ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም የውጫሌ ውልን እንደማይቀበሉና ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከወራሪ ጠላት እንዲከላከሉ የሚያሳስብ ታሪካዊ አዋጅ ካስነገሩ በኋላ፣ ጦራቸውን ይዘው ከአዲስ አበባ ወደ ዓድዋ ጉዞ የጀመሩት ከ124 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም) ነበር።
ንጉሰ ነገሥቱ ዙፋናቸውን ለአጎታቸው ለርዕሰ-መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ (የአባታቸው የንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ ወንድም) አደራ ሰጥተው ወደማይቀረው የነፃነት ፍልሚያ ጉዞ ጀመሩ። ከአዲስ አበባ ሲነሱም ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱም አብረው ለመጓዝ ተነሱ።
ይህንን የዓድዋ ዘመቻ ጉዞ የተመለከተው አንድ የባህር ማዶ የታሪክ ፀሐፊ ‹‹ … ኢትዮጵያውያን ሲጓዙ በደንብ ተመልክቻለሁ፤ ዳገቱን ሲወጡ፣ ቁልቁለቱን ሲወርዱና ሸለቆውን ሞልተው ሲሄዱ እየተጯጯሁ ነው፤ ለውጊያ የሚሄዱ አይመስሉም። ሴቶች፣ ሽማግሌዎች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሕፃናትና ቄሶች ሁሉ ሳይቀሩ አብረው በአንድነት ይጓዛሉ፤ እኔ እንዳሰብኩት ለጦርነት የሚሄዱ የጦር ወታደሮች አይመስሉም። ሕዝቡ በሙሉ ተነቅሎ ለወረራ የሚሄድ ይመስላል›› በማለት በግርምት ጽፏል።
በሌላ በኩል ለዘመቻው የሄደው ሰው ለጉዞ የሚሆን ደንበኛ ልብስ ስለሌለው ሐሩር እያቃጠለው እንደነበር፣ ሲታመምም የባህል መድኃኒት እንጂ ሌላ የተሻለ ህክምና እንደማያገኝ፣ የረባ መሣሪያ እንዳልታጠቀ … ሌሎች የታሪክ ፀሐፍት ጽፈዋል።
ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የሰው ደም በከንቱ እንዳይፈስ ደጋግመው ሰላማዊ የመፍትሄ አማራጭ ቢያቀርቡም የኢጣሊያ መንግሥት ምላሽ ግን «አሻፈረኝ» ሆነ። በመጨረሻም ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ተካሂዶ ኢትዮጵያ ዓለም የማይረሳው፣ ጊዜ የማይሽረው አንጸባራቂ ድል አስመዘገበች።
መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም የታወጀው አዋጅ የሚከተለው ነበር።
‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፤ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም፤ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁን ግን ሀገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚያስለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፤ እኔም ያገሬን ከብት ማለቅና የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር።
አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፤ ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ! ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህና ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ! ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ! አልተውህም! ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም! ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ!››
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
አንተነህ ቸሬ