ዓለም አቀፉ የእርቅ፣ የሰላም፣ የግልግልና የሽምግልና ረቡኒ (መምህር ) ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ «የሰላምና ዕርቅ ትርጉምና መንገዶች» በሚለው ማለፊያ መፅሐፋቸው የሰላም የእርቅ አድማሶች በማለት በመጀመሪያ ሰው ከራሱ ጋር ከዚያ ከጎረቤቱ፣ ከማህበረሰቡ ጋር በመጨረሻም ከተፈጥሮ ጋር እርቅ፣ ሰላም ማውረድ እንዳለበት ይተነትናሉ ። ሰሞኑን የተከበረው የኢሬቻ በዓል ሰው በመጀመሪያ ከራሱ ጋር በመቀጠል ከጎረቤቱ ከዚያም ከተፈጥሮ ጋር የሚታረቅበት ማዕድ ነው ። ኢሬቻን ቀርቦ ለመረመረው በውስጡ የመደመር ስልትና ፅንሰ ሀሳብ ማለትም መሰብሰብን፣ ማከማቸትንና ማካበትን አቅፎ ይዟል ማለት ይቻላል።
ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነት የሚፈፀምበት በመሆኑ አብሮነትን ስለሚያበረታታ አሰባሳቢ ነው። ጥልን ቂምን ጥላቻን እያራገፈ መልካም መልካሙን ማለትም ሰላምን ዕርቅን የሚያጠናክር ስለሆነ በውስጠ ታዋቂ ማካበትን ይዟል። ኢሬቻም ሆነ ዐብይ መገለጫው የሆነው እርቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ፣ ሲቀባበል፣ ሲወራረስ የመጣ በሂደትም እያደገ እየጎለበተ ስለሆነ ማከማቸትን አካቷል።
የኦሮሞ ባህልና ታሪክ ተመራማሪና ፀሐፊ ኦቦ ድርቢ ደምሴ ኢሬቻ ማለት ኦሮሞ ለምለም ሳርና አበባ ይዞ ፈጣሪን የሚያመስግንበት ክዋኔ ሲሆን በሀይቅ፣ በወንዝ፣ በምንጭ ወይም በውሃ ዳርና በተራራ ብቻ የተወሰነ ግን አይደለም ይላሉ። ልጅ ሲወለድ፣ አዲስ ቤት ሲሰራ፣ ሙሽራ ሲወጣ፣ ዘር ሲዘራም፣ ወዘተ . ኢሬቻ ይደረጋል በማለት ከማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር ምን ያህል የተቆራኘ እንደሆነ ያስረዳሉ። የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት ኦቦ ሙሉጌታ ደበበ (ፒ ኤች ዲ) በሌላ በኩል ኢሬቻ የገዳ ሥርዓት አንጓ ነው ይላሉ። በማሳያነት ከሚጠቀሱት አበይት ምክንያቶች ቀዳሚው የሥርዓቱ ክዋኔ በቃሉና በአባ መልካ አጋፋሪነት መመራቱ ነው በማለት በዋቢነት ይጠቅሳሉ ።
ኢሬቻ በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚከወንና የመጀመሪያው በበልግ በተራራ ላይ አምላክን የሚያመሰግንበትና ዝናብ የሚለማመንበት ሲሆን ቱሉ ኢሬቻ ይሰኛል። ኦቦ ድርቢ ቱሉ ኢሬቻ መሬት አፏን ከፍታ የበልግ ዝናብን የምትጠብቅበት ወቅት ስለሆነ ፈጣሪን ዝናብ የሚለማመኑበት ጊዜ መሆኑን ይገልጻሉ። ባለፈው ሳምንት ለምለም ሳርና አበባ ተይዞ በሀይቅ፣ በወንዝ፣ በምንጭ ዳር የተከበረው የምስጋና በዓል ደግሞ መልካ ኢሬቻ በመባል እንደሚታወቅ ኦቦ ሙሉጌታ ያብራራሉ።
ፈጣሪ ዝናብ ስለሰጠ ከክረምት ወደ ብራ ስለ አሸጋገረ የሚመሰገንበት እንዲሁም አዝመራው ደርሶ ተሰብስቦ ወደ ጎተራ እንዲገባ የሚለመንበት መሆኑን አክለው ይገልጻሉ። በፕሮፌሰር የሰላም አድማስ እይታ መሠረት ኢሬቻ ሦስቱንም የሰላም አለባውያን በአንድነት የያዘ የእርቅ፣ የሰላም ገበታ ነው ማለት ይቻላል። ሦስቱን የሰላም አድማሶች ከኢሬቻ እሴቶች አንጻር አንድ በአንድ እናመሳክር ፦
1ኛ . ከራስ ጋር ሰላም
ዓለም አቀፍ አሸማጋይ እና የሰላም አባት ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ በዚሁ መጻፋቸው ገፅ – 102 ላይ «ውስጣዊና መንፈሳዊ ሰላም ከራስ ጋር ሰላም ማውረድ፣ መታረቅ ነው። ከፈጣሪ ጋር ሰላም ከማውረድ ጋር ትስስር አለው። ውስጣዊ ሰላም ከሌሎች ጋር ለሚመሰረት ሰላም ወሳኝ ነው። ውስጣዊ ሰላም ያለው ሰው ምን ያህል ከሌሎች ጋር በሰላም እንደሚኖር እና ሰላም እንደሚያካፍል ይታወቃል።
ውስጣዊ ሰላም ያላቸው ሰዎች አስታራቂና ሰላም ገንቢም ናቸው። ሰላማቸው ወደሌሎች ይፈሳል። ከራሱ ጋር የታረቀና ውስጣዊ ሰላም ያለው ሰው የሕይወትን መስተጋብር የተገነዘበ ስለሆነ ከማህበረሰቡና ከተፈጥሮ ጋርም ሰላምና እርቅን ያወረደ ነው። ከራስ ጋር የሚፈጠር ሰላም ለሰላም አድማሶች መነሻም ውጤትም ነው ። …»
ኢሬቻ ከመደረጉ በፊት ከራሱ ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር የተቀያየመ የተጋጨ ካለ እንዲወጣ ሽማግሌዎች በኦሮሞኛ «እውነትን ከአምላክ ፆታን ከምድር መደበቅ አይቻልም። በውሻም ሆነ በልጅ ምክንያት የተጋጨ ካለ ከፈጣሪ ጋር እንዳያቀያይመን ይውጣ» በማለት እንደሚያግባቡ ይህን ሳያደርጉ ቢቀሩ ደግሞ በማህበረሰቡ ዘንድ እንደሚያስወቅሳቸው ኦቦ ድርቢ ያስረዳሉ። የሀገር ሽማግሌዎች ቢያንስ በመጋቢትና በመስከረም በዓመት ሁለት ጊዜ እርቅ የማውረድ የመሸምገል አጋጣሚ እንዳላቸው ይገልጻሉ።
ሰሞኑን የተከበረው መልካ ኢሬቻም ሆነ በወርሀ መጋቢት የሚከበረው ቱሉ ኢሬቻ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ከራስ ጋር መታረቅ ሰላም ማውረድ ማህበራዊ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነና በዓሉ ቤትን ራስን በእርቅ የማፅዳት፣ የጥል ግድግዳን የማፍረስና ፋይል ዘግቶ ወደ አዲስ ምዕራፍ የመሻገሪያ ድልድይ መሆኑን ኦቦ ሙሉጌታ አክለው ያብራራሉ። ኢሬቻ ቂም ይዞ ምስጋናን ስለማይፈቅድ ከበዓሉ በፊት በአባ ገዳዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኦቦ ሽመልስ አቀራራቢነት ልዩነታቸውን መፈታቱን በአብነት አንስተዋል ።
2ኛ . ማህበራዊ ሰላም
ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ ስለ ሁለተኛው የሰላም አድማስ ገፅ – 103 ላይ «ማህበራዊ ሰላም ከራስ ጋርና ከተፈጥሮ ጋር ከሚደረግ ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። ይህ ማለት ግን ማህበራዊ ሰላም ከሌለ ውስጣዊ ሰላም አይኖርም ወደሚል መደምደሚያ አያደርስም። ሆኖም ብጥብጥና ሁከት ባለበት ውስጣዊ ሰላምን ማስፈንንም ሆነ ማስቀጠልን ፈታኝ አያደርገውም ማለት አይደለም።
ሌላው ማህበራዊ ሰላም ከተፈጥሮ ጋር ከሚደረገው ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው መሆኑን መገንዘብ ነው። ግጭትና ጦርነት በተደጋጋሚ የተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ስለሚጎዳ ደኑም ስለሚጨፈጨፍ አካባቢው ይራቆታል። በዚህም ሥነ ምህዳሩ ስለሚዛባ የከባቢ አየር ለውጥን ያስከትላል። ለዚህ ነው የማህበራዊ ሰላም መኖር ለፍጥረትና ለአካባቢ ጥበቃ ዋስትና ተደርጎ የሚወሰደው።»
ፕሮፌሰር እንደሚሉት ከራስ ጋር የሚፈጠር ውስጣዊ ሰላም ከጎረቤት፣ ከማህበረሰብ ጋር የሚደረግ እርቅ መሠረት ነው። በኢሬቻ ለመታደም ከራስ ጋር መታረቅ ማህበራዊ ቅድመ ሁኔታ ነው ። ከራሱ ጋር ሰላም ያለው ደግሞ ከጎረቤቱ ጋር የመጋጨት አጋጣሚው ዝቅተኛ ነው ።
ሆኖም ከጎረቤቱ ጋር ወይም ከሌላ ሰው ጋር ግጭት ቢፈጠር ሀገር ሽማግሌዎች በቱሉ ወይም በመልካ ኢሬቻ የማስታረቅ መልካም አጋጣሚም ኃላፊነትም ስላለባቸው ማህበራዊ ሰላምን ከመታወክ ይታደጉታል። ለዚህ ነው የሥነ ማህበረሰብ አጥኚዎች መጀመሪያ ከራስ በመቀጠል ከጎረቤት ጋር የሚፈጠር ሰላም ከተፈጥሮ ጋር ለሚደረስ ሰላም መደላድል እንደሆነ የሚያስረዱት። ታላቁ መፅሐፍስ «እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።» አይደል የሚለው ! ?
3ኛ . የተፈጥሮ ሰላም
ፕሮፌሰር በገፅ – 104 ላይ «የተፈጥሮ ሰላም ከማህበራዊ እና ከውስጣዊ ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። ከተፈጥሮ ጋር ሰላም፣ እርቅ ማውረድ አካላችን ከታነፀበት ምድር ጋርም መታረቅ ነው። ከተፈጥሮ፣ ከዩኒቨርስ ሥርዓትና ኃይል ጋር መንሰላሰል የውስጣዊ ሰላም ምንጭ ነው። …የተፈጥሮ ፍቅርና እንክብካቤ ለማህበራዊ ሰላም መስፈን የማይተካ ሚና እንዳለው የተለያዩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። …« ኢሬቻ ከሁለቱ የሰላም አድማሶች ይልቅ ከተፈጥሮ ጋር ለሚደረግ እርቅ ያደላል ቢባል ማጋነን አይሆንም ።
በቱሉ ኢሬቻ ፈጣሪውን ለበልግ እርሻ፣ ለከብቶች ግጦሽና ለውሃ ዝናብ የሚለምንበት መሆኑ መልካ ኢሬቻው ደግሞ ፈጣሪው ዝናብ ስለሰጠው፣ ከክረምት ወደ ብራ ስላሸጋገረው የሚያመሰግንበት በሌላ በኩል ያልተሰበሰበውን እህል በአደራ የሚሰጥበት የአምላክን ጥበቃ የሚለማመንበት መሆኑ በተለይ ለምለም ሳርና አበባ ይዞ ውሃ ዳር ፈጣሪ የሚመሰገንበት መሆኑ ከተፈጥሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ያሳያል። ይሁንና ኢሬቻ ደረጃው፣ ስፋቱ ፣ ጥልቀቱ በየሰላም አድማሱ የተለያየ ቢሆንም ሰው ከራሱ ፣ ከጎረቤቱ በመጨረሻም ከተፈጥሮ ጋር በአንድ የእርቅ ፣ የሰላም ፣ የመቀባበል ፣ ወዘተ . ማዕድ ቀርቦ የሚቋደስበት ስለመሆኑ አያጠያይቅም።
ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ «…በተለያዩ ማህበረሰቦች ሀገር ግንባታ Nation Building በመሀላቸው ያለውን ልዩነት አጥብቦ ግድግዳዎችን አፍርሶ የጋራ ማንነት መገንባት ነው ። …» ይላሉ። የሀገር በቀል እውቀቶችና የባህል ተመራማሪው አቶ አብዱልፈታህ አብደላ ይሄን የፕሮፌሰር ሀሳብ ይጋራሉ። በዓሉ በአዲስ አበባ ሌሎችን የማህበረሰብ ክፍሎች ባሳተፈ አግባብ መከበሩ ለሀገረ ግንባታ መሠረት ጥሏል ማለት ይቻላል ሲሉ ዘላቂ ፋይዳውን ያመላክታሉ። የጋራ የሆኑ እሴቶችን ባህሎችን እያጎለበትን እያሳደገን በሄድን ቁጥር መተዋወቅ፣ መከባበር፣ መቀባበል ስለሚጨምር እኔነት በእኛነት እየተተካ ስለሚሄድ ለሀገርም ሆነ ለሀገር መንግሥት ግንባታ እርሾ እንደሚሆን ተመራማሪው ያስረዳሉ።
ዛሬ ከምንገኝበት መንታ መንገድ ላይ የደረስነው ባህሎቻችንን እሴቶቻችንን ለሀገር መንግሥትም ሆነ ለሀገር ግንባታ ባለማዋላችን ነው ሲሉ አቶ አብዱልፈታህ ይሞግታሉ። ኦቦ ሙሉጌታ በበኩላቸው እንደ አድዋ ያሉ የድል በዓሎቻችን ፣ ኢሬቻ ፣ ሻደይ ፣ አሸንዳ፣ ፍቼ ጨምበላላ፣ ወዘተ . አንድ የሚያደርጉን ባህሎች በበዙ ቁጥር ኢትዮጵያዊነታችን ይጠናከራል። ከተገኘንበት ብሔር ይልቅ ኢትዮጵያዊነታችን እየገዘፈ ይሄዳል። እየተዋሀድን ፣ እየተቀባበልን፣ እየተከባበርን በሄድን ቁጥር እየተዋደድን እንሄዳለን አንድነታችንም በዚያው ልክ ይጎለብታል ሲሉ ይጠቁማሉ ።
ለከርሞ…! ?
ፈጣሪ የከርሞ «ሕዝብ» ካለን ኢሬቻም ሆነ ጊፋታ፣ መስቀላዮም ሆነ ፍቼ ጨምበላላ አሸንዳ ሻደይም ሆነ ሶለል ፣ ወዘተ . ሲከበሩ መደገም መታየት የሌለባቸውን ነውሮች ስህተቶች አርሞ፣ ነቅሶ የመምጣት ጉዳይ ከወዲሁ ልዩ ትኩረት ሊሰጠውና ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል። በሽግግር፣ በመሰራት ላይ እንዳለ ሀገርና ሕዝብ በተወጠረች ፖለቲካዊ ገመድ በጥበብ በማስተዋል መጓዝ ግድ ይለናል። እሴቶቻችን ባህሎቻችን በራሳቸው ሙሉ፣ ጮኸው የሚናገሩ ፣ ከሩቅ እንደ ቀስተ ዳመና ደምቀው የሚታዩ ስለሆኑ ምንም ዓይነት ማጋጌጪያ አያሻቸውም።
ቱባ መሆናቸው በራሱ ሙሉኡ አድርጓቸዋልና። አቶ አብዱልፈታህ ኢሬቻ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ይዞልን የሚመለሰው ምስጋናን፣ ይቅርታን ፣ ሰላምንና አንድነትን እንጂ ሌላ አጀንዳን ሊሆን አይገባም ይላሉ። ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ኢሬቻ ወደ ጋራ መድረክ ወደ አንድነት ሲመጣ እንኳን ደህና መጣህ ብሎ ሊቀበለው ይገባል በማለት አበክረው አሳስበው ነበር። በዓሉ ከመከበሩ በፊት የሰጡትን ምክር ዛሬ ላይ ስናስታውሰው የአዲስ አበባ ነዋሪ ከሞላ ጎደል እህል ውሃ በማቀበል፣ ማደሪያ በመስጠት ሲያከብረው የኢሬቻ አጋፋሪዎችም ሆነ ታዳሚዎች ግን በከፊል ችላ ያሉት ይመስላል። ያለምንም ኮሽታ በሰላም መጠናቀቁ ትልቅ ድል ነው።
ሆኖም የክልል ሰንደቅ አላማ እና የፓርቲ አርማ በማንገብ ፖለቲካዊ ቡልኮ መደረቡ ተገቢ አልነበረም። ይህ ከኢሬቻ እሴት ጋር የሚጣረስ ከመሆኑ ባሻገር አቃፊነቱ ላይ ጥያቄ፣ ብዥታ፣ ግርታ ሊያስነሳ ይችላል። ከባህላዊ፣ እሴታዊ አንድምታው ይልቅ ፖለቲካዊ ቱማታው ላይ ጊዜያዊ ነጥብ ለማስመዝገብ ጭምር የታቀደ ያስመስላል። ሆኖም ከሀገራዊ፣ ከቀጣናዊ፣ ከአህጉራዊና ከዓለም አቀፋዊ ስትራቴጂና ሕልማችን አንጻር ግን አሉታዊ ተፅዕኖው ሚዛን ይደፋል።
ከሁሉም በላይ ልንከተለው ካሰብነው የመደመር ስልት ጋር ይጣረሳል ማለት ይቻላል። በነገራችን ላይ ባህልን ከፖለቲካ ጋር የማጣቀስ አባዜያችን ትናንት የተጀመረ አይደለም። የዋለ ያደረ አባዜ እንጂ። ይህ ጥርሻ በዜጎች መካከል መጠራጠርን፣ ልዩነትን የሚያነብር ስለሆነ ሰከን ብሎ ማሰብ ይገባል። ለብሽሽቅ፣ ለእልህ ፖለቲካ በር እንዳይከፍት ጥንቃቄ ማድረግም ያስፈልጋል።
ከሁሉም በላይ እንደኛ በሽግግር ላይ ላለ እና ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ላልገነባች ሀገርና ሕዝብ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት Political Correctness የልብ ትርታዋ ሊሆን በተገባ። ሆኖም በገዥው ፓርቲም ሆነ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍ ወለምታ፣ ግራ ቀኙን ካለማመዛዘን ፣ የመራጭን constituncy ቀልብ ለመግዛት፣ የተሟጋችን Activist ቡራኬ ለማግኘት የሚፈፀሙ ፖለቲካዊ ስህተቶች ሀገርንም ሆነ ለውጡን ያልተገባ ዋጋ እያስከፈሉት ነው። ፖለቲከኞቻችን ለጭብጨባ ተሟጋቾቻን ለ Like ሲሉ በስሜት ከመጋለብ ሳይረፍድ ራሳቸውን በልጓም፣ በልባብ ሊገቱ ይገባል።
ወደ መነጋገሪያው ቀርቦ አንደበትን ከመክፈት በፊት ሁለት ሦስቴ ማሰብ፣ ከስሜታዊነት መታቀብ ያስፈልጋል። ገና ብዙ ያልተሻገርናቸው ሸለቆዎች፣ ገደሎች አሉብንና በእንቅርት ላይ … እንዳይሆን አበክረን ልንጠነቀቅ ይገባል። ከጊዜያዊ ድል ዘላቂውን የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ማስቀድም ትልቁን የተስፋ ስዕል አሻግሮ ማየት ያስፈልጋል።
ታዋቂው አሜሪካዊ የጥቁሮች መብት ተሟጋችና የሰላማዊ ትግል ሐዋርያ ማርቲን ሉተር ኪንግ «… እያንዳንዳችንን በቀጥታ የሚጎዳ ሁላችንንም በተዘዋዋሪ ይጎዳል። …» ሲል የተናገረው ሰሞነኛውን አውድ ይዋጃል ብዬ ስለአሰብሁ አጋርቼ፤ በመጀመሪያ ኦቦ ድርቢ በመቀጠል ኦቦ ሙሉጌታ በዚያ ሰሞን ባስተላለፉት አባታዊና ወንድማዊ ዘመን ተሻጋሪ ምክር መጣጥፌን ልቋጭ ። «… ባለቤቱ የእኔ ነው በማለት ትልቅ ቦታ የሰጠውን በማጣጣል ጣትን መቀሰር አይገባም ። »
«…ከ150 ዓመታት በፊት ኢሬቻ በአዲስ አበባ እንዳይከበር በማድረጉ ሂደት የዛሬው የየትኛውም ብሔር ትውልድ ተጠያቂ አይደለም ። …»
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012