
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብሩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል ኢንዱስትሪ አንዱ ነው። ዜጎች እንዲሁም የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ በስፋት እንዲሰማሩ ለማድረግ፣ የዘርፉን የቦታ፣ የመሰረተ ልማት፣ የገበያ ወዘተ. ችግሮች ለመፍታት ብዙ ተሰርቷል።
ለውጭ ባለሀብቶች እና ለውጭ ገበያ ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በሚል በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች /አሁን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ተብለዋል/፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ገብተው እንዲሰሩ ተደርጓል።
ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የመስሪያ ቦታ በማቅረብ፣ መሰረተ ልማት በመዘርጋትና የገበያ ትስስር የሚፈጥሩባቸውን ኢግዚቢሽኖችና የመሳሰሉትን በማዘጋጀት የሚያድጉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንዲሁም የማሽነሪ ጥያቄዎቻቸውን በሊዝ ፋይናንሲንግ ስርዓት ለመመለስ ጥረት ተደርጓል።
ይህን ሁሉ ተከትሎም ውጤታማ ኢንዱስትሪዎች ከአነስተኛ ኢንዱስትሪ ወደ መካከለኛ፤ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ እየተሸጋገሩ ይገኛሉ። በኢንዱስትሪው ዘርፍ መሰል ለውጦች መታየት ቢጀምሩም፣ እንደ ኮቪድ 19፣ የሰሜኑ ጦርነት በመሳሰሉት ተግዳሮቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግን የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ አልነበሩም።
መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በ2014 ወደ ትግበራ አስገብቷል። በዚህም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ጨምሯል፤ ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ማምረት ተችሏል። በአጠቃላይ በዘርፉ መነቃቃት መታየት ጀምሯል።
ኢንዱስትሪዎቹ በተለይ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የልማቱ አጋዥ መሆን እየቻሉ ናቸው። ለኮሪደር ልማቱ የሚያስፈልጉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን በሀገር ውስጥ እያመረቱ ያሉበት ሁኔታም ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል። በአዲስ አበባ እና በሀረር ከተሞች የሚገኙት እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን እያመረቱ ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ ለተጀመረው ጥረት አጋር መሆን ችለዋል።
በዛሬው የኢንቨስትመንት አምዳችም በሀረር ከተማ የሚገኘው ‹‹ማስ ኢንጂነሪንግ ኢንተርፕራይዝ›› ለሀረር ከተማ የኮሪዶር ልማት ሥራ የሚያመርታቸውን ግብዓቶች እንቃኛለን።
ማስ ኢንጂነሪንግ ኢንተርፕራይዝ በሀረሪ ክልል በብረታ ብረት ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማራ ድርጅት ነው። ኢንተርፕራይዙ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት እንደ ሀገር የታየዘውን እቅድ ለማሳካት በትኩረት እየሠራ መሆኑን የኢንተርፕራይዙ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወሂብ ኡመር ይገልጻሉ።
ደርጅቱ ከተመሰረተ አምስት ዓመታትን እንዳስቆጠረ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ በእነዚህ ዓመታት ከኮረና ወረርሽኝ መከሰት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩትን ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተጽዕኖች ተቋቁሞ አሁን ላለበት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካቱ ሥራ መድረሱን ይጠቅሳሉ።
ከለውጡ ወዲህ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተደረጉ ሪፎርሞች ማስ ኢንጂነሪንግ ኢንተርፕራይዝ የመፈጸም አቅሙን በማሳደግ በተለይም በሀረሪ ክልል በሚደረጉ የልማት ሥራዎች ላይ የራሱን ዐሻራ እያኖረ መሆኑንም ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅትም ኢንተርፕራይዙ ማስፋፊዎችን አድርጎ አዳዲስ ቴክሎጂዎችንና ማሽኖችን በማስገባት እንዲሁም የሰው ኃይል አቅሙን በማጎልበት የሥራ አማራጮችን ይገኛል። ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕይራዙ ሥራ የጀመረው በ12 ሚሊየን ብር ካፒታል ሲሆን፣ ካፒታሉ በአሁኑ ሰዓት እስከ 60 ሚሊየን ብር ይገመታል።
ፋብሪካው በዋናነት ሺት ሜታሎችንና ፕይፖችን ፕሮሰስ እንደሚያደርግ የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፣ ሥራ በጀመረበት ወቅት ዘመናዊ በርና መስኮቶችን እያመረተ ለግለሰቦችና ለመንግሥት ተቋማት ያቀርብ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እንደሀገር ከተጀመረው የኮሪዶር ልማት ጋር ተያይዞ በተለይም ለሀረር ከተማ የኮሪዶር ልማት የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ ልማቱን እየደገፈ እንደሚገኝ ይናገራሉ። ለኮሪደር ልማቱ ግብዓት ከሆኑ የፋብሪካው ምርቶች አንዱ የመብራት ምሰሶ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህንንም በስፋት በማምረት ጥቅም ላይ እንዲውል እያደረገ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
በፋብሪካው የሚመረቱ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች እና የአምፖል ማቀፊያዎች ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ መንገድ ከመብራት መስመር ዝርጋታ ባለፈ የማሕበረሰቡን ባሕል በሚገልጹ መልኩ ውበትን እንዲላበሱ አርጎ እንደሚሰራቸው ተናግረዋል። ይህም ለከተማው ልዩ ድምቀት መስጠት እንዳስቻለ ያስረዳሉ።
እስከ አሁን በሀረር ከተማ ለኮሪደር ልማት የዋሉ በርካታ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን በሚያምር ዲዛይን አምርቶ ጥቅም ላይ ማዋሉን የሚናገሩት አቶ ወሂብ፣ በቀጣይም የከተማዋን ሙሉ መስመሮች የሚሸፍኑ ምሰሶዎችን በአስር እጥፍ ለማሳደግ እየሠሩ መሆናቸውን ያብራራሉ።
በኮሪዶር ልማቱ በሀረር ከተማ የተተከሉ የመብራት ምሰሶዎችን የተመለከቱ አጎራባች ክልሎች ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ በቀጣይም ለሶማሌ ክልል፣ ለድሬዳዋ እና ለኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን የየአካባቢዎቹን ባሕሎች የሚገልጹ የጎዳና ላይ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን እና የአምፑል ማቀፊያዎችን ለመሥራት መዘጋጀቱን ይገልጻሉ።
ድርጅቱ የሜካኒካልና ኤሌክትሪካል የሜታል ወርክ መሀንዲሶች እና ሙያተኞች እንዳሉት ገልጸው፣ በኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ላይ የሚዘረጉት የኤሌክትሪክ ሽቦዎችም በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች የሚሠሩና ሲስተማቸው አስተማማኝ መሆኑ እየተፈተሸ ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ገልጸዋል።
እስከ አሁን ድርጅቱ 35 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረ ጠቅሰው፤ በቀጣይም እስከ መቶ ለሚሆኑ ሠዎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅማቸውን እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።
ጉቱ አልይ ከሀረር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በብረታ ብረት የሙያ ዘርፍ ተመርቆ በማስ ኢንጂነሪንግ ኢንተርፕራይዝ በማጠፊያና ቅርጽ ማውጫ ማሽን ላይ ሲሠራ ያገኘው ወጣት ነው። ፋብሪካውን በተቀላቀለ በአንድ ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ልምድ እንዳዳበረ ይናገራል። ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን በሚታዘዘው ዲዛይን መሰረት ቀርጽ ያስይዛል፤ በዚሁ መሰረት ላሜራዎችን ያጥፋል፣ ይቆራርጣል። እንደ በር፣ መስኮት፣ የቢሮና የቤት እቃዎች ያሉትን ቅርጽ እያወጣ እንደሚገጣጥምም ይጠቅሳል።
አሁን አዳዲስ ሥራዎችን የመሥራት እድል አግኝቷል። ፋብሪካው ለሀረር ከተማ የኮሪዶር ልማት የሚውሉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን ማምረት በመጀመሩ የብረታ ብረት ቅርጾችን በማውጣት ይበልጥ መጠበብ መጀመሩን ይገልጻል።
ለሀረር ከተማ ድምቀት የፈጠሩ የኤሌክትሪክ የብረት ምሰሶዎችና አምፖል ማቀፊያና ጌጦች የእሱ የእጁ ውጤት መሆናቸውን ሲመለከት ልዩ ኩራት እንደሚሰማውም ነው የተናገረው። እነዚህ ሥራዎቹ ሌሎች ሥራዎችን የመሥራት መተማመን እንዲያድርበት ማድረጋቸውን ያስረዳል።
ሌላው በፋብሪካው ወስጥ ሲሠራ ያገኘው ወጣት ዳንኤል ዳዊት ነው። ዳንኤል በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ እዚያው ደሴ ከተማ ወይዘሮ ስህን ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት በ10+3 (በሌቭል ሶስት) በሜታል ዎርክ የሙያ መስክ ስልጠና ተከታትሏል። ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በጋራዦችና በተለያዩ ቦታዎች ተቀጥሮ መሥራቱን ይገልጻል።
የማስ ኢንጂነሪንግ ኢንተርፕራይዝ በእርሱ ሙያ የሰለጠነ ሰው እንደሚፈልግ በጓደኞቹ አማካኝነት መረጃ ሲደርሰው ከአዲስ አበባ ወደ ሀረር በመሄድ በፋብሪካ ውስጥ በሌስ ማሽን፣ በቶርኖ ማሽን እና በቅርጻቅርጽ ሙያተኝነት መቀጠሩን ይናገራል።
ዋና ሥራው እየተቆራረጡ የሚቀርቡለትን ላሜራዎች እና ብረቶች መገጣጠም ነው። የሚሠራቸውን ባለጌጥ ቅርጻቅርጾችና አምፖል ማቀፊያዎች በኤሌክትሪክ ምሰሶው የተለያዩ ክፍሎች ላይ ተገጥመው ለሀረር ከተማ ልዩ ድምቀት መስጠታቸውን እኛም ተመልከተናል።
በፋብሪካ ውስጥ መስራት ከጀመረ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው ወጣት ዳንኤል፣ ጠቅላላ ሥራው በሀገር ውስጥ ሙያተኞች እንደሚከናወን ይገልጻል። ከሙያ አጋሮቹና ፋብሪካው ከፈጠረለት ምቹ ሁኔታ ከፍተኛ ልምድ እንዳካበተ ጠቅሶ፣ የእርስ በእርስ መማማሩና ልምድ መለዋወጡ በሌሎች ማሽኖችም ላይ እንዲሰራ እድል እንደፈጠረለት አስታውቋል።
ሰው ሙያ ካለው ይፈለጋል፤ ተፈላጊነት ካለው ደግሞ የትም ሀገር ሰርቶ መኖር ይቻላል የሚለው ዳንኤል፣ ከተወለደበት አካባቢ ርቆ እንዲኖር ያደረገው ተፈላጊነቱ መሆኑን ይጠቅሳል። እርሱም ባለው ሙያ የተሻለ ክፍያ ፈልጎ በመምጣቱ አሁን ላይ የተሻለ ሕይወት በመኖሩ ደስተኛ መሆን መቻሉን ገልጿል።
በሀረር ከተማና አካባቢዋ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ የጠቀሰው ዳንኤል፤ ይህም በኢንዱስትሪው ዘርፍ አዳዲስ እውቀቶችን ለማግኘትና አቅምን ለማጎልበት ጥቅም እንዳለው ይገልጻል። ከትልልቅ ማሽኖች ጋር መተዋወቅና በእነርሱ ተጠቅሞ መሥራትም ሌላ መሆኑን ይገልጻል።
በሀገራችን የብረትና ብረት ነክ ማዕድናት እንዳሉም ጠቅሶ፣ እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች አልምተን ጥቅም ላይ ባለማዋላችን ምክንያት ማሽኖችንም፣ ግብዓቶቻቸውም ከውጭ እያመጣን ያለበት ሁኔታ በእጅጉ ያስቆጫል ሲል ተናግሯል።
ሀገራችን ትልልቅ ማሽኖችን የማምረት አቅም ባይኖራትም፣ ማሽኖቹ የሚጠቀሟቸውን ጥሬ እቃዎች ከሀገር ውስጥ ሀብት መጠቀም ቢቻል ጥሩ እንደሆነ ጠቁሟል። አንዳንድ ጊዜ በውጭ ምንዛሪ እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶች ለፋባሪካው ከውጨ የሚመጡ ጥሬ እቃዎች ሲዘገዩ ሥራ ፈትተው የሚቀመጡበት አጋጣሚ እንዳለ ጠቅሷል። ራስን በትምህርት እያበለጸጉ የሀገር ውስጥ ሀብቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ችግሩን መፍታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።
የሀረር ከተማ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤሊያስ የኑስ የሀረር ከተማ ኮሪደር ልማት በመጀመሪያው ዙር ከታሪካዊው ጀጎል ቅርስ መጀመሩን ጠቅሰው፣ በሁለተኛው ዙር ወደ ተለያዩ የከተማዋ ኮሪደሮች እየተስፋፋ መሆኑን አስታውቀዋል። በሁለተኛው ዙር ከ22 ኪ.ሜ በላይ የከተማዋን ዋና ዋና መንገዶች ለማልማት እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል ከተማዋን የማይመጡኑ የእግረኛ እና የመኪና መንገዶች በብዛት እንደነበሩ አስታውሰው፣ የብስክሌት መንገድ የሌላቸው፤ የማረፊያና የመዝናኛ ሥፍራዎች የማይታዩባቸው፤ የመንገድ መብራቶቻቸው ጎልተው የማይታዩባቸው አካባቢዎች በርካታ እንደነበሩም አስታውሰዋል። በኮሪደር ልማቱ እነዚህ ሁሉ ችግሮች እየተፈቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከተማዋ አሁን ውበትና ድምቀት እየተጎናጸፈች መምጣቷን ተናግረዋል። የኮሪዶር ልማቱ የሀረሪ ክልል ሕዝብ፣ መንግሥትና ኢንዱስትሪዎችም ጭምር እየተሳተፉበት እንደሆነም ገልጸዋል።
በተለይም በመንገድ መብራቶቹ ላይ የተገጠሙት አምፑል ማቀፊያዎች የአካባቢውን ባሕልና ወግ የሚገልጹ ሆነው መሠራታቸው ለከተማዋ ሌላ ድምቀት ያጎናጸፉ የፈጠራ ሥራዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። ማስ ኢንጂነሪንግ ኢንተርፕራይዝ እና ሌሎች መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በሚያመርታቸው የመንገድ መብራት ምሰሶዎች ላይ የከተማዋ ወጣቶች የአካባቢውን ማሕበረሰብ የሚገልጹ ዲዛይኖችን እና ቅርጾችን በማውጣት ተሳትፎ ስለማድረጋቸውም ገልጸዋል።
የመንገድ ዳር መብራቶች ሲበላሹ በቀላሉ መጠገን ያስቸግር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኤሊያስ፣ በኮሪደር ልማቱ ተመረትው የተተከሉት የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ግን የመተጣጠፍና የመዘርጋት ባህሪ እንዲኖራቸው ተደርገው የተሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አምፖሎች በሚበላሹ ጊዜ በቀላሉ የታሰሩበትን ብሎን ፈትቶ አናታቸውን ወደ ታች ዝቅ በማድረግ ያለምንም መሰላል ጠግኖ ወደ ነበሩበት መመለስ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የኤሌክትሪክ ዲፓርትመንት ሰራተኞች ከኢንዱስትሪዎቹ ጋር በመተባባር የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል። በመካካለኛ ኢንዱስትሪዎች እየተሰሩ የሚተከሉት የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን ተረክቦ እድሳትም የሚሠራው በማዘጋጃ ቤቱ ስር ያለው የኤሌክትሪክ ሥራ ዘርፍ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ሥራው ከተጠናቀቀና ኮንትራክተሮች ሥራቸውን አስረክብው ከወጡ በኋላ ለቀጣይ የጥገና ሥራ አስተማማኝ የሰለጠነ ኃይል እንዳለም ተናግረዋል። ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ክፍሉ ሁሉ በኮሪደር ልማቱ የተሠሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችም በሙሉ በማዘጋጃ ቤቱ አረንጓዴ ልማት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት እየተመሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሀረር ከተማ እየተከናወነ ካለው አጠቃላይ የኮሪዶር ልማት ለኮንትራክተሮች ተሰጥቶ እየተሠራ ያለው ከ50 በመቶ አይበልጥም ያሉት አቶ ኤሊያስ፣ የተቀሩት የመብራት ምሰሶዎችን፣ አረንጓዴ ልማቶችን፣ መዝናኛ ስፍራዎችን የመሳሰሉትን ወጣቶች ተደራጅተው እንደሚሠሯቸው አስታውቀዋል። ይህም ከፍተኛ የሥራ እድል የፈጠረ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ፊት በሌሊት የመሥራት ልምድ እንዳልነበር ጠቅሰው፤ የኮሪዶር ልማቱ የክልሉን የሥራ ባሕል የቀየረ አዲስ ልምምድ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የኮሪዶር ልማቱ በኢንዱስ ትሪዎችም እየተደገፈ ይገኛል። ኢንዱስትሪዎቹም ለኮሪደር ልማቱ ግብዓት በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል። ሥራው በአመዛኙ በከተማዋ ወጣቶች ተሳትፎ የተሠራ በመሆኑም ወጪ መቀነስ አስችሏል፤ የአካባቢው ወጣቶችም ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ረድቷል።
ሀረር ከተማ በዩኔስኮ የተመዘገቡ አንድ የሚዳሰስና አንድ የማይደስስ ቅርሶች ያሉባት ከተማ መሆኗን የተናገሩት አቶ ኤሊያስ፣ የኮሪዶር ልማቱ ታሪካዊ ቅርሶችን ጠብቆ በመሠራቱ የቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨምር እያደረገ ነው ብለዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም