በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሊግ ኮሚቴ በአራት ጨዋታዎች ላይ የመርሃ ግብር ለውጥ ማድረጉን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከልን መረጃ እንደገለጸው፤ ታህሳስ 17 ሊካሄድ የነበረው የባህርዳር ከተማ
እና የሽሬ እንደስላሴ እንዲሁም የመቐለ ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ በተጨማሪም ታህሳስ 18 ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ የመርሀ ግብር ለውጥ ተደርጎበታል። በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ8ኛ ሳምንት ጨዋታ በታህሳስ 20 በጅማ አባጅፋርና በወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ መካከል የሚደረገው ጨዋታም የቀን ለውጥ ተደርጓል።
የጅማ አባጅፋር ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሚያደርጉት ጨዋታ ወደ ታህሳስ 22 ሲሸጋገር፤ የባህርዳር ከተማ ከሽሬ እንደስላሴ ፣መቐለ ከተማ ከፋሲል ከተማ፣ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ቀን እንዳልተቀመጠለት መረጃው አመላክቷል።ጨዋታዎቹ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችና በልዩ ልዩ ምክንያት ቀደም ሲል በወጣላቸው ፕሮግራም መሠረት ሳይካሄዱ ቀርተው ወደ ሌላ ጊዜ በተስተካካይነት የተላለፉ መሆኑ ይታወሳል።ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ከሳምንታት በፊት የተስተካካይ ጨዋታዎቹ ዋናው የጨዋታ ፕሮግራም ሳይስተጓጎል ታህሳስ 17 እና 18 ቀን 2011ዓ.ም እንዲካሄዱ የሊግ ኮሚቴ ወስኖባቸው የነበሩ መርሃ ግብሮች ናቸው።የእነዚህን ጨዋታዎች መርሀ ግብር በቀጣይ እንደሚያሳውቅ አስታውቋል ።
ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ድሬዳዋ ከተማ ከደቡብ ፖሊስ የሚያደረጉት ተስተካካይ ጨዋታ የስታዲየም ለውጥ መደረጉን በደረሰን መረጃ ጠቅሷል። ጨዋታው በሐረር ስታዲየም ታህሳስ 17 ለመከናወን መርሀ ግብር የተያዘለት ሲሆን፤ በዕለቱ በ 9 ሰዓት እንዲከናወን የሊግ ኮሚቴው መወሰኑን አስታውቋል።
ፌዴሬሽኑ የጨዋታዎቹን መርሀ ግብር ለመለወጥ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ማብራሪያም ሆነ ፍንጭ ያልሰጠ ሲሆን ፤ፕሪሚየር ሊጉን በውድድር ህግና ደንብ በመምራት ውድድሩ በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቅ ስለመቻሉ ጥያቄ እንዲያጭር ያደርጋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
ዳንኤል ዘነበ