ለአውሮፓ ህብረት መስፈርት ምላሽ ዝግጁነትን የማጠናከር ጥረት

ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የሚታወቀው ቡና ባለፉት የለውጡ ዓመታት በዘርፉ የተደረጉ ሪፎርሞችን ተከትሎ ይህ ሚናው እየጨመረ መጥቷል:: ወደ ውጪ በሚላክ የቡና መጠንም ከዚህ በሚገኝ የውጭ ምንዛሬም እምርታዎች እየተዘመገቡ ይገኛሉ::

ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስሥልጣን የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው፤ በ2014 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበው 300 ሺህ ቶን ቡና አንድ ነጥብ 42 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል ፤ በ2015 በጀት ዓመት ከ240 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አንድ ነጥብ 331 ቢሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ በ2016 በጀት ዓመትም እንዲሁ ከ298 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አንድ ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል::

በ2017 በጀት ዓመትም የቡና ምርትና ምርታማነት እያደገ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ እቅድ በማዘጋጀት ነው ወደ ሥራ የተገባው:: በበጀት ዓመቱ ወደ 400 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገባት ታቅዶ ሲሠራ ቆይቷል::

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉትም፤ በለውጡ ማግስት 700 ሚሊዮን ገደማ ዶላር በዓመት ከቡና ኤክስፖርት ይገኝ ነበር፤ ባለፈው ዓመት ደግሞ ብዙ እመርታ ተመዝግቦ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፤ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ የቡና ኤክስፖርት ተብሎ በወቅቱ ተመዝግቦም ነበር::

ዘንድሮ /በ2017 በጀት ዓመት/ ግን አምና ወደ ምርት ያልገቡ ቀደም ሲል የተተከሉ ቡናዎች ስለተጨመሩ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከቡና ኤክስፖርት ማግኘት ተችሏል ብለዋል::

የዛሬ አምስት ስድስት ዓመት ሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር ኤክስፖርት የምታደርግ ሀገር በዚህ ዓመት ከሞላ ጎደል ሁለት ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ታደርጋለች ማለት ቡና ላይ ስር ነቀል ለውጥ መጥቷል ማለት ነው ሲሉም ገልጸዋል::

ሀገሪቱ በቀጣይም የቡና ልማቱን በማስፋፋት፣ በጥራት ላይ በመሥራት በስፔሻሊቲ ቡና ላይ የመጣውን ለውጥ ይበልጥ በማሳደግ፣ መዳረሻ ገበያዎችን በማስፋት፣ እሴት የተጨመረበት ቡና ለውጭ ገበያም በስፋት በማቅረብ ከቡናዋ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እየሠራች ትገኛለች:: የዘርፉን ተግዳሮቶች ለይቶ በመፍታት ላይም በትኩራት ትሠራለች::

ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን ቡና በተመለከተ በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት ያስቀመጣቸው መስፈርቶች ለውጭ ገበያ በምትልከው ቡና ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳርፍ ለማድረግም እየሠራች ትገኛለች:: የአውሮፓ ህብረት ላቀረበው መስፈርት ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት በማድረግ ላይ ናት::

ይህን የአውሮፓ ህብረት ጥያቄን በተመለከተ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አዘጋጅነት ሰሞኑን በሸራተን አዲስ ሆቴል የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ተደርጓል:: የመድረኩ ዋና ዓላማ በአውሮፓ ህብረት የተቀመጡትን መስፈርቶች በመፈተሽ በቀጣይ መደረግ ስላለበት መምከር ነው::

በመድረኩ ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቶ አስቻለው አላምሬ፣ የኢንዱስትሪና ማዕድን ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አማረ መንግሥቱ (ዶ/ር)፣ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ሰብሳቢ አቶ ሙባረክ ኤሊያስ ተገኝተዋል::

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን፣ መድረኩ የተዘጋጀው የአውሮፓ ህብረት ቡናን በተመለከተ ባቀረበው መስፈርት ላይ እንደ ሀገር ማድረግ ባለብን ላይ ለመወያየት፣ ለመወሰን እና ዝግጁነታችን በአሳማኝ እውነታ ለማሳየት እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት እንደቅድመ መስፈርት ለሀገራችን የኤክስፖርት ገበያ ያቀረበው ጥያቄ በአስተባባሪ ኮሚቴው በኩል ምላሽ የሚያገኝበትን አቅጣጫ ለማስቀመጥ ሲሉ አብራርተዋል::

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ በአውሮፓ ህብረት ከተቀመጠው ቀነ ገደብ ማብቂያ በፊት እስከመጪው ሰባት እና ስምንት ወራት ድረስ ሀገሪቱ በኤክስፖርቱ ዘርፍ ነጻ እና እንደዚህ ቀደሙ ተደራሽነቷን ባረጋገጠ መልኩ ምርቷን ለዓለም ገበያ የምታቀርብበትን መንገድ መክፈት የውይይቱ አንዱ እና ወሳኝ ዓላማ ነው:: ለዚህም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ቀጣይነት ያለው ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሠራ ነው::

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ካለፉት ዓመታት ወዲህ ወደውጪ በሚላከው ምርት በተለይም በቡናው ዘርፍ ላይ ጥራትን በተመለከተ ከተረካቢ ሀገራት ጥያቄ ሲነሳ ቆይቷል:: እስከ ፈረንጆቹ 2026 መጀመሪያ ድረስ ገደብ በተቀመጠለት የህብረቱ መስፈርት መሠረት የኤክስፖርቱ ዘርፍ ሀገሪቱ በቂ እና አስተማማኝ ምላሽ ይዛ እንድትቀርብ የአንድ ዓመት ጊዜ ተሠጥቷል:: ቀነ ገደቡ ከመድረሱ በፊት ለአውሮፓ ህብረት ጥያቄ ምላሽ ለማሰናዳት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል:: ባለፉት ሶስት እና አራት ወራትም በመሰል ምክክር እና የሃሳብ ልውውጥ ተደርጓል::

የአውሮፓ ህብረት በተወሰኑ የኤክስፖርት ምርቶች ላይ ያስቀመጥኳቸውን መስፈርቶች ካላሟላችሁ ምርቶቻችሁን ወደአውሮፓ ገበያ መላክ አትችሉም የሚል አቋም ላይ ደርሷል ሲሉም አቶ እንዳለው ጠቅሰው፣ ለዚህ አቋሙ ምላሽ ለመስጠት ሀገራት ዝግጅት እንዲያደርጉ የአንድ ዓመት ያህል ጊዜ ሰጥቷል ብለዋል:: ይሄን አቋም ምክንያታዊ በሆነ ግብረ መልስ ለመሻር እና ለመስፈርቱ ብቁ ሆኖ ለመገኘት መንግሥታዊ የሆኑ ሁሉም ተቋማት ውይይት እና የመፍትሄ ሃሳቦች እየመነጩ መሆናቸውን አመልክተዋል::

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያሲኒን ውሀረቢ በበኩላቸው በእንደቅድመ መስፈርት የተቀመጠው የአውሮፓ ህብረት ጥያቄ ሀገሪቱ ለምታካሂደው የኤክስፖርት እንቅስቃሴ አስጊ ነው ብለን አናስብም ሲሉ አስታውቀዋል:: ቡናን ለዓለም በማስተዋወቅ፣ አምራች ከሆኑ እና በተፈጥሯዊ ምርቶቻቸው ከሚታወቁት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ ህብረቱ ያቀረባቸው ጥያቄዎች የተሻለ እድል የሚፈጥሩልን አጋጣሚዎች ናቸው ብለዋል::

በመድረኩ ኢትዮጵያ ውስጥ አምስት ሚሊዮን የቡና አምራች ገበሬዎች እንዳሉ የተጠቆመ ሲሆን፣ የአውሮፓ ህብረት ጥያቄ መሠረት ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑትን አምራች አርሶ አደሮች ወደሲስተም የማስገባት እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ተመላክቷል:: ግማሽ ያህሉን አምራች አርሶ አደር ወደተጨባጭ ሂደት አስገብቶ በሚመጣው ለውጥ መሠረት ቀጣይ እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉም ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ያሲኒን ውሀበረቢ ገልጸዋል::

የአውሮፓ ህብረት እንደመስፈርት ካስቀመጣቸው መካከል የመጀመሪያው “ኢንፎርሜለሽን ሪኳይርመንት” የሚለው አንዱ ነው:: ይህም ቡናው የሚበቅልበትን አካባቢ ከማጥናት፣ ከማወቅ ጋር ይያያዛል:: በዚህ ቦታ፣ በዚህ ሙቀት፣ በዚህ ግብዓት የተመረተ መሆኑን ለማወቅ የተቀመጠ መስፈርት ነው:: መስፈርቱ ለእዚህ እንደ ምሳሌ የተወሰደው ጓንት ሲሆን፣ አንድ ድርጅት ጓንት ቢያመርት ጓንቱ ከምን አይነት በሬ፣ ከምን አይነት ቆዳ፣ በምን አይነት ጥራት እንደተመረተ ለማወቅ ወሳኝነት ይኖረዋል::

ሌላኛው እንደመስፈርት የተቀመጠው ጉዳይ ‹ሪስክ አሰስመንት› የሚለው መሆኑ ተጠቁሟል:: ከሪፎረስቴሽን /ደንን መልሶ ማልማት/ ጋር የተያያዙ በተለይም ጥያቄ በተነሳበት የቡና ኤክስፖርት ዙሪያ ያለውን ሂደት ያጠቃልላል:: እነዚህን ጥናቶች በማዘጋጀት በቂ እና ምክንያታዊ ምላሽ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል:: በዘርፉ ላይ እየሰሩ ካሉ ማህበራት፣ አርሶ አደሮች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በተፈጠረ ጥምረት ዋስትና ሊሰጡ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች በሂደት ላይ ይገኛሉ::

በሶስተኛነት የተቀመጠው መስፈርት ‹ወርክ ሾፕ› ነው:: ለዚህም የሚሆን እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ተመላክቷል:: በቀጣዩ ጊዜ አመርቂ ውጤት የሚመጣበትን የትስስር ውይይት ለማድረግ ዝግጁነት እንዳለም ተጠቁሟል:: የውህደት እና የምክክር አስፈላጊነት ለውጦችን እና ነውጦችን በየደረጃው ለመመልከት የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ በላኪና በተቀባይ መካከል ያለውን ትስስርም ያቀላጥፋል:: የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠንከር ለውጥና ተግዳሮቶችን እየፈቱ ወደፊት ለመሄድ ብሎም ለጋራ ውጤታማነት ብዙ ድርሻ አለው::

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አስቻለው አላምር በበኩላቸው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከተገነባባቸው የኤክስፖርት ምርቶች መካከል ቡና ቀዳሚው እንደሆነ ጠቅሰው፣ ከአጠቃላይ የኤክስፖርት ምርቶች ቡና ብቻውን 30 ከመቶ እንደሚሸፍን አስታውቀዋል:: በዚህ የገበያ ዘርፍ ላይ የተነሳው ጥያቄ እንደተቋም ሳይሆን እንደሀገር እና እንደሉዓላዊነት ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል:: ‹‹ሀገራችን ከነበረችበት የኤክስፖርት ገበያ ወጣች ማለት ዳፋው የከፋ ነው›› ሲሉም አስታውቀዋል::

የጥራት መንደር በመገንባቱ የተሻሉ ምርቶችን ወደውጪ ሀገራት ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመው፣ በቀጣይ መሰል ሥራዎች ላይ በማተኮር የኤክስፖርት ዘርፉን ማገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል::

አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው አውሮፓ በቡና ምርታችን ላይ ያስቀመጠችው መስፈርት እንደሀገር ሊታይ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል:: ከሀገሪቱ ሉዓላዊነት እና ከመጪው ጊዜ የማደግ እና የመበልጸግ መሻት ጋር ሊቆራኝ እንደሚችልም ገልጸዋል::

በሕግ በተመራ የገበያ ሥርዓት ብቁና ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ይኖርብናል ሲሉም ጠቁመው፣ ለዚህም የሚረዱ በሳል ሃሳብ አቅጣጫዎችን መጠቀም ግድ እንደሚል አመልክተዋል::

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ እንዳለው መኮንን አውሮፓ ህብረት ላቀረበው ጥያቄና ለእዚህም ምላሽ ለመስጠት እየተደረገ ባለው ጥረት ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ባለፉት አምስት እና ስድስት ዓመታት በተሠሩ ሕዝባዊ የአረንጓዴ ዐሻራ የንቅናቄ ሥራዎች ሰባት በመቶ የነበረው የደን ሽፋን ወደ ሃያ ሶስት ከመቶ መድረሱን ጠቅሰው፣ ይህም በእኛ በኩል እንደአንድ የመፍትሄ ሃሳብ ይቀርባል ብለዋል::

ከደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተመው፤ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት ዘጠና ሁለት ሄክታር የሚሆን ደን ይጨፈጨፍ ነበር:: አሁን ይሄ መጠን ቀንሶ ለደን ልዩ ትኩረት የተሰጠበት ጊዜ ላይ ተደርሷል::

በመጪዎቹ ዓመታት በሚደረገው መሰል እንቅስቃሴ የደን ሽፋኑ ከዚህም በላይ ሊያድግ እንደሚችል አመልክተው፣ ይህም ቀጣይ ሂደቱን የተሳካ እንደሚያደርገው ተናግረዋል:: በአምስትና ስድስት ዓመታት ውስጥ በተሠራው የደን ሽፋን መጨመር ሥራ በተለይ በቡናው ዘርፍ ላይ የተሻለ እምርታ መታየቱን ገልጸዋል::

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለአውሮፓ ህብረት ቅድመ መስፈርት ምላሽ ይሆናሉ ካላቸው ውስጥ ሌላው ጉዳይ እንደሀገር ከላይ እስከታች ሁሉንም ያሳተፈ ሰፊ ንቅናቄ ማድረግ የሚለው ታምኖበታል:: ኤክስፖርቶች ላይ ብቻ የሚተው ግዴታና ውዴታ አለመኖሩ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከአምራች እስከ ላኪ ድረስ ባለው ሂደት ላይ የሁሉም ተሳታፊነት ወሳኝ ሚና እንዳለው ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል:: በተጠና እና ዝግጁነት ባየለበት ሰፊ የድርጊት መርሀ ግብር ከገበያው ሳንወጣ በተሻለ የምርት አቅርቦት እና ተጠቃሚነት ገበያው ላይ ተጽዕኖ የምንፈጥርበት ሌላው የመፍትሄ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል ሲሉም አብራርተዋል::

አቶ እንዳለው አውሮፓ ህብረት እንደመስፈርት ላስቀመጣቸው መጠይቆች እኛም ግልጽ ምላሽ ልናሳይ ይገባል ሲሉ ጠቅሰው፣ ሕጎቻችን ነጻና ግልጽ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል:: ከታች እስከላይ ባለው አሠራር ውስጥ የማያሻማ ሕግ መኖሩ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ አሻሚና እኛ ያልተረዳናቸው ሕጎች ሌሎች ጋ ሄደው ለውጥ አያመጡም ብለዋል::

በውይይቱ ላይ ከተሳታፊዎች ገንቢና ሁሉንም ተሳታፊ ያስማሙ ሃሳቦች ቀርበዋል:: በተለይ የሀገሪቱ የዘርፉ ባለሙያዎች ሰፋ ያለ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ በቀጣይ አስቻይ ሁኔታዎችን ተጋግዞ መፍጠር እንደሚገባ ተመላክቷል:: እንደዋና መፍትሄ ከተነሱት መሀል ዝግጁነት አንዱ ነው:: እንደላኪ ሀገር ምርቶቹ ተመራጭ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ቅድመ ዝግጁነት ማድረግ ወሳኝነት እንዳለው ተጠቁሟል::

ዝግጁነት የተነሱትን ጥያቄዎች ከመመለስ በላይ በኤክስፖርቱ ዘርፍ በቀጣይ እንደሀገር የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት ጉልበት እንደሚሆኑም ታምኖባቸዋል:: አውሮፓ ህብረት ከዚህ በፊት በተናጠል ሲያቀርበው የነበረውን ጥያቄ እንደተቋም ሲያነሳ በጠንካራ ዝግጁነት መልስ መስጠት ችግሩን መቅረፍ ሚናው ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል::

ለአውሮፓ ህብረት ጥያቄ መልስ ለመስጠት በኢትዮጵያ በኩል ምን መሠራት እንዳለበት አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ እዚህም እዚያም የተበታተኑ ነገሮችን አስተካክሎ ወደአንድ አቅጣጫ ማምጣት ይገባል የሚለው አንዱ ነው:: የሚመለከታቸው አካላት፣ ባለድርሻ አካላት፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የሆሊቲካልቸር፣ የቡናና ሻይ ተቋማት ተቀናጅተው በመሥራት እስከመጪዎቹ ሶስትና አራት ወራት ድረስ ወሳኝ ነጥብ ላይ መድረስ እንደሚገባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል::

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You