የወርቅ ልማቱ አበረታች ውጤት – በሲዳማ ክልል

የማዕድን ዘርፍ ለሀገር ምጣኔ ሃብት ያለው ፋይዳ ታሳቢ ተደርጎ የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ ተደርገው ከተያዙት መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል። ዘርፉ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ለማድረግም ሲሰራ ቆይቷል። ይህን ተከትሎም አንዳንድ የማዕድን ሀብቶችን በማልማት ተጠቃሚ መሆን እየተቻለ ነው። ከእነዚህ መካከል የድንጋይ ከሰል አንዱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ይህ ማዕድን በስፋት እየተመረተ ይገኛል። ከድንጋይ ከሰል ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ቅሬታ የሚፈቱ የድንጋይ ከሰል ማጠበያ ፋብሪካዎች እየተተከሉ ወደ ሥራ ገብተዋል።

ለግንባታ ማጠናቀቂያነት ከሚያገለግሉት የኮንስትራክሽን ግብአቶች መካከል መካከል ሴራሚክ አንዱ ነው። ይህ ምርት ሙሉ ለሙሉ ከውጭ ሲመጣ ቆይቷል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሀገሪቱ የሚገኘውን ለሴራሚክ ማምረቻ ግብአት የሚሆን ጥሬ እቃ በመጠቀም ሴራሚክ በስፋት ማምረት ተችሏል።

በአንጻሩ ደግሞ በሀገሪቱ ወርቅ ባብዛኛው በባሕላዊ መንገድ በስፋት ሲመረት የኖረ ቢሆንም፣ የሕገወጦች ሲሳይ ሆኖ ቆይቷል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ሀገሪቱ ከወርቅ ሀብቷ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ አልነበረችም።

ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥት ግብረ ሀይል አቋቁሞ ብዙ ጥረት አርጓል፤ በቅርቡ ሥራ ላይ ያዋለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና እሱን ተከትሎ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ማሻሻያ ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እንዲጨምር አስችለዋል።

ሰሞኑን መንግሥት እንዳስታወቀውም በዚህ 2017 በጀት ዓመት ከማዕድን ዘርፉ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው።

የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ እንዳመለከተው፤ በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት በማዕድን ዘርፉ ኤክስፖርት አንድ ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። ለውጪ ገበያ እየቀረቡ ካሉ ማዕድናት መካከል ወርቅ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። በስምንት ወራት ስድስት ቶን ወርቅ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ፤ 22 ነጥብ 5 ቶን ወርቅ ማቅረብ ተችሏል፤ ይህ ትልቅ ስኬት ነው።

ከወርቅ አምራች ክልሎች ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እየጨመረ ስለመምጣቱም መረጃዎች ይጠቁማሉ። ወርቅ ከሚመረትባቸው ክልሎች አንዱ የሲዳማ ክልል ነው፣ ክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በወርቅ ምርት አበረታች አፈጻጸም ማስመዝገቡን የክልሉ ማዕድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ አስታውቋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን መጩካ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ ክልሉ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ ማዕድናት መካከል አንዱ በሆነው የወርቅ ማዕድን ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራቱ ውጤታማ ሆኗል።

በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወርቅ አምራች ማሕበራት ከሚያመርቱት የወርቅ ምርት 12 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ታቅዶ፤ 10 ነጥብ 2 ኪሎ ግራም ወርቅ ማቅረብ መቻሉን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በዚህም የእቅዱን 85 በመቶ ያህል ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ወርቅ በኮንትሮባንድ መንገድ ወደሌላ አካባቢ እንዳይዘዋወር ለማድረግ ፍቃድ በተሰጣቸው አዘዋዋሪዎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ አዘዋዋሪዎቹ ወርቅ እያሰባሰቡ ለብሔራዊ ባንክ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል። እነዚህ አዘዋዋሪዎች ዘንድሮ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ከፍተኛ የወርቅ ምርት ማስገባት መቻላቸውን ይገልፃሉ።

በመሆኑም በአዘዋዋሪዎች 166 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መግባቱን ጠቅሰው፣ በድምሩ በክልሉ 176 ነጥብ ሁለት ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል።

የወርቅ አዘዋዋሪዎች ወርቅ ከአምራቾች በመግዛት ለብሔራዊ ባንክ እንደሚያቀርቡ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አዘዋዋሪዎቹ ወርቅ በሕገወጥ መንገድ እንዳይዘዋዋር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአዘዋዋሪዎቹ የሚቀርበው ውስን እንደነበር አስታውሰው፤ በ2017 በጀት ዓመት በተለየ መልኩ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረባቸውን አመልክተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በክልሉ ወርቅ የማምረት ፍቃድ የወሰዱ ማሕበራት አብዛኛውን በባሕላዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ ናቸው። ከእነዚህ ባሕላዊ ወርቅ አምራቾች አንዳንዶቹ እስካቫተርና ማጠቢያ ማሽን ማቅረብ ከሚችሉ ባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት የሽርክና ማሕበር መስርተው በዘመናዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱበት ሁኔታም አለ።

በባሕላዊ መንገድ ወርቅ ሲመረትባቸው በነበሩ ቦታዎች ጠለቅ ብሎ በእጅ በመቆፈር ወርቅ ማምረት እንደሚከብድ ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳ ምርት እያነሰ ሲመጣ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ወደ ማምረት መግባት መጀመሩን ተናግረዋል። አምራቾቹ በቴክኖሎጂ ሊያግዟቸው ከሚችሉ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና /70 በ30 በሚባል አሰራር/ የሚሰሩበት ሁነታ እንዳለ ያመላክታሉ። በዚህም 70 በመቶ ያህሉን ገቢ ማሽኑን ላቀረበው (ቴክኖሎጂውን ላቀረበው ባለሀብት እንደሚሰጥ፣ 30 በመቶው ደግሞ ማሕበሩ እንዲጠቀምበት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በዘጠኝ ወራት ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ምርት ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ካደረጉ ዋንኛ ምክንያቶች መካከል አንዱ አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ አግኝተው ማስገባት መቻላቸው ነው። ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ለውጥ የታየበት ነው፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ እንደ ክልል ትኩረት የሚደረግባቸው የማዕድን አይነቶች በአብዛኛው ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ የሚችሉ ማዕድናት ናቸው። ሀገሪቱ ከውጭ በከፍተኛ ዶላር የምታስገባቸውን የኢንዱስትሪ ግብአት ማዕድናትን መተካት የሚችሉ ግብአቶን ማምረትም ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ነው።

ዋና ዳይሬክተሩ የክልሉ የማዕድናት ሀብቶች ገና ብዙ እንዳልተጠኑ ጠቅሰው፣ ለእዚህም ሰፊ የጥናት ሥራዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ አመላክተዋል። ለኢንዱስትሪና ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት በሚውሉ ማዕድናት እና የከበሩ ማዕድናት ላይ ጥናት ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። በክልሉ መንግሥት፣ በጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኢንስትቲዩትና በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሚያደርገው ድጋፍ ሰፊ የጥናት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ የኢንዱስትሪ ግብአት ማዕድናትም እንደሚመረቱ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ በዘጠኝ ወራት አፈጻጸም አራት ሺ ቶን ታልክና ፊልድስፖር የተሰኙ የኢንዱስትሪ ማዕድናት ለማምረት ታቅዶ፤ ሦስት ሺ ስድስት መቶ ሰላሳ ቶን ለገበያ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል። ሌሎች ወደ ምርት ያልገቡ የኢንዱስትሪ ግብአት ማዕድናት እንዳሉም ጠቁመዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ ‹‹ሩታየል›› የሚባል በከፊል የከበረ የሚባል የጌጣጌጥ ማዕድን እንደሚመረትም አስታውቀዋል። በዘጠኝ ወራቱም 70 ቶን የሩታየል ማዕድን ለማምረት ታቅዶ፤ 65 ቶን ተመርቶ ለገበያ መቅረቡን ይገልጻሉ።

ይህ ማዕድን አብዛኛውን ጊዜ ወደ ቻይናና ሕንድ እንደሚላክ ተናግረው፣ እሴት ተጨምሮበት ለጌጣጌጥ የሚውል ማዕድን እንደሆነ ይገልፃሉ። ማዕድኑ እስካሁን ምንም እሴት ሳይጨመርበት በጥሬው ለውጭ ገበያ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፤ እሴት ተጨምሮበት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉም አመላክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ለአካባቢው የኮንስትራክሽን ሥራ ግብዓትነት የሚውሉ ድንጋይና አሸዋን የመሳሳሉ ማዕድናት ላይም ይሰራል። በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዮብ የኮንስትራክሽን ግብዓት ለማቅረብ ታቅዶ፤ ሶስት ሚሊዮን 366 ሺ 689 ሜትሪክ ኪዮብ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ ተችሏል። አፈጻጸሙም ከእቅድ በላይ ነው።

በክልሉ በማዕድን ዘርፉ በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከሮያሊቲ ክፍያ፣ በገቢ ግብርና መሰል ሌሎች ክፍያዎች 11 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 12 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል። የማዕድን ምርት መጠን ከፍ ማለቱ ገቢውም ከፍ እንዲል ምክንያት ሆኗል። ከታቀደው በላይ ወደ ገበያ የቀረቡ ተጨማሪ ምርቶችም እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የማዕድን ሀብቶችን በማልማት ሥራ ላይ 162 ማሕበራት ተሰማርተዋል። አብዛኞቹ ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት የሚውሉ ማዕድናት ለማምረት የተሰማሩ ናቸው።

የማዕድን ዘርፍ በርካታ የሥራ እድሎችን በመፍጠር የሚታወቅ እንደመሆኑም ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠርም ሌላው እየተከናወነ ያለው ተግባር ነው። በዘጠኝ ወራቱ ለአምስት ሺ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ፤ ለአራት ሺ 83 ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል። የሥራ እድሎቹ በክልሉ በማዕድን ዘርፋ የተሰማሩ ማሕበራት የፈጠሯቸው የሥራ እድሎች ናቸው።

የክልሉን ማዕድናት ለይቶ ለማወቅ ጥናቶች እየተደረጉ መሆናቸውን የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጥናቶቹም ለጥናት ተብለው በተለዩ ወረዳዎች ላይ እየተካሄዱ መሆናቸውን ይገልጻሉ። በሦስትና አራት ወረዳዎች ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት የሚውል ግራናይት በሰፊው መገኘቱን ጠቅሰው፤ በዚህ ማዕድን ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች የምርመራ ፍቃዶች መሰጠታቸውንም አስታውቀዋል። በአንድ ወረዳ እምነ በረድ የተገኘበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው፣ በእምነበረድ ልማት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደው ወደ ምርመራ ሥራ የገቡበት ሁኔታ እንዳለም አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ተጨማሪ የወርቅ ቦታዎች በጥናት የተገኙ ቢሆንም፣ ገና ለማሕበራት እንዳልተሰጡ ተናግረዋል። አንዳንዱ የማዕድን አይነት ቀደም ሲል ያለ ቢሆንም፣ በሌሎች ወረዳዎች ላይ በተጨማሪ እየተገኘ እንደሆነም ጠቅሰዋል። በክልሉ ባሉ ሁሉም ማዕድናት ላይ ጥናት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ የማዕድን ሀብቶችን በማልማት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ማሕበራት በክልሉም ሆነ በወረዳ ደረጃ ፍቃድ ይሰጣል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ፍቃድ ከወሰዱ በኋላ ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግም ተናግረዋል። የፍቃድ አሰጣጡም ለኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረት የሚውል ማዕድን ማምረት ከሆነ በወረዳ ደረጃ እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ለሚውሉና ለከበሩ ማዕድናት ልማት ሲሆን ደግሞ በክልል ደረጃ እንደሚሰጥ ያመላክታሉ፡፡

‹‹ማሕበራቱ ሁሉም ሥራ ላይ ያሉ ቢሆኑም በበቂ ደረጃ አቅም ኖሯዋቸው ላያመርቱ ይችላሉ፤ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ማሕበራት ባሕላዊ ደረጃ የሚያመርቱ በመሆናቸው አቅማቸው ያነሰ ነው ›› ይላሉ፡፡

ማዕድን በማምረት ሂደቱ የተጎዱ ቦታዎችን መልሶ ማልማትና አካባቢው የተጠበቀ እንዲሆን የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህም በዘጠኝ ወራት 30 ሄክታር መሬት መልሶ ለማልማት ታቅዶ፤ ብዙ አካባቢ የሚሸፍን ቦታ ላይ መልሶ የማልማት ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል።

በማዕድን ዘርፉ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል አንዱ በክልሉ አንዳንድ በማዕድናት ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶች ቶሎ ወደሥራና ምርት አለመግባት እንደሚታይባቸው ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ አንዳንድ የማምረቻ መሳሪያዎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡ መሆናቸውና የውጭ ምንዛሬውን ማግኘት አለመቻል ወደ ሥራ ለመግባት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ችግር እየሆነ እንደሚገኝ ይገልጻሉ። ለእዚህም ባለፈው ዓመት ግራናይት ለማምረት ፈቃድ ወስደው ግራናይት መቁረጫ ማሽነሪ አለማግኘት ጋር በተያያዘ እስካሁን ሥራ ያልጀመሩ እንዳሉም በአብነት ጠቅሰዋል። በክልሉ በማዕድናት ላይ የሚፈጸም ሕገወጥ ድርጊትን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባይቻልም በአብዛኛው መከላከል ተችሏል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አቶ መስፍን በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ኢንቨስትሮች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰው፣ ‹‹እኛ ጋር ቢሮክራሲ የሚባል የለም፤ ኢንቨስተሩ ገብቶ ቅኝት ማድረግ ይቻላል፤ በማዕድን አዋጁ ከሚከላከሉ ቦታዎች በስተቀር በቀላሉ ወደ ሥራ ይሰማራል ሲሉም አስታውቀዋል። በማዕድን ልማቱ የተሰማሩ ባለሀብቶችን የገጠመ ችግር እንደሌለም ገልጸው፣ ‹‹ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በመጠቀም እና በየኤግዚቢሽኖቹ በመገኘት የክልሉን ማዕድናት እያስተዋወቅን እንገኛለን›› ይላሉ። ወደ ክልሉ መጥተው ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ ባለሀብቶችም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በቀጣይ የክልሉን የማዕድን ሀብቶች ለየቶ ለማወቅ የሚደረጉ ጥናቶች በስፋት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀው፣ ወደ ምርት ያልገቡ ማዕድናትን በማስተዋወቅ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ይደረጋል ብለዋል። በተለይ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብአት ማዕድናትን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You