አዲስ አበባ፡- አጋር ፓርቲዎችን ያካተተ የኢህአዴግ ውህደት እንዲኖር በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መኖራቸውን እና አሁንም ውህደቱን አጥብቀው እንደሚፈልጉት የአጋር ፓርቲዎች የቀድሞ እና የአሁን አባላት ተናገሩ፡፡
ቀድሞ በአጋር ፓርቲዎች ውስጥ የነበሩ፤ አሁን ግን የሌሉ እና አሁንም በአጋር ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ የአፋር፣ የሶማሌ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የጋምቤላ ክልል አጋር ፓርቲዎች የሆኑት የአብዴፓ፣ ሶህዴፓ፣ ቤጉህዴፓ እና ጋህአዴን አባላት ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ «ቀድሞም ቢሆን እንደሁለተኛ ዜጋ መቆጠር የለብንም፤ የሚገባንን ክብር እና ውክልና አግኝተን አገራዊ ውሳኔ ላይ ድምፃችን ይሰማ» የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ታዳጊ ክልል እየተባለ ከሚሰጣቸው ድጎማ ይልቅ በአገሪቱ በሚካሄዱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆነው የክልላቸውን ሕዝብ ተጠቃሚ የማድረግ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን በማመልከት፤ የኢህአዴግን ውህደት አጥብቀው የሚፈልጉት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለስድስት ዓመታት በአብዴፓ አባል እንደነበሩ አሁን ግን ከፓርቲው መውጣታቸውን የተናገሩት የሰመራ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ መሃመድ አህመድ እንደተናገሩት፤ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) አጋር መባሉ በክልሉ ሕዝብ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮ ነበር፡፡አጋር በመሆናቸው ብቻም በአገር ጉዳይ ላይ መወያየትም ሆነ መወሰን እንዳይችሉ ተደርጎ ቆይቷል፡፡በዚህ ምክንያት በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ የነበረ ሲሆን፤ በዚህም የተነሳ የክልሉ ኢኮኖሚ በእጅጉ እንዲጎዳ ማድረጉንም አመልክተዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል አቶ መንግስቱ ቲሳም በአገራዊ ትልልቅ ውሳኔዎች ላይ መሳተፍ አለመቻላቸውና ሌሎች የወሰኑትን ተቀብለው በሚሰጠው አቅጣጫ ብቻ ተመስርተው መስራታቸው በራስ ውሳኔ እንደመስራት
የሚቀልል አለመሆኑን እና ሕዝቡንም ተጠቃሚ ለማድረግም እጅግ እንደሚያዳግት ተናግረዋል፡፡ይሁንና አሁን ኢህአዴግ ሊተገብረው እያሰበው ያለው ውህደት የዓመታት ጥያቄያቸው እንደሚመልስና በአገራቸው ጉዳይ እኩል ተሰታፊ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2012
ምህረት ሞገስ