በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አይነታቸውም ሆነ ቁጥራቸው ብዙ ሲሆኑ፤ ከነዚህም መካከል አንዱ፤ ያለዕድሜ ጋብቻ ነው፡፡ ይህ የታዳጊ ሴቶችን ሰብዓዊ መብት የጣሰ ተግባር በአገራችን ሲሰማ አዲስ አይደለም፡፡ ስለ መፍትሄው ሲመከርበትም እንደዛው፤ ይሁን እንጂ፤ ችግሩ እልባት ሲያገኝና የታዳጊ ሴቶች መብት ሲከበር አይታይም፡፡ እንዲያውም እየባሰበት ካልሆነ በስተቀር፤
ይህንኑ አቢይ ጉዳይ በተመለከተ ባለፈው ሰሞን ከዚሁ አዲስ አበባ በሚገኘው ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል አንድ ዝግጅት ተካሂዷል፡፡ በዝግጅቱም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን የሴቶች፣ ህፃናት ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ፀጋይ ይህን ዘርፈ ብዙ የታዳጊ ሴቶች ችግር ለመፍታት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ፤ ሆኖም ግን ጉዳዩ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግሩን ለመቅረፍ መረባረብ እንደሚገባቸው በማሳሰብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዩኒስኮ ተወካይ ወይዘሮ ሻሊኒ ቡጋያ በሴቶች፣ በተለይም በታዳጊ ሴቶች ፆታዊ ጥቃት፣ በትምህርት ተሳትፎና በመሳሰሉት ጉዳዮች ዙሪያ ጠንክሮ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከአስር ታዳጊ ሴቶች መካከል አራቱ ለያለ ዕድሜ ጋብቻ የተጋለጡ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ ይህንን ችግር በመሰረታዊነት ለመፍታትም በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላት ከፍተኛውን ድርሻ ሊጫወቱ የግድ ነው፡፡
ሌላው ከሴቶች መብት ጋር ተያይዞ የሚነሳው የሥርዓተ-ፆታ ዕኩልነት ጉዳይ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓትም በስፋት እያነጋገረ ይገኛል፡፡
ከሥርዓተ-ፆታ ዕኩልነት ጋር በተያያዘ፤ ዓለማችን የሴቶች መብት አይከበሩባትም፤ በወንዶች የበላይነት ቁጥጥር ስር ውላለች በሚል ለዘመናት ስትወቀስ መስማት አዲስ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያም የዚሁ አካል ሆና ቆይታለች፡፡
ይሁን እንጂ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በተቋቋመው አዲስ ካቢኔ ውስጥ ከላይ የተጠቀሰው ወቀሳ ቀርቷል፡፡ “ያማ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጥቶ” እንዲሉ፤ በምትኩም የሥርዓተ-ፆታ ዕኩልነትን ከማስፈን አንፃር ኢትዮጵያ የዓለም ምሣሌ በመሆን ላይ ትገኛለች፡፡
ይህ ጥቅምት 16 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የሰየሙት አዲስ ካቢኔ የሚኒስትሮቹን ቁጥር ዕኩል (አሥር ወንድ፤ አሥር ሴት) በማድረጉ በአገራችን ታሪክ ቀዳሚ ነውና በተለይ ሊጠቀስ ግድ ብሎታል፡፡ በተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ዘንድ ከዕለቱ ጀምሮ ሳያቋርጥ ውዳሴው እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ይህ በመንግሥት የተጀመረው የሥርዓተ-ፆታ ዕኩልነትን እውን ማድረግና ሴቶችን ወደ ፖለቲካ ተሳትፎና መሪነት ደረጃ የማምጣቱ ጉዳይ በራሳቸው በሴቶቹ ላይ የፈጠረውና እየፈጠረ ያለው መነቃቃት በቀላሉ የሚታይ ሆኖ አልተገኘም፡፡
ሰሞኑን የቢቢሲ አማርኛው ፕሮግራም ከእንግዲህ “ሴቶችን የማያሳትፉ ተቃዋሚዎችን (የፖለቲካ ፓርቲዎችን) እንቃወማለን” የሚሉ የሕዝብ አስተያየቶችን ማስነበቡም ሆነ፤ አቶ ሞሼ ሰሙ፤ ‹‹በዚህ የአደረጃጀትና የካቢኔ ለውጥ ውስጥ ( መንግሥት) ለብሔር ወንበር ከማከፋፈል መውጣቱ የሚበረታታ ነገር ነው፡፡ ሌላው መሰረታዊ ነገር የሴቶች ሚና ከፍ ማለቱ ነው፡፡ ዓለምንም ያነጋገረ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሕዝቧ ከ50 በመቶ በላይ ሴቶችን ይዛ፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሰፊው እያንቀሳቀሱ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሆነው እያለ የተሳትፏቸው ጉዳይ ግን ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቶ ነበር፡፡ አሁን ለዚህ ዋጋ ሰጥቶ ሚናቸውን ለማሳደግ የተወሰደው እርምጃ ጠቃሚ ነው›› በማለት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ መግለፃቸው ለዚህ አባባል ዋቢ ነው፡፡
ቢቢሲ ከላይ በጠቀስነው ጽሑፉ እንደዘገበው ሕዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር የምርጫ ሥርዓትን ስለማሻሻል የመከሩበት መድረክ በአዛውንት ወንድ ፖለቲከኞች የተሞላ መሆኑ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። ክስተቱ “ወጣት ሴቶችና ወጣት ወንዶች በተቃውሞ የፖለቲካ ተሳትፎ ቦታቸው የት ነው?” የሚል መሰረታዊ ጥያቄ በሕብረተሰቡ ዘንድ ለኩሷል። “ሴቶችን የማያሳትፉ ተቃዋሚዎችን እንቃወማለን” የሚሉ አስተያየቶችም ከመደበኛው አልፈው በማሕበራዊ ሚዲያም እንዲንፀባርቁ ምክንያት ሆኗል።
“ሴቶችን የማያሳትፉ ተቃዋሚዎችን እንቃወማለን” በማለት ድምፃቸውን ካሰሙት መካከል አንዷና የሥርዓተ-ፆታና የሕግ አማካሪ የሆነችው ህሊና ብርሃኑ፤ “ያለውን ሥርዓት ክፍተትና ጉድለት እሞላለሁ ብሎ የተነሳ ተቃዋሚ ሴቶችንና ወጣቶችን አካታች አለመሆኑ ተቃርኖ አለው፤” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። “አንድን ሥርዓት የተሻለ አደርጋለሁ ብሎ አካታች አለመሆን፣ ፍትህና መፍትሄ ሳይዙ መምጣት ዕርስ በዕርሱ የሚጋጭ ነገር ነው። አካታች ሳይሆኑ ተቃዋሚ መሆን አይቻልም፡፡ ሴቶችን፤ በተለይም ወጣት ሴቶችን ሳይዙ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር የሚቻል አይደለም።” ማለቷንም ቢቢሲ በዘግባው አመልክቷል፡፡
ይህ ጉዳይ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ወገን፤ በተለይም በተቃውሞ ፖለቲካው መስመር የተሰማሩ ሁሉ ሊያስቡበት የሚገባ መሰረታዊ ጉዳይ ነው በማለት አስተያየታቸውን በማህበራዊ ሚዲያው የሰነዘሩ በርካቶች ናቸው፡፡
የሥርዓተ-ፆታና የሕግ አማካሪዋ ህሊና ጉዳዩን በቀላሉ ያየችው አትመስልም፤ “አካታች ያልሆነ፣ ብዙኃኑን የማይጨምር ፖለቲካ በብሔር ቢሆን ኖሮ ያስነውር ነበር” የምትለው ህሊና “ወጣቱ አገር ተረካቢ ነው” እንዲሁም “የሴቶች ተሳትፎና ወደ አመራርነት መምጣት ቀስ በቀስ ይስተካከላል” የሚለውን አትቀበለውም። ለዚህም ምክንያቷን ስትገልፅ “ወጣት የነገ መሪ ነው፤ ወጣት የሆንኩት፣ ሰው የሆንኩትና ጉዳይ ያለኝ ዛሬ ነው። ስለዚህ የዛሬ እንጂ የወደፊት አይደለሁም” በማለት ሃሳቧን ታጠናክራለች። እንደ ህሊና አስተያየት ቀስ ብሎ ነገር የለም፤ ለመደለል ካልሆነ በስተቀር።
“ምህዳሩ በጣም ገዳቢና ነፃነት የሌለው ነበር። እስከ ዛሬ በተቃውሞ ያሉት በስልሳዎቹ ወጥተው ደፍረው መናገር የቻሉ ናቸው። ወጣቱ ግን የሴቶች፣ የወጣት ማህበርና ወጣት ሊግ እየተባለ ታፍኖ የቆየ ነው። የፖለቲካው ሴቶችን አሳታፊ አለመሆን የአባታዊ ሥርዓት ውጤት” ነው የሚሉት ደግሞ የአረና ፓርቲ መስራች የሆኑት የቀድሞ የህወሓት ታጋይ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ ናቸው። ወ/ሮ አረጋሽ ሴቶች ለራሳቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅም በመደራጀት ይህን እውነታ መቀየር እንዳለባቸው ይመከራሉ። በመሆኑም የአሁኖቹ ሴት አመራሮች ይህን ታሪክ ይቀይራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “በመጨረሻም ፍትህ ተፈፀመ” በማለት ሂደቱን ካደነቁ በኋላ “አሁን የተሾሙት ሴቶች ከዚህ በኋላ የሰውን ትኩረት በእጅጉ ይስባሉ፡፡ ሰዎች ከእነሱ ጉድፍ ለመፈለግ ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ አሁን ከሌላው ጊዜ በተለየ የሰዎች መነፅር ከፍተኛ ሊሆን ስለሚችል በዚህ በኩልም ዝግጁ መሆን አለባቸው “ሲሉ ተመራጮችን አሳስበዋል። በቅርቡ በተደረገው የፓርላማ ሴት ተወካዮች ውይይት ላይም የመወያያ ርዕሰ-ጉዳይ የነበረው ይኸው ሲሆን፣ የተደረሰበትም ስምምነት ሴቶቹ ተመራጮች ጠንክረው መሥራት ያለባቸው መሆኑን ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አስተዳደር ኢትዮጵያ እየተቀየረች ትመስላለች። ሴቶች ከተለመደውና ባህላዊ ከሆነው በቤተሰብ ላይ የተንጠለጠለን ኃላፊነት በማለፍ ከፍተኛ በሚባሉ መንግሥታዊ ቦታዎች እየታዩ ነው፤ የሚለው የቢቢሲ ዘገባ የሚከተለውን መረጃ በማጠናከሪያነት ያቀርባል፤
@ 25% የሚሆኑት ሴቶች ትልልቅ ውሣኔዎችን ለባሎቻቸው አሳልፈው ይሰጣሉ።
@ 50% የሚሆኑት ሴቶች በትዳር አጋራቸው ጥቃት ይደርስባቸዋል።
@ ከ20% በታች የሚሆኑት ሴቶች ብቻ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ይከታተላሉ።
@ ከ40% በላይ የሚሆኑት ደግሞ 18 ዓመት ሳይሞላቸው ወደ ትዳር ይገባሉ።
ከዚህ ሁሉ ችግር አንፃር፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ሴቶችን ወደ ከፍተኛ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች የማምጣት ውሣኔ በብዙዎች ዘንድ ይሁንታ አግኝቷል፤ በማለት አስተያየቱን አስፍሯል።
ባለፋት ሁለት አስርት ዓመታት በተከተልነው ትክክለኛ የልማት መስመር ሴቶች በተፈለገው መንገድ ባይሆንም በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የሚገልጡት የአይጋፎረምዶትኮም ፀሐፊ ፍስሀ መረሳ ደግሞ በተደረገው የፆታ ማመጣጠን ብዙም የረኩ አይመስሉም። ይህንንም አሁን በለውጥ ስም በቅርቡ 50% የሚሆኑ ሴቶች ወደ ከፍተኛ ሥልጣን እንዲመጡ መደረጉ ለሴቶች ይጠቅማቸዋል? ወይስ ለጊዜው ነው? እነሱን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ፤ የመጨረሻ ውጤቱ ግን ሴቶችን ሊጎዳ የሚችል አካሄድ ነው የሚለውን በትክክል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ሴቶች ተጠቅመዋል ወይም አልተጠቀሙም ልንል የምንችለው በአብዛኛው በእርሻ የተመሰረተ ኑሮ የሚገፉ ሴት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፤ እንዲሁም በከተማ የሚኖሩ ሴቶችን ህይወት በመሰረታዊ ደረጃ የመቀየር ጉዳይ እንጂ የ10 ካቢኔ አባላት ወደ ሥልጣን የመምጣት አለመምጣት ጉዳይ አይደለም ሲሉ ተችተውታል፡፡
የሕግ ባለሙያዋ ህሊና ግን በዚህ ሃሳብ አትስማማም፤ ለዚህም “እነዚህ ሴቶች ወደ ሥልጣን የመጡት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁንታ ስላገኙ ወይም በሥርዓቱ ችሮታ ሳይሆን፤ ለቦታው የሚመጥን ከፍተኛ ብቃት ስላላቸውና ጠንካራ ሠራተኞች ስለሆኑ ነው” ስትል ሃሳቡን ትሞግታለች።
ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ የተደረገውን የፆታ ማመጣጠን በማድነቅ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “አዳዲሶቹን ሴት ሚኒስትሮች ወደ ሥልጣን በማምጣት ሴት መምራት አትችልም የሚለውን የተዛባ አባባል ከመሰረቱ ይንደዋል” በማለት በዕለቱ የተናገሩትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ሁላችንም ሞቅ ብቻ ሳይሆን፣ ሞቅ-ደመቅ አድርገን “ሹመት ያዳብር” ያልንላቸው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ከተመረጡ 100 ሴት ልሂቃን መካከል አንዷ፤ ከአፍሪካም ብቸኛዋ ጥቁር ሆነው መመረጣቸው አንዱ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥንካሬ ማሳያ ነው። ይህን የሰሙ አንጋፋዎች “የምኒልኳ ንግሥት ጣይቱ ፍሬ አፈራች” ሲሉ መደመጣቸው ተሰምቷል።
ባጠቃላይ፤ በዚህ ሹመት አጠቃላይ የሴቶች ዕኩልነት ጥያቄ በቂ መልስ አግኝቷል ማለት አይደለም። በመሆኑም ወደ ሥልጣን የመጡት ሴት አመራሮችም ሆኑ ሌሎች የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በዘላቂነት እንዲረጋገጥ፤ ሌሎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችንም ከማስቀረት አኳያ ጠንክረው መሥራት ያለባቸው ስለመሆኑ የብዙዎች እምነት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ የሴቶችን እኩልነት፤ በተለይም የታዳጊ ሴቶችን ፆታዊ ጥቃት የማስወገዱ፣ የትምህርት ተሳትፎን የማረጋገጡና የመሳሰሉትን ሰብዓዊ መብቶች መሬት ላይ የማውረዱ ጉዳይ ተግባራዊ ካልሆነ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ሴቶችን ወደ ከፍተኛ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች የማምጣት ውሣኔ ብቻውን አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ ከመሆን አይድንም፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
ግርማ