የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት መርሐግብር በሳምንቱ የእረፍት ቀናትም በተለያዩ ከተሞች ተካሂዷል።የሊጉ መሪ ሃዋሳዎች በአስደናቂ ብቃት በአሸናፊነታቸው የዘለቁበት ውጤት አስመዝግበዋል። በስድስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ከፈረሰኞቹ ጋር ነጥብ የተጋሩት ሀዋሳዎች በሜዳና በደጋፊያቸው ፊት ስሁል ሸረን አስተናግደው በሰፊ ውጤት ማሸናፍ ችለዋል።
ሃዋሳዎች ከጨዋታ የበላይነት ጋር ግማሽ ደርዘን ግብ በተጋጣሚያቸው ላይ አስቆጥረዋል። በስድስተኛ የሊጉ መርሐ ግብር ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ የተለያዩት ስሁል ሽረዎችም በጨዋታው ከወትሮው በተለይ በመከላከል ረገድ በእጅጉ ተዳክመው ታይተዋል።
ሌላኛው የሰባተኛው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡናን ከአዳማ ከተማ ጋር አገናኝቷል። ከጨዋታው ቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ለአዳማ ደጋፊዎች የሞቀና በስፖርታዊ ጨዋነት የታጀበ አቀባበል በማድረግ ለሌሎች ክለቦች አርዓያ የሚሆን ተግባር ሲፈፅሞ ታይተዋል።
በሜዳና በደጋፊያቸው ፊት የተጫወቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጨዋታው መጨረሻ ሰዓት ባስቆጠሯት ብቸኛ ግብ ሙሉ ሦስት ነጥብ አግኝተዋል። አቡበከር ናስሩ ያስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ቡናማዎቹን አስፈንድቃለች። በስድስተኛው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ከመቀሌ ሰባ እንደርታ ጋር በሜዳው ያደረገው ጨዋታ 3 ለ 1 ያሸነፈው አዳማ ከተማ በጨዋታው አሳዛኝ ተሸናፊ ሆኗል።
በስድስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር በበርካታ ደጋፊዎች የታጀበው ጃኮ አራፋት ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ቡና 1ለ0 ያሸነፉት የጣና ሞገዶች፤ ደቡብ ፖሊስን አስተናግደው አንድ ለዜሮ ማሸነፍ ችለዋል።
ባህርዳሮች ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ የሚችሉ ከሆነ ፕሪሚየር ሊጉን እስከመምራት የሚደርሱ ይሆናል። ክለቡ በተለይም በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጪ የሊጉን ትላልቅ ክለቦች ማሸነፍ መቻሉ ለብቃቱ በቂ ምስከር ሆኖም ይቀርባል።
ባሳለፍነው ዓመት ጅማ አባጅፋር በመጀመሪያ ዓመት የሊጉ ተሳትፎው አስደማሚ ብቃት በማሳየት የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱ የሚታወስ ሲሆን፣ የዘንድሮው ባህር ዳር ከተማ ወቅታዊ ብቃትም ሊጉ የጅማ ዓይነት ታሪክ የሚያሳይ ሌላ ክለብ የማግኘት ዕድል ሊኖረው እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።
በመጀመሪያ ዓመት ተሳትፎው አስደናቂ ብቃት በማሳየት ስኬታማ ጉዞን ማድረግ የቻለው ባህር ዳር ከተማ ምንም እንኳን የሊጉ መርሐ ግብር ገና ሰባተኛ ሳምንቱ ላይ ቢሆንም ስለቀጣዩ የክለቡ ጉዞ ከወዲሁ መናገር አስቸጋሪ ቢሆንም ወቅታዊ ብቃቱ ግን የበርካቶች አድናቆት አልተለየውም።
ሌላኛው የሰባተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ጨዋታ መቀሌ ላይ መቀሌ 70 እንደርታ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን አገናኝቷል።ይህ ጨዋታም ያለምንም ግብ ተጠናቋል።ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ ይቀራቸዋል።
በተለይ ፕሪሚየር ሊጉ ሊጀመር ሲል አሰልጣኙን ያሰናበተው ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮው አቋሙ መልካም የሚባል እንዳልሆነ እየታየ ነው። በዘንድሮው የሊጉ ፍልሚያ አምስት ጨዋታዎችን አድርገዋል።አንድ ጨዋታ አሽንፏል። ሁለት ጨዋታዎችን ተሸንፏል። ሁለት ጨዋታዎችን ደግሞ አቻ ተለያይቷል። ይህን ውጤቱን ተከትሎም በአምስት ጨዋታዎች አምስት ነጥቦችን ሰብስቧል። በደረጃ ሰንጠረዡም ዘጠነኛ ላይ ተቀምጧል።
የሰባተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር በድሬዳዋ ስታዲየም እድሳት ምክንያት ጨዋታውን በሐረር ስታዲየም ያደረገው ድሬዳዋ ከተማን ከፋሲል አገናኝቷል። በጨዋታውም እንግዳው ክለብ አሸናፊ ሆኗል። በስድስተኛ ሳምንት መከላከያን በሜዳቸው አስተናግደው ሁለት እኩል የተለያዩት አፄዎቹ፤ ከድሬዳዋ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ምርጥ እንቅስቃሴ አሳይተዋል። ሱራፌል ዳኛቸው ባስቆጠራት ብቸኛ ግብም ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል። ድሉም ለአፄዎቹ የዓመቱ ሁለተኛ ከሜዳ ውጪ ድል ሆኖ ተመዝግቧል።
በሌላ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታ ወላይታ ዲቻዎች ደቡብ ፖሊስን አስተናግደዋል። ዲቻዎች አንዱዓለም ንጉሴ አቤጋ ባስቆጠራት ግብ ባለድል ሆነዋል። ወልዋሎዎችም ደደቢትን አስተናግደው በአፈወርቅ ኃይሉ ግብ አሸናፊ ሆነዋል።
የዘንድሮን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሃዋሳ ከተማ ሙሉ መርሐ ግብሮችን በማድረግ፤ አሥራ አራት ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል። ፋሲል ከተማ ኢትዮጵያ ቡናና ባህርዳር ከተማ እያንዳንዳቸው 11 ነጥቦችን በመሰብሰብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ኢትዮጵያ ቡናና ፋሲል ከተማ አንድ አንድ ቀሪ ጨዋታ ይቀራቸዋል። የጣና ሞገዶቹ ባህርዳሮች ሁለት ቀሪ ጨዋታን የሚያደርጉ ይሆናል።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በወራጅ ቀጣና ስሁል ሽረ 14 ፤ደቡብ ፖሊስ 15ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ከወትሮው በተለየ መልኩ የከበደው ደደቢት ካለምንም ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 16ተኛ ላይ ተቀምጧል።ስሁል ሽረና ደቡብ ፖሊስ አንድ አንድ ቀሪ ጨዋታ፤ደደቢት ደግሞ ሁለት ጨዋታዎች ይቀሯቸዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011
ታምራት ተስፋዬ