ኢትዮጵያ የአስራ ሶስት ወር ፀጋ ባለቤት ፣ የራሷ ፊደል ያላት፣ የራሷ የዘመን መለወጫ የምትከተል ሀገር ናት ። ይሄ ልዩ መታወቂያዋ ለእኛም መኩሪያችን እና መለያችን ነው። እንዲሁም ደግሞ የተለያዩ ብሄሮች የራሳቸው የዘመን መቁጠሪያ እና የዘመን መለወጫ በዓላት አሏቸው። ይሄም መስቀልን ተከትሎ ወይም የክረምቱን መውጣትና የበጋውን የአደይ አበባ ወር መግባት መነሻ በማድረግ የሚከተሉት አቆጣጠር ነው።
የሲዳማ ፍቼ ጨምበላላ፣ የሀዲያ ያሆዴ፣ የወላይታው ጊፋታ እንዲሁም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ ጋሪ ዎሪ ተጠቃሾች የዘመን መለወጫ በዓላት ናቸው። የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ሁሉም በጋራ የሚጠቀምበት ቢሆንም በየብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ እንደሚከበርና መሰረቱም ከዋክብትና ጨረቃ ጋር የተያያዘ መሆኑን የነገሩን የተለያዩ ምሁራኖች ናቸው።
የሲዳማ ዞን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገነነ አበራ እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ የበርካቶች ብሔሮች ብሔረሰቦች መኖሪያ ነች። በዚህም እንደአገር ከሚከበረው የዘመን መለወጫ በተጨማሪ ብሔረሰቡ በሚያምንበትና ዘመን ተለወጠ በሚልበት ቀናትንና ወራትን እንዲሁም ዓመታትን በመከፋፈል የራሱ ስያሜ ሰጥቶ ያከብረዋል። ለዚህም በሲዳማዎች ዘንድ ‹‹ፊቼ ጫምባላላ›› አንዱ ነው።
ፊቼ ጫምበለላ በከዋክብት ዑደት ላይ የተመሠረተና የተቀመረ ሲሆን፤ የከዋክብት ቀማሪዎቹ ‹‹አያንቶዎች›› ይባላሉ። ብርሃናቱን፣ ፀሐይና ጨረቃን እንዲሁም ከዋክብትን በመቁጠር በዓሉ መቼ ላይ እንደሚያርፍ፣ ምን ዓይነት ዘመን እንደሚሆንና መቼ ከምን መጠበቅ እንደሚገባም ይናገራሉ። ከዚያ የእምነቱ አባቶች ለብሔረሰቡ ያሰሙና ህዝቡ ተዘጋጅቶ በዓሉን እንደሚያከብር ያስረዳሉ።
ፍጥረታት የተፈጠሩት ስለ አራት ነገሮች መሆኑን በኦሪት ዘፍጥረት እንደተቀመጠ የሚናገሩት አቶ ገነነ፤ ለምልክቶችና ለዘመኖች፣ ለዕለታትና ለዓመታት በማለት ትውፊታዊውና ኦሪታዊው መጽሐፍ ስለ ብርሃናት ተፈጥሮ ይገልጻል። ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ በሰማያት ብርሃናት ተደረጉ ይላል። ይህ ማለት ደግሞ ታላቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፣ ታናሹ ብርሃን በማታ እንዲገዛ ከዋክብትንም ፈጠረ። ስለሆነም የሃይማኖት አባቶችም ይህንን መሰረት አድርገው ዘመን ተለወጠ ይላሉ። የሲዳማ ህዝብም የእምነቱን አባቶች ተከትሎ የዘመን መለወጫ በዓል እንደሚያከብሩ ይገልጻሉ።
ከክዋክብቱ መካከል አውራ የሆነችው ኮከብ ከጨረቃ መቅደሟን ሲያረጋግጡ ፊቼ በቀጣይ ቀናት ውስጥ ባለው የቃዋዶ ዕለት እንደሚውል ይናገራሉ። ስለዚህም ይህ ቀመር ነው ህዝቡ በየዓመቱ ዘመን መለወጫውን እንዲያከብር ያደረገው ይላሉ።
ጊፋታ ማለት መሻገር ማለት ሲሆን፤ ከዓመት ወደ ዓመት፣ ከጥላቻ ወደ ዕርቅ፣ ከመጥፎ ሥራ ወደ ጥሩ ሥራ መሻገርን የሚያመላክት ቃል እንደሆነ የሚያነሱት ደግሞ በወላይታ ስፖርት መምሪያ ውስጥ የባህልና ስፖርት የኪነት ቡድን አስተባባሪና የባህል ሙዚቀኛ የሆኑት አቶ አክሊሉ አዶሌ ናቸው። እርሳቸው እንደገለጹት፤ ጊፋታ ማለት መስከረም ወር ማለት ሲሆን፤ የመጀመሪያ፣ ታላቅ፣ በኩር እየተባለም ይጠራል።
ጊፋታ ወርን ለማግኘት በከዋክብት ቆጣሪዎች ዘንድ እንደሚባለው፤ ሦስት የገበያ ሳምንታት ካለፉ በኋላ ነው። ስለዚህም ከአንድ ጨረቃ ወይም አጊላ በኋላ አንድ ተብሎ ይቆጠርና 12ኛ ወር ላይ ይደርሳል። ከዚያ መልሶ አንድ ሲባል የጊፋታ ወርን አራተኛ የገበያ ሳምንትን እናገኛለን። እናም የሁሉ ነገር መታደስን ለማመልከት ወይም ከጭለማው ወደ ብርሃኑ ተሸጋገርን ለማለት ጊፋታን እንደዘመን መለወጫ ተደርጎ ይከበራል።
የጊፋታ ሳምንት የሚባለው ሁልጊዜ መስከረም ወር በገባ ከ14 እስከ 20 ቀን ያለው ጊዜ ሲሆን፤ እሑድ ሲደርስ ዮዮ ጊፋታ እየተባለ ብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ በዓሉን የሚያከብርበት እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አክሊሉ፤ አንድ አጊና አንድ ወር እንደማለትም መሆኑን ይናገራሉ። ስለሆነም በጨረቃ ቆጠራ የሚታወቁ አባቶች ገበያውን፣ወሩን ቆጥረው ጊፋታ የሚውልበትን ጊዜ ይወስናሉ።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዳይሬክተርና የብሔረሰቡ ባህልና ቋንቋ አጥኚው አቶ ናሲሳ ውበቴ በበኩላቸው፤ ከዘመን መለወጫው ስያሜ ስንነሳ ጋሪ ማለት ነጋ የሚለውን ይይዛል። ይህም ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን፤ ከክረምት ወደ በጋና ለምለሙ ወቅት ተዘዋወርን የሚለውን ይገልጻል። የሚጠገብበት ወቅት ደረሰልን፤ተስፋን ተቀዳጀን ለማለት በመስከረም ወር ይህ የዘመን መለወጫ እንዲውል ተደርጓል ይላሉ።
የሺናሻዎች ዘመን መለወጫ ‹‹ጋሪ ዎሮ›› እንደሌሎቹ ብሔረሰቦች ሁሉ በጨረቃ አቆጣጠር አማካኝነት ጊዜው የሚቀመር እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ናሲሳ፤ ከዋክብትንና ጨረቃን የሚቆጥሩ አባቶች ለጊዜው ቀመር ያወጣሉ።ለምሳሌ ከነሀሴ እስከ መስከረም ያለውን ጨረቃ በባህሉ አዋቂዎች ‹‹ፁኡሚ›› እያሉ ይጠሩታል። ይህ ማለት ደግሞ እኝኝ ይብላ፣ ጭጋጋማ፣ ዝናብ የማይለየው ማለት ነው። ከመስቀል በኋላ የሚመጣውን ደግሞ ጋሪ ያሉት ብርሃን፣ ፀሐይ፣ለምለም ምድር የሚታይበትና ደስታ የሚሰፍንበት እንዲሁም ዘመድ ከዘመድ ጋር የሚገናኝበት በመሆኑ ጋሮ ወይም የብርሃን ወር እንዳሉት ይናገራሉ።
በሀድያ ዞን በባህልና ቱሪዝም መምሪያ
የቋንቋና ሥነጥበብ ስራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት ኤርሲዶ አንተሴ እንደሚናገሩት፤ ሁሉም በየብሄረሰቡ የሚያከብሩት የዘመን መለወጫዎች ቀናቸው የሚቀመረው በከዋክብትና ጨረቃ ቆጠራ ነው። የሀድያ ብሔረሰብም እንዲሁ የዘመን ቅመራው ኮከብና ጨረቃን መሰረት በማድረግ የሚወሰን ሲሆን፤ ዘመን መለወጫው ያሆዴ መስቀላ ይባላል።
እንደ አቶ ኤርሶዴ ገለጻ፤ ያሆዴ እንደሌሎቹ ብሔረሰቦች የብሔሩ ዘመን መለወጫ ጊዜ ቢሆንም ለየት የሚያደርገው የራሱ ባህሪ አለው። ይኸውም አዲስ ዓመት የሚባለው መስከረም 16 ነው። ከዚያ ውጪ መሆን አይችልም ። ለዚህ ምክንያቱ የጨረቃና ፀሐይ ሙሉ ለሙሉ መታየት ነው። ስለዚህም የማንኛውም እድሜ ሲቆጠር ስንት ያሆዴ ሆነህ በሚል ነው።
በሀዲያ ባህል ዘመን መለወጫ ከብቱም ሆነ ሰው ከሞት እንደተረፈ ተደርጎ ይታሰባል፤ ብርሃን እንዳየም ይቆጠራል። ስለዚህም ለዚያ ለአበቃው አምላክ ምስጋና እያቀረበ መጪው መልካም እንዲሆንለትም ይመኝበታል። ለዚህ ደግሞ መሪዎቹ ኮከብና ጨረቃን የሚቆጥሩ አዋቂ አባቶች በመሆናቸው ወጥተው ቀጣይ ዘመኑ ምን እንደሚመስል ይመለከታሉ። በምን መልኩ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።
በየብሔሩ እንዲህ አይነት የዘመን መለወጫ በዓላት እየተከበሩ መምጣታቸው በቀጣይ አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅ ዕድል ይፈጥራል። አገሪቱ እያራመደችው ያለውን የመደመርና የአንድነት እሳቤ በእጅጉ ያጠነክራል። ባህሉ ያለውን እምቅ እውቀት ለመለየትም ያስችላል። ትውልዱ በስነምግባርና በአብሮነት ባህል እየተገነባ እንዲሄድ፤ በአገሪቱ ሰላም፣ መረዳዳትና እድገት እንዲመጣም ያግዛል። መቻቻል ሰፍኖ፣ ዕርቅ ወርዶ ልማት እንዲፋጠንና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩም ያደርጋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው