አሁን ወቅቱ የፍሬው ወቅት ነው። እርግጠኛ ነኝ እኔ ማለት የፈለኩት አልገባችሁም። አይፈረድባችሁም፤ የጥቅምት ወር የፍሬ ወቅት ነው። አበባው አብቦ የሚጎመራበት፣ እሸት የሚደርስበት፣ በአጠቃላይ ብዙ የሰብል አይነቶች የሚያፈሩበት ስለሆነ የፍሬ ወቅት መሆኑ ግልጽ ነው።
ነገሩ ግን ወዲህ ነው። ‹‹ፍሬው›› ማለት ‹‹ፍሬሽ›› የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ሲቆላመጥ ነው። ‹‹ፍሬሽ›› ማለት ደግሞ በአማርኛ ‹‹አዲስ›› ማለት ነው። ይህ ቃል ለብዙ ነገር ቢያገለግልም ለአዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብቻ የተሰጠ እስከ ሚመስል ድረስ የሚዘወተረው ለተማሪዎች ነው።
ይሄን ቃል በአማርኛ ‹‹አዲስ›› እያሉ መጠቀም ይቻል ነበር። ዳሩ ግን ግቢ ውስጥ ፈጽሞ አዲስ ተብሎ አይጠራም፤ አልፎ አልፎ በጽሑፍ ማስታወቂያ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም የግቢው ሰራተኛ ‹‹ፍሬሽ ተማሪዎች›› እየተባለ ነው የሚጠራው። እዚያ ውስጥ ‹‹አዲስ›› የሚል ቃል የሚጠቀም ካለ የፍሬሽ ትርጉም እስከማይመስል ድረስ ለተማሪዎች ነው ተብሎ አይታሰብም። በግቢው ውስጥ ያሉ አገልግሎት ሰጪ አካላት ሁሉ የፍሬሽ እየተባሉ ነው የሚጠሩት። ፍሬሽ ካፌ፣ ፍሬሽ ቤተ መጽሐፍ፣ ፍሬሽ ዶርም፣ ፍሬሽ መማሪያ… ማለት የተለመደ ነው።
በሌላ በኩል ግቢ ውስጥ የሚበዛው ወጣት ነውና የአራዳ ቃላትም ይበዛሉ። እነዚህ የአራዳ ቃላት ደግሞ አብዛኞቹ ከእንግሊዘኛ ጋር የሚዳቀሉ ናቸው። ለማቆላመጥ ተብሎ አጠር የሚደረጉ ወይም ደግሞ ባያጥሩም አጠራራቸው ቀየር የሚደረግ ናቸው። ለምሳሌ ‹‹አይመችም›› ወይም ‹‹ጥሩ አይደለም›› ለማለት ‹‹አይሞድም›› ይባላል። ‹‹ሙድ›› የለውም እንደማለት ነው፤ ‹‹ሙድ›› ራሱ የአራዳ ቃል ነው።
ወደ ፍሬያችን እንመለስ። ‹‹ፍሬሽ›› የሚለው እንግሊዘኛ ቃል ለማቆላመጥ ተብሎ ‹‹ፍሬው›› ሲባል አማርኛ ሆነ ማለት ነው። አዲስ ገቢ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ በጣም ብዙ ገጠመኞች አሏቸው፤ እነዚህ ገጠመኞቻቸውን ዓመቱን ሙሉ ሲያወሯቸውና እርስበርስ ሲቀላለዱባቸው ይከርማሉ። ብዙ ገጠመኞችም በመሸወድና በመጭበርበር የሚፈጠሩ ናቸው።
ለእነዚህ አዳዲስ ተማሪዎች መሸወድና መጭበርበር ዋናው ምክንያት ነባር ተማሪዎች ናቸው። ነባር ተማሪዎች እንዲያላምዷቸውና እንዲያስተዋውቋቸው ይባላል እንጂ የሚያጭበረብሯቸው ነው የሚበልጠው። ነባር ተማሪዎች ይሄን ነገር እንደ አራዳነት ነው የሚቆጥሩት። በመሰረቱ ግን የማያውቅን ሰው ማጭበርበር አራዳነት ሳይሆን ፋራነት ነው። በአጠቃላይ ማጭበርበር አራዳነት ነው ባይባልም ባይሆን የሚያውቅን ሰው ማጭበርበር አራዳነት ቢባል ይሻላል። አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ።
በተማርኩበት ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሆነ ነው። ልጁ በግቢው ውስጥ አራዳ ተብሎ የሚታወቅ ነው። አጭበርባሪነቱና አታላይነቱም እንደ አራዳነት ተቆጥሮለት ‹‹እንዲህ አደረገ›› እየተባለ ይደነቅለታል። ብዙ የማጭበርበር ሥራዎቹም አዳዲስ ተማሪዎች ላይ ነው።
አዳዲስ ተማሪዎች ወደ ግቢ በሚገቡበት ወቅት አንድ ዕለት በጣም ነውር የሆነ ጥፋት ሰራ። በዚህም በፖሊሶች ተይዞ፣ መታወቂያውን ተቀምቶ ታስሮ ነው የተለቀቀው። እንዲህ ነበር ያደረገው።
አዲስ ተማሪዎች ሻንጣ ይዘው እየገቡ ነው። እነዚህን ተማሪዎች ላግዛችሁ፣ ላሳያችሁ ብሎ እየመራ ይሄዳል። ተማሪዎችን ከተመደቡበት የመኝታ ክፍል አሳልፎ ወደ ስቴዲየም ይሄዳል። የዩኒቨርሲቲው ስቴዲየም በግቢው በኩል ወጣ ብሎ ነው፤ ከስቴዲየሙ በኋላ የዓብይ ወንዝ ነው ያለው።
በስቴዲየሙ በኩል የሚያጠኑ ተማሪዎች መጽሐፍ እና ደብተር ይዘው እንጂ ሻንጣ ይዞ መሄድ የተለመደ ስላልሆነ ነገሩ አዲስ የሆነባቸው ፖሊሶች አስቆሟቸው። ወዴት እየሄዱ እንደሆነ ሲጠየቁ ተማሪዎች ወደ ግቢ እየገባን ነው አሉ፤ እየመራቸው የመጣም ልጁ መሆኑን ተናገሩ። ፖሊሶች ልጁን ይዘው፤ ተማሪዎችንም ወደ መኝታ ክፍላቸው አደረሷቸው። ልጁም የዲሲፕሊን ቅጣት ተቀጣ።
የዚህን ልጅ መሃይምነት ልብ በሉ! ከወለጋ ወይም ከመቀሌ የመጣና ለመጀመሪያ ጊዜ ባህርዳርን የሚያይ ሰው ማታለል ምኑ ነው አራዳነት? ማንም ሰው የቱንም ያህል አዋቂ፣ የቱንም ያህል ብልህ፣ የቱንም ያህል አራዳ ቢሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሄድበትን ቦታ መግቢያና መውጫ ሊያውቅ አይችልም፤ እንዲህ አይነትን ሰው ማታለል እንደማታለል ይቆጠራል? ለመጀመሪያ ጊዜ ግቢው ውስጥ የሚገባ ሰው የቱንም ያህል ብልህ ቢሆን እያንዳንዱን ቦታ ሊያውቅ አይችልም። ካፌውን ቤተ መጻሕፍት ነው ቢሉት ይሄዳል፣ የመኝታ ክፍሉን የመማሪያ ክፍል ነው ቢሉት ይሄዳል። ምክንያቱም አያውቀውም።
አዳዲስ ተማሪዎች ደግሞ በመታለላቸው ሀፍረትና መሸማቀቅ ይሰማቸዋል፤ መሳቂያ መሆናቸው ያሳፍራቸዋል። እዚህ ጋ ግን አጭበርባሪውም ሳቂውም ፋራ ነው። ግቢውን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያይ ሰው ተሳሳተ ብዬ ሊያስቀኝ አይችልም!
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የሚያስቁ እና የሚያዝናኑ ገጠመኞችም አሉ። እነዚህን ገጠመኞች ታዲያ አስቂኝ የሚያደርጋቸው አዲስ ተማሪ በመሳሳቱ ሳይሆን ከቆየ በኋላ በጭንቅት (ቴንሽን) ስለሚያደርጋቸው ነው። ገና ትምህርት እንደተጀመረ ውጥረትና ጭንቀት ይበዛል። በተለይም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ደግሞ መጫር (መባረር) አለ ስለሚባል በጭንቀት ነው ተማሪው ጥናቱን የሚያካሂደው። ይሄ ግን እንደየ ተማሪው የስነ ልቦና ጥንካሬ ይለያያል።
በንባብ (በተማሪዎች ቋንቋ ችከላ ይባላል) ሰሞን ብዙ አስቂኝ ገጠመኞች ይኖራሉ። እስኪርቢቶ ይዞ እስኪርቢቶ መፈለግ፣ ወደ ትምህርት ሲሄዱ የመማሪያ ክፍሉን አልፎ መሄድ፣ ልብስ ገልብጦ መልበስ፣ ቤተ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ማውራት (በድንገት)… የመሳሰሉት ግቢው ውስጥ ከቆዩና ከተላመዱት በኋላ የሚታዩ አስቂኝ ክስተቶች ናቸው። ግቢው ውስጥ ብዙ የቆየ ተማሪ ሲሳሳት ያስቃል፤ ምክንያቱም ያን ቦታ ብዙ ቀን ተመላልሶበታል። የተሳሳተው በቀልብ መወጣጠር ነው። ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመው የቦታ መሳሳት ነው። አንድ ጓደኛችን የነገረንን ገጠመኝ ልንገራችሁ።
የመኝታ ክፍል ያለበት ሕንጻ ውስጥ የፎቅ እና የክፍል መሳሳት ያጋጥማል። ፎቅ እየቆጠርን እንወጣለን (ቁጥር የሌለው ስላለ)። ክፍል ደግሞ በእያንዳንዱ በር ላይ ቁጥር ይጻፍበታል። በአንዳንድ ተማሪዎች በር ላይ ደግሞ ሌላ የቅጽል ስም ይጻፋል። ወይም የታዋቂ ሰዎች ፎቶ ሊደረግ ይችላል።
እናም ያ! ጓደኛችን በችኮላ ወደ መኝታ ክፍል እየሄደ ነው። አንዳንድ ጊዜ የተጻፈውን ቁጥር ሳናይ በልማድ ስንተኛው ላይ እንዳለ እናውቀዋለን፤ ለምሳሌ አንድ በር ወይም ሁለት በር አልፈን የሚገኝ ከሆነ፣ ወይም መጀመሪያው ላይ የሚገኝ ከሆነ ዝም ብለን በልማድ እንገባለን። ይሄው ልጅ እሱ ፎቅ ላይ ሳይደርስ ይታጠፋል። ይታጠፍና እሱ ያለበት ክፍል ተመሳሳይ ረድፍ ላይ ያለ ክፍል ውስጥ ገባ። የእሱ አልጋ ከሥር ነበር፤ የእሱው አልጋ ባለበት አቅጣጫ በኩል ተንደርድሮ ሄዶ ሊቀመጥ ሲል የአንሶላውና የብርድ ልብሱ አይነት ተቀየረበት። ማነው የቀየረው ብሎ ሊደነፋ ቀና ሲል በግርምት የሚያዩት ሰዎች ሁሉ ሌላ ናቸው፤ የዶርም ጓደኞቹ አይደሉም። ግራ ተጋባ፤ በጣም አፈረ። እንደምንም እፍረቱን ተቆጣጥሮ፤ ይቅርታ ብሎ ሹልክ ብሎ ወጣ።
ልጁ አንሶላውና ብርድ ልብሱ ተቀይሮ ሲያይ ወዲያውኑ ተሳስቻለሁ ብሎ አይደመድምም፤ ምክንያቱም እንዲህ አይነት መቀያየር ያለ ስለሆነ። አንዳንዱ ከላይኛው አልጋ ላይ መተኛት ይፈልጋል፤ አንዳንዱ ከሥር ያለው አልጋ ላይ መሆን ይፈልጋል። መቀያየሩ በፈቃደኝነት ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሌለበት ስለሚደረግ ነው ለቁጣ ተዘጋጅቶ የነበረው።
ሆን ተብሎ ዶርም ውስጥ የሚደረጉ ነገሮችም አሉ። ከዶርም ውስጥ አንደኛው ጓደኛችን መኝታ ያበዛ ነበር። ልክ እንደገባ ቶሎ መተኛት ነው። በዚህ ባህሪውም አልጋው ላይ ሰው ካገኘ ያለምንም ይሉኝታ ና ውረድ ብሎ ይናገራል። እናም አንድ ቀን በሌለበት ጉድ ሰራነው።
የሌሎቻችንን ትራስ ቀጣጥለን የተኛ ሰው አስመሰልነው፤ ከላይ የራሱን ብርድ ልብስ አለበስነው። ከሌላ ቦታ የመጣ እንግዳ ነው ለማለትም ተስማማን። በዚህ ሴራ ላይ እያለን ጓዳኛችን መጣ።
እንደመጣ ያልተለመደ ስለሆነበት ትንሽ ተንቆራጠጠ፤ ምክንያቱም የሚመጣ ሰው ጋደም ብሎ ያወራል እንጂ ከሰው አልጋ ላይ ለጥ ብሎ እንቅልፍ አይተኛም። ትንሽ ግራ ከተጋባ በኋላ ‹‹ማነው የተኛው?›› ብሎ ጠየቀን። ዶርም ቁልፍ ሆኖበት ከእነገሌ ዶርም የመጣ ነው ብለን ተናገርን። በይሉኝታና በብስጭት መሃል ሆኖ አሁንም ሲንቆራጠጥ ቆየ። በኋላ ግን ከሁኔታችን የሚረዳው ነገር ሁሌ የተንኮል ሴራ መሆኑን ጠረጠረ። ሌላ ነገር እያወራን ስንስቅ ያ! የሳቅንበት ነገር ለመሳቂያነት ብቁ እንዳልሆነ ሲጠረጥር ገለጥ አድርጎ አየው፤ ከዚያ በኋላማ ምኑን ልንገራችሁ! እሱ በቁጣና በስድብ፤ እኛ በሳቅ ዶርሙን በአንድ እግሩ አቆምነው!
አንዳንድ ገጠመኞች አስቂኝ ሲሆኑ አንዳንዶች ደግሞ ችግር የሚያስከትሉም አሉ። በግቢ ውስጥ በጣም የሚፈራው ነገር ወደ ሴቶች መኝታ ክፍል መሄድ ነው፤ ምክንያቱም ቅጣቱ ከባድ ነው። ታዲያ ብዙ አዲስ ተማሪዎችን የሚያጭበረብሯቸው በዚህ ነው። ደግነቱ ገና ሲገቡ ከሆነ አለማወቃቸው ከግምት ውስጥ ስለሚገባ አይቀጡም። ካፌ ውስጥም ከካፌው አሰራር ውጭ የሆነ ነገር በመንገር ያሳስቷቸዋል።
በነገራችን ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ተማሪዎች ወደ ግቢ ሲገቡ የሚቀበሉ ተማሪዎች ይዘጋጃሉ። እነዚህ ተማሪዎች ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ናቸው፤ ለታማኝነታቸውም የሚለብሱት የደንብ ልብስና የአንገት ባጅ አለ። ዩኒቨርሲቲው ከሚገኝበት ከተማ መናኸሪያ ተቀብለው ግቢ ያደርሳሉ። የዩኒቨርሲቲው ተሽከርካሪዎች በዚያን ሰሞን ሥራቸው ይሄው ነው። ተማሪዎች የራሳቸው ሰው የሆነ ነባር ተማሪ ካለ ግን ከእሱ ጋር ሊሄዱ ይችላሉ። ለመቀበል ኃላፊነት የሚሰጣቸው ተማሪዎች አዲስ የመጣውን ተማሪ ጠይቀው አረጋግጠው ነው፤ ከነባር ተማሪ ጋር እንዲሄድ የሚፈቅዱለት፤ አለፍ ሲልም በደንብ አስከባሪዎች ብቻ እንዲገቡም ይደረጋል። ነባሮቹን አለማመን ብቻ ሳይሆን ግርግር ስለሚፈጥር ነው።
ነባር ተማሪዎች አዲስ ተማሪን ማጭበርበር አራዳነት አይደለምና ከድርጊታቸው ቢቆጠቡ! ለአዲስ ተማሪዎች መልካም የትምህርት ዘመን!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
ዋለልኝ አየለ