አዲስ አበባ፡- የሠላም፣ የእርቅ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ስሜት እንዲዳብር ማድረግ ያስችላል የተባለው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ለማቋቋም የወጣው ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ፡፡
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት በአካሄደው መደበኛ ስብሰባው የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንደገለጹት፣የሰላም ጉዳይ የሁሉም ህብረተሰብ እንጂ ለአንድ ኮሚሽን የሚተው አይደለም፡፡
የእርቀ ሠላም ኮሚሽኑ ዋና ዓላማም በሀገራችን በተፈጠረው ችግር ተበድያለሁ የሚል አካል አለ፡፡ ይህ ተበድያለሁ የሚለውን ሰው ስሜት ተረድቶ በደሉን ከልቡ እንዲያወጣ ማድረግና ያለፈውን ይቅር በማለት የሠላም፣ የእርቅ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ስሜት እንዲዳብር ማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ በማህበረሱ ውስጥ ያለውን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቅራኔ መነሻው ምንም ይሁን ምን የቅሬታውን መንስኤ አጥርቶ የውሳኔ ሃሳብ በማቅረብ የእርቅ ስርዓት የሚያከናውን እንጂ ከዚህ ውጪ ያለውን የፖሊስና የፍርድ ቤት ሥራ የሚሠራ አይደለም ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ በምርመራ ሂደቱ የተከናወኑ ተግባራትን፣ በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የሥራ ኃላፊዎችን፣ በምርመራ ሂደት የተለዩ ዋና ዋና ጭብጦችንና የተደረጉ ማሻሻያዎችን በዝርዝር አቅርቧል፡፡ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ተከትሎም ከአባላቱ የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ወ/ሮ ላዋይሽ ተወደህ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ያለመኖሩን በዚህ ምክር ቤት አረጋግጠናል፡፡ ስለሆነም በዜጎች መካከል የተፈጠረውን ቁርሾ ለማከም የእርቀ ሠላም ኮሚሽን መቋቋሙ ተገቢነት አለው ብለዋል፡፡
እርቅ የሚጀምረው ከራስ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ መሀመድ አህመድ፣ እርቅ ለኢትዮጵያውን አዲስ ነገር ባይሆንም የኮሚሽኑ መቋቋም ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ በሀገሪቷ አሁን እየታየ ያለውን ችግር በዚህ የእርቀ ሠላም ኮሚሽን ብቻ መፍታት እንደማይቻልና ከዚህም በላይ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች እና የህግ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች መርምረው ያቀረቡትን የእርቀ ሠላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1102/2011 ሆኖ በአንድ ተቃውሞና በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል፡፡
በዕለቱ የምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤም በሙሉ ድምፅ ጸድቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
በፍሬህይወት አወቀ