ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በፓርላማ ተገኝተው ካቀረቧቸው ዋና ዋና የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ ምርጫን ይመለከታል:: ዘንድሮ በሚካሄደው ምርጫ ያለፉት ምርጫዎች ግድፈት እንዳይደገም እርምት እንደሚወሰድ ፕሬዚዳንቷ አስታውቀዋል:: የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ያለፈው ግድፈት እንዳይደገም መንግሥት የያዘውን ቁርጠኛነት አድንቀው፣ ለትግበራው የበለጠ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/ የሙያ ማህበራት ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ወንድወሰን ተሾመ እንደሚሉት፣ በአንድ የመድብለ ሥርዓት ውስጥ ትልቁና ዋነኛው ጉዳይ ምርጫ ሲሆን፣ለዚህም የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡በቀደሙት ምርጫዎች የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና ደካማ መሆን ለምርጫዎች መበላሸት አንድ ምክንያት በመሆን ይጠቀሳል፡፡
አቶ ወንድወሰን፣‹‹ ያለፈውን ግድፈት:: የማረሙ ሥራ የብዙዎችን ድጋፍ ይፈልጋል፣ፕሬዚዳንቷም ለባለድርሻ አካላት የቤት ሥራ ማስተላለፋቸውም ይበል ያሰኛል ብለዋል፡፡
‹‹እኛ የሚመለከተንና ጥሪውን የሰማን ኃይሎች ራሳችንን ቆም ብለን መፈተሽ አለብን፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪውና የመጨረሻ ግብ ኢትዮጵያ ናት፡፡የፓርቲዎችም ጥያቄ ኢትዮጵያን መምራት ነው፣ ኢትዮጵያ ግን መኖር አለባት፡፡›› ሲሉም ያስገነዝባሉ::
እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ያለፈውን ግድፈት የማረም ሥራ መጀመር ያለበት ከመንግሥት ነው:: እንደ አገሪቱ ርዕሰ ብሄር ፕሬዚዳንቷ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ግልፅ በሆነ መልኩ ይካሄዳል ብለው በዚህ መልክ አቅጣጫ ለህዝብ ማቅረባቸው አንድ እርምጃ ወደፊት እንደ መሄድ ይቆጠራል፡፡ ከምርጫው አኳያ መልካም ጅማሬዎች እየታዩ ቢሆንም፣ ይህን ወደ ተግባር የመለወጡ ሥራ የበለጠ መንቀሳቀስን ይጠይቃል፡፡
ይህ ከሆነ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምትገነባበትን ምዕራፍ ጀምራለች ብለው እንደሚያምኑም አቶ ተሾመ ተናግረዋል፡፡ ይህ ወቅት የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለማምጣት በኢትዮጵያ መልህቅ የሚጣልበት የአምስት ዓመት ጅማሬ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም ነው ያስታወቁት፡፡
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፕሬዚዳንት ዶክተር አረጋዊ በርሄ ፣ ‹‹ከምርጫ ቦርድ ጋር ባደረግነው ተከታታይ ውይይት እንዲሻሻሉ የተስማማንባቸው 33 አንቀፆች ቢሻሻሉ መልካም ነው›› ይላሉ፡፡ እንዲሻሻሉ የተጠየቁት አንቀጾች የምርጫው ያለፉት ጊዜያት ግድፈት ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ያመለክታሉ፡፡
‹‹እነዚህ የሚሻሻሉ ከሆነ ምርጫው አግባብነት ያለው መስመር ይዟል ብለው እንደሚያምኑ፣ይህ ካልሆነ ግን አቅጣጫው ከንግግር የዘለለ እንደማይሆን ይናገራሉ:: ቦርዱ ይበልጥ መንቀሳቀስ እንዳለበት የሚናገሩት ዶክተር አረጋዊ፣130 የፖለቲካ ድርጅቶች ከሚገኙበት ምክር ቤት ጋር በመነጋገር ግድፈቶችን ማስተካከል እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግምባር /ኦነግ/ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ‹‹ለቀድሞው ግድፈት ዋናው ተጠያቂ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆን ነው፡፡›› ይላሉ፡፡ዴሞክራያዊ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ምርጫ እንዲካሄድ ቦርዱ ገለልተኛ ሊሆን እንደሚገባም ያመለክታሉ፡፡አቶ ቶሌራ ፤ቦርዱ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ መዋቅሩን እስከታች በማውረድ ካለፈው የተሻለ ይሰራል ብለው ተስፋ ጥለውበታል፡፡
እንደ አቶ ቶሌራ ገለጻ፣ድርጅታቸው ቀደም ሲልም ጀምሮ ምርጫው ነፃና ገለልተኛ እንዲሁም ፍትሃዊ ሆኖ እንዲካሄድ ይፈልጋል፡፡በምርጫ ስም ህዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ መታለል የለበትም፡፡በየምርጫ ጣቢያዎቹ ምርጫውን የሚቆጣጠሩ አካላት እንደውም በፓርቲው የተመደቡ ማለትም የመንግሥት ደጋፊ የመሆኑ ነገር መደገም የለበትም:: በዚህ መልኩ መስራት ያለፈውን ግድፈት ለማረም ያስችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2012
አስቴር ኤልያስ