አዲስ አበባ፦ የፌዴራል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግሥት ኢትዮጵያ ለምታስገነባው አዲስ የፓርላማ ህንፃ 370 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል መግባቱን አስታወቀ::
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ዳባ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ የምክር ቤቱ ዲፕሎማሲ ሥራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ማዕከል በማድረግ የመንግሥትን የልማት ግብ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው::
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለፃ፤ በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ የልዑካን ቡድን በቅርቡ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ያደረገው የሥራ ጉብኝትና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤታማ ነው:: ሁለቱ ፓርቲዎች መግባባት ላይ ደርሰው የአረብ ኢምሬትስ ገንዘቡን ለመርዳት ቃል በመግባትም በወዳጅነት መፈራ ረም ችለዋል፡፡
እርሳቸው እንዳብራሩት፤የአዲሱ የፓርላማ ህንፃ ግንባታ ለምክር ቤቱ አባላት ጠቃሚ ሚና አለው:: ለአባላቱ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን ምቹ ዐውድ የሚኖረውና ሥራቸውን በተሻለ መልኩ እንዲያከናውኑ ይረዳቸዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ አክለው እንደተናገሩት፤ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የልዑካን ቡድን ከአረብ ኢምሬትስ አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱ ሀገራት በፓርላማዎቻቸው መሃል የሚደረግ ትብብርን ለማሳደግና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ግንኙነት በሁሉም አቅጣጫ እየተሻሻለ እና የልማት ትብብሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት እያሳየ ይገኛል:: በአገልግሎት ላይ ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህንፃ አባላት እንዲሰበሰቡ እኤአ በ1930ዎቹ የተሠራ መሆኑ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር