ስፖርት ለሰላም ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ማህበራዊ ክንውን እንደሆነ ይነገራል። በተለያዩ አጋጣሚዎች የታዩ ሁነቶች ስፖርት ወደ ሰላም የሚያደርስ አሳንሰር ተደርጎ እንዲቆጠር ማድረጉም አብሮ ይነሳል። ለዚህ ማሳያ የሚሆን አንድ ክስተት ጠቅሰን እንለፍ። እኤአ በ1998 ፈረንሳይ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ወቅት እንዲህ ሆነ። በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በዓለም አቀፉ የፖለቲካ መድረክ ስፖርት ለሰላም፣ ለወንድማማችነት፣ ለአንድነት፣ ከዛም በላይ የመሆኑን ሃቅ በተግባር ታየ፡፡ ኢራንና የዘመናችን ልዕለ ኃያል አገር አሜሪካ በውድድሩ መድረክ ተገናኙ፡፡ በወቅቱ በጠላትነት የተፈራረጁት ሁለቱ አገራት በሰላማዊ ጦርነት ለፍልሚያ ተዘጋጁ፡፡ ይህም አጓጊና ልብ አንጠልጣይ ነበር፡፡
በብዙዎች ዘንድ ‹‹ምን ይከሰት ይሆን?›› የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ተነሳ፡፡ ጥቂት የማይባሉ የሁለቱ አገራት እግር ኳስ አፍቃሪያንና ደጋፊዎች አንድ ጉንጫቸውን በአሜሪካን አንድ ጉንጫቸውን ደግሞ በኢራን ሰንደቅ ዓላማ በማስዋብ የስታዲየሙን ድባብ ባልተጠበቀ መልኩ ቀየሩት። በዚህም የእግር ኳስ ስፖርት በአገሮችና በሕዝቦች መካከል መቀራረብና ሰላም እንዲፈጠር የሚያስችል መድረክ መሆኑን በተግባር ለዓለም ማሳየት ችለዋል። የሁለቱ አገሮች ደጋፊዎች በውድድሩ ወቅት ያሳዩት ሰላማዊ ጨዋነትን የተላበሰ አደጋገፍ «ስፖርት ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነት፣ ለትብብር፣ ለወንድማማችነት …» የሚለውን የስፖርት መርህ ከፍ አድርጎ ለዓለም ሕዝብ ያሳየ ነበር።
እንደ ሁለቱ አገራት ሁሉ በቅርቡ በሰሜን ኮሪያ አዘጋጅነት የተካሄደው የዊንተር ኦሎምፒያድ ክስተት ሌላው የስፖርትን የሰላምና የእርቅ ማዕድነት በይበልጥ አስረድቷል፡፡ ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ በሚል ራሳቸውን ለሁለት ከፍለው በጠላትነት ሲፈራረጁ ዓመታትን ተራምደዋል። የአገራቱ ከሰላም የራቀው ጉርብትና ደግሞ አንዱ ተንኳሽ ሌላው እንደ ተተንኳሽ የሆነ ትዕይንት ነበር። ሁኔታው «ከዛሬ ነገ ዳግም ወደ ጦርነት ያመሩ ይሆን?» የሚሉ ትርክቶችና ትንታኔዎች እንዲበረክቱ በር ከፍቷል ።በሰሜን ኮሪያ አዘጋጅነት የዊንተር ኦሎምፒያድ ግን ትንታኔዎችም ሆነ ትርክቶችን አፈር አደረጋቸው። የሁለቱ አገራት የጦርነት ጉዞ «ሟርት»እንጂ እውነት መሆን ሳይችል እንዲቀር ያደረገ ታሪካዊ አጋጣሚ ተፈጠረ።ደቡብና ሰሜን ኮሪያዊያን በስፖርታዊ ክንውኑ ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው በመቅረብ አንድነታቸውን ለአለም ህዝብ በማስመልከት ስፖርታዊ መድረኮችን ወደ እርቅ መንደርደሪያ ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር የቻለ ነበር።አጋጣሚው ስፖርት የሰላም አሳንሱር ብቻ ሳይሆን የእርቅ መድረክን የመሆኑን እውነታ በሚገባ አስምስክሮ ያለፈም ጭምር ነበር፡፡
ስፖርትን የሰላም፣የወዳጅነት፣ለወንድማማችነት አለኝታነቱን የገለጠበትን ሌላ አጋጣሚ እናንሳ። እኤአ በ2013 በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ሌላው ማሳያ ይሆኗል። በአፍሪካ ዋንጫ ከ31 ዓመት በኋላ ዋልያዎቹ በመሳተፋቸው ብሄራዊ ስሜት ሲገነፍል ለመታዘብ ተችሏል። አጋጣሚው ብሄራዊ ስሜቱን ፈጥሮ ብቻ ሳያበቃ ዋሊያዎቹን ለመደገፍ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን በአንድነት በስታዲየም እንዲገኙ ያደረገ ነበር። ወቅቱ ደግሞ የሁለቱ አገራት መንግስታት በጠላትነት ተፈራርጀው ለጦርነት ሰበብ የሚሹበት ነበር። የሁለቱ አገራት ዜጎች በአንድነት የመቆሙ ትዕይንት ሁኔታውን አስገራሚና ትኩረት እንዲስብ ያደረገ ነበር። የሁለቱ አገራት መንግስታት ቁርሾ እንጂ ህዝብ ለህዝብ ልዩነት አለመኖሩን፤ የኢትዮ−ኤርትራ ጦርነት የሁለት ዝሆኖች ጸብ እንጂ የሁለት ወንድማማቾች አለመሆኑን ያሳየ ነበር።
በተነሱት ሁነቶች ውስጥ ስፖርት ለሰላም መስፈን ያለውን ጉልህ ድርሻ የሚያሳዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ናቸው። የስፖርትን የሰላም አሳንሰርነት የተለያዩ ክስተቶች በማሳያነት ለማቅረብ የተሞከረው ያለምክንያት አይደለም። በአገራችን የአሁን ሁኔታ በህዝብ ለህዝብ ዘንድ ያለመተማመን፣ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች፣ አስተማማኝ ያልሆነ የሰላም ሁኔታ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ የስፖርት ዘርፍን እንደ ቁልፍ መፍትሄ መጠቀም ቢቻል የተሻለ መሆኑን ለማሳየት ነው።
አገራችን በአሁኑ ወቅት በትልቅ ተስፋ ውስጥ እየገሰገሰች እንደምትገኝ እሙን ነው። ለውጡ ያልጣማቸውና ከለውጡ በተቃራኒ የተሰለፉ ቡድኖችና ግለሰቦች አካሄዱን ለማደናቀፍ የተለያዩ መሰናክሎችን ሲፈጥሩ ይገኛሉ። በህዝቦች መካከል መተማመን ለማጥፋትና የአንድነት ስሜትን ለመሸርሸር ደግሞ በስፖርት ማዘውተሪያዎች አካባቢ ግጭቶችን የመፍጠሩ አካሄድ አንዱና ዋነኛ መንገዳቸው ካደረጉት ሰነባብተዋል። በአገሪቱ ሰላም የለም ለማስባል በክልሎች መካከል አለመተማመንን መፍጠር፣ የብሄር ግጭት እንዲቀሰቀስ መሞከር፣ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ በማነሳሳት …አገሪቱን መንግስት አልባ ለማስባል እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ ይገኛሉ። እነዚህ እኩይ ተግባራት የተለያዩ ግጭቶችና አለመተማመኖች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል።
የአገሪቱን የሰላም ሁኔታ ለመመለስ መንግስት የተለያዩ ስልቶችን እየተከተለ የሚገኝ ቢሆንም ፤ የሰላም ማዕከል የሆነውን የስፖርት ዘርፍ ግን የዘነጋው ይመስላል። ከመነሻው ለመጥቀስ እንደተሞከረ ስፖርት የሰላም መድረክነቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች አስመስክሯል።በአገራችን አሁናዊ ሁኔታ ክልሎች በጎሪጥ ነው የሚተያዩት፤ የኔ ብሔር፣ያንተ ጎሳ በሚል የጠበበ አስተሳሰብ መገፋፋቱ ጎልቶ እየታየ ነው፤ የአብሮነት ብሂሉ ጠፍቶ ከክልሌ ውጣልኝ በሚል መሳደድ ውስጥ ወድቋል፤ ዩኒቨርሲቲዎች ለብሄር ጠብ ማዕከል ሆነዋል፤ የኢትዮጵያዊነቱ ድምጽ በብሄርተኛነቱ ተሸፍኗል። እነዚህ አይነት ስንኩሎች ለለውጡ ሂደት ስንኩል መሆናቸውን ተከትሎ የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር የተለያዩ የሰላም መድረኮችን በማዘጋጀት ጥረቱን ቀጥሏል።የሚኒስቴሩ ጥረት የሚደነቅና የሚደገፍ ነው ።የስፖርቱን ዘርፍን በተለየ መልኩ መሰረት ማድረግ ጥረቱን በጥራትና በፍጥነት ፍሬያማ የሚያደርግ እንደሆነ ይታመናል።
በተለይ ደግሞ በአገሪቱ ህዝቦች መካከል መቻቻልን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን…የሚሰብኩ የውድድር መድረኮችን ቀርጾ ወደ ተግባር መግባት ቢቻል የሸፈተውን ብሄራዊ ስሜት መመለስ እንደሚቻል እሙን ነው። ለምሳሌ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለ«ኢትዮጵያችን እንሩጥ» የሚል ሀሳብ የያዘ ውድድር አዘጋጅቶ፤ አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ ብሄራዊ ስሜት፣ ባጠቃላይ ኢትዮጵያዊነት የሚያንጸባረቁባቸውን መልዕክቶች በማስተላለፍ የልዩነቱን ግንብ የመናድ አጋጣሚ መፍጠር ይቻላል። እንደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሁሉ በሌሎች የስፖርት አይነቶችም አንድነትን ፣ ሰላምን የሚያጎሉ ስፖርታዊ ክንውኖች ማዘጋጀት ቢቻል አትራፊነቱ ከፍ ይላል። ምክንያቱም ስፖርት ሰላምን ለማስፈን ያለውን አቅምና ውጤታማነት በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ለመመልከት ተችሏል። የዘርፉ የሰላም አለኝታነት ደግሞ በትላልቅ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር ቅቡልነቱ ያለው መሆኑን መመልከት ይገባል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭቱን ለመፍታት ከተጠቀመባቸው ዋነኛ መንገዶች ስፖርት አንዱ ነበር። ስፖርቱን እንደ መፍትሄ ለመጠቀም ምክንያት የነበረው ክስተት ከሁለት ዓመት በፊት ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በደቡብ ሱዳን እና በጋቦን መካከል የተደረገው ጨዋታ ነበር። የደቡብ ሱዳን ብሄራዊ ቡድን የጋቦን አቻውን 1ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። የጨዋታው ውጤት ግን ያልተጠበቀ ክስተት ይዞ ነበር የመጣው። በደቡብ ሱዳን እርስ በእርስ ጦርነት የቆሸሸውን የአንድነት ስሜት ከተቀበረበት ገንፍሎ እንዲወጣ አደረገ። የአገሪቱ ህዝቦች በብሄር፣በጎሳ ተመዳድበውና በጠላትነት ተፈራርጀው እርስ በእርስ ከመጋደል በአንድነት ስለ ደቡብ ሱዳን እንዲያዜሙ ያደረገ ክስተት ተፈጠረ። የልዩነት ቀለም ደብዝዞ የአንድነትና የወንድማማችነት ስሜቱን ከፍታ ያስመለከተ የማይታመን ሁኔታ የፈጠረ ነበር።
ከእግር ኳስ ድል የሚቀዳ ድብቅ የብሄራዊ ስሜት ሲፍለቀለቅ ያስመለከተ ትልቅ አጋጣሚም የተፈጠረ ሲሆን፤ ለተባበሩት መንግስታት በደቡብ ሱዳናዊያንን መካከል እርቅ የመፍጠሪያው ዘዴ ስፖርቱና የስፖርቱ ዘርፍ ብቻ የመሆኑን ብልሀት ያቀበለም ነበር። በአገሪቱ የነበረውን የልዩነት ስሜት ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ የእግር ኳስ ውድድር በማዘጋጀት ወደ አንድነት ስሜት ለማሸጋገር ተራምዷል። የደቡብ ሱዳን የጸጥታ ጉዳዮች ልዩ ተወካይ ስፖርት ለሰላም በሚል ያደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆኑን ነበር የረጋገጠው። የተባበሩት መንግስታት በደቡብ ሱዳን ወጣቶች መካከል የጎሣ መከፋፈል ጥቃት ለማስወገድ እና ጥላቻን ለመዋጋት አስደናቂ አማራጭ መንገድ አድርጎ እየሰራ መሆኑን በወቅቱ አስረድቷል። ይሄም የፈጠረው የወንድማማችነት ስሜት የተሳካ መሆኑንም ለአለም ተናግሯል።
በደቡብ ሱዳን የልዩነት ትርክቱ ለሰላም «ጉቶ » በመሆን የነበረውን ደም አፋሳሽ ሂደት በማርገብ ረገድ ስፖርቱ ላለው ሚና እንደ ማሳያ ይቀርባል።ይሄንኑ ዘዴ በኢትዮጵያም ወቅታዊውን ሁኔታ በማገናዘብ «ስፖርት ለሰላም እና ብሄራዊ መግባባት» ለመፍጠሪያ አንዱና ዋነኛው መሳሪያ አድርጎ መስራት ቢቻል ርቀቶችን የሚያቀራርብ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። የስፖርት ሳይንስ ልሂቁ ፒተር አልጊ ስፖርት እርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በልዩነት የምትታመስ አገርን ወደ ሰላም ለመመለስ፤ ህዝቡ ወደ አንድነት እንዲመጣ ዋነኛ መፍትሄ እንደሆነ ይናገራል። ስፖርት ለሰላም ሁለንተናዊ ግልጋሎቱን በአንድ አገር ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች የግንኙነት ሰንሰለት ከማጥበቅ አኳያ ትልቅ ሚና ያለው ዘርፍ እንደሆነም የሰጠውን ምስክርነት እንደማጠናከሪያነት ማንሳት ያስፈልጋል። ስፖርትን ሰላም፣ አንድነት፣ወንድማማችነት … የማጠናከር አቅሙን በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ተግባራዊ ማድረግ ቢቻልስ?
በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የሁከት ድምጽ ጎልቶ ይሰማል። የግለሰቦች ጠብ ወደ ብሄር የማደጉ ዝንባሌ ከፍተኛ በመሆን ሰላምን አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል። በመንግስት ተቋማት ውስጥ እንዲህ አይነቱ ሁኔታ እንዳይከሰት የስፖርት ዘርፉን አይነተኛ የመፍትሄ መንገድ ማድረግ ተገቢ ይሆናል። ኢትዮጵያዊ ስሜትን፣ አንድነትን የሚያጎሉ መልዕክቶችን የቀረጹ ውድድሮችን ማዘጋጀትና ብሄራዊ ስሜትን ለማስረጽ መንቀሳቀሱ አስፈላጊ ነው። የመንግስት ከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎችን ከማወያየት ባለፈ፤ የመቀራረብና የአንድነት መንፈሳቸውን ይበልጥ የሚያጎሉበትን ስፖርታዊ መድረኮችን አዘጋጅቶ ማቀራረብ ዋነኛ አማራጭ ቢያደርጉት ውጤታማ መሆን ይቻላል። በተመሳሳይም በክልሎች መካከል የሚታየውን መፋጠጥ ለማርገብ እንደመፍትሄ ሊታይ ይገባል። «ስፖርት ለሰላምና ለአንድነት» የሚል መሪ ቃል ያዘሉ የውድድር መድረኮችን በማዘጋጀት በክልሎች መካከል አፍጥጦ የመጣውን የልዩነት፣ ጠብን የመሻት አባዜ ማስከን የሚያስችል እድል ይፈጥራል። በአገር አቀፍ የውድድር መድረኮች ለምሳሌ እንደ መላው ኢትዮጵያ፣ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል አተያያቸውን በማረምና ልዩነትን ወደጎን በመተው የአንድነቱን ነጋሪት አብዝቶ በመጎሰም የዘርፉን ሚና መጠቀም ይቻላል።
በአጠቃላይ መንግስት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የስፖርቱን ዘርፍ መሰረት አድርጎ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጋራ በመሆን ያደረገው እንቅስቃሴ ነበር። ሁለቱ አካላት በጥምረት በመሆን ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ስፖርት ሰላምን ለማስፈንና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚል በአዲስ አበባ ባህል ማዕከል ከሳምንታት በፊት ውይይት አድርገዋል። የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሀት፣ ‹‹ስፖርት አክብሮትንና ትብብርን ለማጠናከር ዓይነተኛ መሣሪያ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በሕግ መመራቱ፣ በራሱ ቋንቋና መርህ መሠረት ዴሞክራሲን በራሱ መርህና መመርያ በመተዳደር ለስፖርቱ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እምቅና ትልቅ አቅም ያለው መሣሪያ ነው››። ከንግግሩ ስፖርት ሰላምን በማስፈን ረገድ ያለውን ሚና በተጨባጭ መረዳት ቢቻልም የዘርፉን አቅም መሰረት አድርጎ ወደ ተግባር እንዳልተገባ እሙን ነው።
በአሁኑ ወቅት ያለውን የልዩነትና የሰላም እጦትን ለማስቀረት ከቃላት ወደ ተግባር መቀየር ግን የሚያስችል ስለመሆኑ ጥያቄ ያስነሳል። በመሆኑም ያለውን የሰላም ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በስፖርት ላይ እምነት ከመጣል በተጓዳኝ፤ ሰላምን ያዘሉ የውድድር መድረኮችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ለሰላም እንሩጥ፣ ለኢትዮጵያ እንሩጥ ወዘተ የሚሉ ስፖርታዊ ክንውኖችን ቀርጾ ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል።በዚህም ስፖርቱ ወደ ሰላም መሸጋገሪያ አሳንሱር መሆን ይችላል። በአገራችን ሰላም ላይ ጉቶ በመሆን የሚፈጠሩት ችግሮች እንዲያከትሙ፤ ብሄራዊ ስሜት አሸንፎ እንዲወጣ ስፖርቱን መሳሪያ ማድረግ ተገቢ ይሆናል ባይ ነን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
ዳንኤል ዘነበ