የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ከሚገኙት ክልሎች ውስጥ በቆዳ ስፋትና በህዝብ ቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ እና ከጥንት ጀምሮ ለረጅም ጊዜያት የራሱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በገዳ ሥርዓት ስር ተደራጅቶ ተግባራዊ በማድረግ ሲተዳደር የቆየና የራሱን የባህል እሴት ለትውልዱ ማቆየት የቻለ ነው።እኛም ተቀድቶ ከማያልቀው የብሔረሰቡ የባህል መገለጫ ከሆኑት መካከል ስለ ባህላዊ ዕቃዎች ልናነሳ ወደድን ።ለዚህም በኦሮሞ ባህል ማዕከል የመረጃ ማህደር ተብለው በስራ ባልደረቦቻቸው የሚጠሩትን የማዕከሉ አስጎብኚ አቶ አደም ባሪሶን አነጋግረናል።
አቶ አደም ባሪሶ ኦሮሞ የብዙ ባህሎች ባለቤት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ከባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓል ጋር ተያይዘው የሚወጡ ቁሶች ዓይነተ ብዙ እንደሆኑ ነው የሚናገሩት።እነዚህ ቁሶች ከስንደዶ ፣ ከሸክላ፣ ከእንጨት፣ ከብረት … እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ፣ የአየር ንብረት፣በብዛት እንደሚያገኙት ጥሬ ዕቃዎች ብዙ ባህላዊ ቁሶች ይመረታሉ።
የኦሮሞ ባህላዊ ዕቃዎችን በሙሉ መጥቀስ ቢያስቸግርም እንደየዞኖቹ የተወሰኑትን ማንሳት ይቻላል።ሁሉም ዞኖች ያሉ ባህላዊ ቁሶች የኦሮሞን ባህል የሚያወሱ ናቸው፤ ነገር ግን ከቅርጽ ከዲዛይን እንዲሁም ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ደግሞ ይለያያሉ።ለምሳሌ ያህል ይላሉ አቶ አደም ሌማት ፣ ገበቴ ፣መሶብ ፣ ወርቅ ፣ጨርፊ ፣ሜሶ፣ ጉቹማ፣ ጮጮ የሚባሉት በየቀኑ የኦሮሞ ህዝብ የሚጠቀምባቸው ባህላዊ ቁሶች ናቸው።
ከእነዚህ በተለየ ደግሞ ይላሉ አቶ አደም በዓመት አንዴ የሚወጡ ባህላዊ ቁሶች አሉ።ለምሳሌ የኢሬቻ ቀን የምትወጣ ጮጮ “ጉራቲ” ትባላለች። ይህች ጮጮ ጉራቲ አባገዳዎች ፊት የስንቄ እናቶች ይዘዋት የሚወጧት ናት።ሁሉም ለኢሬቻ ሲሄድ ቤት የሚቀሩት ከብቶች ደግሞ በዚህች ወተት መያዣ ይወከላሉ።ሌላኛው የጮጮ ጉራቲ ምልክት ኦሮሞ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ገቢ የሚያገኘው በከብቶች እርባታ እንደሆነ ለማሳየትም ጭምር ነው።
ጫጮ ሌላኛው የባህል ዕቃ ነው፤ከዛጎል እና ከቆዳ የሚሰራ በጎንዮሽ የሚታሰር ባህላዊ ዕቃ ነው። ሴቶች ራሳቸውን ለማስዋብ ይጠቀሙበታል፤ቆዳው ላይ ያለው ዛጎል የሚገኘው ከባህር ውስጥ ነው፤ ባህር ደግሞ በባህሪው አቃፊ ነው ።በየብስ ከሚኖረው በባህር ውስጥ እንደሚኖር ጠቁመው፤ ኦሮሞም አቃፊ እንደሆነ ለማሳየት የሚደረግ ባህላዊ ቁስ ነው።ሌላኛው ሲንቄ ነው በኦሮሞ ባህላዊ የጋብቻ ስርዓት የተጋባች ማንኛውም እማወራ የምትይዘው ዘንግ ነው።
ሌላው ይላሉ አቶ አደም አባ ገዳዎች ግንባራቸው ላይ የሚያደርጉት ባህላዊ ቁስ “ከሌቻ” ይባላል።የስልጣን፣ የአንድነት፣ የሰላም ምሳሌ ነው። ሌላኛው የአባገዳ ዱላ “ቦኩ” በመባል ይታወቃል።ቦኩም የራሱ የሆነ ትርጉም ስላለው ከብት አይነዳበትም፣ ሌላ ቦታም ተይዞ አይኬድም ፤ለእሬቻ እና ጉማ ቀን ብቻ የሚወጣ ነው።
የመመገቢያ ቁሳቁሶችም ሆነ የወተት መጠጫ ጮጮዎች በአዘቦት ቀን ብቻ ሳይሆን ለተለየ ቀን የተለየ ምግብ ለማቅረብም የሚረዱ ባህላዊ ቁሶች መኖራቸውን ይናገራሉ:: ለምሳሌ “ቡና ቀላ” ጀንፈል ቡና ተቆልቶ ከተነጠረ ቅቤ ጋር በማዋሃድ ለምግብነት ይቀርባል። ይህ ባህላዊ ምግብ የሚቀርብበት ቁስ” ክላ ቡና ቀላ “ይባላል።ክላ ቡና ቀላ ከእንጨት አሊያም ከሸክላም ሊሰራ እንደሚችል አቶ አደም ይናገራሉ።
ሌላኛው ባህላዊ ቁስ “ሽኙቴ” ትባላለች።ለተለያዩ የሰርግ ፕሮግራሞች ሴቶች በመያዝ እየነቀነቋት በምታወጣው ድምጽ ይጨፍራሉ፤ሌላኛው የሸኙቴ ጥቅሟ ወንድሞቻቸው ሲያገቡ የኦሮሞ እንስቶች በስጦታ መልክ ትዳር ለመሰረተው ወንድማቸው የሚያበረክቱት ነው። ሸኙቴም የምትወጣውም ለዚሁ የሰርግ ቀን ብቻ ነው።
ሌላኛው “ግንዶ ቦሬ” ይባላል፤ አብዛኛው የሚታወቀው ወደ ወለጋ አካባቢ እንደሆነ አቶ አደም ይናገራሉ፤ መካከለኛ የሆነ የስፌት ውጤት ስትሆን ሰርገኞች መጥተው በሙሽሪት ቤት የሚደረግላቸው አቀባበል ሁሉም ስርዓት ካለቀ በኋላ ቤተሰቦቿ ከቤት ያወጧታል:: ከዚያም ሙሽሪት በጓደኞቿ ትከበባለች፤ከጓደኞቿ መካከል ጠንካራ የሆነችው ትመረጥና ግንደ ቆሬውን ትይዛለች:: የሙሽራው ቤተሰብ ጠንካራ ወጣቶችን ይመርጡና ሴቶቹ የያዙትን ግንደ ቦሬ በመታገል ከቆሙ በኋላ ነው ሙሽሪትን በሰላም ይዘው መሄድ የሚችሉት።ይህ ምልክቱ ልጃችን ውድ ናት፤ ታግሎ መውሰድ አለበት የሚል መልዕክት የያዘ ነው።
“ባሬ” በአሩሲ እና በባሌ አካባቢ የሚታቅ ነው።የሙሽሪት እናት ሁለት ነገሮች በሰርጉ ቀን ለሙሽራው አደራ ትሰጣለች፤አንደኛው ትልቅ የሆነ የወተት ማስቀመጫ ባሬን ሲሆን ሁለተኛው ሙሽሪትን ነው። “ሆ ባሬ ኦ በርሼ” ባሬውንም እንካ ትንሿ ልጄንም ይሄው እንደማለት ነው።ይህም ማለት ልጄ ትንሽ ልጅ ናት ተንከባከባት ለማለት እንደሆነም አቶ አደም ነግረውኛል።
ለሃይማኖታዊ ዝግጅት ብቻ የሚወጡ ደግሞ አሉ፤ከእነዚህ መሃል አንዱ ገበታ ነው። ገበታ በጣም ሰፊ ነው። ከሸክላ ወይም ከእንጨት ሊሰራ ይችላል።የኦሮሞ ሙስሊም ማህበረሰብ ለሰደቃ ወይም ችግረኞችን ሰብስቦ ለማብላት ይጠቀሙበታል።
አቶ አደም እንደሚሉት ኦሮሞ ሰፊ ባህልም ባህሉን የሚተገብርበት ቁሳቁሶች ያሉት ድንቅ ህዝብ ነው።ታዲያ ይህ ዕድሜ ጠገብ ባህል ለህብረተሰቡ በሚገባ ልክ ሊደርስ አልቻለም። ይህንን ለመቅረፍ ከዚህ ቀደም እንደምናደርገው የተወሰኑ በራሪ ወረቀቶችን በአፋን ኦሮሞ ብቻ በማሳተም ባህላችንን ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ጋር መጋራት አያስችለንም።
ስለዚህም ኦሮሞ በሚያከብራቸው ህዝባዊም ሆነ ባህላዊ ሁነቶች ላይ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በተለያዩ ቋንቋዎች በማሳተም የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችን በመጠቀም ለማስተዋወቅ እንጥራለን። እኛም የአገር በቀል ባህል እና እውቀትን በመጠቀም ለአገር አንድነት እና ሰላም እንዲውሉ እና የተለያዩ አገር በቀል እውቀቶችን ከብሄረሰቦቻችን እየተዋዋስን አገራችን ወደ ብልጽግና ማማ እንድትመጣ ምኞታችን ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012
አብርሃም ተወልደ