መንግስት አርሶ አደሩን ሁለት ሶስት ርምጃ በማሻገር ራሱንና ቤተሰቡን ከመመገብ ባለፈ ምርታማነቱን ማሳደግ አለበት፡፡ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እንዲላመድ በቅርበት እገዛና ድጋፍ እየሰጡ በማብቃት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር የጎላ ሚና ያበረክታሉ፤ በዚህም ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሆነውን የሥራ አጥነትን ችግር ይቀርፋሉ በሚል ተስፋ ከጣለባቸው ተቋማት አንዱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ መሆኑን የሚያመለክቱት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብዲሳ አብዱላሂ ናቸው፡፡
የሀገራችን የኢኮኖሚ ምሰሶ ግብርና ነው፡፡ ግብርና ላይ የሚካሄደው ሥር ነቀል ለውጥ የሀገርን ኢኮኖሚ መለወጥና ማሻገር ይችላል፡፡ ስለዚህ በአርሶ አደሮቻችን ዘንድ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲቀረፉ እና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በግብርና ኮሌጆች ማሰልጠን አለብን፡፡ በስልጠናው ሂደት ክትትል በማድረግ ሰልጣኝ አርሶ አደሮች ከነበረባቸውና ክፍተታቸው ተለይቶ ከተሰጣቸው ሥልጠና የጨበጡትን ቁም ነገር መመዘንና ማወቅ እንዲቻል ፣በቀጣይም በዘላቂነት መደገፍ እንዲቻል የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ወስደው ማለፍ ይኖርባቸዋል በሚል መሰረት የተሻለ ሥራ መስራት መቻሉን የትግራይ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ ሀዱሽ ይናገራሉ፡፡
ዶክተሩ እንዳሉት፤ ክልሎች ለአርሶ አደሮች ሥልጠና እና የብቃት ምዘና ትኩረት እየሰጡ አለመሆናቸው ሀገሪቱ ከድህነት ተጣብቃ እንድትኖር መፍረድ ነው፡፡ ሃላፊነቱን በተገቢው የማይወጣ አካል ተለይቶ መታረም አለበት የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ አርሶ አደሮቻቸውን በተገቢው ማሳመን ባለመቻላቸው እንጂ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ከነበረበት የተሻለ ምርት በእጥፍ እንደሚያገኝ በተግባር ካሳዩት ለመጠቀም ወደ ኋላ አይልም፡፡
ለዘመናት ከሚጠቀምበት ባህላዊ የአስተራረስና አሰራር የተሻለውን ካሳዩት፣ምርጥ ዘርና የተሻሻሉ ግብዓቶች ተጠቅሞ መለወጥ እንደሚችል በተግባር ካረጋገጡለት፣ምርጥ የእንስሳት ዝርያዎችን ተጠቅሞ በአጭር ጊዜ ለውጥ እንዲያይ ካደረጉት፣ብቁ በሆኑ እና የአርሶ አደርን ሥነልቦና በሚያውቁ ባለሙያዎች ከልብ እንዲለወጥ ክትትል ካደረጉለት አርሶ አደሩ ራሱ ፈልጎ ተግባር ውስጥ መግባት አያዳግተውም፡፡
ባለው እውቀት ላይ ተጨማሪ ክህሎት የሚፈጥር ስልጠና ካገኘ ወደ ኋላ በፍጹም አይመለስም፡፡ በዚያው ልክ በማይጠቅም ስልጠና ወይም ስብሰባ ጊዜውን ማጥፋትም አይፈልግም፡፡ የትግራይ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት በሁሉም ወረዳዎች ተደራሽ አለመሆናቸው እንጂ የሥልጠና ማዕከላቱ ባሉባቸው (በተሟሉባቸው) 26 ወረዳዎች አርሶ አደሩን በተግባርና በአመለካከት የሚለውጥ ሥራ መሰራቱን ዶክተር ሙሉጌታ ይገልፃሉ፡፡
የአርሶ አደሩን አሰራር በማዘመንና በማሻሻል ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል በተጨባጭ ከትግራይ ክልል አርሶ አደሮች ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል፡፡ በኩታ ገጠም አዋጭና በገበያ ላይ ጥሩ ገንዘብ ሊያስገኙ የሚችሉ፣ እንዲሁም በአካባቢው በሰፊው ምርት የሚሰጡ ሰብሎችን ግብዓት በልክ ተጠቅሞ እንዲያመርት የሚያስችል ሥልጠና ካገኘ እንዴት አይቀበልም? እንዴት አይፈልግም? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሙሉጌታ አገላለጽ፤ የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚለውጥ ሥራ እስካልተሰራ ድረስ በሌሎች አካላት ላይ ለውጥ የሚያመጣ ስራ መስራት አዳጋች ነው። የሀገሪቱ ሰፊ አካል የሆነው መለወጥ ሲጀምር እያንዳንዱ ችግር ይቃለላል፡፡ በምግብ እህል ራስን መቻል፣ ሥራ አጥነትን ማስወገድ እና በኢንዱስትሪዎችና በግሉ ዘርፍ ተሰማርቶ ውጤታማ መሆን የሚችል አምራች መፍጠር ይቻላል ባይ ናቸው፡፡
ሌሎች የተቋሙን ተልዕኮም ችላ አለማለታቸውን የተናገሩት ዶክተሩ፤ ሁሉንም ተልዕኮዎች በእኩል ደረጃ መፈጸምና ሀገራችን የምትናፍቀውን ለውጥ በየዘርፋችን በማስመዝገብ ለኢኮኖሚው የድርሻ ችንን ማበርከት ይገባናል።አርሶ አደሮችን አሰልጥኖ የብቃት ምዘና እንዲወስዱ ማድረግ ቀላል ተግባር አይደለም፡፡ በቅንጅት መስራትን ይጠይቃል፤ መውጣት መውረድን፣ መድከምን ይጠይቃል፡፡
በመሆኑም ትግራይ በቀጣይም ከዚህ የተሻለ ለመስራት በ2012 ዓ.ም በመደበኛ 36 ሺህ፣በአጫጭር 120 ሺህ እና በአርሶ አደር 45 ሺህ ሰልጣኞች ለማስተናገድ ማቀዳቸውን ጭምር ለተሞክሮ አንስተዋል፡፡ ሁሉም ክልሎች እኩል አፈጻጸም ካላመጣን እንደሀገር መራመድ ይሳነናል፡፡ ስለዚህ እኩል መራመድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አኳታ ኡሚዮ ኡጁሉ በበኩላቸው፤ በብቃት ምዘና ዙሪያ የህብረተሰቡ አመለካከት አልተቀየረም፡፡ በሌሎች ክልሎች እንደሰማነው ምዘናው እስከ አርሶ አደሮች ድረስ እየተሰራበት ነው፡፡ ለእኛ ጥሩ ተሞክሮ ይሆናል፡፡ ስልጠናውን ወስዶም መመዘን የማይፈልገው ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡ በቀጣይ በትኩረት መስራት እንደሚገባን ብዙ ልምድ መቅሰም መቻሉን በማስታወስ፡፡
በአጠቃላይ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አርሶ አደሮችን ጨምሮ አጫጭር ስልጠናዎች እንዲወስዱ በማድረግ ከስልጠናው በፊት የጀመሩትን ስራ ውጤታማ በሆነ አሰራር አጠናክረው የሚያስቀጥሉበት ነው፡፡ በመሆኑም ገበያ ተኮር በሆኑ እድገት ተኮር ዘርፎች በቂ ክህሎት በብቁ ባለሙያ በማስጨበጥ ምርታማነታቸውን ማሳደግ አስፈላጊ ሲሆን በቂ የገበያ ትስስር መፍጠርም ተገቢ ነው፡፡ በስልጠናዎች ራስን በማጎልበት የብቃት ምዘና በድፍረት ወስዶ ብቁነቱን ማረጋገጥ የቻለ የሰው ሃይል ማብቃት ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2012
ሙሐመድ ሁሴን