መምህርት ስመኝ ተሰማ በሐረሪ ክልል በጊሌላ ወረዳ ጀግኖች መታሰቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በማስተማር ላይ የሚገኙና 36 ዓመት የሥራ ልምድ አላቸው። መምህርቷ በትጉህነታቸው ተጠቃሽ ከሚባሉ መምህራን አንዷ ሲሆኑ ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ሀገር አቀፍ ድረስ የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችንና ሜዳሊያዎችን በመሸለም ሞዴል ተብለዋል።
ገና የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ያስተምሯቸው የነበሩ መምህራን በሙያው ላይ ፍላጎት እንዳሳደሩባቸው ይናገራሉ። መምህርነት ትውልድን መቅረጽና ሀገርን ማነጽ እንደሆነ የሚናገሩት መምህርቷ የሥራቸውን ፍሬ በተማሪዎቻቸው ላይ እያዩ መምጣታቸውም ሙያውን የበለጠ እየወደዱት እንዲመጡ አድርጓቸዋል። በነበራቸው ቆይታ ሴት ተማሪዎችን ማብቃትና ተተኪ መምህራንንም ማፍራት ችለዋል።
እርሳቸውም ሆኑ የትምህርት ቤታቸው ባልደረቦች ከትምህርት ባለድርሻ አካላትና ከወላጆች ጋር በቅርበት በመሥራት ተማሪዎችን በመምከር፣ በመደገፍና በመከታተል ከሱስ የፀዱና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ ዜጎችን በማፍራት ትምህርት ቤታቸው አርአያ እንደሆነ ይናገራሉ።
ተማሪዎች በሥራ ላይ ሲሰማሩ የሚገጥሟቸውን ተቋማዊ አሠራሮችና ማህበራዊ መስተጋብሮች በትምህረት ቤት እያሉ እንዲለማመዷቸው ክበባት ሚና እንዳላቸው የትምህርት ቤታቸውን ተሞክሮና የራሳቸውንም ሚና ይናገራሉ። በትምህርት ቤታቸው የተማሪዎችን ምክር ቤት በማቋቋም አፈ ጉባኤና አስር ሚኒስትሮችን በመሰየም ሁሉም ተማሪ በግቢው ደንብና መመሪያ እንዲተዳደሩ ማድረግ ተችሏል።
ይህ አሠራር ታዲያ በአንድ ወቅት መምህራን ለልምድ ልውውጥ እርቀው ሲሄዱ ተማሪዎች ሰዓት ጠብቀው በመግባትና በመውጣት ለሦስት ቀናት ያለምንም መምህር ርዕስ በርዕስ እየተማማሩ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል። ስለዚህ መምህራን ሁሉንም አማራጮች በመጠቀምና ከወላጅ ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ሥነ ምግባር ያለው ተማሪን ማፍራት እንደሚቻል ምሳሌ የሆነ ትምህርት ቤት ነው ብለዋል። መምህራን የተማሪዎቻቸውን አኗኗር፣ ባህሪና ዳራቸውን በመረዳት እገዛ በማድረግ ትክክለኛ አቅጣጫ ማስያዝ ይጠበቃል።
ተማሪዎች መምህራንን እንደ ሞዴል ይጠቀሙባቸዋል ያሉት መምህሯ በትምህርት ቤታቸው ወጣት መምህራን ከአንጋፋ መምህራን ልምድ በመውሰድ ለተማሪዎቻቸው ጥሩ አርአያ መሆናቸውም አሁን ላለው መልካም ገጽታ አስተዋጽኦ አድርጓል።
መምህር ቦርሳሞ ቦሎሎ በአዋሳ ከተማ ታቦር መሰናዶ ትምህርት ቤት የጂኦግራፊ መምህር እና የ38 ዓመት ልምድ አላቸው። በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል። መምህርነትን ከየትኛውም ሙያ አብልጠው ስለሚመለከቱ ወደ ሌላ መስሪያ ቤት የመግባት ዕድል ቢኖራቸውም አልፈለጉም።
ይልቁንም የተማሩ ዜጎችን ከማፍራት በላይ የሚያስደስታቸው ነገር የለም። መምህር ቦርሳሞ ከሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ሀገር አቀፍ ድረስ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ትምህርት ሀገርን ለማበልፀግ ብቸኛው መንገድ መሆኑን በመረዳት መምህራን ሀገራቸውን ለማሳደግ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ይመክራሉ።
መጀመሪያ ትምህርት ቤቶችን ከፖለቲካ አመለካከት ነፃ ማድረግ የትምህርት ጥራትንና የመማር ማስተማሩን ሥርዓት ነፃ ለማድረግ ይረዳል። ተማሪውንም መምህሩንም ትምህርት ቤቱንም ከፖለቲካ ነፃ ማድረግ ያስፈልጋል። ዛሬ የደረስንበት ቴክኖሎጂ፣ የተማሪው ዕድሜ እና የሀገሪቱ ሁኔታ በተማሪው ሥነ ምግባር ላይ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ተገንዝቦ ከወላጅ ጋር ተቀራርቦ በመሥራት የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ከተሞክሯቸው አጋርተውናል።
ተማሪዎች አንድ ለአምስት በሚል መደራጀታቸውና መምህራንን እንዲገመግሙ መደረጉ በተማሪው ሥነ ምግባር ላይ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ጉዳዮች እንደሆኑ አስታውሰዋል። እውቀት አንድ ተማሪ ስለ ባህሉ፣ ስለሀገሩ፣ ስለ አኗኗር ሥርዓቱ ስለ ወላጆቹና ታላላቆቹ አክብሮት ከማወቅ ይጀምራል። የሁሉም ባለድርሻ ርብርብ ለትምህርት ጥራት ቁልፍ ተግባር እንደሆነ መምህሩ ይናገራሉ።
መምህርት አለምፀሐይ ክፍሌ በትግራይ ክልል ራያ አላማጣ ከተማ ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት የኢንግሊዘኛ ቋንቋ መምህርት ናቸው። መምህርቷ 40 ዓመት የሥራ ልምድ ያላቸው ሲሆን በሙያቸው ግንባር ቀደም ናቸው። በዚህም ከሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ሀገር አቀፍ ድረስ በርካታ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል። ተማሪዎች በእውቀትም ሆነ በሥነ ምግባር ታንፀው እንዲወጡ ተግቶ መሥራት የዘወትር ተግባራቸው እንደሆነ የሚገልፁት መምህርቷ ከሚሰጣቸው ሽልማት በላይ እርሳቸውን የሚያስደስታቸው የተማሪዎቻቸው ፍሬያማ መሆን ነው።
ማስተማር የአዕምሮ ሥራ ነው የሚሉት መምህሯ፤ መምህር ከማስተማር ሥራው ውጭ በሌሎች ነገሮች በመጠመዱ በሥራው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ይላሉ። በዚህ ዘመን በመምህሩ እንዳይላወስ የሚያደርጉ የተለያዩ የወረቀት /የጽሁፍ/ ሥራዎች መብዛታቸው ትኩረቱን ያስቱታል ባይ ናቸው። እያንዳንዱ መምህር ሌላ ተግባራትን ከመፈፀም ይልቅ አንብቦ አቅሙን የሚያሳድግበት ሁኔታ ሊመቻችለት እንደሚገባና መልካም ሥነ ምግባርን በመላበስ ለተማሪዎች ምሳሌ መሆን እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2012
ኢያሱ መሰለ