አዲስ አበባ፤- መሬት በህገ መንግስቱ ከተደነገገው ውጭ እንደሚሸጥ፣ ከተሸጠ በኋላም ገዢዎች እንደሚነጠቁ፣ የፍትህ አካላት መረጃ የመስጠትና የተጠያቂነት መጓደል እንደሚታይባቸው በጥናት ማረጋገጡን የፌዴራል የፍትህ፣ የህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የኢንስቲትዩቱ የምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ማዳ፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት የመሬት ይዞታ ዋስትና ማስተላለፍ፣ የፍትህ አካላት የመረጃ ተደራሽነትና ተጠያቂነት ላይ ጥናትና ምርምር በክልሎችና በፌዴራል ተቋማት ላይ ማድረጉን ገልጸው፤ በህገ መንግስቱ መሬት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ የማይሸጥ የማይለወጥ የጋራ መሆኑን ቢደነገግም፤ በተደረገው ጥናት ግን መሬት ለሽያጭ ይቀርባል፤ ከተሸጠም በኋላ ህገ ወጥ ነው ተብሎ ከገዥው በመንጠቅ ባለቤቱ አላግባብ እንደሚጠቀምበት ይደረጋል።
አቶ ምትኩ በፌዴራልና በክልሎች በሚወጡ ህጎችና መመሪያዎች መካከል ልዩነትና ክፍተቶች መኖራቸውን፣ በህገ መንግስቱ ላይ ከተቀመጠው ውጭ መሬት የአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ አድርጎ የማሰብ ሁኔታ እንዳለ መረጋገጡን፣ በቅርቡ ለነበረው ግጭትም ምክንያት እንደሆነ፣ በተለያዩ ክልሎች የተለያየ ገጽታ ቢኖርም የዜጎች መብት አላግባብ የሚነጠቁበትና በዜጎች የኢኮኖሚና የማህበራዊ መብቶቻቸው ላይ ጉዳት መድረሱንጥናቱ ማመላከቱን አስረድተዋል።
ችግሩን ለመፍታትም መሬት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሆኑን ግንዛቤ መፍጠር። በፌዴራልና በክልሎች መካከል ያሉትን ህጎች አጣጥሞ ማውጣት። በአሰራር ላይ ያሉ ክፍተቶችን ማረም እንደሚገባ ጥናቱ በመፍትሄነት ማስቀመጡን አቶ ምትኩ ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ የፍትህ አካላት ማለትም ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቶች፣ ማረሚያ ቤቶችና ጠቅላይ አቃቢ ህግ ለተገልጋዮች የመረጃ ተደራሽነት ላይ ባደረገው ጥናትም ህጎች ቢኖሩም አተገባበሩ ችግር አለው። ከተቋም ተቋም ቢለያይም መረጃን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ክፍተት እንዳለም በጥናቱ መረጋገጡን አቶ ምትኩ ተናግረዋል።
ተቋማት መረጃ እንደሚከለክሉ፣ የከለከሉበትን ምክንያትም ለተገልጋዮች እንደማይገልጹ፣ የአንዳንዶቹ ተቋማት ምክንያት የአደረጃጀት ክፍተት መሆኑም፣ መረጃ ባለማግኘታቸውም ዜጎች ፍትህን ሊያጡ እንደሚችሉ ጥናቱ ማመላከቱን አስረድተዋል።
ተጠያቂነትን በሚመለከትም በተደረገው ጥናት፤ የፍትህ አካላት ሀላፊነትን በአግባቡ እንደማይወጡ ፣ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው የሚደነግጉ የህግ ማዕቀፎች ቢኖሩም ያሉትን ህጎች በአግባቡ ተፈፃሚ ከማድረግ አንፃር ክፍተት መኖሩና ባለሙያዎቹም ህጎቹን ያለመገንዘብ ችግር እንዳለባቸው ጥናቱ ማመላከቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ጥናቶቹ በነገው ዕለት በፍሬንድሺፕ ሆቴል ባለድርሻ የሆኑ የክልልና የፌዴራል አካላት በተገኙበት ይፋ ይደረጋሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ