የኢትዮጵያ ክለቦች የአጭር፣ የመካከለኛ፣ የርምጃና የሜዳ ተግባራት ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ስታዲየም በይፋ ተጀመረ። ሻምፒዮናው በሴቶች የ3000 ሜትር መሰናክል ውድድር የተከፈተ ሲሆን፤ በሩጫው ጥሩ ፉክክር ታይቶበታል። ውድድሩን ሀዋሳ ከነማን ወክላ የተወዳደረችው መስዋዕት አስማረ በአንደኛነት አጠናቅቃለች። መስዋዕት አስማረን በመከተል በሁለተኛነት ያጠናቀቀችው የቡራዩ ከተማዋ ሎሚ ሙለታ ስትሆን፤ ብዙአየሁ መሃመድ ከፌዴራል ማረሚያ ሶስተኛ በመሆን የርቀቱ አሸናፊ ሆነዋል።
የሴቶች የርዝመት ዝላይ በእለቱ የተካሄደ ውድድር ነው። በውድድሩም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንደኛና ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ ባለድል ሆኗል። ለንግድ ባንክ 5 ነጥብ 46 ሜትር በመዝለል አራያት ዲቦ ነ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አንደኛ እንዲሆን ያስቻለችው። የሲዳማ ቡናዋ አሉንካን ደሞጋ 5ነጥብ 28 ሜትር በመዝለል ሁለተኛ ደረጃ ስትይዝ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ኪሩ ኡማን 5 ነጥብ 27 ሜትር በመዝለል ሶስተኛ ደረጃ ይዛለች።
የወንዶች ዲስከስ ውርወራም በመክፈቻው እለት ከተስተናገዱት ውድድሮች አንዱ ነበር። በዚህ ውድድር ሲዳማ ቡና አንደኛ በመሆን አሸንፏል። ሲዳማ ቡናዎች በለማ ከተማ አማካኝነት ባለድል መሆን ችለዋል። ለማ 44 ነጥብ 72 ሜትር በመወርወር አሸንፏል። በዚህ ውድድር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገበየሁ ገብረየስ በወረወረው 40 ነጥብ 01 ሜትር ሁለተኛ ሆኗል። መከላከያ ሃይሌ ወረደ 40 ነጥብ 57 ሜትር ወርውሮ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል።
በዓመታዊው የክለቦች አጭር፣ መካከለኛ፣ ርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ23 ክለቦች የተው ጣጡ 611 አትሌቶ ች ተሳታፊ ሆነዋል። የኢትዮጵያ ክለቦች አጭር፣ መካከለኛ ፣ ርምጃና የሜዳ ተግባራት ሻምፒዮና ድምቀቱን እንደያዘ እስከ ታህሳስ 21ቀን 2011 ዓ.ም የሚዘልቅ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
ዳንኤል ዘነበ