አዲስ አበባ፡- በ2011 በጀት ዓመት የህፃናትና የእናቶችን ሞት በመቀነስና የቤተሰብ እቅድና የክትባት ሽፋንን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። የሥርዓተ ምግብ አገልግሎትን በተመለከተ መሻሻሎች መኖራቸውም ተጠቁሟል።
21ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ ትናንት በስካይ ላይት ሆቴል በተከፈተበት ወቅት የ2011 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርትን ለተሳታፊዎች ያቀረቡት የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበጀት ዓመቱ በተለይ የእናቶችና የህፃናትን ሞት በመቀነስ፣ የክትባት ሽፋንን በማሳደግና የቤተሰብ እቅድን በማስፋት ረገድ ከፍተኛ መሻሻል የታየ መሆኑን ገልፀዋል።
ሚኒስትሩ እ.ኤ.አ በ2019 የተሰራውን መለስተኛ የስነ ህዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት ዋቢ በማድረግ እንደገለፁት፣ የአምስት ዓመት የልደት በዓላቸውን ሳያከብሩ የሚሞቱ ህፃናት ቁጥር እ.ኤ.አ በ2016 ከነበረበት 67 ሞት ከአንድ ሺ ህፃናት ወደ 55 ሞት ማውረድ ተችሏል። ለዚህም በእናቶችና ህፃናት ጤና ዙሪያ ለተከታታይ ዓመታት የተተገበሩ ፕሮግራሞች መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል።
በዚሁ ጥናት መሰረት የቅድመ ወሊድ፣ወሊድና ድህረ ወሊድ አገልግሎት ከፍተኛ መሻሻል ማስመዝገቡን ሚኒስትሩ የጠቀሱ ሲሆን፣ በሰለጠነ ባለሙያ የሚሰጠው የወሊድ አገልግሎት እ.ኤ.አ በ2016 ከነበረበት 28 በመቶ በእጥፍ በመጨመር እ.ኤ.አ በ2019 ወደ 50 በመቶ ከፍ ማለቱንም አስታውቀዋል።
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትም በተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት 35 በመቶ ሽፋን ወደ 41 በመቶ በመድረስ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡንም ሚኒስትሩ ገልፀው፤ የህፃናት ጤናን በተመለከተ በዋናነት የሚጠቀሰው የክትባት አገልግሎት በዳሰሳ ጥናቱ መነሻነት አጠቃላይ የክትባት አገልግሎት ያገኙ ህፃናት ሽፋን እ.ኤ.አ በ2016 ከነበረበት 39 በመቶ ወደ 43 በመቶ ማደጉን ጠቁመዋል።
የሥርዓተ ምግብ አገልግሎትን በሚመለከትም የመቀንጨር፣መቀጨጭና ክብደት መቀነስ መለኪያዎች በየጊዜው መሻሻል እያሳዩ እንደሚገኙም አያይዘው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ መቀንጨርን እ.ኤ.አ በ2016 ከነበረበት 38 በመቶ ወደ 37 በመቶ፣ መቀጨጭን ከ10 በመቶ ወደ 7 በመቶ እንዲሁም ክብደት መቀነስን ከ24 በመቶ ወደ 21 በመቶ መቀነስ እንደተቻለ ገልፀዋል። የጤና ሚኒስትርና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሴክተር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በጋራ በመሆንና የስነ ምግብ ፖሊሲ በመቅረፅ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ፀድቆ ወደተግባር መገባቱንም ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
ትናንት በተከፈተው 21ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ ከ 800 መቶ በላይ የሚሆኑ የጤናው ሴክተር ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን በጤናው ዘርፍ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የጤና ባለሙያዎችና የዘርፉ ኃላፊዎች ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በእለቱም የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለአራት ልዩ ተሸላሚዎች ተጨማሪ የቤት ሽልማት አበርክተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2012
አስናቀ ፀጋዬ