በኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የምትታትረው ኢትዮጵያ የወቅቱ የኢኮኖሚ መሰረቷ ግብርና ነው፡፡ እናም ግብርናው በሚፈለገው መልኩ ኢኮኖሚውን ተሸክሞ የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዲያደርስም በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በዚህም የተነሳ የአገሪቱ የግብርና ምርት በመጠንም ሆነ በዓይነት እያደገ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ግብርና አሁንም ከባህላዊው የአመራረት ስልት እምብዛም ያልተላቀቀ በመሆኑ በተለይ በምርት ስብሰባና ክምችት ወቅት የሚደርሱ የምርት ብክነቶች በአርሶአደሩ ብቻ ሳይሆን በአገር ኢኮኖሚም ላይ ጫና ማሳደራቸው አልቀረም፡፡ እኛም ለዛሬው ዕትማችን የ2010/11 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት ሰብል ስብሰባና ክምችት በምን መልኩ እየተከናወነ ነው፤ በሚለው ዙሪያ የምናተኩር ይሆናል፡፡
ዕቅድና የስብሰባ ሂደት
አቶ አለማየሁ ብርሃኑ፣ የግብርና ሚንስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የ2010/11 የምርት ዘመን የመኽር እርሻ የምርት አሰባሰብ ሂደቱ በተቀመጠው እቅድ መሰረት የሄደ ባይሆንም፤ አሁን ላይ ያለው የአየር ሁኔታ አመቺ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምርትን የመሰብሰብ ሂደቱ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ነው፡፡ በእቅዱ መሰረት እስከአሁን በአብዛኛው ቦታ ተሰብስቦ መጠናቀቅ የነበረበት ጊዜ እንደመሆኑ ቢያንስ ከ80 በመቶ በላዩ ተሰብስቦም ሪፖርት መደረግ ነበረበት፡፡ ከዚህ አኳያ ክልሎች የተጠቃለለ ሪፖርት ስላልላኩ አሁን ላይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያለው መረጃ እንደሚያሳየው የስብሰባ ሂደቱ ከ50 በመቶ የዘለለ አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ የምርት ስብሰባ ቀጣይ ሥራው ትልቅ ርብርብ የሚጠይቅ ነው፡፡
ምክንያቱም ቀደም ሲል በዚህ ወር አጋማሽ ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር ይችላል የሚል ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሰረት የምርት መሰብሰብ ሂደቱ ላይ ሰፊ ርብርብ ተደርጎ ነበረ፡፡ ሆኖም ዝናቡ ትንሽ ዘግየት በማለቱና በመቆሙ የመዘናጋት ሁኔታ መታየቱ የራሱን ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ከዚህ ባለፈም በአንዳንድ አካባቢዎች ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የሰብል ስብሰባ ሂደቱ ላይ የራሱን ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ሆኖም በብዙ አካባቢዎች የምርት አሰባሰብ ሂደቱ በተደራጀና በተሻለ ሁኔታ እየተሰበሰበ ስለመሆኑ ግንዛቤ ተይዟል፡፡
በኦሮሚያ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የሰብል ልማትና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ሂርጳ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በ2010/11 የምርት ዘመን በተለይዩ ሰብሎች ከተሸፈነው 5ነጥብ9 ሚሊዬን ሄክታር መሬት ውስጥ እስከአሁን ድረስ 3ነጥብ4 ሚሊዬን ሄክታሩ ወይም 58 በመቶ ያህሉ ተሰብስቧል፡፡ በዚህም ደቡብ ኦሮሚያ፣ ቦረናና ቆላማው የባሌ ክፍል እንዲሁም ሌሎች የክልሉ ደጋማ አካባቢዎች ካልሆኑ በስተቀር የምርት አሰባሰቡ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው፡፡
የሚጠበቅ ውጤትና ተግዳሮቶች
አቶ ደጀኔ እንደሚሉት፤ በምርት ዘመኑ 203 ሚሊዬን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እቅድ ተይዟል፡፡ በዚህ ትንበያ መሰረትም በምርት ዘመኑ የተቀመጠው የምርት መጠን እንዳይገኝ ሊያደርጉ የሚችሉ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተገምቶ ነበር፡፡ እነዚህ ምክንያቶችም በተለያየ ሁኔታ የሚያጋጥሙ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ሲሆኑ፤ በተለይም የተለያዩ ተባዮች፣ ጎርፍ፣ በረዶና ሌሎች ችግሮች እቅዱ እንዳይሳካ ከሚደርጉት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህ መሰረትም ከ203 ሚሊዬን ኩንታል ውስጥ ወደ 170 ሚሊዬን ኩንታል እንደሚገኝ ተገምቷል፡፡ እስከአሁን ተሰብስቦ ወደጎተራ የገባው ግን 26 ሚሊዬን ኩንታል ምርት ነው፡፡
ባለፉት ሦስት ሳምንታት በክልሉ የሰብል ስብሰባ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ሆኖም በሂደቱ የሰብል ስብሰባውን የሚያውኩ የተለያዩ ችግሮች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሲሆን፤ ይህም ድርሻው ጉልህ ባይሆንም የምርት ስብሰባ ሂደቱን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የማስተጓጎል አቅም ነበረው፡፡ ሆኖም ወደ አርሲና ባሌ፣ እንዲሁም ምሥራቅ ሸዋና ጉጂ አካባቢዎች እንደ ኮምባይነር ዓይነት የሰብል መሰብሰቢያ ማሽኖችን ተጠቅሞ ምርቱን መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ወደ ማዕከላዊና ምዕራብ አካባቢዎችም ያላቸውን ዘመናዊና በሰው ኃይል የሚንቀሳቀሱ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ምርትን የመሰብሰብ ልምድ እየተተገበረ ነው፡፡
ከዝናብ ባሻገር በኦሮሚያና ቤኒሻንጉልጉሙዝ አዋሳኝ አካባቢዎች የነበረው የጸጥታ ሁኔታ የተወሰነ ችግር ፈጥሯል፡፡ ይሄም በምርት አሰባሰብ ሂደት ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ለምርት ብክነትም ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የጸጥታው ሁኔታ የተረጋጋና ችግር በሌለበት ቦታ የምርት አሰባሰብ ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው፡፡
አቶ አለማየሁ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በመኽር እርሻ ወደ 14 ሚሊዬን ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈን ተችሏል፡፡ ይህም እቅዱን መቶ በመቶ ያሳካ ነበር፡፡ ከምርት አኳያ ደግሞ ወደ 375 ሚሊዬን ኩንታል ምርት ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፤ ይህን ውጤት የማግኘቱ ጉዳይ ግን በተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ሂደት በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ቦታዎች በዝናብ እንዲሁም በጸጥታ የሚገለጹ ችግሮች እየተስተዋሉ ሲሆን፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተወሰነ ለውጥ ሊኖር ቢችልም የከፋ የምርት ቅናሽ ይኖራል የሚል ግምገማ ግን የለም፡፡
የምርት ክምችትና ቀጣይ ሥራዎች
እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ፤ የድህረ ምርት ችግር ጉዳይ ከመሰረቱ ጀምሮ የመጣ ነው፡፡ ምክንያቱም ለድህረ ምርት አያያዝ ያለው ግንዛቤ እጅጉን አናሳ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከተመረተው ምርት ያልተናነሰ በድህረ ምርት የምርት ብክነት እንደሚያጋጥም ታይቷል፡፡ በመሆኑም ይሄንን ችግር ሊቀርፍ በሚችል መልኩ የድህረ ምርት አያያዝና አከመቻቸት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ሲሆን፤ ክልሎች በዚህ ዙሪያ እየሠሩ ይገኛል፡፡ አርሶአደሮች ሰፊ ጉልበት አፍስሰው ያመረቱትን ምርት ጎተራ እስኪገባና ከጎተራም ለምግብ ወይም ለገበያ ደርሶ ለአርሶአደሩ የገቢ ምንጭ ሆኖ እስኪያገለግል ድረስ ባለው ሂደት ያለው የምርት ብክነት በሚቀነስበት አግባብ ምክረ ሃሳብ እየተሰጠ ነው፡፡
የድህረ ምርት ብክነትን ለመከላከል የሚከናወነው ተግባር ከማሳ እስከ ገበታ ወይም እስከ ጉርሻ ያለውን ሂደት የሚያጠቃልል ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰብል ታጭዶ፣ ተወቅቶና ተጓጉዞ ጎተራ እስኪከማች ብቻ ሳይሆን በክምችት ወቅት የሚከሰት ብክነትንም የሚመለከት ነው፡፡ በአብዛኛው አርሶአደር ደግሞ እነዚህን ሥራዎች የሚያከናውነው በባህላዊ መንገድ ነው፡፡ እናም ይሄን ብክነት ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ይሄን የባህላዊ አሠራርን በቴክኖሎጂ ተደግፎ የመሥራት ልምድ እንዲዳብርና በሜካናይዜሽን እንዲተካ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ፣ በአጨዳ፣ ወደ አውድማ በማጓጓዝ፣ በውቂያ ወቅት የሚከሰት ብክነትን በኮምባይነር በማጨድ ብቻ ማስቀረት ይቻላል፡፡ እናም የድህረ ምርት ብክነትን የመከላከል ሥራው በዚህ መልኩ መከናወን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የግንዛቤ ማስጨበጥና እውቀት መፍጠር ሥራ መሠራት እና የቴክኖሎጂ አቅርቦቱም መድረስ አለበት፡፡
ከዚህ አኳያ አርሶአደሮች እህል ከማሳ ተሰብስቦ ከመጠናቀቁ በፊት የእህል ማከማቻ ጎተራዎችን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ የሚዘጋጁ የእህል ማከማቻ ጎተራዎች ደግሞ በተቻለ መጠን ዘመናዊ ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ ካልተቻለ ግን የባህላዊ የእህል ማስቀመጫዎችን በአግባቡ አዘጋጅቶና አጽድቶ ተባይና ሌሎች የብክነት ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን አስወግዶ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ የከረመውን እህል ከአዲሱ ሳይቀላቅሉ ማከማቸት ይኖርባቸዋል፡፡ ምርቶችን በጥራት ማከማቸት፣ በእርጥቡ ከመክተትና ሌሎች ለምርት ብክነትና ጥራት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን በማስወገድም የልፋታቸውን ውጤት መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡
አቶ ደጀኔ እንደሚሉት ደግሞ፤ ምርት ተሰብስቦ ወደ ጎተራ ከገባ በኋላ በተለያዩ ተባዮች የመጠቃት ዕድል አለው፡፡ በዚህ መልኩ የሚከሰትን የምርት መባከን ከመከላከል አኳያም አርሶአደሮች የተለያዩ ዘመናዊ የምርት ማከማቻዎችን እንዲጠቀሙ ለማስቻል በተለያዩ ቦታዎችና አጋጣሚዎች የማስተዋወቅ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ወደ ዞኖች ጭምር ወርዶ በተሠራው የማስተዋወቅና ግንዛቤ የማስጨበጥ ብሎም ገዝተው እንዲጠቀሙ የማስቻል ተግባራት አርሶ አደሮችም እነዚህን ቴክኖሎጂዎች እየተጠቀሙ ነው፤ሥራውም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
በዚህ መልኩ ከሚከናወኑ ተግባራት ባለፈ ግን አርሶአደሩ በራሱ ሊወስዳቸው የሚገቡ የድህረ ምርት ክምችት ጥቃቄዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ሰብሉን በንጹህ ቦታ ላይ ሊወቃና ተበጥሮ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተረፈ ምርቶቹን ሙቀትና እርጥበት በሌለባቸው እና ለተባዮች ምቹ ባልሆነ በቀዝቃዛና ደረቅ ቦታ ላይ መከማቸት ይኖርባቸዋል፡፡ አዲስ የሚያስገቡትን ሰብል ቀደም ባሉት ዓመታት በጎተራ ካሉ ሰብሎች ጋር አቀላቅሎ ማስቀመጥ አይገባም፡፡ የቀደመውን ሰብል አውጥቶ በሌላ ዕቃ ውስጥ በማስቀመጥ ነው አዲሱን ሰብል ጎተራ ማስገባት የሚገባው፡፡ ተቀላቅለው የሚቀመጡ ከሆነ በቀደመው ሰብል ውስጥ የነበሩ ተባዮች ወደ አዲሱ በቀላሉ እንዲተላለፉና እንዲያበላሹት ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ ዓይጦች ወደጎተራ ገብተው ምርቱን እንዳያበላሹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግና የመከላከል ሥራዎችንም ማከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የአርሶአደሩ ጥንቃቄና ተግባርም በባለሙያዎች ሊደገፍ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
ወንድወሰን ሽመልስ