አዲስ አበባ፡- በወላይታ ሶዶና በደሴ ከተማ የታየው የመጠጥ ውሃ ጥራት በሌሎችም ከተሞች ሊታይ እንደሚገባ የውሃ ልማት ኮሚሽን አስታወቀ። የወላይታ ሶዶ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ለህብረተሰቡ የሚያሰራጨውን ውሃ በኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ተመርምሮ የኢትዮጵያ የመጠጥ ውሃ የተቀመጠለት መስፈርት በማሟላቱ የ ሲኢኤስ – 58 አይሶ ፡ 2019 (CES-58 ISO :2019) ጥራት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት አገኘ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር በሻህ ሞገሴ የሰርተፍኬት ማግኘቱን ምክንያት በማድረግ ትናንትና በብሉ ስካይ ሆቴል የዕውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም ላይ እንደገለፁት በሀገራችን በሁለቱ ከተሞች የታየው የውሃ ጥራት በኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ተመርምሮ አልፏል፤ ይህ ተሞክሮ ሌሎች የሀገራችን ከተሞች ሊተገብሩት ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የውሃ ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙክታር አህመድ በበኩላቸው በታዳጊ ሀገሮች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ የከተሞች በሽታ ሲታይ የውሃ ወለድ በሽታ ነው። ስለዚህ ከተሞች በቁርጠኝነት የውሃ ጥራት ላይ በመስራት የህብረተሰቡን ጤና መታደግ ይችላሉ ብለዋል።
እንደ አቶ ሙክታር ማብራሪያ ከተሞች የውሃ ደህንነት ዕቅድን በየተቋማቱ ተግባራዊ ቢደረግ ለስኬታማነታቸው ያግዛቸዋል ። የወላይታ ሶዶ ከተማም ይህን ተግባራዊ ስላደረገ ነው ለዚህ የበቃው ብለዋል።
ከተማው ዛሬ ሰርተፍኬት በማግኘቱ ሌላ ሥራ አይጠበቅበትም ማለት አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ በየሶስት ወሩ ክትትል እየተደረገና እየታየ ስኬታማነታቸው የማይቀጥል ከሆነ ሰርተፍኬቱን እንደሚቀሙ
አስታውቀዋል። ይህ ለወላይታ ከተማ ትልቅ የማንቂያ ደውልና ጠንክረው እንዲሰሩ ያደርጋቸዋልም ብለዋል።
ሌሎች ከተሞች ከዚህ ተሞክሮ ወስደው እንዲሰሩ ፌዴሬሽኑ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚወጣም ተናግረዋል።
የወላይታ ከተማ ከንቲባ አቶ አንጀሎ ደሴ በበኩላቸው ይህ ውጤት እንዲገኝ የወላይታ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡን በማሳተፍ በሰራው ሥራ ውጤታማ መሆን ችሏል ብለዋል።
እንደ ከንቲባው ገለፃ ይህ ውጤት በህብረተሰቡ በጋራ ርብርብ የመጣ ስለሆነ አሁንም በጋራ በበለጠ ለመስራትና ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የደሴ ከተማም ከዚህን ቀደም በኢትዮጵያ ተስማ ሚነትና ምዘና ድርጅት ተመርምሮ በኢትዮጵያ የመጠጥ ውሃ በተቀመጠለት መስፈርት በማሟላቱ ሰርተፍኬት ማግኘቱ የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2012
ሐይማኖት ከበደ