የሰው ሀገር ሰው ነው። ለሀገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ የትውልድ መንደሩን ለቅቆ ሲወጣ ያለምክንያት አልነበረም። ሰርቶ ማደር አግኝቶ መለወጥ ይሻል። ለመማርና ለሌሎች ወጪዎች አርሶ አደር ቤተሰቦቹን ሲያስቸግር ቆይቷል።
ዕድሜው ሲጨምርና መብሰል ሲጀምር ግን የወላጆቹ ሸክም መሆኑ ይሰማው ያዘ።
ጌታሁን አየነው ከቀዬ ከመንደሩ ሳይርቅ እስከስምንተኛ ክፍል በርትቶ ተማረ የዛኔ ያገኘው ውጤት መልካም የሚባል በመሆኑ በእጅጉ አስደሰተው። የልፋቱን ፍሬ በማፈሱም ጥንካሬ ተሰማው። ይህ ደስታው ግን ሙሉ አልነበረም።
ቀጣዩን የዘጠነኛ ክፍል ለመማር ወደ ከተማ መዝለቅ ይኖርበታል። ለከተማ ህይወት ደግሞ የቤት ኪራይ የቀለብ የትምህርት መሳሪያና ሌላም ያስፈልገዋል።
አሁን ወጣቱ ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። ቤተሰቦቹ ለእለት ወጪው የሚተርፍ አቅም የላቸውም። ያለፉትን ዓመታት በችግር ተጎሳቁለው አስተምረውታል።
ለእኛ ሳይሉ ለእርሱ ሲያደርሱ ቆይተዋል። ከዚህ በኋላ እነሱን ማስቸገርና መጠየቅ እንደማያምርበት አምኗል። በእርሱ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ ከተማ ዘልቆ ቤት ተከራይቶ ትምህርቱን ቢቀጥል ይወድ ነበር።
የቤተሰቦቹን ውለታ የሚመልሰው ደግሞ ሲማርና በወጉ ሲለወጥ ብቻ ነው። ይህ ሃሳቡ ግን ከህልም አልዘለለም። ምን ቢያስብና ቢመኝ የድህነቱ ጉዳይ ርቆ የሚያራምደው አልሆነም።
ጌታሁን የቀዬውን ልጆች ታሪክ ያውቃል። አብዛኞቹ ከተማ ዘልቀው ክረምቱን ሰርተው ለትምህርታቸው ያተርፋሉ። እንዲህ ሲሆን ወላጆች ይደሰታሉ።
ከትምህርት ወጪያቸው በዘለለ ለማዳበሪያ መግዣ ጭምር ስለሚደጉሙ መሄዳቸውን አይቃወሙም። እርሱም ቢሆን ከአንድም ሁለቴ ወደ አዲስ አበባ ተመላልሷል።
ክንያት አልነበረም። አዲስ አበባ በክረምት ስራ አይጠፋም። ሎተሪ መሸጥ ቀን ስራ መዋልና ሌላም አይታጣም። ክረምቱ ሲያልፍ ለመስከረም ትምህርት የሚቋጠር አይጠፋም። ልብስ መቀየር ገንዘብ መያዝ የተለመደ ነው። አሁን ግን የገጠመው ከዚህ ይለያል። ለክረምት ስራ ብቻ የሚገኝ ገንዘብ አይበቃውም። ለዘለቄታው የሚተረፍ ጥሪት መያዝ ይኖርበታል።
ወጣቱ ደግሞ ደጋግሞ አስቦ ከራሱም ሲመካከር ሰነበተ። የመጨረሻ ውሳኔው ከቀዬው አሻግሮ መሀል አዲስ አበባ አደረሰው። የነገ ህልሙን ለመፍታት ወደ ሸገር መዝለቅ አለበት። እንዲህ ሲያደርግ ግን ትምህርቱን ማቋረጥ ግድ ይለዋል። አዎን! ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ መወሰን አማራጭ የለውም።
ጌታሁን፡- በእንግድነት የሚያውቃትን አዲስ አበባ ቤተሰብ ሆኖ ሊቀላቀላት ፈጠነ። ከእርሱ ቀድሞ የመጣው ታላቅ ወንድሙ በግንበኝነት ራሱን ያስተዳድራል። ታናሹ ሲመጣ አልተከፋም። ጠባብ ክፍሉን ከፍቶ መኝታውን አጋራው። ውሎ አድሮ ጌታሁን ወደ ሥራ ገባ። የእርሱ ምርጫ እንደ ወንድሙ አልነበረም።
ዓይኖቹ መጻሕፍት ላይ አነጣጠሩ። መጻሕፍቱን ሲመለከት ውስጡ በሐሴት መሞላት ያዘ። የማንበብ ፍላጎቱ የማወቅ ሃሳብና ዓላማውም ከሌሎቹ የተለየ ሆነ። የስራ ምርጫው መጽሀፍ መሸጥ ከሆነ በኋላ በርካታ ጥራዞችን ተሸክሞ መሄዱ አልከበደውም። ይህን ሲያደርግ በዕውቀት መሀል የመሸገ ያህል ይሰማዋል። ትናንት ያጣውን ትምህርት በማንበብና በመረዳት የተበቀለው ያህል ይቆጥረዋል።
ጌታሁን ከዚህ ሙያ ያገኘውን ጥቅም ያህል ሸጦ ማትረፍ እልፍ ሲልም ያልታሰበ ሲሳይ እንደሚገኝ አውቋል። ለዚህኛው መንገድ ደግሞ አንዳንድ ጓደኞቹ አቋራጩን አሳይተውታል። እንደርሱ መጻሕፍትን ለሽያጭ ተሸክመው የሚሄዱ አንዳንዶች ማጭበርበር ተክነዋል። ለመጽሃፍ ከተሰጠው ዋጋ በላይ አክለው መሸጥ ተለማምደዋል።
ወጣቱ ይህን ዘዴ ካወቀ በኋላ እንደነርሱ መሆን ተመኘ። ከሽያጩ ከሚገኘው ትርፍ በላይ ተጨማሪ ገንዘብ ቢያገኝ አይጠላም። ወዲያው ዘዴውን ተጠቅሞ መጻሕፍቱ ጀርባ ላይ ያለውን ዋጋ ፈቀፈቀ።
በምትኩም ይበጀኛል ያለውን የገንዘብ መጠን የሚያሳይ ቁጥር ተክቶ ይዞት መዞር ጀመረ። ይህ ዘዴው ያዋጣው ቢመስለው ልምምዱን ቀጠለበት። ጥቂት ትርፍም ወደኪሱ መግባት ሲጀምር በችሎታው ተማመነ።
አንድ ቀን ማለዳ ጌታሁን መጻሕፍቱን ቆልሎ ለሽያጭ ይዞ ወጣ። አያያዙ በጥንቃቄ ነው። በላብ እንዳይበላሽ በዝናብና በአቧራ እንዳይጎዳ ማድረጉን ያውቅበታል። በትከሻና በደረቱ መሀል የያዘውን ክምር ተሸክሞ መንገዱን ቀጠለ። ሁሌም ሰዎች ሰብሰብ ወዳሉበት ስፍራ መግባት ያዘወትራል።
ትልልቅ ሆቴሎች ካፌና ሬስቶራንቶችም የገበያው ቦታዎች ናቸው። አንዳንዴ በነዚህ ቦታዎች በርካቶች መጻሕፍት ይጠይቃሉ። አንዳንዶች ደግሞ ፈጽመው የማየቱ ፍላጎት የላቸውም። ጥቂቶች ግን የሚፈልጉትን ጠይቀውና አረጋግጠው ይወስዳሉ።
ጌታሁን እነማን መጽሀፍ እንደሚገዙ ከልምድ ተምሯል። እይታቸውን ገምቶና ለይቶም «እነሆ!» ሲል ይሰጣቸዋል።
የዛን ዕለት ማለዳም የሆነው ይኸው ነበር። መጻሕፍቱን እንደተለመደው ተሸክሞ በነዚህ ስፍራዎች ተዘዋውሯል። ጥቂት ራመድ እንዳለ አንድ ድምጽ ወደ ኋላ ሊመልሰው ግድ ሆነ። የጠራውን ሰው ያውቀዋል። ከዚህ ቀደም ሌሎች መጻሕፍት ሸጦለታል። ሰውየው የሚፈልገውን መፅሀፍ ጠየቀ። ጌታሁን በእጁ እደሚገኝ ነግሮት ካሉት መሀል ነጥሎ አስረከበው። ገዥው የተጠየቀውን ክፍያ ሰጥቶ መፅሀፉን ወሰደ። ጌታሁንም የሆዱን በሆዱ አድርጎ ባስተካከለው ዋጋ ተጨማሪ ክፍያ ተቀበለ።
ጥቂት ቆይቶ መፅሀፍ ሻጩ ወደቀድሞው ስራ ተመለሰ። ለጠየቁት እየመለሰ፣ ለገዙትም እየሸጠ ቀኑን አጋመሰ ይህ ሁኔታ ግን እስከማምሻው አልዘለቀም። ጌታሁን በእጅ በእግር ሲፈልጉት በነበሩ ፖሊሶች እይታ ወደቀ። እነርሱ ብቻቸውን አልነበሩም። አብሯቸው አንድ ግለሰብ ይታያል። ሰውየው ከሰዓታት በፊት ከጌታሁን መፅሀፍ ገዝቷል። በወቅቱ የተባለውን ዋጋ ሲከፍል አልተከራከረም። አለፍ ብሎ ሌሎችን ሲጠይቅ ግን መጭበርበሩ ገባው። የመጽሀፉ ዋጋና ክፍያው በእጀጉ የተራራቀ ነበር።
ሰውየው በፖሊሶቹ እንደታጀበ ወደሻጩ ቀርቦ ጠየቀ። መፅሀፍ ነጋዴው ዋጋው መሸጫው መሆኑን ተከራክሮ ሊያሳምነው ሞከረ። ይህኔ ሰውዬው በንዴት ጦፈ። ሻጩ ከድርጊቱ ይታረም ዘንድም ወደ ፖሊስ ጣቢያ አድርሶ ለ24 ሰዓታት አሳሰረው።
ይህ ታሪክ ከተፈፀመ ጊዜያት ተቆጥረዋል። ጌታሁን ከዛች ዕለት አጋጣሚ በኋላ ከራሱ ጋር ተማምሎ ከድርጊቱ ራቀ። መጻሕፍቱን ተረክቦ በመሸጥም የሚገባውን ብቻ መውሰድ ጀመረ። ዛሬ ላይ ያንን ሙከራውን ሲያስታውስ በእጅጉ ይፀፀታል። በእርሱ ዕምነት ያልተገባን መውሰድ ሌብነትና ሀጢያት ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉ ሲገጥሙት ይመክራል። ይቆጣልም። ይህ ፅናቱ ዛሬን በጥንካሬ እያራመደው ነው። የጌታሁን ስራ መጽሐፍ ተሸክሞ መዞርና መሸጥ ብቻ አይደለም። ቀኑን ሙሉ ይዞት ከሚዞረው መፅሀፍ ዕውቀት ለመቅሰም ምሽቱን በንባብ ያጋምሳል። ሁሌም ታሪካዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው ፅሁፎች የሚማርኩት ጌታሁን በእጁ የገቡትን ሳያገላብጥ ለሽያጭ እንደማያሳልፍ ይናገራል፡፡
አንዳንዴ ተፈላጊ የሚባሉ መጻሕፍት ለሽያጭ ከመቅረባቸው ከገበያ የሚጠፉበት አጋጣሚ ይኖራል። ይህን የሚያውቀው ወጣት ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ ለደንበኞቹ አስቀምጦ ያስረክባል። ይህን በማድረጉም ታማኝነቱን ያፀናበታል፡፡ ያኔ ያደረገውን ሙከራም እስከ ነውርነቱ እንደፋቀለት ይሰማዋል። ጌታሁን ዛሬም የትናንት መነሻውን አልዘነጋም። ትምህርቱን ማቋረጡ ይቆጨዋል። ይሁን እንጂ ጥቂት ገንዘብ ይዞ ህይወቱን እንደሚቀይር እምነቱ ነው።
ገጠር ታናናሽ ወንድሞቹ በትምህርት ላይ ናቸው። እነርሱ በችግር ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡና የእርሱን ታሪክ እንዳይደግሙ የተቻለውን እያደረገ ነው። ከአንድ የመፅሀፍ ሽያጭ እስከ 15 በመቶ ጥቅም የሚያገኘው ወጣት ነገ የራሱን መጻሕፍት ቤት የመክፈት ህልምም ሰንቋል።
አንዳንዶች ክብደት ያላቸውን ጥራዞች ተሸክሞ በመዋሉ ያዝኑለታል። ጥቂት የማይባሉትም የስራ ምርጫውን እንዲቀይር ይመክሩታል። እርሱም ቢሆን ድክም ባለው ጊዜ ስሜታቸውን ይረዳል። ከሁሉም ግን ከመጻሕፍቱ ገጾች በየቀኑ የሚቀምሰው ጣዕም ከማር በላይ እየጣፈጠው ስራውን ለመተው ተቸግሯል። ለእርሱ ከመጻሕፍቱ የሚያገኘው ጥቅም እያመዘነበት ነው። ሙያውን ከነፈተናው ተቀብሎ እንጀራው በማድረጉ ይደስታል። ሌሎች ዕውቀቱን ነጥለው በጉልበት አዳሪ መሆኑን በገመቱ ጊዜም “ለላም ቀንዷ አይከብዳት” ሲል ለራሱ ደጋግሞ ይነግረዋል። የሜጫው ወጣት የነገው ህልመኛ ጌታሁን አየነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011