አዲስ አበባ፡- “ኢትዮጵያ ከየትኛውም ጊዜ በላይ የየዘርፉን ጀግኖች የምትፈልግበት ወቅት ላይ ናት” ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ፡፡ 12ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን ድምር ውጤት የአንድነታችን ምሰሶ›› በሚል መሪ ሐሳብ በህዝብ ተወካዮች ምር ቤት ተከብሯል፡፡
ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከበረው የብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንደገለፁት፣ አገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የየዘርፉን ጀግኖች የምትፈልግበት ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ በተለይም ድህነትን ከላይዋ ላይ አራግፎ የሚጥልላት፣ ሰላምና ደህንነቷን የሚያስጠብቅላትን ቁርጠኛ ትውልድ ትሻለች፡፡
ፕሬዚዳንቷ እንደተናገሩት፤ ልዩነትን የሚያራግቡ ሳይሆኑ አንድነትንና መቻቻልን የሚሰብኩ እንዲሁም እኔ ብቻ ሳይሆን አገሬና ህዝቤ የሚሉ ደፋርና ኃላፊነት የሚሰማቸውን ዜጎችን ኢትዮጵያ አጥብቃ ትፈልጋለች፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ትናንት፣ ዛሬንና ነገን አጣምሮ የያዘ ታሪክ ነጋሪ፣ ከምንም በላይ ደግሞ ልዩነት ቢኖር እንኳን ብሄራዊ አንድነትና መግባባትን በጋራ የሚይዝ ነው፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ሰንደቅ ዓላማ አገርን መወከሉ፣ የሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑና ከሌሎች አገሮች ጋር እኩል ስለመሆናችን የሚያሳይ መሆኑ የብሄራዊ ማንነት መገለጫ ነው ያስብለዋል፡፡
ከዚህም በላይ ፍቅርና ዜግነት የሚገለፅበትም ነው፡፡ ስለዚህም ለሰንደቅ ዓላማ የተለየ ክብር ሊሰጠው ይገባል፡፡ አዲሱን ትውልድም የሰንደቅ ዓላማን ክብር እናስተምር፤ ሰንደቅ ዓላማችን የፖለቲካ መሳሪያ እንዳይሆን እንከላከል፤ ክብሩን ደግሞ እንጠብቅ፡፡
‹‹ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ዋነኛ መለያችን በመሆኑ የክልሎች ባንዲራዎች በተውለበለቡበት ቦታ ሁሉ ከፍ ብሎ እንዲገኝ እናድርግ:: ብሄራዊ አንድነትን ማጠንከር የምንችለውም ይህን ስናደርግ ነው:: የተቀደደ፣ ቀለሙ የለቀቀና ያረጀ ሰንደቅ ዓላማ አገራችንንም ሆነ ዜጎቿን አያስከብርም፡፡›› ሲሉም አክለዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሽታዬ ምናሉ በበኩላቸው፤ ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን የተለየ ትርጉም አለው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የነፃነት ልዩ ምልክትና የቃልኪዳን ዓርማ በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም በህገ መንግሥቱና በአዋጅ እውቅና ያገኘውን ሰንደቅ ዓላማ መጠቀምና ማክበር የግድ ይላል፡፡
በዕለቱ የሰንደቅ ዓላማን ቀለማትና አርማውን በተመለከተ አጭር ፅሑፍ ለታዳሚዎቹ ያቀረቡት የምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዳብራሩት፤ የሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ መታየት የህዝብና የአገር ክብር ከፍ አለ እንደማለት ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ የአንድነት ጉዞ በሰንደቅ ዓላማው ላይ መግባባትን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም ሰንደቅ ዓላማ ለሰላምና ለአንድነት እንደመሳሪያ ሆኖ ማገልገል እንጂ ለጥል መንስዔ መሆን የለበትም፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ አይሻሻልም ተብሎ የተደመደመ ነገር የለም፤ ይሁንና ህገ መንግሥቱ በሚፈቅደውና ህጉ በሚለው መሰረት የሚስተናገደው ነገር እስከሚስተናገድ ድረስ በህግ አግባብ እያገለገለ ያለውን ሰንደቅ ዓላማን አለመቀበል የሚያስጠይቅ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡ በመሆኑም ለኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማና ብሄራዊ ዓርማው ተገቢውን ክብር መስጠት ያስፈልጋል፡፡
በዕለቱ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የበዓሉን ታዳሚዎች በአገራቸው ሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃላ መሃላ አስገብተዋቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2012
አስቴር ኤልያስ