አዲስ አበባ፡- የምርትና አገልግሎት ጥራት ደረጃን የማስጠበቅና ተወዳዳሪነት የማሳደግ ሥራ በሚፈለገው መጠን ውጤታማ ባለመሆኑ የአገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪ ብሎም የአገሪቱን ተወዳዳሪነት ማሳደግ እንዳይቻል ማድረጉ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ‹‹የቪዲዮ ደረጃዎች ዓለም አቀፍ መድረክን ይፈጥራሉ›› በሚል መሪ ሐሳብ የተከበረውን የዘንድሮውን የዓለም የደረጃዎች ቀን በማስመልከት ከአምራችና አገልግሎት ሰጪዎችና ዋና አስፈጻሚዎች ጋር ትናንት በስካይ ላይት ሆቴል ውይይት አድርጓል።
በመድረኩ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረእየሱስ እንደገለፁት፤ አገራት በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ያሉትና ተወዳዳሪነታቸውን እየጨመረ የመጣው የምርትና አገልግሎት ደረጃዎችን በመተግበር ደረጃ የዓለም የንግድ ቋንቋ መሆኑን ተገንዝበው ቁልፍ ተግባራቸው አድርገው በመያዛቸው ነው።
‹‹በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የምርትና አገልግሎት ጥራት ደረጃን የማስጠበቅና ተወዳዳሪነት የማሳደግ ሥራ ውጤታማ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም።››ያሉት አቶ ተካ፣በአስፈጻሚና በአምራቹ ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ መኖር፣ደረጃዎችን የማስተግበር አቅም ማነስ፣የቁጥጥር ሥርዓቱ ደካማ መሆንና የፖሊሲ ትስስር አለመኖር አገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪ ብሎም ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንዳትችል ማድረጉን አብራርተዋል።
መድረኩም ስለ የደረጃ ትግበራ ሥርዓት ግንዛቤ በመፍጠር በከፍተኛ ኃላፊዎች ዘንድ እንደ አንድ ስትራቴጂክ ተግባር ተድርጎ እንዲወሰድ እድል የሚሰጥ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን፣አስፈጻሚና አምራቾች አራተኛ የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን የጥራት ደረጃ ዋነኛ የመወዳደሪያ መሳሪያ መሆኑን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። ኤጀንሲውም ይህ እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ላይ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የቤካስ ኬሚካል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ በቀለ ፀጋዬ በበኩላቸው፤ የአገሪቱ ኢንዱስትሪ መሪዎች ለደረጃዎች ያላቸው ግንዛቤ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን ተናግረዋል።‹‹ገበያ ላይ የምርት እጥረት በመኖሩና ውድድሩ ከባድ ባለመሆኑ ገዢ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፤ ይህም ኢንዱስትሪና መሪዎቻቸው ለደረጃ እንዳይጨነቁ ያደርጋቸዋል›› ያሉት አቶ በቀለ፣ሕብረተሰቡም ከጥራትና ደረጃ ይልቅ ቅናሽን መሰረት በማድረግ የመገበያየት ልምድ ማዳበሩ ለችግሩ መንሰራፋት የላቀ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።
የዩኒቨርሳል ፕላስቲክ ፋብሪካ የጥራትና ደህንነት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ ይልማ፣‹‹የአገር ውስጥ ምርቶች የጥራት ችግር እንዳለባቸው የማይካድ ሃቅ ነው፣ በአምራቹ፣ በተቆጣጣሪውና በተጠቃሚው ዘንድ ትስስር አለመኖሩም የችግሩ ምክንያት ነው።››ብለዋል። ችግሩን ለማስወገድ በቅንጅት ከመስራት ባሻገር ስለ ጥራት ደረጃ የሚሰጡ መረጃዎችን ማጎልበት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። ኤጀንሲው ስለደረጃ ትግበራ ሥርዓት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጠርቶ ማናገሩም አንድ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2012
ታምራት ተስፋዬ