነት ብዛት እየተፈታተነን ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ የህብረተሰቡን አንድነት የሚያጠፉ ቅስቀሳ መሰል ስርጭቶች ሲካሄዱ እየተስተዋሉ ነው፤ እነዚህ አካላት ከህገወጥነታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ወንድወሰን፦ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በህግ የተሰጡትን ተግባርና ሀላፊነቶች ወደ ተግባር ከመተርጎሙ በፊት እራሱ ያለበት ቁመና መስተካከል ነበረበት። መስሪያ ቤቱ ይህንን ትልቅና ወሳኝ ኢንደስትሪ እንዲመራ ከተደረገ ይህንን መሸከም የሚያስችል አቅም ላይ መገኘት ነበረበት። ይህ ሲባል ደግሞ ተቋሙ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሃይል፣ በአደረጃጀት፣ በስልጣንና ሃላፊነት በኩል ያለው ሁኔታ እንደገና መታየት ነበረባቸው።
በለውጡ ማግስት የመገናኛ ብዙሀኑን በደፈናው “እንትናን ተችታችኋል፤ ይህንን አድርጋችኋል” ከማለት ይልቅ የሰሩትን ስህተት ሳይንሳዊ በሆነና በተጨባጭ መልኩ ሊያረጋግጥ የሚችል ስራን ለመስራት በአገሪቱ ውስጥ በጠቅላላው ያስተላለፏቸውን ፕሮግራሞች እስከ ስድስት ወር ድረስ መረጃቸውን አጠናቅሮ ሊይዝ የሚችል መሳሪያ (ማሽን) ተክለን ስራ አስጀምረናል። ይህንን ቴክኖሎጂ ደግሞ በሰው ሃይል አግዘን መገናኛ ብዙሀኑን ለመቆጣጠር የሚያስችል ቁመና ላይ እንዲገኝ እራሳችንን እያዘጋጀንም ቆይተናል። አሁን ላይ የተወሰኑ ሚዲያዎችን ይህንን ግድፈት ሰርታችኋል አርሙ የሚል መልዕክት እየላክን ነው ፤ በቀጣይም በሁሉም ተቋማት ላይ ተግባራዊ እናደርገዋለን።
ይህ የሚያሳየው ደግሞ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አይነተኛ አቋም ማሰር፣ መቅጣት፣ ማሳደድ፣ መዝጋት፣ ማጥፋት ከሚሉ አሉታዊ ከሆኑ አስተሳሰቦች ውጪ መሆኑን ነው ። ከዚህ በተቃራኒው መገናኛ ብዙሀኑ ራሳቸውን እንዲገነቡና እራሳቸውን አውቀው ከስህተታቸው እንዲታረሙ የማድረግ ስራ ነው እየሰራን ያለነው።
በሌላ በኩል በቅርቡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ካለው ስልጣን ባሻገር ተጨማሪ ሀላፊነቶችን የሚጨምርለትና በብሮድካስት ላይ ብቻ ያጠነጠነውን ሀላፊነቱን ወደህትመት ዘርፉም የሚያሳድግ ህግ ተረቅቆ ወደሚመለከተው አካል ተልኳል፤ ምናልባትም ከአንድ ወር በኋላ ጸድቆ ሰፊ ስራ የምንሰራበት ሁኔታ ይፈጠራል።
አዲስ ዘመን፦ ብዙዎች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተሰጠውን ስልጣንና ሀላፊነት እየተወጣ አይደለም ይላሉና እርስዎ ተወጥቷል፤ እየተወጣም ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ወንድወሰን፦ የእኛ ግብ መገናኛ ብዙሀኑን በአቅም መገንባት ነው፤ ይህንን ባላደረግንበት፣ ነጻ የመናገር መድረክ ባልፈጠርንበት፣ ባላላመድንበት፣ በሙያ ማህበራት ተደራጅተው እርስ በእርሳቸው እንዲረዳዱና አቅም እንዲገነባቡ ባለደረግንበት ሁኔታ ቶሎ ብለን ወደ እርምጃ መግባት የለብንም የሚል አቋም ነው የያዝነው፤ ከዚህ አንጻር ባለሙያዎች በአገር ውስጥና በውጭ አጫጭር ስልጠናዎችን እንዲያገኙ አድርገናል ህጉን የማሻሻልና ተቋሙን በሰው ሃይል የማደራጀት እንዲሁም በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ ሰርተናል።
በሌላ በኩልም ከመስመር እየወጡ ባሉ አንዳንድ
ሚዲያዎች ላይም ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግና በችግሮች ዙሪያ በመነጋገር የሚበጀውን በማሳየት ወደ መስመር ለማስገባት ፍሬአማ ነው ባይባልም ጥረቶችን አድርገናል፤ ሆኖም በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነና ማህበረሰቡንም ሰላም የማይሰጡ ከመሰለን በቀጣይ ህግ የማስከበር አቅሙም ፍላጎቱም ስላለው ወደዛ ለመግባት እንገደዳለን ።
አዲስ ዘመን ፦ የክልል ሚዲያዎች አንዱ አንዱን በመወንጀልና ስም በማጥፋት የሚያሰራጩትን ዘገባ በተመለከተ ብሮድካስት ባለስልጣን ለመገናኛ ብዙሀን የጻፈው ደብዳቤ እንደነበር ይታወሳል፤ በቀጣይስ የክልል የሚዲያዎች በእስከ አሁኑ አካሄዳቸው ይቀጥላሉ ወይስ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የእርምት እርምጃ ይወስዳል?
አቶ ወንድወሰን፦ አሁን በመገናኛ ብዙሀኑ ላይ ያለው ትኩሳት በሁለት ምክንያት የሚፈጠር ነው፤ የመጀመሪያው ተቋማቱ ከፖለቲካ መሪዎቹና ከፖለቲካው ትኩሳት ነጻ የሆኑ አይደሉም፤ ይህ ደግሞ ተቋማቱ መንግስት የከፋው ቀን ይከፋቸዋል ሲደሰትም ይደሰታሉ፤ ከዚህ ውጪ ግን ነጻ ሆነው ልክ መሆንና አለመሆንን ተገንዝበው የመዘገብ ቁመና ላይ አልደረሱም። በርግጥ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እዚህ ከፍታ ላይ እንዲደርሱ ይሰራል። ሌላው በክልሎች መካከል በፖለቲካው ሳቢያ የሚፈጠሩ ቅያሜዎችና አለመግባባቶች ወይንም ደግሞ ክልሎችን በሚመሩ አመራሮች መካከል የሚከሰቱ አሉታዊ ምልክቶች መገለጫ ሆነዋል።
ስለዚህ በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ እንጂ በመገናኛ ብዙሀን እሰጣ አገባ የሚፈጠርባቸው እንዳይሆኑ መንግስት የበኩሉን ጥረት ያደርጋል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ይህንን ያበረታታል ይደግፋል። ከዚህ ባሻገር ችግሮቹ እስኪፈቱና ጠንካራ መሰረት እስከሚይዙ ድረስ የመገናኛ ብዙሀኑ እንደዚሁ ድንጋይ እየተወራወሩ ይዘልቃሉ ማለት አይደለም። ምክንያቱም አየር ሞገድ የህዝብ ሀብት ነው። ይህንን ሀብት ደግሞ ለእነርሱ የሚሰጣቸው ማህበረሰቡን የሚጠቅም ህጋዊ ነገር እንዲሰሩበት ብቻ ስለሆነ። ለእስከአሁኑ ጥፋታቸው በደብዳቤ የማስጠንቀቅ፣ በስልክ የመነጋገር፣ መረጃዎችን ደግሞ ከላይ በጠቀስኩት ማሽን አማካይነት እያጠናቀርንና የተላለፈው ፕሮግራም በመስፈርቱ መሰረት እየመዘንን፣ የአገሪቷን ህግ በተከተለ፣ አለም አቀፍ ህጎችንና የብሮድካስት አዋጁን መሰረት በማድረግ እንዲታረሙ እየሰራ ነው። በዚህ የማይመለሱ ከሆነ ግን አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን።
አዲስ ዘመን ፦ ተቋሙ አቅሙን ሳይገነባ ሌሎችን መቆጣጠር አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል፤ ሆኖም የእርሱ አቅም እስከሚገነባ የሚበላሸውንስ ነገር በኋላ ማስተካከሉ አያስቸግርም ይላሉ?
አቶ ወንድወሰን፦ መርዶ ተላምዶን ብስራት ነው እየጨነቀን ያለው፤ አንዳንዱ ሆን ብሎ፣ ሌላው ደግሞ ባለማወቅ፣ ገሚሱ ደግሞ ተምታቶበትም ጭምር ብዙ ነገሮች እየተበላሹ እንደሆነ እናያለን። ለምሳሌ ዘውዳዊው ስርዓት ተወግዶ ወታደራዊው ደርግ ስልጣኑን ሲቆጣጠር በገበሬው፣ በተማሪው፣ በምሁሩ፣ በእናቶችና አባቶች ዘንድ ዴሞክራሲ ወደ አገሪቱ ይገባል የሚል ተስፋ ተሰንቆ ነበር፤ ይህም ለተወሰነ ግዜ ታይቶ ከሰመ። ከዛ በኋላም ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ በርካታ ጋዜጦችና መጽሄቶች እንዲሁም የብሮድካስቱ ሁኔታ ሁሉ ለየት ያለ ሆኖ ነበር፤ ምናልባትም በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሆኖም መንግስት ረበሹኝ ብሎ ያመነባቸው መገናኛ ብዙሀን ብቅ ብቅ ሲሉ ግን በተጀመረው መልኩ መቀጠል ሳይቻል ቀረ። ብዙ ጋዜጠኞች ለስደት߹ ለእንግልት ተዳረጉ፤ ብዙ ፍቃዶችም ተሰረዙ፤ አንዳንድ መገናኛ ብዙሀንም እንዲዘጉ ሆነ።
አሁን የመጣው ለውጥም በነጻነት የመናገር መብትን ያለገደብ እሰጣለሁ ብሎ ቃል ገብቶ በውጭ ያሉ መገናኛ ብዙሀንም ወደአገር ቤት እንዲገቡ ሆኖ ስራ እየሰሩ ናቸው፤ ይሁን እንጂ ሰዎችን የሚያስቆጡ የአገርን አንድነት የሚሸረሽሩ ነገሮች መጡ፤ ስለዚህ ይህ ነገር ከተፈጠረማ ብሎ መንግስት እርምጃ መውሰድ ከጀመረ ቀድሞ ያጣናቸውን ዴሞክራሲን ስር እንዲሰድ የሚያደርጉ እድሎች ዳግም ልናጣቸው ነው። ስለዚህ “ያንጠለጠልነውን እየጣልን የጣልነውን እያነሳን “ በዚህ አዙሪት ውስጥ እስከመቼ ድረስ እንዘልቃለን በሚል መንግስት ትዕግስትን መርጧል።
በሌላ በኩልም እስከ አሁን የመጣንባቸው አካሄዶች ብዙ መስዋዕትነት ያስከፈሉን ከመሆናቸውም በላይ እነሱን ማድረግ ከቻልን ደግሞ ታግሰን ዴሞክራሲን ስር እንዲሰድ ለማድረግ አይሳነንም እስቲ ትንሽ እንታገስ፤ ይህ ሁኔታ ዛሬ ለእኛ ጭንቀት ቢሆንም ለልጆቻችን የተሻለ ቀን የሚያመጣ ነው በማለት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ትዕግስቱን ህግ ከማስከበር ጋር አጣጥሞ ለመሄድ እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ ካለው ወቅታዊ የመገናኛ ብዙሀን ልቅነት ጋር ተያይዞ ብዙ ሰዎች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የለም እስከማለት እየደረሱ ነውና እናንተ የህዝቡን ስሜት ያጠናችሁበት ሁኔታ ይኖር ይሆን?
አቶ ወንድወሰን፦ አዎ በተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ እየተዘዋወርን መድረኮችን እያዘጋጀን ነው፤ በእነዚህ መድረኮች ላይም ህብረተሰቡ መገናኛ ብዙሀኑ አካሄዳቸው ትክክል አይደለም ለእኛ የሚበጀንን ነገር እያደረጉ አይደለም ፤ ከቻሉ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጡልን፤ አይ ካሉ ደግሞ ዝም ይበሉ እያለ ነው፤ ከዚህ አንጻር ደግሞ ተቋማቱ የህዝቡን ድምጽ ይሰማሉ ብለን እናምናለን፤ ጥያቄው ከህዝብ ስለመጣ ተቋሙም ህዝብን የማገልገል ሀላፊነት ስላለበት ህግ የማስከበር ስራውን ይሰራል።
አዲስ ዘመን፦ መገናኛ ብዙሀን ላይ ያሉ ባለሙያዎች ሙያዊ ስነምግባራቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ እንደ ተቆጣጣሪ አካል በእናንተ በኩል የሚሰራው ስራ ምንድን ነው?
አቶ ወንድወሰን፦ በትልቁ እናስባለን ነገር ግን ከትንሹ እንጀምራለን፤ የሚል አጠቃላይ የሆነ የለውጥ ቅኝት ውስጥ ነው ያለነው፤ በአጠቃላይ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያውን ሙያዊ ብቃቱን፣ ክህሎቱንና ሁለንተናዊ ግንዛቤውን ከፍ ከማድረግ አንጻር የተለያዩ ስራዎች ይሰራሉ። ለምሳሌ ከአለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር በመሆን ጋዜጠኞች ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እያደረግን ነው፤ በቀጣይም ከ15 ቀን በኋላ ከ110 በላይ ለሚሆኑ ጋዜጠኞች ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቱ ተጠናቋል። በሌላ በኩልም በትምህርት ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ተግባር ተኮር ስልጠናን አግኝተው ዘርፉን የሚቀላቀሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ከኳታር መንግስትና ከአልጀዚራ ጋር በመተባበር በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ የሚገባ የሚዲያ ኢንስቲትዩት የማቋቋም ስራም እየሰራን ነው፤ ከዚህም ባሻገር የሚዲያ አመራሮች ነጻ ሆነው ጋዜጠኞቻቸውን ማብቃት እንዲችሉ የሙያ ማህበራት በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግም የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አንድ ሰው የመገናኛ ብዙሀን ባለቤት ለመሆን ሲያስብ ማሟላት የሚገባው መስፈርት ምንድን ነው?
አቶ ወንድወሰን፦ ከዚህ በፊት ዋናው የሚጠየቀው ገንዘብ ነበር፤ ስምንት ሚሊየን ብር ያለው ሰው ስራውን መስራት ይፈቀድለታል። ይህ አካሄድ ደግሞ ብቸኛ ምክንያት ነው ባንልም አሁን እየተፈጠረ ላለው ቀውስ የራሱን አስተዋጽዖ አበርክቷል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቅርቡ የኤፍ ኤም ሞገዶችን ጨረታ አውጥቷል በዚህ መሰረት ተወዳዳሪዎችን ስናወዳደር የሙያው ባለቤት መሆን ትልቅ ዋጋ እንዲኖረው አድርገናል፤ አንድ ሰው የሰለጠነበት የሙያ ዘርፍ ያለው የስራ ልምድ ክህሎት ሚዲያ የመምራት ብቃት እና ሌሎችም ከግንዛቤ ውስጥ እንዲገቡና ገንዘቡም ወደ 4 ሚሊየን ብር ዝቅ እንዲል ሆኗል። ይህ መሆኑ ደግሞ በዘርፉ ልምድ ያላቸው እውቀትና ክህሎቱን የተላበሱ ሰዎች ከስራው ጋር እንዲገናኙ ከማድረጉም በላይ ዘርፉን መስመር ለማስያዝም ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለን ስለምናምን እናበረታታለን።
አዲስ ዘመን፦ ከዚህ አንጻር በአገራችን ያሉትን የመገናኛ ብዙሀን ባለቤቶችና መሪዎች ምን ደረጃ ላይ ናቸው ማለት ይቻላል?
አቶ ወንድወሰን፦ እዚህ ላይ ናቸው ብሎ ለመናገር ጥናት ይጠይቃል፤ ግን ከማየው እና መገናኛ ብዙሀኑን የሚመራን ተቋም እንደመምራቴ ዘርፉን የማያውቁት ብቻ ናቸው እያጠፉ ያሉት ለማለት እቸገራለሁ። ምክንያቱም ዘርፉን የሚያውቁት ግን አውቀው የተኙ፤ ቢጠሩም የማይሰሙ አካላት እዚህም እዚያም የሚያጠፉትን ጥፋቶች እየተመለከትን ነው። በአንጻሩ ደግሞ ዘርፉን ባያውቁትም ፍላጎቱ ስላላቸው ብቻ ጥሩ የሚሰሩም አሉ።
ለአገር ለህዝብ የሚበጅ የአገሪቱን ነገ የሚያሳይ፣ ህዝብን የሚያሻግር ስራ ለመስራት ዘርፉን ማወቅ አንድ መስፈረት ነው። ግን ከዚህ ባሻገር ሞራል፣ ሀይማኖት የሚባሉ ነገሮች አሉ። ከአገርና ከወገን ፍቅር በተጨማሪም ለህግ ተገዢ መሆን አለ። እነዚህ ነገሮች ደግሞ የግድ ባለሙያ መሆንን አይጠይቁም፤ ከዚህ አንጻር ዘርፉን ያላወቁት ስለመሩት ይበላሻል፤ የሚያውቁት ሲሆኑ ደግሞ ጥሩ ይሆናል፤ ለማለት አይቻልም። ነገር ግን እከሌ ከእከሌ ሳንል ጥሩ የሚሰሩትን ማመስገን ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ ሆነው አንታረምም ላሉ ሩቅ በማይባል ጊዜ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ህግን ሊያስከብር ይገደዳል።
አዲስ ዘመን፦ በውጭ አገር ሆነው በሳተላይት የፖለቲካም የመዝናኛም ሊሆን ይችላል ፕሮግራሞቻቸውን የሚያስተላልፉ የመገናኛ ብዙሀንን በምን ያህል ደረጃ ትቆጣጠሯቸዋላችሁ?
አቶ ወንድወሰን፦ በዚህ በኩል ሁለት ዓይነት ነገር ነው ያለው፤ አንደኛው ሙሉ በሙሉ በውጭ አገር ሆነው ፕሮግራሞቻቸውን የሚያስተላልፉ ነበሩ፤ አሁን ላይ ይህ አካሄድ ብዙም አይደለም አብዛኞቹ በአገር ውስጥ ቢሯቸውን ከፍተው መረጃዎችን እያገኙ የሚያሰራጩ ናቸው። በዚህ ምክንያትም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ፍቃድ ማግኘት አለባቸው። ስለዚህ እነዚህን አካላት እንቆጣጠራቸዋለን። ነገር ግን በተለይ አሁን ያለውን ችግር እየፈጠሩ ያሉት እነሱ ብቻ አይደሉም።
ከዚህ ሁሉ ግን ያስቸገረው ከዚህ ቀደም የሌለ ነጻነት ሲገኝ እስከምን ድረስ እንጠቀመው የሚለውን አለማወቅ ነው። ነገር ግን መሰረታቸውን አገር ውስጥም ይሁን ውጪ አድርገው አገሪቱ ላይ ችግር እየፈጠሩ ነው ብሎ የሚያምንባቸውን መጀመሪያ በመነጋገርና በመመካከር ራሳቸው እንዲያርሙ በማድረግ፣ አቅማቸውን በመገንባትና ግንዛቤያቸውን በማሳደግ ለመለወጥ ጥረት ይደረጋል፤ ሆኖም ህግን ማስከበር ሲኖርበት አያስከብረም ማለት ግን አይደለም።
አዲስ ዘመን፦ የባለሥልጣኑ ትዕግስቱ አልበዛም? ይህንን ያልኩት ትዕግስት ልክ አለው ምን እስክንሆን ድረስ ነው የሚጠበቀው የሚሉ ስላሉ ነው?
አቶ ወንድወሰን ፦ አዎ! እንደዚህ ዓይነት ድምጾች እዚህም እዚያም እየተሰሙ ነው፤ ግን ነጻነትን መንሳት የመስጠት ያህል ከባድ አይደለም፤ መንግስት የቤት ስራውን የሚያበዙበት መገናኛ ብዙሀን እንዲታገሱለት ይፈልጋል። ግን እንደዛ አይደለም መሆን ያለበት ብሎ ስላሰበ ነው። እዚህ ላይ መንግስት የፈራ ይመስላል፤ እሹሩሩ እያለ ነው፤ ይባላል እንሰማለን ግን አንድን መገናኛ ብዙሀን ለመዝጋት ሁለት ፖሊስ እንኳን ላያስፈልግ ይችላል፤ በደብዳቤ የሚያልቅ ጉዳይ ነው። ነጻነት ከሰጠን አይቀር ትንሽ እንታገስ የሚል ሀሳብ ስላለ ነው ዝም የተባለው፤ በዚህ አጋጣሚ ትዕግስቱን የማይረዱና በጀመሩት አካሄድ ለመቀጠል የሚያስቡ ካሉ ግን ህግን ከማስከበር የሚመልሰው ነገር አይኖርም።
አዲስ ዘመን፦ በቀጣዮቹ ጊዜያትስ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምን አዲስ ነገር ይጠበቅ?
አቶ ወንድወሰን፦ በቀጣዮቹ ጊዜያት ለሁሉም የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ያሉባቸውን ድክመቶችና ጥንካሬያቸውን እያሳየ ራሳቸውን እያረሙና እያበቁ እንዲሄዱ የማድረግ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል። ቅድም እንዳልኩት የዘርፉ ባለሙያዎች መሪዎችና ጋዜጠኞች አቅማቸው የሚገነባበትን መንገድ ለማመቻቸት ከአጋር አካላት ጋር የውጭና የአገር ውስጥ ስልጠናዎችን ያመቻቻል።
የሚዲያ ስልጠና ተቋም ለመክፈትም እየተሰራ ነው። ከዚህ ባሻገር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸድቀዋል ተብሎ በሚጠበቀው አዋጅ መሰረት ከኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙሀን በተጨማሪ የህትመት ዘርፉን ፍቃድ የመስጠትና የመቆጣጠር ስራውን ይሰራል።
ሌላው እዚህም እዚያም ያለውን ጩኸት በግንዛቤ እንዲሁም በህግ ለማስከበር የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት እቅድ ይዟል።
አዲስ ዘመን፦ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ወንድወሰን፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 5/2012
እፀገነት አክሊሉ