አዲስ አበባ፡- የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምዝገባ ክፍያ ሥርዓት ኋላቀር በመሆኑ ባጋጠማቸው የጊዜ መባከንና መጉላላት መማረራቸውን ተማሪዎች ተናገሩ። ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ጠቁሟል ።
ጥቆማ አቅራቢዎቹ ተማሪዎች ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ የዩኒቨርሲቲው የምዝገባና የመረጃ አያያዝ ስርዓት ኋላ ቀር ነው። በአሁኑ ወቅት ትናንሽ የትምህርት ተቋማት ሳይቀሩ በበይነ መረብ አማካኝነት ምዝገባ እያካሄዱ ዩኒቨርሲቲው ግን ምዝገባ የሚያካሂደውና መረጃ የሚያደራጀው በወረቀት ነው።
ይህ አሰራሩ በምዝገባ ወቅትና መረጃዎችን ለማግኘት ለረጃጅም ሰልፍና ለእንግልት ዳርጎናል። ከዚህም በተጨማሪ የተማሪዎች ውጤት የሚገለጸውም በወረቀትና በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ነው። አሰራሩ ወቅቱን የማይመጥን ኋላቀር በመሆኑ ማስተካከል አለበት ።
የማታና የዕረፍት ቀናት ተማሪዎች በቡከላቸው ‹‹ዩኒቨርሲቲው ክፍያ በባንክ በኩል መፈጸም እየተገባው በየመንፈቅ ዓመቱ በደረሰኝ እጅ በእጅ በመሆኑ ከፍያ ለመፈጸም እንጎላላለን፣ የሚመደቡልን መምህራን ብቁ አይደሉም። በወቅቱም አይመደቡም። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ችግሮቹን በመፍታት አገልግሎቱን ቀልጣፋና ጥራት ያለው ሊያደርግ ይገባዋል ››ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ‹‹ ዩኒቨርሲቲው በሽግግር ላይ ነው። የመረጃ አያያዝም ሆነ አሰራራችን ዘመናዊ ነው ማለት አይቻልም። በሽግግር ሂደት ሁሉም ነገር የተሳካ እንዲሆን የሚያስብ ካለ ሽግግር ያልገባው ነው።
በሂደት እያስተካከልን እንሄዳለን። ሁሉንም በአንድ ጀምበር ማድረግ አንችልም፣ እንደዚያም የሚል ሰው የእራሱን ፍላጎት ብቻ የሚጠብቅ ነው›› ሲሉ ችግሩ መኖሩን ይጋራሉ።
ፕሬዚዳንቱ የፋይናንስ ሥርዓት ለማስተካከል የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት፣ ከባንክ ጋር እየተነጋገሩ ቢሆንም ይህን በቶሎ ወደ ሥርዓት ለማስገባት እንደሚያስቸግር፣ እንዲያም ሆኖ ግን አሰራሩን በአውቶሜሽን ለማድረግ ትልቅ በጀት ተመድቦ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር እየተሰራ ሲሆን፤ ሥራው ሲጠናቀቅ ችግሩ እንደሚፈታ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ‹‹የሰው ሀብት፣ ፋይናንስና ሌሎች አሰራሮችን ለማዘመን እየሰራን ነው። በሥራው ሂደት ግን የዩኒቨርሲቲው ደመወዝ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ስለማይስብ ባለሙያዎችን ለማግኘት ፈታኝ ሆኖብናል። ሥራውን እየሰራነው ቢሆንም በርካታ ፈተናዎችም እንዳሉብን ተረድተው ተማሪዎቹ በየቦታው ሄደው ከመክሰስ ይልቅ በግንባር እየመጡ ተነጋግረን ችግሩን በጋራ እየፈታን መሄድ አለብን ›› ብለዋል።
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን የቀድሞው የኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ በሚል ስያሜ እ.አ.አ በ1959 የተቋቋመ ሲሆን፤ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ተጠሪነቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሆኖ በ2016 ዓ.ም ወደ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ያደገ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ