ከትውልድ ሀገሩ ርቆ ለመውጣት ምክንያቱ ከወንድሙ ያለመስማማቱ ነበር። በልጅነቱ የትምህርት ዕድል ያለማግኘቱ ሲያበሳጨው ኖሯል፡፡ ያም ሆኖ ግን ዕድሜው ከፍ ሲል ትዳር ይዞ ልጅ በመውለዱ ደስተኛ ነበር፡፡ ይህ መሆኑ ብቻ ግን በቂ አልነበረም። ከታላቅ ወንድሙ ጋር የነበራቸው ቁርሾ መሬቱን አስነጥቆ ለስደት አብቅቶታል፡፡
ቀዬውን ለቆ አዲሰ አበባ በገባ ጊዜ ደግሞ የከተማ ህይወት ቀላል አልሆነለትም። ይጠጋበት ዘመድ አልነበረውምና ጎዳና ውሎ በማደር ቀናትን ገፍቷል፡፡ እያደር ግን ኑሮውን ተላመደ፡፡ እሱን መሰሎች መኖራቸውን ሲረዳ የቀንሥራ ሠርቶ ለዕለት ጉርሱ ማግኘት ጀመረ።
ደረሰ የአዲስ አበባን መውጫና መግቢያ ካወቀ ወዲህ ከበርካቶች ተላምዶ የኔ የሚላቸውን ባልንጀሮች አፈራ፡፡ የከተማ ህይወት መልከ ብዙ መሆኑን ያውቃል። በተለይ አዲስ አበባ ለፍተው ካደሩባት የድካምን ዋጋ የማትነፍግ መሆኑ ከገባው ቆይቷል፡፡
ከገጠር ከወጣ ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ገንዘብ ኪሱ ገብቷል፡፡ ከተሜዎችን ለመምሰል ያደረገው ሙከራ ደግሞ ጊዜ አልፈጀበትም። ያማረውን ለብሶ የፈለገውን ተጫምቶ እንደጓደኞቹ የሆነባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አልነበሩም፡፡ ያም ሆኖ ግን በሌሎች ዘንድ የሚያየው የኑሮ ለውጥና መሻሻልን ከእራሱ ጋር እያወዳደረ መናደዱ አልቀረም፡፡
አንዳንዶች በድካም ወገባቸው ሳይጎብጥና እጃቸው በሥራ ሳይሻክር እንዳማረባቸው ሲራመዱ አይቷል፡፡ ጥቂት የማይባሉትም ያለምንም ተግባር ከአንድ ስፍራ ተቀምጠው የሚውሉና እንዳሻቸው ገንዘብ የሚመነዝሩ ናቸው፡፡
ደረሰ እነሱን ባየ ጊዜ ሁሌም ራሱን ይጠይቃል፡፡ ያለፋበትን ገንዘብ አግኝቶ፣ ያለድካም አምሮ መታየት የሚቻልበት ሚስጥር ያስገርመዋል፡፡ ውሎ አድሮ ግን የጥያቄውን ምላሽ የሚያገኝበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ከአንዳንድ ያገሩ ልጆች ጋር በዋለ ጊዜ እውነታውን አወቀው፡፡ ይህኔ እንደነሱ ለመሆን አስቦ በመንገዳቸው ሊጓዝ ከቁርጥ ውሳኔ ደረሰ፡፡
አሁን የገጠሩ ወጣት የኑሮን አቋራጭ መንገድ አውቆታል፡፡ ሁለቱ ያገሩ ልጆች ከእሱ ተላምደው ሚስጠሩን ከነገሩት ወዲህም ለሙከራ ያስጀመሩት ቅምሻ በእጅጉ ጥሞታል፡፡ እንደዋዛ ገንዘብ ሲያገኝና የልቡ ሲሞላ ደግሞ ከእነሱ ልቆ አዳዲስ ስልቶችን እስከመንደፍ ደርሷል፡፡
ደረሰና ጓደኞቹ ዝርፊያን መተዳደሪያቸው ካደረጉ ሰነበቱ፡፡ እስከዛሬ የመረጡትን ቦታ ለይተው፣ ሌሊቱን ለመዝርፍ ያደረጉት ሙከራ ሲሳካላቸው ቆይቷል፡፡ ሁሌም ለዝርፊያ ከመውጣታቸው በፊት በጠረጴዛ ዙሪያ ይመክራሉ፡፡ ሀሳብ ተለዋውጠውና በጥያቄና መልስ አዳብረው ከውሳኔ ይደርሳሉ፡፡
የሌሊት ዘራፊዎቹ ቅድሚያ የሚሰጡት ቤት ሰብሮ ሥርቆትን ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉ መቼ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ያውቃሉ። ለእነሱ ጊዜና ሰዓቱ ወሳኝ የሚባል ነው። ሌሊቱ ሲጋመስና አየሩ ዝናብ ሲሆን ይበልጥ ይመቻቸዋል፡፡ ውድቅት መሆኑና ጭር ማለቱ ደግሞ ለእነሱ መልካም የሚባል አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡
ሁሌም ተግባራቸውን ለመከወን የሚያግዛቸውን መሣሪያ ይይዛሉ፡፡ ገመድ፣ መሰርሰሪያና የእጅ ባትሪን ከጎናቸው እይነጥሉም። በለስ በቀናቸው ጊዜ ደግሞ ከአንድ በላይ ቤት ይዘርፋሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ ሥራቸው የጋራ ነው፡፡ አንዳቸው ለመዝረፍ ውስጥ ሲዘልቁ አንዳቸው ሰው መምጣቱን ይቃኛሉ፡፡ አስፈላጊ ከሆነም ሳይቀደሙ ለመቅደም ይዘጋጃሉ፡፡
ሦስቱ ባልንጀሮች በዓይን ብቻ ይግባባሉ። ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉና ነገራቸው ሁሉ በምክክር ነው። ዘረፋ ባላቸው ጊዜ ሰዓቱ እስኪደርስ የሚያሳልፉበትን ስፍራ ያውቃሉ፡ ፡ ከሚሰረሰረው ቤት የሚነቃና የሚታገላቸው ካለም ራሳቸውን ለአደጋ አያጋልጡም፡፡ መውጫ መግቢያውን ለይተው ለማምለጥ የሚቀድማቸው የለም፡፡
እነሱ በሚመክሩባቸው መጠጥ ቤቶች የሚቀላቀላቸውን አይፈልጉም፡፡ የያዙትን ፉት እያሉ ያስቀዱትን እየጨለጡ ሲወያዩም በሚስጥር ነው፡፡ ሰዓቱ ደርሶ ካሰቡት ግቢ ሲደርሱ ደግሞ ጭካኔን ይላበሳሉ፡፡ የመጣውን ከመጋፈጥ ይልቅ ያዩትን ለማጥቃት ጥንቃቄያቸው የተለየ ይሆናል። በተለይ ደረሰ በዚህ ጉዳይ ያለው አቋም ከሌሎቹ ይለያል፡፡ ጥርጣሬ በያዘው ልቡ ፈጣን ዓይኖቹ ካረጋገጡለት ቀድሞ ርምጃ ለመውሰድ የሚያህለው እንዳማኖር ይታወቃል፡፡
ሁሌም የደረሰን ፈጣን ውሳኔ የሚያውቁ ባልንጀሮቹ ከዘረፋው ይልቅ የማጥቃት ሥራውን ይሰጡታል፡፡ ጨካኝነቱ ከፍጥነት ጋር መሆኑን ስለሚረዱም ሀሳባቸውን በእሱ ትከሻ ጥለው ያሰቡትን ያደርጋሉ፡፡
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቀጠና የመረዳጃ ዕድር አካባቢ ያሉ አንዳንድ ነዋሪዎች ሁሌም በሥጋት ውስጥ ናቸው። ቤቶቻቸው በእነዚህ ዘራፊዎች ተሰርስሮ መዘረፉን ከነጋ በኋላ በማወቃቸው በቁጭት ሲብከነከኑ ቆይተዋል፡፡
እስከዛሬ እነዚህን የሌሊት ሌቦች እጅ ከፍንጅ ይዞ ለሕግ ያቀረበ የለም። አንዳንዶች ቢሞክሩ እንኳን ከእጃቸው ሳይደርሱ ያመለጧቸው አጋጣሚዎች ይበረክታሉ። እነ ደረሰ ብዙ ጊዜ የነዋሪውን በእንቅልፍ መዳከሚያ ሰዓት ለይተዋል። ጭር ሲልና ጨለማው ሲጠናም የሚያደርጉትን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ደጋግመው በፈፀሟቸው ዝርፊዎች ያለመያዛቸው ደግሞ ሁሌም በአዲስ ዕቅድና በሌሎች አካባቢዎች ጭምር እንዲገፉበት ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡
የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም ምሽት
በዚህ ቀን ምሽት ከአንድ መጠጥ ቤት በቀጠሮ የተገናኙት እነደረሰ በለሊቱ ተግባራቸው ላይ በትኩረት መምከር ይዘዋል። ስፍራው በአረቄ ሽያጭ የሚታወቅ ቢሆንም እነሱ ግን ከሌሎች በተለየ ቢራ እየተጎነጩ ነው፡፡
የዛን ቀን ከሦስቱ ባልንጀሮች ውጭ ሌላ አንድ ሰው ተቀላቅሏቸዋል። ይህ እንግዳ ከእነሱ የተለየ ባለመሆኑ ሚስጥራቸውን መደበቅ አላስፈለጋቸውም። በአንድ ጠረጴዛ ከበው ሲወያዩ ይህ ሰው ሀሳብ በመስጥትና ተጨማሪ ዕቅዶችን በመንደፍ ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ ከቢራው እየደገሙ ምሽቱን ሲያጋምሱ ደግሞ ለዘረፋ የሚሰማሩበትን አካባቢ ለይተው ከስምምነት ደርሰው ነበር።
መጠጥ ቤቱ እንደሚዘጋ ሲገባቸው ሁሉም ሂሳባቸውን ከፍለው በየተራ ወጡ፡፡ ያሰቡት ሰዓት እስኪደርሰ ከአንድ ቦታ መቆየት እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ ከዚህን ሰዓት በኋላ የሚቆዩበት ሌላ ስፍራ እንደማይኖር እርግጠኞች ሆነዋል፡፡ እናም ጊዜውን ከአንድ ቦታ ተሸሽገው ማሳለፍ እንዳለባቸው ተነጋግረው ከስምምነት ደረሱ፡፡
ሌሊቱ ተጋምሶ የናፈቁት ሰዓት እስኪቃረብ ሰፊውን ሜዳ አቋርጠው መንደሮቹን አለፉ፡፡ ጨለማውን ተተግነውም ከአንድ ጥግ ጎናቸውን አሳረፉ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ በዚህ ሰዓት በመንገዱ የሚያልፍ መንገደኛ ከተገኘም እንደማይምሩት እየናፈቁ ኮቴና ድምጽ ሲያዳምጡ ቆዩ፡፡ ብቅ ያለ አንድም ሰው እንደሌለ ሲያውቁም ጨረቃዋን አንጋጠው እያዩ የእጃቸውን ሰዓት መቁጠር ጀመሩ፡፡
አሁን ከሌሊቱ 9 ሰዓት ተኩል ሆኗል። በእነሱ አቆጣጠር ይህ ሰዓት ላሰቡት ዓለማ መልካም የሚባል ነው፡፡ የጊዜውን መድረስ እንዳወቁ ከተኙበት ፈጥነው ተነሱና የመንገዳቸውን አቅጣጫ ለዩ። በተስማሙበት መንገድ ጉዞ ሲጀምሩም ዝናብ ማካፋቱን አስተውለው በደስታ ተያዩ፡፡ እነሱ ለዝርፊያ ሲሰማሩ ዝናብ የሚጥል ከሆነ ገዳቸው የሰመረ ይሆናል፡፡ ዝናቡ በዕንቅልፍ ላይ የሚገኙትን ነዋሪዎች አባብሎ እንዳይነቁ በማድረግ ተባባሪያቸው ሆኖ ቆይቷል፡፡
ሰመረና አራቱ ጓደኞቹ በርቀት አይተው ለመዝረፍ ከተስማሙበት መኖሪያ አጠገብ ሲደርሱ እንደተለመደው ሥራዎችን ተከፋፈሉ። ሰመረ ወደግቢው ዘሎ ሲገባ አንዳቸው ከውጭ ቆመው እንዲቃኙና ሌሎቹም ወደውስጥ ዘልቀው ዝርፊያውን እንዲፈፅሙ ተነጋገሩ፡፡ ወዲያው እንዳሰቡት ሆኖ ግቢውን ለዘረፋ አመቻቹት፡፡
ወደውስጥ አልፈው ጥቂት ከመራመዳቸው በፊት ግን ግቢውን በተጠንቀቅ ሲጠብቁ የነበሩ ጆሮዎች ነቅተው ያሰቡት ስላልተሳካ በሩጫ እግሬ አውጭኝ ሲሉ ተፈተለኩ፡፡ በየአቅጣጫው ተከፋፈለው ጥቂት እንደቆዩ ግን ዳግም ተገናኝተው በቀጣዩ ዘረፋ ላይ ተነጋገሩ፡፡
ከንቁዎቹ ጠባቂዎች ካመለጡ በኋላ ቀሪ የዝርፊያ ጊዜ እንዳላቸው ሲያውቁ ከአንድ መኖሪያ ቤት ገብተው መሰርሰራቸውን ቀጠሉ፡፡ እንዳሰቡት ሆኖም ሞባይሎችና ሌሎች ንብረቶችን ይዘው ወጡ፡፡ አሁንም ሰዓታቸውን ዳግመኛ ተመለከቱ፡፡ ጊዜ እንዳላቸው ሲያውቁ ሌላ ዕድል ሊሞክሩ ከአንድ ግቢ ዘለቁ፡፡ በስፍራው የነበሩትን ልብሶች ሰብስበው ከአካባቢው ለመራቅ ያገዳቸው አልነበረም፡፡
በለስ የቀናቸው የሌሊቱ ዘራፊዎች አሁን በድርጊታቸው መነቃቃት ይዘዋል:: የጊዜው አለመንጋትና የዝናቡ ማየል ደግሞ እያገዛቸው ነው፡፡ ይህ መሆኑም ለተጨማሪ ተመሳሳይ ዝርፊያ ዕድላቸውን የሚያሰፋው ሆኗል፡፡
ባለቆርቆሮው በር ግቢ
ከሁለቱ መኖሪያ ቤቶች የተሳካ ዘረፋ በኋላ አራቱ ሰዎች በትኩረት ካነጣጠሩበት አንድ የቆርቆሮ ግቢ በራፍ ላይ ደርሰው ማኝዣበብ ጀምረዋል፡፡ ይህ ግቢ ዙሪያውን በጥቅጥቅ የእንጨት አጥር የተከበበ ስለመሆኑ በርቀት ያስታውቃል፡፡ ይህ መሆኑ ግን ልበ ሙሉዎቹን ዘራፊዎች ለሥጋት አልጣለም፡፡
ግቢውን ዘልቀው ወደ ውስጥ ለማለፍና እንደነገሩ የተሸጎረውን በር እጃቸውን አሾልከው ለመክፈት ለእነሱ በጣም ቀላል ሆኗል፡፡ ከግቢው መሀል ከደረሱ በኋላም ለዝርፊያው ማስቀደም ያለባቸውን ቤት ለመምረጥ ጊዜው ነበራቸው፡፡
በግቢው ከነበሩት ቤቶች መሀል የሁሉንም ቀልብ የሳበው ፊት ለፊት የሚታያቸው ፀጉር ቤት ሆኗል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ደግሞ የሚዘረፉ ዕቃዎች እንደሚኖሩ አራቱም እርግጠኞች ሆነዋል፡፡ ፊትና ኋላ ሆነው የገቡት ዘራፊዎች ይህን ሲያስቡ በእጃቸው ያለውን መሰርሰሪያና ጉጠት መጠቀም እንዳለባቸው ተግባቡ፡፡
ያሰቡትን ከማድረጋቸው አስቀድሞ ግን እንደተለመደው ሥራ ተከፋፍለው በየቦታቸው ተገኙ፡፡ ደረሰም አንዳች የሚያህል ጥርብ ድንጋይ ይዞ ዝርፊያውን ሊያስጀምር ለአጋሮቹ ምልክት ሰጠ፡፡
እንዲህ ከሆነ አፍታ ጊዜ በኋላ የግቢው ውሻ ኮቴ ቢጤ ቢሰማት ጠጋ ብላ ጠረን አሽተተች። በድንገትም ሰዎቹን ብታይ ባልተለመደ ሁኔታ ጩኽት እያሰማች ተሸከረከረች፡፡ ይህኔ ከግቢው የዘለቁት ዘራፊዎች በድንጋጤ ተያዩ፡፡ ሰብረው ከገቡበት ፀጉር ቤት ሆነውም ይይዙት ይጨብጡት አጥተው ተቁነጠነጡ፡፡ ከውጭ በኩል አካባቢውን በንቃት የሚቃኘው አራተኛው ጠባቂ ጓደኞቹ ያገኙትን ይዘው እስኪወጡ ከላይ ከታች ይላል፡፡ ደረሰ ደግሞ ከትልቁ ቤት በረንዳ ሥር ትልቅ ድንጋይ እንደጨበጠ የሚሆነውን ይጠብቃል፡፡
አሁን የግቢው ጭርታ በትንሸዋ ቀይ ውሻ ጨኸት ተረብሿል፡፡ ይህ አይነቱ አጋጣሚ ደግሞ የተኙትን ከዕንቅልፍ ቀስቅሶ ግቢውን ሊያስፈትሽና እነሱንም እጅ ከፍንጅ ሊያሲዝ ይችላል፡፡ ደረሰ ይህን አስቦ ሳይጨርስ በድንገት የሳሎኑ በር ተከፍቶ የቤቱ አባወራ ሲወጡ ተመለከተ፡፡
ሰውዬው በስፍራው የሆነውን በመጠ ርጠራቸው ከበርንዳው ወርደው ወደ ግቢው መሀል አመሩ፡፡ ሁኔታቸው የገባው ደረሰ ግን ጓደኞቹ ያሉበት ክፍል ከመድረሳቸው በፊት በእጁ የያዘውን ትልቅ ድንጋይ ወርውሮ ግንባራቸው ላይ አሳረፈው፡፡
ድንገቴውንና ከባዱን የድንጋይ ምት መቋቋም ያቃታቸው አባወራ ፊታቸው በትኩስ ደም ተሸፍኖ በጀርባቸው ተዘረሩ፡፡ ይህኔ ዘራፊዎቹ በእጃቸው የገባውን ንብረት ተሸክመውና የግቢውን በር ከፍተው ሰፈሩን አቋርጠው ተራመዱ፡፡ ጥቂት አለፍ እንዳሉ ይዘውት የነበረውን የእጅ ባትሪ ረስተውት እንደወጡ ትዝ አላቸው፡፡
ሌቦቹ በዛን ሌሊት በለስ ቀንቷቸው ሦስት ቤቶችን ዘርፈዋል፡፡ በአንደኛው መኖሪያ ሰዎቹ ነቅተው ሲያባርሯቸው በዚህኛው ቤት ደግሞ ሳይቀደሙ በፊት ቀድመው ያሰቡትን አድርገዋል። ይህን እያወሩ በመንደሮቹ መሀል አቋረጡ። ለዛሬው በእጃቸው የገባው እንደሚበቃ ተስማምተዋል፡፡ አሁን እየነጋ በመሆኑ ወደየማረፊያቸው መሄድ ይኖርባቸዋል፡፡
አራቱ ከየቤቱ የሰበሰቡትን ንብረት ተሸክመው መንገዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሳያስቡት ከተመልካች ዓይን እንዳይገቡም እየተጠነቀቁ ነው። እንዳቀዱት አልሆነም። ድንገት ከሁለት ሰዎች ጋር ተፋጠጡ። ሰዎቹ አለባበስና አረማመዳቸው የተለየ ነው፡፡ ፖሊሶች፡፡
አራቱ ባልንጀሮች እነሱን ባዩ ጊዜ የተሸከሙትን ወርውረው ‹‹እግሬ አውጭኝ›› ሲሉ ፈረጠጡ፡፡ ፖሊሶቹ እንዲቆሙ እያስገደዱ ተከተሏቸው፡፡ ሦስቱን አልደረሱባቸውም፡፡ ደረሰ ላይ ግን ደረሱበት። ይዘውትም ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመሩ፡፡
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ በመንደሩ መሀል የተዘረፉ ንብረቶችን ትተው ካመለጡት ሌቦች መሀል ሁለቱን በጥቆማ አግኝቶ በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡ ዘራፊዎቹ በሰጡት የዕምነት ክህደት ቃልም በአባወራው ግቢ ወስጥ ስለፈፀሙት ድርጊት ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ አባወራው በድንጋይ በተፈፀመባቸው ከባድ ጥቃትና ባጋጠማቸው የከፋ ጉዳት ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ፖሊስ አራተኛውን ተጠርጣሪ ባያገኝም በሦስቱ ጓደኛሞች ላይ የጀመረውን ምርመራ ቀጥሏል፡፡ በመዝገብ ቀጥር 796/2008 የተከፈተው ፋይልም በመርማሪ ፖሊስ ምክትል ኢንስፔክተር ግርማ በቀለ መረጃ ተሰንዶበት ተዘጋጅቷል። ፖሊስ የተከሳሾችን ድርጊትና ማንነት በአግባቡ ካወቀና የፈፀሙትን ድርጊት በበቂ ማስረጃዎች ካረጋገጠ በኋላ ጉዳዩን ለዓቃቤ ሕግ አስተላልፏል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
መልካምስራ አፈወርቅ