አፍሪካ በተፈጥሮ ጸጋ በእጅጉ የታደለች አህጉር ናት። ዜጎቿ በችግር፣ በረሀብ፣በስራ አጥነት የሚሰቃዩባት፤ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ትውልድ የሚገኝባት፣ ሀገሩን ለቆ ወደ ስደት የሚሄደው ወጣት ቁጥር የበዛባት አህጉር ነች። ይህ ቢሆንም ቅሉ በየሀገራቱ መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲ፣ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልና ግልጽነት ከሰፈነ አፍሪካ ወጣቶቿን በማስተማር ከድህነትና ኋላቀርነት እንደምትወጣ ይታመናል።
አንዱም መሰረታዊ ችግር የትምህርትና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመስፋፋት ሲሆን ይሄም በሂደት ይለወጣል የሚል እምነት አለ። አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛዋ የአለማችን ፈጣን ታዳጊ የቱሪስት ኢንዱስትሪ ሆናለች። ወደ አህጉሪቱ የሚደረገው ጉዞ ርካሽና ቀላል በመሆኑ መንግስታት በአዲስ ተነሳሽነት የቱሪዝምን ንግድና ገበያ እያስፋፉ ነው ሲል አፍሪካ ቢዝነሰ ኦን ላይን ዘግቧል፡፡
በ2018 (እኤአ) በአፍሪካ ጉዞና ቱሪዝም ዋነኛው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ በመሆን 8 ነጥብ 1 አጠቃላይ አህጉራዊ ምርት አስመዝግቧል። 194 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለአህጉሪቷ ኢኮኖሚ ማስገኘቱን የአፍሪካ ኢ-ኮሜርስ ካምፓኒ የሆነው ጁሚያ ባወጣው አዲስ ሪፖርት ገልጿል።
በ2019 (እኤአ) የጁሚያ ሆስፒታሊቲ ሪፖርት መሰረት የአህጉሪቱ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ በ2018 (እኤአ) በ5.6 ፐርሰንት ከእስያና ፓስፊክ ሁለተኛ በመሆን በአመት 3.9 ፐርሰንት አድጓል። በ2018 (እኤአ) 67 ሚሊዮን ቱሪስቶች ወደ አፍሪካ ተጉዘዋል። ይህም በ2017 (እኤአ) ከነበረው 63 ሚሊዮን ቱሪስት እንዲሁም በ2016 (እኤአ) ከነበረው 58 ሚሊዮን ቱሪስት የ7 ፐርሰንት ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ከማራካች ጫፍ (ሰሜን አፍሪካ) እስከ ደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን ድረስ ባለው የተንጣለለ ሰፊ ግዛት በአፍሪካ የቱሪስቶች ዋነኛው መዳረሻ የነበሩት ሞሮኮና ደቡብ አፍሪካ ሲሆኑ፤ በየአመቱ 10 እና 11 ሚሊዮን ቱሪስቶች ይጎበኛሉ። በኢትዮጵያ ያለው የማያጨናንቅ የቪዛ ስርአት ከተሻሻለው የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ጋር ተዳምሮ የቱሪስት ኢንዱስትሪዋን በ2018 (እኤአ) 48.6 ፐርሰንት በማሳደግ በአጠቃላይ 7. 4 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች።
አብዛኛዎቹ የውጭ ጎብኚዎች የበአል ጎብኚዎች ሲሆኑ 71 በመቶ የቱሪስት ወጪያቸውን በመላው አፍሪካ በመንቀሳቀስ በመዝናኛ ቦታዎች ያሳልፉሉ። ሪፖርቱ በመንግስት ተነሳሽነት የቱሪስቶችን ቁጥር ለማሳደግ በኬንያ ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ የቱሪዝም ንግድ ለመሳብ ጥረት መደረጉን ይገልጻል። ይህንን ነው ሪፖርቱ አዲሱ መንገድ ያለው። ይህ የቱሪዝም እድገት ስትራቴጂዎችን ያቀፈ ሲሆን ሀገሮች አለም አቀፍ ንግድን ለመሳብ ክዋኔዎችን ለምሳሌም ስብሰባዎች፣ ማበረታቻዎች፣ ኮንፈረንሶች፣ ኤግዚቢሽኖችን ያዘጋጃሉ።
አሁንም ቢሆን አፍሪካ ከአለም አቀፉ የቱሪዝም ገበያ በአጠቃላይ የያዘችው ትንሽ ቁራሽ ሲሆን ይህም 62.9 ሚሊዮን ወይም (5.1 ፐርሰንት) ነው። በ2016 (እኤአ) 1.2 ቢሊዮን የግሎባል ቱሪዝም ጎብኚዎች ነበሩ፡፡ይህንን ሪፖርት የገለጸው የአፍሪካ ቱሪዝም ሞኒተር ሲሆን የአፍሪካ ልማት ባንክ በሰነድ መልክ ይዞታል። ሆቴሎች ራሳቸውን ለማሻሻልና መስመሮቻቸውን ለማጽዳት ሲሉ የገቧቸውን ውሎች በመሰረዛቸው ምክንያት የሆቴል ኢንዱስትሪው ተቀዛቅዟል። በፓይፕ ላይን እንቅስቃሴ ብቻ (የመስመሮች ዝርጋታ በ2019 (እኤአ) 45.861 ክፍሎች የነበሯቸው 276 ሆቴሎች በ2018 (እኤአ) ከነበሩት በ418 ሆቴሎች ውስጥ ከነበሩት 76.322 ክፍሎች ቀንሰዋል፡፡.
በአፍሪካ ሰማይ ላይ ከፍተኛውን ገንዘብ ያተረፈው አየር መንገድ የአረብ ኢምሬትን ባንዲራ የያዘው አየር መንገድ ሲሆን በ2018 (እኤአ) ብቻ በጣም ታዋቂ በሆኑ ከጆሀንስበርግ ካይሮ ኬፕታወን ሞሪሸስ ባደረጋቸው በረራዎች ከ837 ሚሊዮን ዶላር በላይ አትርፏል።
በጣም ከፍተኛ የሆነው የአየር በረራው መስመር መንገድ ከደቡብ አፍሪካዋ ግዙፍ ከተማ ጆሀንስበርግ የፐርሽያ ገልፍ ማረፊያ ወደሆነችው ዱባይ ከሚያዝያ 2018 (እኤአ) እስከ መጋቢት 2019 (እኤአ) ያደረገው ሲሆን በእነዚህ ምልልሶች ከተጓዦች ብቻ ያገኘው ገቢ 315.6 ሚሊዮን ዶላር ነው። በተመሳሳይ ወቅት የመንግስት ንብረት የሆኑት የአንጎላና የደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶች ከአፍሪካ ውስጥ ሁለቱ ብቻ ነበሩ በጣም ትርፋማና ከአስሩ ዋነኛ ከሚባሉት በመጀመሪያዎቹ ረድፎች የነበሩት። ከሩዋንዳ እስከ ሊዝበን ባለው የአየር መስመር በረራ 231.6 ሚሊዮን ዶላር ከፍተኛ ትርፍ አግኝተዋል። ከኬፕታውን እስከ ጆሀንስበርግ በተደረገው በረራ 185 ሚሊዮን ዶላር ማግኘታቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል።
በአፍሪካ መካከል ያለውን የቱሪዝም ገበያ ከፍተኛ ድርሻ ለመቀራመት ሀገራት የሚያደርጉት ሩጫ እንዳለ ሆኖ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ገበያ ስምምነት በየሀገራቱ ውስጥ የሚደረጉትን ጉዞዎች የበለጠ ያስፋፋል። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ያለውን ከፍተኛ እምቅ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ከሁሉም የኢንዱስትሪ ተዋናዮች ትብብርን ይጠይቃል ስትል የጁሚያ የጉዞ ዋና ኃላፊ ኢስቴሌ ቨርዲየር ትገልጻለች። የአፍሪካ መንግስታት ለአፍሪካ ዜጎች ወደሀገራት ለሚያደርጉት ጉዞ የቪዛ ጥያቄዎችን ማስወገድ አለባቸው ብላለች።
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2012
ወንድወሰን መኮንን