አፍሪካ በ 2017/18 የውድድር ዓመት በዓለም አቀፍ ይሁን በአህጉራዊ የስፖርት መድረክና ሁነቶች ስትታወስ ስኬትም ውድቀትንም አስተና ግዳለች። አሳዛኝ ታሪኮችንም አሳልፋለች። ከእነዚህ የውድድር ዓመቱ አብይት ሁነቶች መካከል ደግሞ የሚከተሉት ከሁሉ ልቀው ይታወሳሉ።
አሳፋሪው የአፍሪካ የዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ታሪክ
አፍሪካውያኑ ኮከቦች ምንም እንኳን በተለያዩ ታላላቅ ሊጎች አገራቸውንና ስማቸው ከፍ አድርገው ማስጠራት ቢችሉም በአህጉር አቀፍ ውድድሮች በተለይ በታላቁ የዓለም ዋንጫ የሚያሳዩት አቋም ግን ብዙዎችን ግር ያሰኘ ነበር።
በእርግጥ አፍሪካውያኑ ተጫዋች በዓለም ዋንጫው መድረክ መገኘት የሚያጎናፅፈውን ክብርና የሚሰጠውን የተለየ ስሜት ጠንቅቀው ቢያውቁትም ከተሳትፎ ባለፈ በመድረኩ ላይ አዲስ ታሪክ መስራት የምንጊዜም ህልምና ምኞታቸው ነው።ይሁንና ይህ መሻታቸው ዓለም ዋንጫው ከተጀመረ ዓመታትን ተሻግሮም ውጤት ማምጣትና በዋንጫ መታጀብ አልሆነለትም።
ከወራት በፊት በተካሄደው 21ኛው የሩሲያ የዓለም ዋንጫ በሦስት የሰሜንና በሁለት የምዕራብ አፍሪካ አገራት የተወከለችው አፍሪካ፣ እግር ኳሳዊ የታሪኩ አሸናፊነት አቅጣጫን የመቀየር አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን ይዛ ሞስኮ ብትደርስም የፈለገችውን ግን ማግኘት አልቻለችም።
ከዓለም ዋንጫ መጀመር አስቀድሞ በርካቶች በዓለማችን ታላላቅ ሊጎች ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉና አገራቸውን ወክለው ሩሲያ ያቀኑ ኮከቦችን ዋቢ በማድረግ በዘንድሮው ፍልሚያ አፍሪካ የተሻለ ውጤት እንደሚኖራት ቢተነብዩም በሞስኮ ሰማይ ስር የሆነው ግን ከዚህ ፈፅሞ የተቃርኖ ሆኗል። ከአህጉሪቱ የመድረክ ተወካዮች አንድም ብሄራዊ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻለም።በታሪክም እጅግ በደካማና አሳፋሪ አቋም ና ውጤት ወደመጡበት ተመልሰዋል።
ከዚህ ቀደም ማለትም ከ1986 የሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ ወዲህ አህጉሪቱን ከወከሉ ብሄራዊ ቡድኖች ቢያንስ አንድ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሏል።ይህ ውጤታቸው ደግሞ እ.ኤ.አ 1998 የፈረንሳዩ የዓለም ዋንጫ የተሳታፊ አገራት ቁጥር ወደ 32 ፤የአፍሪካ ተወካዮች ደግሞ አምስት ሳይሆን ሦስት አገራት ብቻ ሆነውም ያልተቋረጠ ነበር።
ከዚህ በተቃርኖ አፍሪካውያኑ በየሩሲያው መድረክ ያሳዩት የወረደ እግር ኳሳዊ ብቃት ከስፔኑ የዓለም ዋንጫ ማለትም ከሰላሳ ስድስት ዓመታት በኋላ ታይቶ የማይታወቅ አድርጎታል። በሩሲያ ምድር ከአሥራ አምስት ጨዋታ አፍሪካውያኑ ውጤት ማምጣት የቻሉት በሦስቱ ብቻ ነው።በአሥሩ ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። ግብፅ፤ሞሮኮ፤ ቱኒዚያና ናይጄሪያ የተሰናበቱትም ገና ከምድባቸው ነበር። በተለይ በመድረኩ የተሻሉ ኮከቦችን የያዙት አገራት አንድም የረባ ጨዋታና ውጤት ሳይዙ መመለሳቸው ብዙዎችን አነጋግሯል።
የኪፕቾጌ አዲስ ታሪክ
አፍሪካ በዓመቱ ከእግር ኳስም በላይ በአትሌቲክሱ ስሟን ከፍ አድርጋ ታይታበታለች። በተለይ የኬንያው አትሌት ኢሊዩድ ኪፕቾጊ ስም ከሁሉ ገኖ ተሰምቷል። አትሌቱም በዓመቱ በማራቶን የውድድር የምንጊዜም ፈጣን ሰዓት አስመዝግቧል። አትሌቱ በጀርመን በርሊን በተካሄደው የማራቶን ውድድር 2፡1፡39 ሰከንድ በመግባት የዓለም ክብረ ወሰን ሰብሯል።
የ 33 ዓመቱ አትሌት በአውሮፓውያኑ 2014 በአገሩ ልጅ ደኒስ ኪሜቶ ተይዞ የነበረውን ሰዓት በ1፡20 ሰከንድ አሻሽሎ በአስደናቂ የአሯሯጥ ብቃት የርቀቱን ክብረ ወሰን በባለቤትነት ተቆጣጥሯል። ከወራት ቀድሞም በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር የዓመቱ ምርጥ ወንድ አትሌት አሸናፊ በመሆን ልፋቱን የሚመሰክር ክብርን ተቀናጅቷል።
የሞሃመድ ሳላህ ከፍታ
ዓመቱ አፍሪካ በድንቅ እግር ኳሳዊ ጥበብ የተካኑ ተጫዋቾች እንዳሏት ግብፃዊው የሊቨርፑሎች ኮከብ መሃመድ ሳላህ ለዓለም ያስተዋወቀበትም ነበር ።በእግር ኳሳዊ የጥበብ ልህቀቱ ዓለምን ያስደመመው ሞሃመድ ሳላህ፤ከሮማ በ 34 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ሊቨርፑል ከተዘዋወረ በኋላ በውድድር ዓመቱ በ 37 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች 31 ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ሉዊስ ሱዋሬዝ 2013/14፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ 2007/08 እንዲሁም አለን ሺረር 1979 እስከ 1996 በአንድ ውድድር ዓመት ካስቆጠሯቸው 38 ጎሎች ጋር እኩል በማስቆጠር ክብረወሰኑን ተጋርቷል።
በአስደማሚ ብቃቱ የሚማረኩ ወዳጆቹ ግብፃዊው ሜሲ ሲሉ የሚያሞካሹት ሳላህ፤ በተወዳጁ ሊግ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋችም ተብሎም ተመርጧል።በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጫዋቾችና ጸሐፊዎች ማህበር የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በመባል ሽልማት አግኝቷል። በዓመቱ በሁሉም ጨዋታዎች 44 ግቦችን ለሊቨርፑል ማስቆጠር ችሏል፡፡
ፈርኦኖቹን ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ ሩሲያው ዓለም ዋንጫ እንዲያልፉ በማድረግ የቁርጥ ቀን ልጃቸው መሆኑን አስመስክሯል። በውድድር ዓመቱ ካስቆጠራቸው ግቦች በላይም ይህች ግብ ክብርና ሞገስን አጎናፅፋዋለች።
ምትሃተኛው ግራ እግር ተጫዋች በውድድር ዓመቱ ባሳያው ምርጥ ብቃት በአህጉር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ልቆ ታይቷል።የፊፋ የአውሮፓ ዓመቱ ምርጥ ተጫዋቾች እጮዎች ውስጥም ስሙን አካቷል። ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የቢቢሲ የዓመቱ የአፍሪካ ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች በመሆን ተመርጧል። በዚህ ታሪኩም ከናይጄሪያዊው ኮከብ ከአውስቲን ጄይ ጄይ ኦኮቻ ጋር ተስተካክሏል። ሳላህ በውድድር ዓመቱ ባሳየው ድንቅ ብቃት የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋችነት ክብርም ተሰጥቶታል። ዓመቱም የተጫዋቹን ብቃት በማስመስከር ስሙን ከፍ አድርጎ ያስጠራባት ሆኗል።
የፊፋና የአፍሪካ አገራት ፍጥጫ
ዓመቱ በተለይ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ከአፍሪካ አገራት ጋር እስጣ ገባውን አጧጡፎ የታየበት ሆኖም አልፏል። በተለይ ጋና፤ ናይጄሪያ ሴራሊዮን የመሳሰሉ አገራት የፊፋን ህግ በተላለፈ ሁኔታ ፖለቲካና እግር ኳስን ቀላቅለው መታየታቸውን ተከትሎ የተቋሙን ቁጣና ቅጣት አስተናግደዋል።
ጋና እና ናይጄሪያ ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳደር ጋር ለገቡበት እስጣ ገባ በቶሎ ለመቋጨት በአገራቱ እግር ኳስ ውስጥ የተንሰራፋውን የአመራር ሽኩቻና ገሃድ የወጣ የሙስና ቅሌት ለማስወገድ መፍትሄ የሚሉትን እልባት ሰጥተዋል።ሴራሊዮን በአንፃሩ እንደ ናይጀሪያና ጋና የቤት ሥራዋን በሚገባ መወጣት ባለመቻሏ የፊፋን እገዳ ማስተናግድ ግድ ብሏታል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ የሚስተዋለው ሙስና ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥርሱን ማግጠጡ የታየውም በዚሁ ዓመት ነው።ተግባሩም የአህጉሪቱን እግር ኳስ በበላይነት ከሚመራው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አመራሮች ጨምሮ እስከ ብሄራዊ ፌዴሬሽን አመራሮች፤ አሰልጣኞች ዳኞችና ተጫዋቾች ዘለቆ ታይቷል።
አዲሱ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ወደ ስልጣን እንደመጡ ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋም ጋር በመሆን የፀረ ሙስና ፍልሚያቸውን ጀምረዋል።
የጋና እግር ኳስ ማህበር ፕሬዚዳንት ክዌሲ ንያንታኪ «ስልጣናቸውን በመጠቀም ያልተገባ ጥቅም ማግኘትና ሰዎችን በማታለል 65 ሺህ ዶላር ተቀብለዋል» የሚል ክስ በመክፈት ባደረገው ምርመራ በተለይ ቁጥር «12» በሚል ርዕስ በምርመራ ጋዜጠኛው አነስ አርሜይው አናስ የተሰራው በጋና እግር ኳስ ውስጥ ስላለው ሙስና የሚያሳይ ዘገባ ፕሬዚዳንቱ ጥፋተኛ ስለመሆናቸው አረጋግጧል።
በመቅረፀ ምስል የተደገፈውን ማስረጃውን የተመለከተው የፊፋ የሥነ ምግባር ኮሚቴ ግለሰቡ በብሄራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ዕድሜ ልክ አግዷቸዋል። ከዚህ ቅጣት ባሻገር እ.ኤ.አ ከ 2017 ጀምሮ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትና የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የአፍሪካ አገሮችን በመወከል እ.ኤ.አ ከ2016 ጀምሮ የፊፋ ምክር ቤት አባል ሆነው የሰሩትን ግለሰብ አምስት መቶ ሺ ዶላር እንዲከፍሉ ውስኗል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ምልክቶች ስንብት
ዓመቱ የአፍሪካ እግር ኳስ ምልክቶች የነበሩ ተጫዋቾች ጫማ የሰቀሉበት ሆኖም አልፏል። የቼልሲውና የአይቮሪኮስት ምልክት ዲዲየር ድሮግባ ሁለት አሥርት ዓመታት የዘለቀውን የእግር ኳስ ህይወቱን በመቋጨት ጫማ የሰቀለው በዚህ ዓመት ነው።
በ24 ሚሊዮን ፓውንድ ቸልሲን በ2004 የተቀላቀለው ድርጎባ ላለፉት 8 ዓመታት በስታንፎርድ ብሪጅ የተለያዩ ድሎችን አጣጥሟል።በሰማያዊው መለያ ለ381 ጊዜያት ተሰልፎ በመጫወት 164 ግቦችን ከመረብ በማዋሃድም ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው። ያስቆጠራቸው የግብ ብዛትም በቼልሲ አራተኛው የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ያደርገዋል። ስታምፎርድ ብሪጅን እንደቤቱ የሚመለከተው ድሮግባ፤ አወዛጋቢው የሚል ቅጽል ያላቸው ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ «በአውሮፓ ምርጡ ተጫዋችና መልካም ስብዕና ያለው» ሲሉም ያንቆለጳጵሱታል።
በሰማያዊዎቹ ቤት ቆይታውም፤አራት የፕሪምየር ሊግና የኤፍ ኤ ዋንጫዎችን አንስቷል።ሦስት የሊግ ካፕ፣ ሁለት ኮሚዩኒቲ ሺልድ እንዲሁም በ2012 የውድድር ዓመት አንድ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫም አሳክቷል።ኢኳቶሪያል ጊኒ እ.ኤ.አ 2015 ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ጋናን በመርታት ዋንጫውን ለማንሳት ችሏል።
የፈርኦኖቹ ግብ ጠባቂ አል ሃድሪ ከሩሲያው የዓለም ዋንጫ ማግስት በ45 ዓመቱ ራሱን ከእግር ኳስ ያገለለበት ዓመትም ነው። በ 22 ዓመታት ቆይታው በክለብም ሆነ በብሄራዊ ቡድን በድል የተንቆጠቆጡ ዓመታትን አሳልፏል።
የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ እጦት
ካፍ በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደው የአፍሪካ ታላቁ የእግር ኳስ ውድድር መድረክ ለማዘጋጀት የተቸገረበት ዓመት ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ 13 አገራት ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።ይሁንና ከዝግጅት ማነስ ጋር በተያያዘ የአፍሪካ እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ተቋም መድረኩን የሚያዘጋጅለት አገር በማጣት ሲባክን ቆይቷል።
ከዝግጅቱ ሂደት መዘግየት ጋር ተያይዞ ካፍ ለካሜሮን ተሰጥቶ የነበረውን የዘንድሮው የአፍሪካ ታላቅ የእግር ኳስ ሁነት የአዘጋጅነት ሚናን ነጥቋል።ይህንን ተከትሎም በአጭር ጊዜ ውስጥ ውድድሩን የማስተናገድ አቅምና ፍላጎት ያላቸው አገራት በማማተር ሲባክን ታይቷል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011
ታምራት ተስፋዬ