እሁድ ሰኔ 13 ቀን 1963 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 31ኛ ዓመት ቁጥር 244 ዕትም “የከብቶች ምላስ እየቆረጡ የሰረቁ በእሥራት ተቀጡ” በሚል ርዕስ ተከታዩን ወንጀል ነክ ዘገባ አስነብቦ ነበር።
የከብቶች ምላስ እየቆረጡ የሰረቁ
በእሥራት ተቀጡ
እየተሰረቁ ሲወሰዱ ከመንገድ ላይ እየጮሁ የከብቶቹን ባለቤቶች እንዲነቁ የሚያደርጉትን ላሞችና በሬዎች ምላሳቸውን የቆረጡትና የዘረፉት ስድስት ሰዎች ተመስክሮባቸው ትናንት በእሥራት ተቀጡ። ወንጀለኞቹ በመናገሻ አውራጃ በአቃቂ፣ በኮተቤ፣ በቦሌ በቀንና በሌሊት እየተዘዋወሩ አስራ ስምንት የቀንድና የጋማ ከብቶች መስረቃቸውን የዓቃቤ ሕጉ ምስክሮች አረጋግጠዋል።
የዘረፋውን ተግባር የፈፀሙት ገመቹ ጭቋላ፣ ቱፋ ሰቦቃ፣ ገመቹ ያደቴ፣ አሰፋ ክብረት፣ ዲሬ ቢሳ፣ የተባሉት ሲሆኑ ከአቃቂ በሰቃ የአቶ ይርጋ ደበሌን አራት በጎች፣ ከቦሌ ወረገነት የአቶ ሮቤል ጉራራን አምስት የጋማ ከብቶች፣ ከቦሌ የአቶ አያኖ በይን ሰባት ላሞች የሰረቁ መሆናቸው አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ተመስክሯል።
ወንጀለኞቹ የዘረፋውን ተግባር የፈፀሙት ከሰኔ 5 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 1962 ዓ.ም ሲሆን፤ አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው በምስክር ተረጋግጦባቸው እያንዳንዳቸው በአምስት ዓመት ፅኑ እሥራት እንዲቀጡ ተወስኖ ባቸዋል። ወንጀለኞቹ ምላሳቸውን የሚቆርጧቸው ላሞቹንና በሬዎቹን ብቻ መሆኑ በክሱ ማመልከቻ ተዘርዝሯል።
***********************
ረቡዕ ግንቦት 25 ቀን 1963 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 31ኛ ዓመት ቁጥር 228 ዕትም “የሥራ ፈቶችን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቋመ” በሚል ርዕስ አንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ስለመክፈቱ አስነብቦ ነበር።
የሥራ ፈቶችን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቋመ
የሥራ ፈቶችንና ትምህርታቸውን እያቋረጡ የሚወጡትን ልጆች የወፊት ዕድል የሚወስን “ኦፖርቹኒቲዝ ኢንዱስትራላይዜሽን ሴንተር” የተባለ ድርጅት በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ማቋቋሙን የድርጅቱ መሪ ዶክተር ሊአን ኤች ሱሊቫን ትናንት አስታወቁ። የድርጅቱ ዋና አላማ የሰው ልጅ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበትንና ከጤናማው ህብረተሰብ የማይለይበትን መንገድ በመፈለግ የአዕምሮና የተግባር እውቀት ሰጥቶ ሥራ ለማስያዝ መሆኑ ተረጋግጧል። … የሥራ ፈቶችና ትምህርት የሚያቋርጡ ልጆች ማሰልጠኛና መደገፊያ ድርጅት ከአፍሪካ መሬት በናይጄሪያና በጋና ሥራ መጀመሩ ታውቋል። …
***********************
መስከረም 23 ቀን 1940 ዓ.ም ኢትዮጵያ ለእንግሊዝ የገንዘብ ዕርዳታ ስለመስጠቷ አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲህ ዘግቦ ነበር ። ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በክረምቱ ሃይለኛነት ምክንያት ጉዳት ለደረሰበት አገር የገንዘብ ዕርዳታ ልከዋል። ይህም ዕርዳታ በለጋሲዮኖች በኩል ሲላክ ቀጥሎ ያለው ደብዳቤ አብሮ ተልኳል።
ለሎርድ ሜዮርክ ናሽናል ዲስትሬስ ፈንድ ለንደን።
ምንም እንኳን እኛም ራሳችን በሕዝባችን ላይ ያለአግባብ በግፍ የደረሰበትን ጉዳት በማቃለል ሥራችን ላይ ብንሆንም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቀው ሃይለኛና ጨካኝ በሆነው ክረምት ሁልጊዜ በምናስባት በለምለሟ ውብ በሆነች አገርዎ ላይ ለደረሰው ጥፋት መጠነኛ የገንዘብ ዕርዳታ መጠየቅዎን ስለሰማን የገንዘቡ ቁጥር ምንም ከፍ ያለ ሳይሆን የኛንና የሕዝባችንን ዕርዳታ ለመገለፅ ያህል አንድ ሺህ ፓውንድ በለጋሲዮናችን በኩል ልከንልዎታል። ”
መስከረም 23 ቀን 1940 ዓ.ም
ከአዲስ ዘመን በተጨማሪ የብሪታንያው ዴይሊ ቴሌግራፍ ጋዜጣ ብሪታንያ ከኢትዮጵያ የቡናና የስንዴ ዕርዳታ ለማግኘቷ እ.ኤ.አ በ 1998 ዘግቧል።
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012