
የዩክሬን ባለስልጣናት ሩሲያ ሌሊቱን በሰው አልባ አውሮፕላን ኪዬቭን ስትደበድብ ማደሯን ገለፁ። ሩሲያ ሌሊቱን በኪዬቭ በፈፀመችው ከፍተኛ የድሮን ድብደባ የተነሳ ከፍተኛ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን እና አካባቢው በጭስ መሸፈኑን ተናግረዋል።
ዩክሬን፣ ሩሲያ 550 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና 11 ሚሳኤሎችን መተኮሷን ተናግራለች። ጥቃቱ የደረሰው በዶናልድ ትራምፕ እና በቭላድሚር ፑቲን መካከል የስልክ ውይይት ከተደረገ ከሰዓታት በኋላ ነው ተብሏል።
ከስልክ ውይይቱ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ፑቲን በዩክሬን ላይ የሚያካሄዱትን ጦርነት ለማቆም ዝግጁ አለመሆናቸው “አሳዝኖኛል” ብለዋል። የዩክሬን አየር ኃይል እንዳስታወቀው ሩሲያ በአንድ ሌሊት ባካሄደችው የአየር ጥቃት 550 ሰው አልባ አውሮፕላኖች የተጠቀመች ሲሆን 72ቱ የአየር መከላከያውን ጥሰው አልፈዋል። ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ምሽት እንዲሁ 537 ሰው አልባ አውሮፕላኖች የዩክሬንን የአየር ክልል ጥሰው ለመግባት ሞክረው ነበር ተብሏል።
ኪዬቭ ለተከታታይ ስምንት ሰዓታት በሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ስትደበደብ የአየር ኃይሉ የአደጋ ጊዜ ደወል ሌሊቱን ሲጮህ አሳልፏል። የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዋና ከተማው ውስጥ “ከክፉዎቹ” ምሽቶች መካከል አንዱ በማለት ጥቃቱን አውግዘዋል። አክለውም “ሞስኮ ሳይዘገይ በጣም ከባድ በሆነ ማዕቀብ መቀጣት አለባት” ብለዋል።
አንድሪ ሲቢሃ በኤክስ ገጻቸው ላይ “በኪዬቭ ፍጹም አሰቃቂ እና እንቅልፍ አልባ ሌሊት ነበር። እስካሁን ከነበሩት አስከፊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ነበር” ሲሉ ጽፈዋል።
ፑቲን ከትራምፕ ጋር ካደረጉት የስልክ ውይይት በኋላ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ፣ ሲቢሃ “[ፑቲን] ሆን ብለው ነው የሚያደርጉት” ሲሉ ጽፈው “ለዩናይትድ ስቴትስ እና ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪ ላቀረቡ ሁሉ ያላቸውን ንቀት በግልፅ ያሳያል” ብለዋል።
የዩክሬን የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል የእሳት አደጋ ሠራተኞች በኪዬቭ ሩሲያ ካደረሰችው መጠነ ሰፊ ጥቃት በኋላ እሳት ለማጥፋት ሲረባረቡ ያሳያል።
እንደ ዩክሬን ባለሥልጣናት መረጃ ከሆነ፤ በኪዬቭ ላይ በተፈፀመው ጥቃት ቢያንስ 23 ሰዎች ቆስለዋል፣ የባቡር መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፣ በመዲናዋ ዙሪያ የሚገኙ ሕንፃዎች እና መኪናዎች ተቃጥለዋል።
ሩሲያ አሁን የፈጸመችው ጥቃት በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው የተኩስ አቁም ድርድር ከቆመ በኋላ አጠናክራ የቀጠለችው ጥቃት አካል ነው። የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት እአአ በየካቲት 2022 የተጀመረ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት ጦርነት እየተካሄደ ነው።
ትራምፕ ባለፈው ሐሙስ ከፑቲን ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ጦርነቱን ለማቆም ምንም አይነት መሻሻል እንደሌለ ተናግረዋል። ትራምፕ “ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ባደረጉት ውይይት በጣም አዝኛለሁ፤ ምክንያቱም እዛ ያሉ አይመስለኝም እና በጣም አዝኛለሁ።” “ማለቴ ጦርነቱን ለማቆም የሚፈልግ አይመስለኝም፤ እና ያ ደግሞ በጣም መጥፎ ነው።” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ክሬምሊን “በዩክሬን ያለውን ጦርነት ዋና መንስኤ” ለማስወገድ መሞከሩን እንደሚቀጥል በድጋሚ ተናግሯል። ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ለኪዬቭ የምትሰጠውን የተወሰነ የጦር መሣሪያ ማቆሟን አስታውቃለች።
በሳምንቱ መጨረሻ ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዩክሬን ላይ ካደረሰችው ትልቁ ነው የተባለ የአየር ላይ ጥቃት ፈጽማለች። በዚህ ጥቃት ከ500 በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ማለትም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ባሌስቲክ እና የክሩዝ ሚሳዔሎችን ተጠቅማለች።
ሞስኮ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 2014 በግዴታ የወሰደቻትን ክራይሚያን ጨምሮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም