
የሲዳማ ክልል ከግብርና ልማት አኳያ ሲታይ እንደ ቡና፣ አቮካዶና በመሳሰሉት ምርቶቹ በእጅጉ ይታወቃል:: በልዩ ሁኔታ የምግብ ዋስትናን ሊያረጋግጡ በሚችሉ ግብዓቶች ላይ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም በማስፋፋትም እንዲሁ ይታወቃል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በዶሮ ልማቱ እየታወቀ ይገኛል::
ቡናና አቮካዶ ለውጭ ገበያ በስፋት ከሚያቀርቧቸው ውስጥ ምርቶች መካከል ይጠቀሳሉ:: እንሰትን ጨምሮ በክልሉ በስፋት የሚለሙት የሥራሥር ተክሎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በትኩረት ይሠራባቸዋል::
የክልሉን የ2017 በጀት ዓመት የግብርና እንቅስቃሴ እና ተሞክሮዎች አስመልክቶ ከሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምህሩ ሞኬ ጋር ባደረግነው ቆይታ እንዳሉት፤ የክልሉ ግብርና ቢሮ አራት ቁልፍ ምሰሶዎች ባሏቸው ግቦች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል:: የምግብና የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደ አንድ የትኩረት አቅጣጫ በመያዝ በክልሉ የሥራሥር እና አገዳ ሰብሎች ታሳቢ ተደርገው እየሠራ ነው::
ሁለተኛው ገበያን መሠረት ያደረገ ግብርና ልማትን ማሳደግ መሆኑን ኃላፊው ተናግረው፣ የኤክስፖርት ምርትን ማሳደግ እና ከውጭ የሚገባውን በሀገር ውስጥ ባሉ ምርቶች የመተካት ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል:: ይህ ሥራ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ ማቅረብን እንደሚጠይቅ ኃላፊው አስታውቀዋል:: ቢሮው በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ ግብዓት የሚሆን የግብርና ምርት ማምረትን እንደ ቁልፍ ጉዳይ በመያዝ ይሠራል::
የቢሮ ኃላፊው እንዳስታወቁት፤ ክልሉ የመኸር ልማትን በከፍታ ቦታዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ያካሂዳል:: በዚህም በዋና ዋና ሰብሎች ከ106 ሺህ ሄክታር በላይ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጡ ሰብሎች 32 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለማልማት ታቅዷል:: በአጠቃላይ ከ138 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ በዋና ዋና ሰብሎች ሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል፤ በሥራ ሥር ደግሞ ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው::
በመሬት ስፋትም ሆነ በምርት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በክልሉ የነበረው የዝናብ መጠን እና ሥርጭት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መልካም እንደነበር ጠቁመዋል:: 266 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ የእቅዱን 94 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸው፣ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር አለማጋጠሙን ገልጸዋል::
የምርጥ ዘር አቅርቦትን በተመለከተ 54ሺህ የሚጠጋ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ በምርጥ ዘር በዋናነት 24ሺህ እንዲሁም በተመሰከረለት ከ78 ሺህ ኩንታል በላይ ማቅረብ ተችሏል:: በመሆኑም በቴክኖሎጂና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም፣ በምርጥ ዘርና በማዳበሪያ አቅርቦት ጥሩ አፈጻጸም መታየቱን ጠቅሰው፣ የምርት ወቅቱ የተሻለ ምርት የተገኘበት ነው ሲሉ ተናግረዋል::
ሁለተኛው ምዕራፍ የዘመናዊ ግብርና ሥራ ሲሆን፣ በክልሉ በበጋ መስኖ ልማት ሆርቲካልቸር ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ሲሉ ገልጸዋል:: ክልሉ የመሬት ጥበት እንዳለበት የቢሮ ኃላፊው አመልክተው፣ ሌሎች ክልሎች በዚህ ወቅት ስንዴ ላይ ትኩረት ሲያደርጉ በክልሉ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል::
በዚህም በሁለት ዙር ከ72 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እቅድ የተያዘ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር 59 ሺህ ሄክታር በማቀድ ወደ 61 ሺህ ሄክታር ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል:: በዚህም ርምጃ በመጀመሪያው ዙር 13 ሚሊዮን ኩንታል በሁለተኛው ዙር 3 ሚሊዮን ኩንታል በአጠቃላይ 16 ሚሊዮን ኩንታል ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅሰው፣ 10 ሚሊዮን ኩንታል መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል::
በዚህ ዓመት የተሻለ የመስኖ ክላስተር መፈጠሩንም ገልጸዋል:: ለዚህም የክልሉን የውሃ አማራጮች እና ትናንሽ ምንጮችን በመጠቀም እና ከሁለት ሺህ በላይ የውሃ ፓምፖችን በማቅረብ የማልማት ሥራ ተሠርቷል ሲሉ አብራርተዋል::
ድርቅ በብዛት በሚያጠቃቸው እንዲሁም አነስተኛ ዝናብ በሚጥልባቸው አካባቢዎች 28 የሚጠጉ በዘመናዊ መንገድ የተገነቡ መስኖዎችን በመፍጠር የተሻለ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል::
በዘር ወቅት የሚያጋጥም የዝናብ ሥርጭት መቀነስና በቂ ውሀ አለመኖር በምርት መጠን ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተናግረው፣ የክልሉ መንግስት ይህንን በማስጠናት በአንድ ወረዳ ሶስት ቀበሌዎች ግማሽ ቢሊዮን ብር በመመደብ ሶስት ጥልቅ ውሃ ጉድጓዶችን አስቆፍሯል ብለዋል::
በዚህም ከ800 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እስከ አሁን 442 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት መቻሉን ገልጸዋል:: ክልሉ ሌሎች አማራጮች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ ደግሞ በጀት በመመደብና ዘመናዊ መስኖዎችን በማሠራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረው፣ በዚህም የበለጠ ውጤታማ መሆን እየተቻለ መሆኑን ገልጸዋል::
ክልሉ በአሁኑ ወቅት በበልግ ሥራ ላይ ትኩረት ማድረጉን ተናግረው፣ በዚህም በዋናነት በዋና ዋና ሰብሎችና ሥራ ሥሮች ልማት ከ140 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት አቅዶ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል:: በዚህ ልማት ትልቁን ድርሻ የሚይዘው በቆሎ መሆኑን ተናግረው፣ በ65 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል:: በአሁኑ ወቅትም ከ60 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማሳ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል::
የክልሉ የበልግ ልማት ሥራ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው አስታውቀዋል:: በምርጥ ዘር አቅርቦት በኩልም 16ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 13ሺህ ኩንታል ማቅረብ መቻሉን ጠቁመዋል:: በዚህም የእቅዱን ከ80 በመቶ በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል::
ክልሉ ከዚህ ቀደም ምርጥ ዘር ከሌሎች አካባቢዎች ገዝቶ እንደሚያቀርብ ያስታወሱት አቶ መምህሩ፣ በአሁኑ ወቅት ግን የክልሉን አቅም በመጠቀም 40 በመቶ ድረስ የምርጥ ዘር በራሱ መሸፈን መቻሉን አስታውቀዋል::
እሳቸው እንዳብራሩት:: ክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚሠራባቸው ዘርፎች መካከል የሥራ ሥር ምርቶች ልማትን ማሳደግ አንዱ ነው:: ይህንንም በዋና ዋና ሰብሎችና የሥራሥር ልማቶች እንዲለማ ከታቀደው 140 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ድንች በ13ሺህ ሄክታር ላይ ለማልማት ታቅዶ በ10ሺህ ሄክታር ላይ እንዲለማ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል::
ለእዚህም 20ሺህ ኩንታል የድንች ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ 11ሺህ ኩንታል ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን አመልክተዋል:: የማሳ ዝግጅቱም ሆነ ማሳውን በዘር የመሸፈን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል::
እንደ አቶ መምህሩ ገለጻ፤ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው መካከል የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ማረጋገጥ አንዱ ሲሆን፣ በክልሉ በስፋት በሚታወቀው የእንሰት ልማት ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል::
እንሰት ድርቅን በመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ተክል መሆኑን ጠቅሰው፣ ልማቱን ተደራሽ ማድረግ ላይ እንደሚሠራ ጠቁመዋል:: ክልሉ ለእዚህ የሚያስፈልጉ ምርጥ ዝርያዎችን በመለየት እና በዚያው አካባቢ በማባዛት ወደሌሎች አካባቢዎች እንዲሰራጩ የማድረግ ሥራን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከዚህም አንጻር 136 ሚሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን በአርሶ አደሩ ማሳ ባለፈው ዓመት ማባዛት የተቻለ ሲሆን፣ 60 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በማዘጋጀትም የተከላ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል:: ድርቅ የሚያጠቃቸው እና እንሰት በስፋት የማይገኝባቸው ቦታዎች ላይ ምቹ የሆነ የእንሰት ዝርያን በመምረጥ የማባዛት ሥራ ከመንግሥት፣ ከግለሰቦች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደ ስትራቴጂ ተወስዶ እየተሠራ ይገኛል::
የዝናብ እጥረት በሚፈጠርበት ጊዜ ሰብሎች የመጥፋት አደጋ ይገጥማቸዋል ያሉት ኃላፊው፣ የእንሰት ዝርያዎችን ወደ እነዚህ አካባቢዎች በማስፋት ሥራ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል::
በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን አቅጣጫ ሊያሳኩ ይችላሉ ተብለው በተለዩ እንደ የድንች፣ ስኳር ድንች፣ ገብስ፣ በቆሎ እና እንሰት ሰብሎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመኸር እና በበጋ መስኖ እየተሠራባቸው መሆኑንም አቶ መምህሩ ጠቁመዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ገበያን ትኩረት በማድረግ ከሚሠሩና ክልሉ ከሚታወቅባቸው ሰብሎች መካከል ቡና እና ፍራፍሬ ይጠቀሳሉ:: በክልሉ ቡና በ172 ሺህ ሄክታር የቡና ሰብል ያለ ላይ እየለማ ይገኛል:: ከዚህ ውስጥ 142 ሺህ ሄክታር የሚሆነው ምርት የሚሰጥ ነው::
በ2017 በጀት ዓመት 40 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 37ሺህ ቶን ቡና የመሰብሰብ ሥራ ተሠርቷል:: ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ምርት ሲሆን፣ በቀጣይም የተያዘውን እቅዱ ማሳካት ይቻላል::
በምርታማነት ረገድ በሄክታር ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ኩንታል የነበረውን የቡና ምርት ወደ 11 ኩንታል ማሳደግ ተችሏል:: በዚህም ክልሉ የቡና ምርታማነትን ማሻሻል የሚችሉ ፓኬጆችን በመጠቀም ላይ ይገኛል:: በአሁን የቡና ማደስ እና የመትከል ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ በዓመት ውስጥ በማይገባ ቦታ የሚገኙ ባሕር ዛፎችን በማስወገድና ያረጁ የቡና ዛፎችን በመንቀል ከ6500 ሄክታር በላይ ተጨማሪ መሬት ማግኘት ተችሏል::
የቡና ምርትን ለማሳደግ ከሚሠሩ ሥራዎች ችግኞችን ማብዛት አንዱ ሲሆን፣ 132 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ 130 ሚሊዮን ችግኞች ማዘጋጀት ተችሏል፤ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የመትከል ሥራ ይከናወናል::
ክልሉ ከቡና ቀጥሎ አቮካዶ ለውጭ ገበያ በስፋት ያቀርባል:: በክልሉ ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ ነባር የአቮካዶ ዛፎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ አዳዲስ ችግኞች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል::
በአብዛኛው ክልሉ የቡናና አቮካዶ ለማምረት ምቹ መሆኑን አመልክተዋል:: በክልሉ ለእዚህ ልማት የሚሆን ሰፊ እና ነፃ መሬት በስፋት እንደሌለም ተናግረው፣ በዋናነት በተቋማት የሚገኙ ነፃ ቦታዎችን በመጠቀም ልማቱን በማስፋት ምርታማነቱን ለማሳደግ እንደሚሠራ ገልጸዋል::
10ሺህ ቶን አቮካዶ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማቅረብ ታቅዶ፣ በአንድ ዙር ብቻ 3500 በላይ ቶን ለማቅረብ ተችሏል ሲሉ ጠቅሰው፣ ከዚህም አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል ብለዋል:: አቮካዶ ከአግሮ ኢንዱስትሪዎች ባሻገር ወደ ሌሎች ቦታዎች እንደሚወሰድ ጠቅሰው፣ ይህንን አጠናክሮ የመቀጠል ሥራ በስፋት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል::
አቶ መምህሩ ክልሉ ቦሎቄም ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል:: ክልሉ በእነዚህ ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ላይ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል:: በአሁኑ ወቅትም አኩሪ አተርን ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት አድርጎ በመውሰድ በስፋት እየሠራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት የቤተሰብ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የቤተሰብ ብልፅግና ፓኬጅን ቀርጾ ጥናት በማድረግ የምግብ ዋስትናን ሊያረጋግጡ የሚችሉ 19 የእርሻ ኢንሼቲቮችን ቀርጾ እየሠራ ነው:: የቤተሰብ ፓኬጅ እያንዳንዱ ቤተሰብ ባለው የመሬት ልክ በአግሮ ኢኮሎጂ እና ባለው አቅም መልማት ታሳቢ በማድረግ እነዚህ 19 ፓኬጆችን ለይቶ ይሠራል::
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት አንዱ እቅድ በማድረግ በአረንጓዴ ዐሻራ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸው፣ ፍራፍሬን፣ ለምግብነት የሚውሉ፣ ለኤክስፖርት እንዲሁም ለእንስሳት መኖነት የሚውሉ ችግኞች በማዘጋጀት ላይ ትኩረት በማድረግ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል:: ችግኞቹ የደን ሽፋንን ለመጨመር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልም እንዲሁም የክልሉን የተፋሰስ ልማት ሥራ እንደሚያሳድጉት ግምት ውስጥ በማስገባት በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል:: በዚህ ውስጥም ከፍተኛ የሕዝብ ንቅናቄ የታየበት መሆኑን አስታውቀዋል::
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም