ስለ ሀገር ከተሰጡ ፍቺዎችና ትንታኔዎች መካከል የደራሲ ከበደ ሚካዔልን ያህል በውሱን ቃላት፤ ነገር ግን በሰፊ ዕውቀት የታጨቀ ድንጋጌ የሚሰጥ ጽሑፍ ወይንም ጸሐፊ እስከ ዛሬ አላጋጠመኝም። ከደራሲው መጻሕፍት ጋር የንባብ አንደቤቴን ማፍታታት የጀመሩኩት ከጨቅላነት ዕድሜዬ ጀምሮ ነበር። የወተት ጥርሴን ሳልነቅል በፊት በወላጆቼ ይነበቡልኝ የነበሩትን እነዚያን መጻሕፍት ዛሬም ድረስ ለሁለት ፀጉር ለመብቃት ዳር ዳር በምልበት የጎልማሳነት ዕድሜ ላይ ሳይቀር ደጋግሜ ባነባቸው አልሰለቻቸውም።
ከአቡጀዲ የተሰፋ የፊደል ማስቀመጫ ከረጢቴን (ቦርሳ ለማለት መዳፈር ይሆናል) በብብቴ ሸጉጬና የባቄላ እንዱሽዱሽ ውሃ በሞላ ጠርሙስ ውስጥ ሰንቄ በባለውለታችን ዬኔታ መዘክር የሰፈራችን አብነት ትምህርት ቤት በገባሁ ዕለት የተበረከተልኝ ታላቅ ስጦታ ከከበደ ሚካዔል መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነው «ታሪክና ምሳሌ» መጽሐፍ ነበር።
ይኸው መጽሐፍ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላም ቢሆን ዛሬም ድረስ በመጽሐፍ መደርደሪያዬ ላይ ሳያረጅ ወይንም ሳይወይብ በክብር ተቀምጧል። ከዘመነ ጨቅላነቴ ጀምሮ መጽሐፉን ደጋግሜ ማንበብ ብቻ ሳይሆን በውስጡ የያዛቸውን ብዙዎቹን ግጥሞች በቃሌ ሸምድጄ ሳነበንብ ወላጆቼም ሆኑ አድማጮቼ ይለግሱኝ የነበረው አድናቆት ለስሜቴ የሙቀት ግለት እየሰጠ ያበረታታኝ ነበር።
ያ የማይረሳ ውለታ ግድ ስላለኝም ነበር እኔም በተራዬ የሀገሬ ሕፃናት በንባብ እንዲጎለብቱ በማሰብ በጻፍኳቸው ስድስት ያህል የልጆች መጻሕፍት ውስጥ መታሰቢያነቱ ለእኒህ ታላቅ ደራሲና ለመሰል ዘመነ አቻዎቻቸው እንዲሆን የወሰንኩት። ይሄው የሀገሬ ጉዳይ ዛሬም ድረስ ከመጽሐፉ ድንጋጌ ባለፈ እጅግ ገዝፎብኝና ሸክሙ ከብዶብኝ ውሎና አምሽቶዬ የሀገሬ ጉዳይ ሊሆን ግድ ሆኖብኛል። የራሮት እንጉርጉሮዬና መዝሙሬም በራሷ ልጆች እየተመሳቀለች ስላለችው ስለ መከረኛዋ ሀገሬ ከሆነ ሰነባብቷል፤
«እንዲህ እንደዋዛ ሲጠራ ቀላል ይመስላል ቃሉ፣
እስኪ ሁላችሁም ሀገር፣ ሀገር በሉ።»
በዚህ የልጅነቴ ቅርስ፣ የጉልምስና መተከዣዬ በሆነው መጽሐፍ የመጀመሪያ ገጽ ላይ የጻፍኩትን ማስታወሻ ሳነብ ትዝታዎቼን የማጅባቸው በብዙ መገረም ጭምር ነው። እነሆ መጽሐፉ ላይ ያሰፈርኩት አጭሩ ማስታወሻ እንዲህ ይነበባል። «ይገርማል! የእኔ ዕድሜ እየነጎደ ነው። ይህ መጽሐፍ ግን ሁሌም አዲስ፣ ልጅና ወጣት ነው። አወይ ልጅነቴ! ዛሬ ትናንትን መሆን አይችል።» ይላል በቁጭት የተጻፈው መተከዣ።
አድናቆት ያዥጎደጎድኩለት ይህ መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ ለንባብ የበቃው በ1934 ዓ.ም ልክ የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ጦር ድል ተመትቶ ከሀገር በተባረረበት ማግስት ነበር። ከዚያ ወዲህ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ መገመት በማያስችል ሁኔታ ሜጋ አሳታሚ ድርጅት መጽሐፉን በተደጋጋሚ ሺህ በሺህ እያባዛ ሲቸበችብ ኖሯል። ለክፋቱ ደግሞ በየትኞቹ ዓመተ ምህረት ምን ያህል ጊዜ እንደተባዛ ያለመጠቀሱ ነው። ለወደፊትም ይህንን መሰል ግዙፍ ስህተት ተቋሙ ባይፈጽም መልካም ይሆናል።
ባለመብቶች በየትኛው ዓመተ ምህረት ምን ያህል ቅጂ ታተመ ብለው እንዳይጠይቁ ከሆነም ድርጅቱ የሞራል ሥነ ምግባርን እየጣሰ ስለሆነ ሕግና ህሊናውን ሊያደምጥና ሊታዘዝ ይገባል ባይ ነኝ። አሳታሚ ድርጅቱ በበርካታ መጻሕፍትም ላይ ሳይቀር ይህንን መሰል ስህተት እየፈጸመ ስለሆነ ቢታረም አይከፋም። ተመራማሪዎች የመጻሕፍትን ተነባቢነት ከሚለኩበት መስፈርት አንዱ የህትመቱን ብዛት እያዩ ስለሆነ አሳታሚ ድርጅቱ ከዕለት እንጀራው አኩል ሀገራዊ አደራውንም እንዲያስብበት አሳስባለሁ።
ከደራሲው መጻሕፍት ጋር በሚገባ የተዋወቅሁት በልጅነት ዕድሜ ቢሆንም ከደራሲ ከበደ ሚካዔል ጋር ግን ፊት ለፊት የተገናኘነው በዘመነ ወጣትነቴ ነበር። ደራሲው ጨካኙ የደርግ መንግሥት ቤት ንብረታቸውን በግፍ ወርሶባቸውና አውላላ ሜዳ ላይ ጥሏቸው ስለነበር አእምሯቸው ተቃውሶ ውሏቸው አራት ኪሎ አካባቢ ነበር። እኚህ ታላቅ ሰው በሀገር ፍቅር ብዙዎችን አንፀው እርሳቸው ግን ሀገር አልባ፣ ባይተዋርና በሽተኛ ሆነው እንዲያልፉ መደረጉ የታሪካችን ውርስ አንዱ ጠባሳ አጋጣሚ ነው።
እኔና ባልደረቦቼ በደራስያን ማኅበር አመራር ላይ በነበርንበት ወቅት እኒህ አይረሴ ደራሲ በመታሰቢያ ቴምብር ላይ ምስላቸው እንዲታተም በማድረግ የህሊና ዕዳችንን ያቀለልን ይመስለኛል። ምስጋናዬ ለኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርና ለኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ይድረስልኝ። የተከበሩት አንጋፋው የሀገራችን ደራሲ ታደለ ብጡል ክብረት (ኢ/ር) ለደራሲ ከበደ ሚካዔል ያደረጓቸውን በርካታ መልካም ተግባራት በተመለከተ ታሪክና ትውልድ ብድሩን ይክፈላቸው ከማለት ውጪ በጎነታቸውን መዘርዘሩ ቦታው ስላይደለ በአነስተኛ ምስጋና ብቻ ለማለፍ ተገድጃለሁ።
ለማንኛውም ከበደ ሚካዔል በ «ታሪክና ምሳሌ – አንደኛ መጽሐፍ» ላይ ለሀገር የሰጡትንና በእኔ ልቦና ውስጥ ሰርፆ ግማሽ ክፍለ ዘመን ስለዘለቀው ተጽእኖው አድናቆቴን ሳልገድብ እንድመሰክርለት የተገደድኩበትን አጭር ጽሑፍ እንደሚከተለው መጥኜ አስነብባለሁ።
«ሀገር በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በልማድ፣ በተስፋ፣ በደስታና በመከራ ተሳስሮ የሚኖር አንድ ወገን የሆነ ሕዝብ የሚኖርበት የዓለም ክፍል ነው። ሀገር ማለት አያት ቅድመ አያት የተወለዱበት፣ አድገውም በጀግንነት ከውጭ ጠላት እየተከላከሉ ለሕዝብና ለመንግሥት የሚጠቅም ሥራ ሠርተው ዕድሜያቸው ሲደርስም ልጆቻቸውን ተክተው የተቀበሩበት ጉድጓድ ነው።
በመወለድ እትብት፣ በመሞት አካል ከአፈሩ ጋር ስለሚዋሃድ የሀገሩ አፈር ሕዝቡ በላዩ የሚኖርበት ማለት ነው። ፈጣሪ ከምድሯ ፍሬ ሕይወት እንዲገኝባት በማድረጉ ሀገር እያጠባች የምታሳድግ፣ ፍቅሯም በአጥንት በሥጋ ገብቶ የማይደመሰስ የሆነች እናት ማለት ነው። ከልጅነት ጀምሮ ወንዙን፣ ተራራውን፣ ሜዳውን፣ ቆላውንና ደጋውን በማየት ስለ ማደግ፤ አባቶች በሕይወትና በሞት የሠሩበት ደግ ሥራ በአእምሮ ታትሞ ስለ ቀረ በሀገር እስካሉ ሲታይ፤ በስደት ሲሆኑ ሲታሰብ ፍቅርና ናፍቆት የሚያሳድር ሀገር ነው። ሀገር አባት፣ እናት፣ ዘመድ፣ ምግብ፣ ጌጥና ሀብት በመሆኑ ድህነትና ጥቃት በመጣ ቁጥር እስከ ሞት ድረስ እንዲሰራበት ከአያት ከቅድመ አያትና ከአባቶች በጥብቅ አደራ የተሰጠ ገንዘብ ነው።»
ስምንት ዓሠርት ዓመታት የሚጠጋ ዕድሜ ባለው በዚህ አዛውንት መጽሐፍ ውስጥ ስለ ሀገር የተሰጠው ጥልቅ ድንጋጌ በእጅጉ እምቅ ሃሳቦችን የተሸከመ ነው። ሀገር የአንድ ቋንቋ ወይንም ሃይማኖት ወይንም ብሔር ተከታዮች ንብረት ሳትሆን የመላው ሕዝብ የደምና የአጥንት ስሪት መሆኗ በሚገባ ተገልጧል። ብዙኃኑ ሕዝብም የተጋመደባቸው እሴቶች ምን ያህል ውስብስብና የተቆራኙ እንደሆነ በሚገባ ተብራርቷል። ዛሬ የምንኖረው ደምና ላብ፤ ነፍስና ሥጋ በተከፈለበት የጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ውርስ እንጂ በጩኸትና በአንደበተ ጮሌነት እኛና «እኛ ባይ ወር ተረኞች» የሰሯት ኢትዮጵያ እንዳልሆነች በሚገባ ሊታወቅ ይገባል።
«አዲሲቷ ኢትዮጵያ» የሚለው የእብሪት ዲስኩርም የራስን አዳፋ አመለካከት የሚያመለክት እንጂ ሌላ ምንም ስም ሊሰጠው አይችልም። «አዲስ» የሚባል የፖለቲካ አስተሳሰብ «ተፈጠረ» ቢባል እንኳ ነባሩን ሥርዓት ይቀይር ካልሆነ በስተቀር «ኢትዮጵያን እንደገና ፈጥሮ አዲስ አያደርጋትም» ሀገሬ ነበረች፣ አለች ወደፊትም በትውልዶች ቅብብሎሽ መቀጠሏ እውነትም፤ እርግጥም ነው።
አንድ ሀገር የታላቋ ዓለማችን ክፋይ እንጂ «ራሴው ለራሴ ብቁ ነኝ! ሁሉም አለኝ፣ ቢያሻም ለሌላው የማበድረው ሀብትና ቅርስ ተትረፍርፎ በሰንዱቄ ውስጥ ሞልቷል፤ ስለዚህም የሌላው ወገን ድጋፍና ርዳታ ለእኔ አያስፈልገኝም።» አሰኝቶ የሚያኩራራ እንዳልሆነም ጎምቱው ደራሲ አስረግጠው ነግረውናል።
ከሁሉም በላይ ሀገራችን የሺህ ታሪክ ምስክርነት ባለበት የዕድሜ ጣሪያ ላይ ልትደርስ የቻለቸው ጀግኖቻችን ለወራሪ ኃይላትና ለእርስ በእርስ ክፍፍል ሳይበገሩ ተደጋጋሚ መስዋዕትነትን ባስከፈለ የደም ማህተም ስላጸኗት እንደሆነም ደራሲው በግልፅ ቋንቋ አትመውልናል። ሀገርን ለመጠበቅና ለማስጠበቅም የትውልዶች የማይበጠስ ሰንሰለት እጅግ መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነ በአፅንዖት ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በበዓለ ሲመታቸው ላይ «ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞትም ኢትዮጵያዊ» በሚለው ኃይለ ቃል አስደግፈው ስለ ሀገር አስደናቂና ዘመን ተሻጋሪ መልዕክት ያስተላለፉት የዚህን መጽሐፍ ሃሳብ የሚያብራሩ ጥበበ ቃላትን በመጠቀም ነበር። እውነት ነው ሀገር በሕይወት ስንኖር የእናት ጓዳ፤ ስንሞት ደግሞ የአፅማችን ማሪፊያ ቤታችን ናት።
ሀገር+ቤት= ? የሚለውን የርዕሴን ፍልስፍና በጥቂቱ ላብራራ። ከትውልድ አካባቢያቸው ወጥተው በሌላው የሀገራቸው ክፍል የሚንቀሳቀሱና የሚኖሩ ዜጎቻችን የተወለዱበትንና የኖሩበትን ቀዬ፣ መንደር ወይንም ዙሪያ ገባ የሚጠሩት ሀገር ቤት በሚል የወል መጠሪያ ነው። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ቢሆኑ ባሉበት ሀገር እየኖሩ ስለ ሀገራቸው ማውራትና መናገር የሚጀምሩት «ሀገር ቤት» የሚለውን መጠሪያ በመጠቀም ነው።
እውነት ነው ሀገር የሚገለጠው በመልክዓ ምድሩ ገጽታ ተራራ፣ ወንዝ ሸለቆ፣ ሜዳ፣ ቆላ፣ ደጋ፣ ወይና ደጋ ወዘተ. እየተባለ ብቻ ሳይሆን ሀገር ቤትም፣ ቅርስም ነው። ቤት ፍቺውና ትንታኔው እጅግ ሰፊና ዝርዝርም ነው። በቁሙ ማደሪያ፣ መኖሪያ፣ ሥራ መሥሪያ፣ በደንጊያ በብረት፣ በጡብና በጭቃ፣ በሳር ወይንም በጨፈቃ የሚሰራ መጠለያ ብቻ አይደለም። ቤት፤ ወገንን፣ ዘርን፣ ትውልድና የደም ውርስን ጭምር ይወክላል። ቤተ እስራኤል፣ ቤተ ጉራጌ እንደሚሉት ዓይነት መሆኑ ነው። ቤት ገንዘብን፣ ሀብትን፣ ጥቅምን ወዘተ. እንደሚወክልም የመዝገበ ቃላት አሰናጁ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ዝርዝሩን ተንትነውልናል።
ስለዚህም ሀገር+ቤት=? ተብሎ መልሱ ሳይሰጥ የተቀመጠው ግማሽ ስሌት የሀገራችንን ወቅታዊና ግራ ገብ አመለካከት ይወክል እንደሆን ብዬ በማሰብ ነው። ለአንዳንዱ ዜጋ በርግጥም ሀገሩ፤ ሀገር ብቻ ሳትሆን መኖሪያውም መቀበሪያውም ጭምር ነች። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ለሀገርህ ክብር ሕይወትህን ሰዋ! ለሉዓላዊነቷ ሞገስም ራስህን አሳልፈህ ስጥ ቢባል ሳያመነታ ፊት ቀደም ለመሆን ይሽቀዳደማል። «አጥንቴም ይከስከስ፤ ደሜም ይፍሰስላት» እያለ መሃላ የሚገባው እውነቱን ነው።
አንዳንድ ዜጎችም አሉ፤ ለእነርሱ ሀገር ማለት ንብረት ማፍሪያ፣ ሀብት መዝረፊያ፤ ክፉ ቀን ሲመጣባቸውም በልጅ በሚስቶቻቸው ስም ያከማቹን ሀብታቸውን ይዘው በመፈርጠጥ ሌላ ሀገርና ቤት የሚሰሩ የእንግዴ ልጅነት ስም የሚሰጣቸው ናቸው። እነዚህን መሰል ዜጎች ኩራታቸው በሀገራቸው ሳይሆን በዘረፉት ሀብት ላይ የተመሰረተ ነው። ትምክህታቸውም ስደትና ጥገኝነት ነው።
አሉ አንዳንዶችም ባለሁለትና ባለ ሦስት ፓስፖርት ባለቤት የሌሊት ወፎች። ነገር ሲጨልም ሸሽተው ለክፉ ቀን ባነጹት የባእዳን ጎሬ ውስጥ የሚወሸቁ። ደግ ብርሃናማ ቀን የመጣ ሲመስላቸው ደግሞ በሸሚዛቸው ላይ ሽቶ ነስንሰው አግዓዚ በመምሰል ብቅ የሚሉ። ለእነርሱ ሀገር ማለት የፖለቲካ ጥቅም ማስከበሪያና በረጅም ምላሳቸው የሚማርኩት የሥልጣን ትርፍ ነው። ለእነዚህ መሰል ግራ ገብ ፍጡራን ስያሜ መስጠት ካስፈለገ የሚቀርበው «ጭንጋፍ» የሚለው ቃል ብቻ ይመስለኛል።
አሉ ሌሎችም፤ እንኳንስ በሀገር እየኖሩ የሀገርን ስም ሊጠሩ ቀርቶ ባሉበት የባእድ ምድር «ኢትዮጵያዊ ጽዩፍነታቸውን» በንግግርም ሆነ በተግባር እየገለጡ ለሙት ገላቸው ማሳረፊያ ቀብድ በመክፈል አስቀድመው መቃብር ቤት የሚያንፁ። ለእነዚህ መሰል «ቋሚ ሙታን» ሀገር – ሀገር ሳትሆን «ሀገር የሙት አካላቸውና መንፈሳቸው ማረፊያ» ቤት ብቻ ነች።
እነዚህ ሰዎች የዜግነትን ክብር በተመለከተ ልባቸውና መንፈሳቸው እንደ ወፍ በሮ ከተሰወረ በኋላም ቢሆን በሚኖሩበት ሀገር አደብ ገዝተው ለመቀመጥ አይችሉም። ምላሳቸውን አስረዝመው ሀገርና ሕዝብን ያዋርዳሉ፣ ንፁሃን ዜጎች ሰይፍ እንዲማዘዙ ያቅራራሉ፣ ከእኔ ፍልስፍና ውጭ የሌላው ሃሳብ «የአርዮስ ነው» በማለትም የስልጡን ሀገራትን አደባባዮች በሰልፍ ይንጣሉ። ሲመቻችላቸውም የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸውና ተሞሽረው ሀገር ቤት ለመግባት ባንዲራ ያሰቅላሉ።
ሀገር እንደዚያም እንደዚህም አይደለችም። ሀገር+ቤት= ሀገር ቤት ነች። በክፉዋ ቀን ታማኝ ልጆቿ ከመከራና ከውርደት የሚጋርዷት። በደጉ ቀን ለብልፅግናዋና ለደስታዋ የሚዘምሩላት። በተፈጥሮ ኅብር ውበት፤ ቋንቋና ብሔር፣ ዘርና ጎሳ፣ ሃይማኖትና ባህል ገደል ያልፈጠሩባቸው የኩሩ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ ነች – ሀገር። ሀገር አትተካም። ሀገር አትዋረድም። ሀገር – ሀገር ብቻ ሳትሆን ሀገር – ቤትም ነች። መነሻዬም ማጠቃለያዬም የከበደ ሚካዔል መልካም ምክር ነው። እነሆ ምክራቸው፤ «ብዙ ገንዘብ፣ ብዙ ርስትና ዝና ከማግኘት ይልቅ ለሀገሩ ትልቅ ሥራ የሠራላት ሰው ስሙ ለዘለዓለም በታሪክ ሲታወስ ይኖራል።» ሰነፉን የሚጠብቀው የታሪክ ዳረጎት ደግሞ ተቀራኒው መሆኑን ልብ ይሏል። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012