የኢ.ፌ.ዴ.ሪ.ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር የመንግሥትን የ2012 በጀት ዓመት ዋና ዋና ዕቅዶች ይፋ የተደረጉበት ነው። በተለይ ኢኮኖሚውን በተመለከተ በርከት ያሉ ቁምነገሮች የተቀመጡ ቢሆንም ያልተዳሰሱ እና በቂ ትኩረት የተነፈጋቸው አበይት ጉዳዮችም እንደነበሩ ለመታዘብ ተችሏል።
ፕሬዚዳንትዋ ስለኢኮኖሚው ምን አሉ?
“…ይህ ዓመት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራት በተጠናከረ ደረጃ የሚከናወኑበት ይሆናል። ለዚህ ዋናው መሪ ሐሳብ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን ተግባራዊ ማድረግ ነው። የዚህ ዋና ዓላማዎች ሦስት ሲሆኑ እነርሱም፣የማክሮ ኢኮኖሚውን ጤንነት መጠበቅ፣የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማሳደግና፣ለዜጎች በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር ናቸው።
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም እነዚህን ዓላማዎቹን ለማሳካት የሚያተኩርባቸው ሦስት ጉዳዮች አሉት። የመጀመሪያው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ማስተካከል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የኢኮኖሚ መዋቅሮችን ማሻሻል ነው። የኢኮኖሚ መዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራሙ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን፣ የኃይል አቅርቦትን፣የቴሌኮም ዘርፍን ማሻሻልን እና የሎጅስቲክስ ሥርዓትን ማቀላጠፍን ያካትታል። ሦስተኛው የማሻሻያ ፕሮግራሙ ትኩረት ደግሞ የኢኮኖሚ ዘርፍ ማሻሻያ ነው። እርሱም የግብርና ምርታማነትን፣ የአምራች ዘርፉን እና የቱሪዝም ዘርፍን ለማሻሻል እንዲሁም የሚያስገኘውን የውጭ ምንዛሪ ሀብት ለማስፋት፣ የአገልግሎት ዘርፉን ለማቀላጠፍ ትኩረት ይሰጣል።
ከኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ጋር አብሮ የሚሄደው የንግድ አሠራር የማሳለጫ መንገዱን (Doing Business) ማቀላጠፍ ሲሆን ሀገራችንን ለቢዝነስ እንቅስቃሴ ተመራጭ ሥፍራ እንድትሆን ያለመ ነው። በየተቋማቱ በሕግና በአሠራር ያሉ እንቅፋቶችን ማስተካከል፣ አካሄዱን በቴክኖሎጂ ማዘመን፣ የሰው ኃይሉን ብቃት መጨመርና በተለያዩ ተቋማት የተበታተኑ አሠራሮችን ለቅልጥፍና በሚያመች መልኩ ማሰባሰብ በዋናነት ትኩረት የሚደረግባቸው ናቸው።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሥራ ፈጠራ ብሔራዊ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን የተጀመረው በሀገር ውስጥና በውጭ አገር ለወጣቶቻችን የሥራ ዕድሎችን የማመቻቸትና የማፈላለግ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል። ወጣቶቻችን ለሥራ ዲሲፕሊን የሚያበቃቸውን ሥልጠና ወስደው፣ ተወዳዳሪና ብቁ ሆነው እንዲሠማሩም ያደርጋል።
በ2011 በጀት ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚውን ከማቃናት አንፃር የተጀመሩ የተጠናከረ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ፣ ከተለያዩ ምንጮች ለልማታችን የሚያግዝ የውጭ ምንዛሪ የማሰባሰብ ተግባር፣ የውጭ ብድር ጫናን ለማቃለል የዕዳ ማሸጋሸግ ድርድር ሥራዎችና የኤክስፖርት ገቢያችንን በ2012 የማጠናከር ጥረት የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
በያዝነው የበጀት ዓመት የተመረጡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወይንም በሙሉ ወደግል የማዘዋወሩ እንዲሁም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት (PPP) የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን የመተግበሩ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። የቴሌኮም ሴክተር እንዲሁም በስኳር ኮርፖሬሽን ሥር የሚገኙ የተወሰኑ ኩባንያዎችና ፕሮጀክቶች በዚህ ዓመት በከፊል ወይንም በሙሉ ወደ ግል የሚዛወሩ ይሆናል።
በ2012 በጀት ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ የሕገወጥ ንግድን መልክ የማስያዝ ሥራ ነው። በዚህ ረገድ ተጠባቂ የሆነ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የመፈፀም አቅም በማሳደግ ኮንትሮባንድ፣ ታክስ ማጭበርበርንና ታክስ መሰወርን፣እንዲሁም በሕቡዕ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት በማምጣት ኢኮኖሚውን ወደ ተሻለ ጤንነት የማሸጋገር የተቀናጀ ሥራ ይከናወናል።
የዋጋ ንረት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይ የሚጎዳ በመሆኑ የዋጋ ንረቱን የመቆጣጠር ሥራ በከፍተኛ ትኩረት የሚሠራ ይሆናል። የዋጋ ንረቱ በዋናነት የሚስተዋለው በምግብ ሸቀጦች ላይ ስለሆነ መንግሥት የመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን በበቂ መጠን ከውጭ በማስገባት የዋጋ ንረቱ ሸማቾችን እንዳይጎዳ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል።
በ2012 በጀት ዓመት ሌላው የሚተኮርበት ጉዳይ የኢንዱስትሪ ዘርፉን የሚያሻሽል ሥራ የመሥራት ነው። የኢንዱስትሪ ፖሊሲያችንንና አፈፃፀማችንን እንደገና በመፈተሽ ውጤታማ የሆነ የማትጊያ ሥርዓት እንዲዘረጋ ማድረግ ይኖርብናል። ይህን በማድረግ በማኑፋክቸሪንግና በሌሎች ዘርፎች ያለው ምርታማነት የሚያሳድግ ሥራ በትኩረት ይከናወናል።
በአጠቃላይ 2012 በኢኮኖሚው ዘርፍ፣ ምርታማነትን በማሳደግ ፍላጎት ተኮር የነበረውን ኢኮኖሚያችንን በአመዛኙ ወደ አቅርቦት ተኮር የመሸጋገሩ ሥራ በስፋት ተግባራዊ ይደረጋል።
በግብርና መስክ ባለፈው ዓመት ትኩረት ሰጥተን ከሠራንባቸው ጉዳዮች አንዱ የሰብል ምርታማነትን ማሳደግ ነው። በዚህ ረገድ የ2010/2011 ምርት ዘመን የሰብል ምርትን 406 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ 316 ሚሊዮን ኩንታል ማለትም 78 በመቶ ለማምረት ተችሏል። ይህም በ2009/2010 ከተመረተው 267 ሚሊዮን ኩንታል ጋር ሲነፃፀር የ4.29 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የእርሻ ግብአቶችን በሚፈለገው መጠንና ወቅት ማቅረብ ሲሆን በዚህ ረገድ በክልሎች ፍላጎት መሠረት ለ2011/12 ምርት ዘመን የሚያስፈልግ አንድ ነጥብ ሁለት ሰባት (1.27) ሚሊየን ቶን የኬሚካል ማዳበሪያ የውጭ ግዥ በማከናወን ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ደርሷል። ሀገራዊ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታትና በዓመት ከግማሽ ቢሊየን ዶላር በላይ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት አዲስ የማዳበሪያ ፋብሪካ ድሬዳዋ ላይ ለማቋቋም ከአንድ የውጭ ኩባንያ ጋር ሽርክና (Joint venture) በመፈራረም ሥራው በቅርቡ ይጀመራል።…”
ዕቅዱ ችግሮችን ይፈታልን?
በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተገለፀው የመንግሥት ዕቅድ ውስጥ ኢኮኖሚው የገባበትን ቅርቃር የመፍታቱ ጉዳይ እንመልከት። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት ሥር የሰደደ የመዋቅር መዛባት የታየበት ሲሆን ከፍተኛ የሆነ የሥራ አጥነት መጨመር፣ የግብር አሰባሰብ ድክመት፣ በግብርናም ሆነ በኢንዱስትሪ ዘርፎች ምርታማነት ማሳደግ አለመቻል፣ የንግድ ሚዛን (የገቢና የወጪ ንግድ) መዛባት፣ በምግብ ራስን አለመቻል፣ በዋናነትም የሁለተኛው የዕድገትና የሽግግር ዕቅድ መክሸፍ ወዘተ ሥር የሰደዱ ፈተናዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት ሲነሣ ይደመጣል። ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ በሀገሪቱ የሚስተዋለው የምርቶች ዋጋ መናር የዜጎች የኑሮ ፈተና ሆኗል።
በሌላ በኩል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ገጥሞናል። ይህ ችግር ለኤክስፖርት የሚያመርቱ ኢንደስትሪዎች ጭምር እያሽመደመደ ነው። አንድ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ያነጋገርኳቸው የኢንዱስትሪ ባለሀብት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከዘጠኝ ወራት ያላነሰ ጊዜ ወረፋ መጠበቅ ግድ ሆኖባቸዋል። በዚህም ምክንያት ያለሥራ የሠራተኞች ደመወዝ እየከፈሉ ለመቀመጥ መገደዳቸውን ነግረውኛል።
ከውጭ አገር ተገዝተው የሚገቡ መድሃኒቶች ጭምር በአንድ በኩል በገበያ ላይ ከፍተኛ እጥረት፤ በሌላ በኩል በተገኙትም ላይ የተጋነነ የዋጋ ንረት የታየው ከዚሁ ችግር ጋር ተያይዞ ነው። የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ አንጋፋውን የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሊያዘጋ የሚችልበት ደረጃ መድረሱን በዚሁ ጋዜጣ ተጽፎ አንብበናል።
የማተሚያ ድርጅቱ እንዳለው በቀጣይ የውጭ ምንዛሪ አግኝቶ ወረቀትና ቀለም የመሳሰሉ ጥሬ ዕቃዎችን ማስገባት ካልቻለ ከሁለት ወራት በኋላ ሥራ መቀበል ሊያቆም እንደሚችል አስጠንቅቋል። እንዲህ አይነት መሰል ችግሮች እዚህም እዚያም ገነው በሚታዩበት በዚህ ወቅት ስለችግሩ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ንግግር በበቂ ሁኔታ አለመዳሰሱ ጥያቄ ያጭራል። መንግሥትም ችግሩን ለመፍታት መጀመሪያ የችግሩን ስፋትና እያስከተለ ያለውን ሀገራዊ ጉዳት ማጤን አለበት። በዚህ ረገድ ምን አይነት እርምጃ ሊወስድ እንደተዘጋጀ አለመገለፁ ለብዙዎች ግራ አጋቢ ሆኗል።
ሌላውና አንገብጋቢው ችግር የዋጋ ንረትን የተመለከተ ነው። በአሁን ሰዓት የተከሰተው የዋጋ ንረት እጅግ አስደንጋጭ ነው። ማዕከላዊ ስታስቲክስ መ/ቤት ከሚናገረውም በላይ ከባድ የኑሮ ሸክምን አምጥቷል። በርካታ የመንግሥትና የግል ድርጅት ተቀጣሪ ሠራተኞች በወር ገቢያቸው ብቻ ኑሮን ተቋቁመው ለመጓዝ የማይችሉበት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። በጡረታና በአነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ገቢዎች የሚኖረው እጅግ በርካታ ሕዝብ ሊነገር በሚከብድ የኑሮ ሰቆቃ ውስጥ ወድቋል።
የማዕከላዊ ስታስቲክስ መ/ቤት እንዳለው በፍጆታ ዕቃዎች ላይ ያለው የዋጋ ግሽበት ከታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ በሁለት አሃዝ ከፍ ብሎ በነሐሴ ወር 15 በመቶ መድረሱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባጠናው ጥናት መሰረት ለዋጋ ንረቱ የደላሎች አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት፣ አርቴፊሻል የምርት እጥረት እንዲከሰት ምርትን በቅንጅት በሚሸሽጉ ነጋዴዎች፣ያለደረሰኝ ግብይት መፈፀም እና ፎርጅድ ደረሰኝ ማቅረብ እንዲሁም የሕብረት ሥራ ማህበራት የአቅም ውስንነቶች ለዋጋ ግሽበቱ ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።
የምርት እጥረት እንዳለ ተደርጎ የዋጋ ጭማሪ የሚደረገው የሕገ ወጥ ነጋዴዎች ተግባር እንጂ በገበያው ላይ የምርት እጥረት አለመኖሩን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መናገሩን ተመልክቷል።
በሌላ በኩል የመንግሥትን የ2011 ዓመት የሥራ አፈፃፀም ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በግንቦት ወር የዋጋ ግሽበት 16 ነጥብ ሁለት በመቶ መድረሱን ይፋ ማድረጋቸውም የሚዘነጋ አይደለም።
የም/ቤት አባላቱ የዋጋ ግሽበት የኑሮ ውድነትን አስከትሎ ህዝቡን እያማረረ ነውና መንስኤውና መንግሥት ግሽበቱን ለመከላከል ምን አይነት ሥራዎችን በአዲሱ በጀት ዓመት ለመሥራት እንዳቀደ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ምላሽ ሲሰጡም፤ መንግሥታቸው የ2012 በጀት ዓመት በትኩረት ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ የዋጋ ግሽበት ቅነሳ አንዱ ነው ብለዋል። አራት የሚደርሱ ዋና የትኩረት ሥራዎችን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም ዋነኛ የግሽበት መንስኤ ነው ያሉ ሲሆን ፍላጎት ላይ ብቻ የተንጠለጠለውን ምጣኔ ሀብት ወደ አቅርቦት መቀየር መንግሥት ሐሳቡ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥት እንደከዚህ ቀደሙ ሸቀጦችን ከውጭ አገር ገዝቶ በማስገባት ዋጋውን ለማረጋጋት መታሰቡን ነግረውናል። ይህ የሰነበተ አሠራር ግን እስከዛሬም ሲተገበር የቆየ ቢሆንም በተግባር ችግሩን በዘላቂነት ሲፈታ አልታየም። በአንዳንድ አካባቢዎች ይባሱኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቅሬታ ምንጭ መሆኑም የሚታወስ ነው።
እናም መንግሥት የአቅርቦት ችግር አለመኖሩን በእርግጥም በትክክለኛ ጥናት አረጋግጦ ከሆነ ሕመሙን ለይቶ በፍጥነት ማከም የሚችልበትን ስትራቴጂ ሊነድፍ ይገባል።
ሌላው የፖለቲካው አለመረጋጋት፣ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ደካማ አፈፃፀም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የመንግሥት ገቢ የመሰብሰብ ችግሮች አስከትሏል። እነዘህ ችግሮች ተደማምረው የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ እንዲቀዘቅዝ ማድረጋቸው መካድ አይቻልም። እናም ፖለቲካውን ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ በማያስከትል መልኩ መግራት አስፈላጊ ይሆናል።
በቴሌኮም ዘርፍ በከፊል ለግሉ ዘርፍ ክፍት ለማድረግ የተያዘው ዕቅድም ቢሆን ከመተግበሩ በፊት በየደረጃው የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቂ ምክክር እና መግባባት ተደርጎበታል ወይ የሚለውም እንዲሁ መታየት ያለበት አብይ ጉዳይ ነው። ወደትግበራ ከመገባቱ አስቀድሞ የተለዩ ድምፆችን ለመስማት መንግስሥት ጆሮውን የማይሰጥ ከሆነ በአፈፃፀም ሂደቱ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳርፍ ብዙዎች በሥጋት መልክ የሚያቀርቡት አስተያየት ሆኗል።
ይህም ሆኖ በተቃራኒው የውሳኔውን ተገቢነት የሚያደንቁ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በብዛት አሉ። ታዋቂው የኢኮኖሚ ምሁር አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር። “ኢትዮ ቴሌኮምን በምሳሌነት ብንወስድ፣ ወቅታዊ የገበያ ዋጋ ግምቱ፣ ከ15 እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮ ቴሌኮም የአህጉሪቱ ግዙፉ የሞባይል አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ነው።
በህዳር 2017፣ የሞባይል ደንበኞቹን ቁጥር ከ57 ሚሊየን በላይ ያደረሰው፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮም፣ በሰፊ የሞባይል ደንበኞች መሰረት፣ የናይጀሪያው ኤምቲኤን በመተካት፣ በአፍሪካ ግዙፉ ኩባንያ ሆኗል። ከዚህ በገሐድ ከሚታይ ስኬት በተቃራኒ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ በአፍሪካ የአገራቸውን የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ወደ ኋላ በመጎተት ከሚታወቁት አምስቱ ቀዳሚ የቴሌኮም ሞኖፖሊዎች ውስጥ የአንደኝነት ደረጃ ተሰጥቶታል።
ኩባንያውን በከፊል ብቻ ፕራይቬታይዝ ማድረግ፣ ወደ ኢኮኖሚው ሊገባ የሚችል ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ከማመንጨትም ባሻገር፣ በታክስና ገቢ ድርሻ ረገድ፣ ቴሌኮም በመንግሥት እጅ ተይዞ ከሚያስገኘው የበለጠ ጥቅም ለመንግሥት ያስገኝለታል።
ኢትዮ ቴሌኮምን ፕራይቬታይዝ ማድረግ፣ ከገንዘብ ጠቀሜታው ባሻገር፣ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ እንቅፋት የሆኑትን ዝቅተኛ የአገልግሎት የጥራት ደረጃና በዓለም ግንባር ቀደሙን የታሪፍ መጠን ለማሻሻልም ያግዛል…”ብለዋል።
እንደማሳረጊያ
በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመንግሥት የ2012 ዕቅድ ውስጥ በተለይ በኢኮኖሚ ዘርፍ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ፣ እንደሥራ አጥነት እና የዋጋ ንረት ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የተያዘው ዕቅድ የሕዝብን ወቅታዊ ችግር ማዕከል ያደረገ ነው። ይህን ዕቅድ በተለመደ አካሄድ ለመፍታት ማሰብ ግን በቀዳዳ በርሜል ውሃ ለመሙላት የመሞከር ያህል ነው። እናም የሕዝብን ተጨባጭ ችግሮች ታች ወርዶ መለየት፣ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማጥናት እና ሳይንሳዊ መፍትሔ ማስቀመጥ ላይ መንግሥት አተኩሮ ሊሠራ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012